አገር ሲያረጅ ጃርት ያፈራል፤ በቀድሞው ጠ/ሚ አክሊሉ ሃብተወልድ ወንበር ላይ አሁን ቴዎድሮስ አድሃኖም ተቀምጧል!

12 Nov

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

በይገረም ዓለሙ

በዕድሜአችን የደረስንባቸውንም ሆነ በታሪክ የምናውቃቸውን በዚህች ሀገር በመሪነትም ሆነ በከፍተኛ ሥልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች ስናስብ የዘመናችን ባለሥልጣናት በብዙ መንገድ አንሰውና ቀለው ነው የሚታዩት፡፡ በውሸታምነታቸው በዘረኛነታቸውና ለሀገርና ለሕዝብ በአላቸው እኩይ አመለካከት ደግሞ አይደለም ትናንት ከነበሩት ወደ ፊትም ከሚመጡት የሚስተካከላቸው የሚገኝ አይመስልም፡፡ ነገረ ስራቸው ሲመዘን፣ የማይታመን የማይጨበጥ ንግግራቸው ሲሰማ እንዲህ የሚያደርጋቸው ከደደቢቱ እኩይ ዓላማቸው በላይ የተቀመጡበት እነዚያን ታላላቅ ኢትዮጵያውያንን ያስተናገደ ወንበር እያቃዣቸው ሳይሆን አይቀርም ያስብላል፡፡

በቃል እየተነገረ በጽሁፍ እየሰፈረ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ ከእኛ ከደረሰውና ለልጆቻችንም ከሚተላለፈው የአባት አናቶቻችንን ብሂላዊ አነጋገር መካከል “አንበሳው መኝታ ጅቡ ተኝቶበት ይባንን ጀመረ በህልሙ እየመጣበት” የሚለው የእነዚህን ዘመንኞች አድራጎት የሚገልጽ ይመስለኛል፡፡ ይህን እንደ አዲስ ለማለት ያበቃኝ ሰሞኑን በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የሰማናቸው የዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም ነገር ነው፡፡

ከወራት በፊት በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የአማርኛው ክፍል ቀርበው አንዳርጋቸው ልማታችንን ማየት አስጎምጅቶት ከተማ እያስጎበኘነው ነው፤ እስር ቤት ላፕ ቶፕ ገብቶለት መጽኃፍ እየጻፈ ነው ከሚለው ጀምሮ ሰሞኑን በሶስት ክፍል በቀረበው ከቀረቡላቸው ጥየቄዎች ጋር የማይዛመድ ምላሻቸው የእነ አክሊሉ ሀብተወልድ መንፈስ እያባነናቸው በቅዠት ውስጥ ሆነው አንጂ በእውን ሆነው በደንብ ነቅተው እያሰቡ የተናገሩት ነው ብሎ ለማመን ይቸግራል፡፡

ክፍል 1
 
ዶ/ር ቴዎድሮስ በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ በድንገት ቀርበው ከተደመጡ በኋላ የተናገሩትን ሲያስቡ አሳፍሮአቸው ይሁን ወይንም በድንብርብር የተናገሩት የሚያስነሳው ጥያቄ አስፈርቶአቸው ባይታወቅም ለጥያቄዎ መልስ ፕሮግራም ላይ ለመቅረብ የገቡትን ቃል ሽረው ቀጠሮ እየሰጡ የውኃ ሽታ ሆኑ፡፡ ሰሞኑን በራዲዮ ጣቢያው በድብቅ ያውም በጨለማ ተገኝተው ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችን ማነጋገራቸው ይፋ ከሆነ በኋላ ቀጠሮ ያሰረዛቸው ፍርሀትም ይሁን ሀፍረት እንዴትና በምን አንደለቀቃቸው ባይታወቅም የሸሹት ፕሮግራም ላይ ተገኝተው በሶስት ክፍል ሰምተናቸዋል፡፡ የሚገርመው ማለት የሚያበዙት ዶ/ር ነገር የሚገርመው ባለፈው ቃለ ምልልሳቸው ከተናገሩትም ሆነ ከተነገራቸው የተማሩም የታረሙም ሆነው አለመገኘታቸው ነው፡፡

Tedros Adhanom at VOAበአንድ ነገር ግን ላመስግናቸው አምነውበት ይሁን ወይንም ሰሞኑን ወያኔ የተያያዘው የማስቀየሻ ስልት አካል ይሁን ባይታወቅም ኩራቴ እትዮጵያዊነቴ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በፍርሀት ይሁን በጥላቻ ኢትዮጵያ የሚለውን የሀገራችንን ድንቅ ስም ላለመጥራት ሀያ አራት አመታት የሀገራችን ሕዝቦች ሲሉ ከምናውቃቸው ሰዎች መካከል ኢትዮጵያዊነት ኩራቴ ሲሉ መስማት የኢትዮጵያዊነትን ኃያልነት የሚያሳይ ነው፡፡በወያኔ አንደበት ይህ አንዲነገር ያበቃ የኢትዮጵያ አምላክ ይክበር ይመስገን፡፡
በክፍል አንድ መጀመሪያ ላይ ኢህአዴግ ከሕዝብ የሚደብቀው ነገር የለም ይሄ ሊሰመርበት ይገባል በማለት በውሸት የጀመሩት ምላሽ በሶስት ክፍል በውሸት ነው ያለቀው፡፡ እኛ የምናውቀው ኢህአዴግ አይደለም ሌላ ሌላውን ሞትን እንኳን ለመደበቅ የሚታገል መሆኑን ነው ፡፡ የአቶ መለስን ሞት በወቅቱ መግለጽ ያልተፈለገው ኢህአዴግ ከጫካ ጀምሮ ይዞት በመጣው የድብቅነት ባህርይው መሆኑን በመግለጽ አቶ በረከት ትክክለኛውን ኢህአዴግ በወቅቱ ነግረውናል፡፡ ሥልጣን ላይ ያለነው ለመከብር ሳይሆን ሀገርና ሕዝብ ለማገልገል ነው አሉን፣ እልሰሜን ግባ በለው ነው የሚለው የሀገሬ ሰው፡፡ አቅለው ብለው ቆለለው እንዲሉ ከ96 ሚለዮን ሕዝብ 8. ምናምን ሚሊዮን ቢራብ ምንድን ነው ሲሉም ሰማናቸው፡፡ በክፍል ሶስት እንዲሁ የሚጠየቁትን መመለስ ትተው የቡና ላይ ወሬ የሚያወሩ ይስል አስር ግዜ ምን መሰለሽ ትዝታ እያሉ መለስን ቀጥል ባንለው አይሞትም ነበር፣ እኔ አሁን ከሁለተኛ ተርሜ በኋላ እለቃለሁ ሲሉ አነጋገራቸው ሁሉ የውጪ ጉዳይ ምኒስትር አልመስል ያላት ጋዜጠኛ በጤና ጥበቃ ምኒስትርነትዎ እንጠብቅዎት አለቻቸው፡፡ እውነት ብላለች ቢያንስ እዛ ቦታ ሳይሻሉ አይቀሩም፡፡ በአጠቃላይ ጋዜጠኛዋ ትዝታና ዶ/ር ቴዲ አልተገናኝቶም፡፡ ጥያቄና መልሱ ሀራምባና ቆቦ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ዶ/ር ቴዲ እነ አክሊሉ ሀኃብተወልድን የመሰሉ ቀን ከሌት ለሀገራቸው ጥቅምና ክብር ይታትሩ የነበሩ ሰዎች የተቀመጡበት ወንበር ላይ ተቀምጠው እያባነናቸው ነው እንዲህ ከእውነት ጋር የሚጣሉት፣ እያቃዡ ለትዝብት የሚዳረጉት አንበል!

ክፍል 2
 
የጋጠኞቹ የሙዚቃ ምርጫም ለዶ/ር ቴዎድርስ መልእክት ያለው ነበር፡፡ በተደጋጋሚ የተያዘላቸውን ቀጠሮ ሰርዘው በመቅረታቸው ጋዜጠኞቹ ይህንኑ ለአድማጮቻቸው ገልጽው በተለያየ መንገድ የደረሱዋቸውን ለዶ/ር ቴዎድሮስ የተጠየቁ ጥያቄዎችን ከአስደመጡ በኋላ ስለሆነ የቀረቡት ለክፍል ሁለቱ መንደርደሪያ ያጫወቱት የሙሀሙድ አህመድን “የዘገየሽበት ምን ይሆን ምክንያቱ” የሚለውን ዘፈን ነው፡፡ ጥሩ ምርጫ፡፡ ዶክተሩ ለተጠየቁት ጥቄ ለአንዱም ቀጥተኛ ምላሽ ባለመስጠታቸውም ይመስላል ጋዜጠኞቹ ወደ ክፍል ሶስቱ ዝግጅት ያንደረደሩን “ፍቅሬ በምን ቋንቋ በምን ቃል ላስረዳሽ” በሚለው የታምራት ሞላ ሙዚቃ ነው፡፡ አዎ ትዝት የራስዋንም የአድማጮችንም ጥያቄዎች ለማስረዳት ብዙ ደክማ አልተሳካላትምና ጥሩ ገላጭ ሙዚቃ ነው የተመረጠው፡፡

ዛሬ ዶ/ር ቴዎድሮስ በተቀመጡበት ወንበር ላይ የነበሩት ጸኃፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ኃብተወልድ ለዚህች ሀገር የደከሙትን በአካል ኖሮም ይሁን የተጻፈ አንብቦ የሚያውቅ በሁለት ነገር የሚያፍርም የሚያዝንም ይመስለኛል፡፡አንደኛ አንደዛ ቀን ከሌት ማድረግ ከሚገባቸው በላይ ለሀገራቸው የደከሙና በርካታ ውጤታማ ተግባራትን ያከናወኑ ሰው ሊሾሙ ሊሸለሙ ብሎም በክብር ሊጦሩ ሲገባ ይህችው ሀገር ባፈራቻቸው ጉዶች በግፍ በመገደላቸው፤ሁለተኛም በርሳቸው ወንበር ላይ እነ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ እነ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም ሲፈራረቁበት በማየቱ፡፡

እነ አክሊሉ በአርቆ አሳቢነት አንድ ያደረጉትን ሀገር የዶ/ር ቴዎድሮስ ቡድን በዘረኛ አሰተሳሰቡ ሁለት አደረገው፤ ከስንት ወሮበላ ነጭ ጋር ታግለው ከስንት ሀገር በቀል ከሀዲ ጋር ተፋልመው ያስከበሩትን የባህር በር ወያኔዎች የግመል መጠጫ ብለው እንደ እንደአልባሌ ነገር ጣሉት፡፡ በአለም መድረክ ያስከበሩትን ኢትዮጵያዊነት አዋረዱት፡፡( ዛሬ ኩራቴ ኢትዮጵያዊነቴ ሲሉ ቢደመጡም) በዚህ ዘመን መገኘት እንዴት አያሳፍር! ዶ/ር ቴዎድሮስን እያዩና እየሰሙ የቀደሙትን እዛ ወንበር ላይ የነበሩ ታላላቅ ሰዎች ሲያስቡ እንዴት አይነድ እንዴትስ ውርደት አይሰማ!

ሰለ ዶ/ር ቴዎድሮስ የመዋሸት ድፍረት ምክንያት እያሰብኩ ዛሬ ርሳቸው በተቀመጡበት ወንበር እነማን ነበሩ በማለት በማስታወስ ሳሰላስል የአክሊሉ ማስታወሻ በሚል ርዕስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በ2003 ያሳተመውን መጽኃፍ አገኘሁ፡፡ ጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ መስከረም 10ቀን 1967 ዓም ለመርማሪ ኮሚስዮኑ ያቀረቡት ጽሁፍ በሚለው በዚህ መጽኃፍ ውስጥ ከብዙ በጥቂቱ የተገለጸው የአክሊሉ ተግባር በርግጥም በወንበራቸው የሚቀመጡትን በተለይም ለቦታው የማይመጥኑትን የሚያባንን የሚያቃዥ ነው፡፡

ወያኔ በማን አለብኝትና በአፍቅሮተ ሻዕቢያ ሰክሮ ያስገነጠላትን ኤሪትሪያን በተመለከተ ያከናወኑትን ተግባር ኤርትራን ለማስመለስ ያደረግሁት ጥረት በማለት ጸሀፊ ትዕዛዝ እንዲህ ገልጸውታል፡፡

…… ያራቱ መንግሥታት በሎንዶን ተሰብስበው የኢትዮጵያን ሀሳብ እኛ አንሰማለንና በዚህች ቀን አንድትገኝ የሚል መልዕክት አርብ /ሁለት ቀን ሲቀረው/አስታወቁ፡፡ ያን ግዜ አውሮፕላን የለን፤ የእንግሊዝ / B.o.c./ የሚመጣው በሳምንት አንድ ቀን ነው፡፡የትራንስፖርት ችግር ስላለብኝ ለአራትና ለአምስት ቀን አስተላፉልኝ ብዬ ጠየቅሁ፡፡ እነሱም ባልነው ቀን ታልሆነ ብለው ጥያቄየን አልቀበል አሉ፡፡ ችግር ላይ ሆንን፡፡አንድ ትንሽ አይሮፕላን ፤ለጃንሆይ የአንግሊዝ መንግሥት የሰጣቸው ፣አንሬጅስተርድ የሆነች፤ይዤ ለመሄድ ቆረጥሁ፡በሱዳን፤ግብጽ፤ግሪክ፤ፈረንሳይ አገር እያረፈች ቤንዚን በመውሰድ መጓዝ ስላለባት ተነኝህ አምባሰደሮች የተጻፈ ወረቀት ተቀብዬ ቅዳሚት ተነሳሁ፡፡ ሱዳን ደህና ተቀበሉን፡፡ ግብጽ ግን ሉክሶር ስንደርስ ወረቀቱን ባሳየውም “እኛ ተእስራኤል ጋር ጦርነት ላይ ነው ያለነው፡፡

ክፍል 3
 
ይህ ወረቀት እውነት መሆኑን አላውቅም፤ፓይለቱም ነጭ ስለሆነ ታስር ሰዓት /4 afternoon/ በኋላ መብረር ክልክለል ነው፡፡ ስለዚህ በቀጥታ ወደ ካይሮ ሄዳችሁ እዚያ ትመረመራላችሁ ፤ በአውሮፕላን እናስከትላችኋለን አለኝ ” እሽ ብለን ተሳፈርን፡፡ ፓይለቱ ምን ላድርግ አለኝ፡፡ ካይሮ የሄድን ጊዜ ተሰኞ ቀጠሮ ሊሰናከልብኝና የኢትዮጵያ ጉዳይ ሊበላሽ ነው፡፡ ለፓይለቱ ዝም ብለህ ቀይ ባህርን እየተከተልክ ሂድ፤ ሪስክ ማድረግ አለብን አልኩት፡፡ በዚሁ ዝም ብለን እየሰጋን ተጓዝን ፡፡ሜዲትራኒየን ባህር ስንደርስ እፎይ አልን፡፡ ማታ በጨለማ በ3 ሰዓት ሼፐር ደረስን፡፡ ቤንዚን አለቀብን፤እንድንወርድ ፈቃድ ጠየቅን፡፡ መብራት ስለሌላቸው የካሚዎን መብራት አብርተው ለመውረድ ቻልን፡፡ አዚያም አደርን፡፡በማግስቱ ዕሁድ ግሪክ ደረሰን፤ደህና ተቀበሉን፡፡ ወዲያው ተነስተን ፈረንሳይ አገር ማርሴይ አረፍን፡፡ ቤንዚንም ታልከፈላችሁ አንሰጥም ብለው ያልታወቀ አውሮፕላን ነው በማለትም አስቸገሩን ፡፡ በእንደዚህ አኳኋን እንደምንም ሎንዶን ደረስን፡፡ ይህ አንዱ ምሳሌ ብቻ አንዲሆን ነው፡፡ ( ገጽ 46)

አክሊሉ እንዲህ ያለ መስዋዕትነት ሊያስከፍል የሚችል ርምጃ እየወሰዱ፤በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መድረክ በእውቀትም በዲፕሎማሲያዊ ጥበብም በድፍረትም እየተከራከሩ ነበር የኢትዮጵያን አንድነት አስጠብቀውና በአለም አቀፍ መድረክ አስከብረው ያቆዩዋት፡፡ በርሳቸው ወንበር የተቀመጡት ግን ተከራክሮ መርታት አይደለም ሲፈረድባቸውና ሲፈረደላቸው አንኳን ማወቅ ተስኖአቸው አለም አቀፉ ፍርድ ቤት ለኢትዮ ኤርትሪያ ግጭት (የለም ለወያኔ ሻዕቢያ ግጭት ማለቱ ነው እውነት የሚሆነው) ምክንያት ተደርጎ የቀረበውን ባድመን ለእኛ ተፈረደልን ብለው አደባባይ ወጥታችሁ ደስታችሁን ግለጹ አሉን፡፡ የተወሰነው ለኤርትራ መሆኑ ታውቆ ውሸታው ሲጋለጥም ሀፍረት አልተሰማቸውም፡፡በርግጥ ሀገር ሲያረጅ ጃርት ያፈራል፡፡
 

%d bloggers like this: