ለችግሮች መፈታትና ለሰላም መስፈን ግድ የሌለው ሕወሃት በፖሊሱና ደኅንነቱ አማካይነት በኦሮሞ ክልል ተማሪዎች ላይ ድል ተቀዳጅቻለሁ ይላል

3 Dec

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

“በጥቂት ፀረ ሰላም ሀይሎች ተከስቶ የነበሩ ሁከቶች [የሕወሃት] ፀጥታ ሀይሎች ከየአከባቢዎቹ ነዋሪዎች ጋር በመሆን በቁጥጥር ስር አውለዋቸዋል” ይላሉ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢብራሂም ሀጂ ረቡዕ ማምሻውን ለፋና እንደተናገሩት። ዜናውን ለራሴ ሳነበው ቅጥፈት መሆኑን ገና ከመጀመሪያው ዐረፍተ ነገር ስለ ተገነዝብሁ የተለመደው ነገር ብየው ወደ ሌላ ሥራዪ ላመራ ነበር። ነግር ግን ግልጽ ላልሆነላቸው ወይንም መውያየት ለሚፈልጉ የራሴን ድርሻ በዚህ ጽህፍ ለማቅረብ መረጥሁ።

ምናልባትም ሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከተሠማራው ኮማንዶ ኃይል ብዛት አንጻር፣ ይህ አባባል በተማሪዎቹ ማፈግፈግ መልኩ ካልሆነ በስተቀር፡ ይህ የፖለቲካ ችግር ኢትዮጵያውያንን ገና ብዙ የሚፈታተን መሆኑን አዛዣቸው ነፍሰ ገዳዩ አባይ ጸሐዬም ሆነ የኦሮሚያው ፖሊስ ኮሚሽነር የተገነዘቡት አይመስልም።

እንዲያውም ሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በድምጽ ተደግፎ በኢሣት ዜና ላይ ሰሞኑን እንዳዳመጥነው፣ ተማሪዎች ፍርሃታቸውንና ሥጋታቸውን ሲናገሩ፡ የዩኒቨርሲቲው ካምፐስ የጦር አውድማ መስሏል ሲሉ ነበር በፈሠሠው ሠራዊት ብዛት!

ለመሆኑ ምን ይሆን ተማሪዎቹ ሕይወታቸውን መሥዋዕት በማድረግ የሚታገሉለት ዓላማ? የካፊቴሪያ ምግብ አልተስማማንም፤ ወይንም ወዘተ፥ ችግራቸው እንደ ሕወሃት የግል ጥቅሞች ላይ ያተኮረ አይደለም። የኦሮሞ ሕዝብ በሕወሃት አስተዳደር መገፋት ላይና በተለይም በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ስም የሚደረገውን የመሬት ዘረፋና እንዲሁም ኦሮሞን ከታሪካዊ እምብርቱ ከተቀበረበት ቦታ ለማፈናቀል የሚደረገውን የትግራዊው ሕወሃትን ደባ ከመገንዘብ የተነሳና ለማክሸፍ የሚደረግ ትግል ነው!

ይህ በሕወት ደም ውስጥ ያለ በብቸኝነት ሕወሃትንና ትግራዊነት የበላይ በማደረግ የሚያምን አመለካከትና ሥር የሰደደ ፖሊሲያቸው ነው! ሌላውስ የራሱ ኢትዮጵያዊነትና የግል ክብሩስ አለ አይደል እንዴ?

መለስ ዜናዊ አዲስ አባባ ደርሶ ገና ሥልጣኑን በእጁ ሳያስገባ፡ አንባብያን ታስታውሱ እንደሆን፡ ለሲ. አይ. ኤ. [CIA] አገናኙ ፖል ሄንዝ [Paul Henz] ሚያዝያ 3 እና 5 ቀን 1990 ዓ.ም. ሲያወራለት የነበረው ሕወሃት ከትግራይ የዘመተው አዲስ አበባ ሥልጣን ይዞ የነበረውን የሸዋ አማራን አገዛዝ ለማፍረስ ነው ሲል ነበር። ከሞላ ጎደል ያ በራሱ ጉልበትና ሌሎች አማሮችንና ኦሮሞችን ከፋፍሎ ሁሉም እርስ በእርስ እንዲባሉ በማድረግ ተሳክቶለታል – ለጊዜው።

ስለሆነም፡ ዛሬ አማራ ጠንካራ ኃይል የለውም ብሎ ስለሚያምን፡ የሕወሃት ትኩረትም በብዛትና ድርጅት ከአማራው ይልቅ ኦሮሞው ለነእርሱ አሳሳቢው ኃይል ነው በማለት፣ የኦሮሞውን ኅብረተሰብ በፖለቲካና በኤክኖሚው መስክ በማዳከም ላይ ይገኝል። ይህ ከላይ የተጠቀሰውና ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው የመሬት ዘረፋ ኦሮሞች ላይ አተኲራልና የተማሪዎቹ ተቃውሞውም ተጠናክሮ ቀጥሏል። ይህም ለመስፋፋቱ ዛሬ ማምሻውን ኢሣት በሰበር ዜናው በሥዕል አስደግፎና ምንጮቹን ጠቅሶ ከዚህ በታች እንደተመለከተው አረጋግጧል።

 
ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር አባባል ትንሽ ያስገረመኝ “በጥቂት ፀረ ሰላም ሀይሎች” በሞላ የኦሮሞን ሕዝብና ሌሎችንም የኢትዮጵያን ሕዝብ የማይመለከትና የጥቂቶች ሥራ ከሆነ፣ ለምድነው ታዲያ በዜናው ላይ እንደተጠቀሰው “በሀሮማያ እና መዳ ወላቡ ዩኒቨርስቲዎች እንዲሁም፥ በምእራብ ሸዋ እና በምእራብ ወለጋ ዞኖች በሚገኙ አንዳንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ፍንቅል አድርጎ ተቃውሞው እንደገና የተነሳውና የተፋፋመው?

ይህ ለችግሩ “ጥቂቶች” እንዲህ አደረጉ የሚባለው አባባል ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ተበልቶበታልና አሁን ለሕወት ፖለቲካ የሚኖረው አስተዋጽኦ አልቋል ተሟጣል የሚለውን መልዕክት፣ ተዘነጋ ወይንም ተቀባይነት አላገኘም እንጂ፡ ሚያዝያ በ2009 ዓ.ም. በብዕር ስሜ (ገነት መርሻ) ባሠፈርኩት ጽሁፌ Current efforts at changing TEPLF’s image: The cart is before the horse በጥሩ ምሣሌ አቅርቤው ነበር!

ይኸውም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስተዳደር ለ2010 ምርጫ ዝግጅት ላይ ስለነበር፡ አቶ በረከት ስምዖን የመረጃ አሰረጫጨትንና ለማጠናከርና ለማስፋፋት ለልምድ ቀሰማ አንድ ከፍተኛ ገንዝብ የተከፈለው ድርጅት ዘንድ ወደ ሎንዶን ይልከዋል። በአዲሱ አሠራር መሠረትም አቶ በረክት ሃገር ቤት ተመልሰው ከጋዜጠኞችና ሌሎችም ጋር ተቀምጦ በተከታታይ ለመወያየት [twon hall] ጅምር ይደርጋል።

ነገሩ እንደገና ለጥቂት ጊዜ ይቋረጣል። በመጋቢት ወር አቶ በረከት እንደገና ባስቸኳይ ወደ ሎንዶን ያቀናል። ሕወሃት ፍርሃትም ሆነ ድፍረት፡ ቤት ውስጥ ያለውን ችግር ሳያስተካክል፡ አውሮፓ ያለውን በቡድን 20 ስብሰባ ወቅት ኢትዮጵያውያን ትልቅ ተቃውሞ ማደረጃታቸው በመሰማቱ፡ አቶ በረከት ሄዶ ተጻራሪ ኃይል እንዲያዘጋጅ መመሪያ ይሰጠዋል።

በለንደን ኢትዮጵያ ኤምባሲ አማካይነት 200 ነዋሪዎች ተጋብዘው፡ በዛ ያሉ ኢትዮጵያውያን ለመምጣት ፍላጎት ሲያሳዩ፡ ባለ ሥልጣኖቹ ፕሮግራሙን ይሠርዙና በግብዣ ብቻ ብለው እንደገና ሌላ መግለጫ ያወጣሉ። እንዴት የዜግነት መብታችን በሆነው እንዲህ ትሠራላችሁ በማለት ኤምባሲው በር ላይ ብዙ ውዝግብ ተፈጥሮ የሜትሮፖሊታን ፖሊስ ጣልቃ ገብቶ ‘እርግጠኛ’ ኢትዮጵያውያንናን ‘የባህር ማዶ’ ኢትዮጵያውያንን በመለያየት (በተአምር) ኤምባሲውና ከአዲስ አበባ የመጡት ባለሥልጣኖችም በየጎራቸው ሲለያዩ፡ አዲስ አበባዎችም ያሰቡት ሳይሳካላቸው ወደ አዲስ አበባ ይመለሳሉ።

ለሎንዶኑ የቡድን ሃያ ላይ ኢትዮጵያውያኑ ተጠራርተው፡ ሚያዝያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም.ከፍተኛ የተቃውሞ ሠልፍ ማድረጋቸው ትዝ ይለኛል።

አቶ በረከት አዲስ አባበ እንደደረሰ፡ መጀመሪያ የፈጸመው ግዙፍ ስህተት፡ ጋዜጣዊ መገለጫው ላይ ሰለዚሁ ሠልፍ ተጠይቆ እንዴት አንዳንኳሰሰው ነው – ‘ከ15 እስከ 25 የሚሆኑ ችግር ፈጣሪዎች’ ግርግር ነው ብሎት አረፈ።

በወቅቱ ክሥዕሎችና ፉቴጅ በወሰድኲት ግምት እኔ በጻፍኩት ወቀሳ ውስጥ የሠልፈኞቹ ቁጥር 30 እስከ ሃምሣ ዕጥፍ በረከት ካለው እንድሚሆን ነበር!

ሁለት ቀናት ከዚህ የለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አሳፋሪ የዘረኝነት ሁኔታ በኋላ፡ The Economist የተሠኘው ሣምንታዊ ማጋዚን The tiny minority በሚል አርዕስት አንድ አስገራሚ ጽሁፍ መጋቢት 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ያወጣል። ለአቶ በረከት የተዘጋጀ እስኪመስለኝ ድረስ፡ በአጠቃላይ ዓላማው ለመንግሥታት ሁሉ ሆኖ፡ ይዘቱም “እነዚህ ጥቂት ሰዎች” እያላችሁ የምታምታቱትን ነገር አቁሙ የሚል ነበር። ሲዘረርዝርም ባጌሆት [Bagehot] እንዲህ ይላል፦

  “Insisting that worrisome minorities are ‘tiny’ is in part a form of wishful thinking, as if saying something often enough could make it true, and rhetorical tininess could shrink reality. This sort of euphemism is sometimes a kind of self-delusion as well as a deception. But it is perilous all the same. All those minorities add up to a society in denial.”

ወደ ሁለተኛው ምክንያቴ ስመለስ፣ ማለትም ለምን ይህ የአሁኑ የኦሮሞ ተማሪዎች ቁጣ “የጥቂች ሥራ አለመሆኑን ለመግለጽ፣ ለኔ የሚታየኝ ባለፈው ዓመት ሚያዝያና ግንቦት ውስጥ በሁሉም የኦሮሚያ ሁለተኛ ደረጃ ትምንህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ክፉኛ የተጠናከር የተማሪዎች ተቃውሞ ተካሂዶ፡ ቁጥራቸው ከ70 እስከ 100 የሚጠጋ የዩኒቨርሲቲና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በአጋዚ አነጣጣሪ ተኳሾች መገደላቸውን እያወቁ፡ ዛሬም ናዚው ሕወሃት እንደሚያስጨፈጭፋቸው ማስጠንቀቂያው በታወቀው ነፍሰ ገዳይ አባይ ጸሐዬ ክተሰጠ በኋላ፡ እነዚህ ተማሪዎች “በጥቂት ፀረ ሰላም ሀይሎች” ብቻ በመነሳሳት ራሳቸውን መሥዋዕት ያደርጋሉ ብሎ ለማሳመን መሞከር የተለመደ የሕወሃት ዐይን አውጣነት ታዋቂ ባህሪ ነው!

በኢትዮጵያዊነት የሚታሰብ ከሆነ፣ ይህ ሕወሃት የሚሄድበት ጎዳና አሳፋሪና ዛሬም ነገም ሃገር ጎጂ ነው! ከሁሉም የከፋ፣ ሕወሃት ዘረፋውን አዲስ አበባ ዙሪያ ላይ ሲያጠናቅቅ ነገ ወደ ደቡብ፣ አርሲ፡ ጎጃምና ጎንደር ወዘተ ተመሳሳይ የጥጋበኛ ዱላውን ከመጠቀምና ዘረፋውን ከማካሄድ ምን ይገታዋል?

እዚህ ላይ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ብሄረስቦች ሊያስቡበት የሚገባው ነገር ቄስ ማርቲን ኒየሞሌር [Martin Niemöller] በችግር ጊዜ ያስታወሰው በራስ ላይ የተመሠረተ ልምድና ክዚያም የመነጨው ጥቅስ ነው፦

  “First they came for the Socialists, and I did not speak out
  — Because I was not a Socialist.

  Then they came for the Trade Unionists, and I did not speak out—

  Because I was not a Trade Unionist.

  Then they came for the Jews, and I did not speak out
  — Because I was not a Jew.

  Then they came for me—and there was no one left to speak for me.”

 

ኮምሽነነር ኢብራሂም ሃጂ ለፋና ሠጡት የተባለው መረጃ የሚከተለው ነው፦

  በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ የትምህርት ተቋማት ተከስቶ የነበረው ሁከት በአብዛኛው በቁጥጥር ስር መዋሉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ

  አዲስ አበባ ፣ ህዳር 22 ፣ 2008 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አንዳንድ የትምህርት ተቋማት ባለፉት ቀናት ተፈጥረው የነበሩ ሁከቶች በአብዛኛው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ።

  የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢብራሂም ሀጂ ማምሻውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ በሀሮማያ እና መዳ ወላቡ ዩኒቨርስቲዎች እንዲሁም፥ በምእራብ ሸዋ እና በምእራብ ወለጋ ዞኖች በሚገኙ አንዳንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በጥቂት ፀረ ሰላም ሀይሎች ተከስቶ የነበሩ ሁከቶች የፀጥታ ሀይሎች ከየአከባቢዎቹ ነዋሪዎች ጋር በመሆን በቁጥጥር ስር አውለዋቸዋል።

  ተቀስቅሰው በነበሩ ሁከቶች እና ይህንንም በቁጥጥር ስር ለማዋል ሲደረግ በነበረው ጥረት ውስጥ በሰው አካል ላይ እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ነው ከሞሽነር ኢብራሂም ያስረዱት።

  ነገር ግን ዛሬ በምእራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጨልያ በተባለ አከባቢ በተፈጠረ ሁከት የአንድ ተማሪ ህይወት ብቻ ማለፉን አስታውቀዋል።

  ይህ ሁከት ጥቂት የሚባሉ የአገሪቱ የለውጥ ጉዞ የማይዋጥላቸው እና ይህንንም ማደናቀፍ የሚፈልጉ ወገኖች አጀንዳ በመፍጠር የትምህርት ተቋማትን ለመጠቀም በመሞከራቸው የተፈጠረ መሆኑን ኮሚሽነር ኢብራሂም አስረድተዋል።

  በአጠቃላይ ግን እስካሁን የተፈጠረው ሁከት ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ አለመውጣቱንም ነው የገለፁት።

  በምእራብ ወለጋ ዞን አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ላይ ፀረ ሰላም ሀይሎች አነሳሽነት ሁከት የመፍጠር ጥረታቸው የሚስተዋል በመሆኑ በእነዚህ አከባቢዎች የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።

  በእስካሁኑም የየአከባቢዎቹ ነዋሪዎች ከፀጥታ ሀይሎች ጋር በመሆን የህግ የበላይነትን ለማስከበር ላሳዩት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

 

%d bloggers like this: