የመንግስት መዋቅር ማሻሻያ ሃሳብ! – ከባለ ለዛው የኢትዮጵያውያን ፖለቲካ ቀልድና ቧልት የተጨለፈ

7 Dec

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
በውብሸት ታደለ

እኔ ውብሸት ታደለ የተባልኩ ፓርቲዬንና መንግስቴን የምወድ ልማታዊ ዜጋ ስሆን የመንግስታችን አወቃቀር ላይ ማሻሻያ እንዲደረግበት የሚከተለውን የማሻሻያ ሃሳብ ሳቀርብ ፓርቲዬና መንግስቴን ያስደስታል በሚል ብቸኛ ዓላማ ነው፡፡

የአገሪቱ ሚንስቴሮችና ሌሎች ተቋማት በየዘርፉ ተዋህደው የተቀናጀ እንቅስቃሴ ቢያደርጉ ለክትትልና ለሪፖርት ስለሚመች ሚኒስቴር መስሪያቤቶችንና ሌሎች ተቋማትን ወደ አራት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ብናጠቃልላቸው መልካም ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ እነሱም የሚከተሉት ናቸው፡-

1ኛ. ልክ ማስገባት ሚኒስቴር፡-

ይህ መስሪያ ቤት የደህንነት፣ መከላከያ፣ ፖሊስ፣ ማረሚያ ቤት፣ ፍርድ ቤት፣ ወዘተ. መስሪያ ቤቶችን ስራዎች በመጠቅለል ህዝብን ልክ የማስገባት ስራ እንዲያከናውን ሆኖ ይዋቀራል፡፡ ዜጎችን በመግረፍ፣ በማሰቃዬት በመግደልና በማሰር ልክ በማስገባት የአገራችንን ህዳሴ እውን ያደርጋል፡፡ በዚህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ የድራማ ዳይሬክቶሬት የሚቋቋም ሲሆን ፍርድ ቤቶች፣ ፀረ-ሽብር ግብረ ሃይልና ብሄራዊ ትያትር በዚህ ዳይሬክቶሬት ስር ሆነው መንግስታችንን የሚረብሹትን ኃይሎች ልክ ለማስገባት አስፈላጊውን ድራማ የሚሰሩ ይሆናል፡፡ የዚህ ሚኒስቴር ሚንስትር እንዲሆኑ በእጩነት እንዲቀርቡ አስተያዬቴን የማቀርበው አቶ አባይ ፀሃዬን ነው፡፡ አቶ አባይ ፀሃዬ በትግል ወቅት ከመለስ ዜናዊ ጎን የነበሩ የመለስ ሜንቶር ሲሆኑ ልክ ማስገባትን ከአቶ መለስ በማይተናነስ መልኩ ያውቁበታል፡፡ በቅርቡም ለህዝባችን የገቡትን ልክ የማስገባት ቃል በማክበር ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በመሆኑም አቶ አባይ ፀሃዬ የልክ ማስገባት ሚኒስቴር እንዲሆኑ አስተያየቴን አቀርባለሁ፡፡
 

2ኛ. የቅጥፈትና ድንቁርና ሚኒስቴር፡-

ይህ መስሪያ ቤት ኢቢሲን፣ ኮሚኒኬሽንን፣ ስታትስቲክስ ባለስልጣንን፣ ትምህርት ሚኒስቴርን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን፣ ገንዘብና ኢኮኖሚን፣ ወዘተ. በማጠቃለል ህዝቡንና ሌሎች አገራትን በቅጥፈት የመሙላትና በድንቁርና የተካነ ልማታዊ ሰራዊት የመፍጠር ስራ የሚሰራ ይሆናል፡፡ የቅጥፈት ስራዎችን ከስድብና ዘለፋ ጋር ጎን ለጎን የሚያከናውን ሲሆን የድርጅታችን ርዕዮተ-ዓለማዊ መሰረት በዚህ መስሪያ ቤት ላይ የሚቆም ይሆናል፡፡ የአጭር ጊዜ ቅጥፈቶችንና ውሸቶችን በመቀመር ህዝብን የማደንቆር ስራን በኢቢሲና መሰል ተቋማት ተሞክሮ ማከናወን የሚቻል ሲሆን ለፈረንጆች የሚቀርብን ቅጥፈት ደግሞ በገንዘብና ኢኮኖሚክስ፣ በስታትስቲክስና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮች ተሞክሮ በዳይሬክቶሬት ደረጃ ማቋቋም ይቻላል፡፡ የረጅም ጊዜ ህዝብን የማደንቆር ተልዕኮን ደግሞ ከትምህርት ሚኒስቴር ልምድ በመቅሰም የዘላቂ የድንቁርና ስራዎች ዳይሬክቶሬት ይቋቋማል፡፡ የቅጥፈትና ድንቁርና ሚኒስቴርን እንዲመሩ በእጩነት ቢቀርቡ ብዬ አስተያየቴን የማቀርበው ለዶ/ር ቴወድሮስ አድሃኖም ነው፡፡ ዶ/ር ቴወድሮስ በቅጥፈት ሙያ የተካኑ ሰው መሆናቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲናገሩ የሰማ ሰው የሚያረጋግጠው ጉዳይ ነው፡፡

ዶ/ር ቴወድሮስ ይህን ሚኒስቴር ቢመሩት በአጭር ጊዜ ውስጥ ድንቁርናን የማስፈን ብቃት አላቸው ብዬ ስላሰብኩ እሳቸውን የቅጥፈትና ድንቁርና ሚኒስቴርን እንዲመሩ አስተያየቴን አቀርባለሁ፡፡
 

3ኛ. የዘረፋ ሚኒስቴር፡-

ይህ መስሪያ ቤት የመንግስታችንን ዋና የልማት ስራ የሚያከናውን ሲሆን የመሬት አስተዳደር፣ የከተማ ልማት፣ ማዕድንና ኢነርጅ፣ ገንዘብና ኢኮኖሚ፣ መንገድ ስራዎች፣ ወዘተ. በዚህ መስሪያ ቤት ውስጥ የሚጠቃለሉ ይሆናል፡፡ የዘረፋ ተግባራችን ሰፊና ውስብስብ በመሆኑ ለዘረፋው ከለላ በመስጠት የሚያገለግለው ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በዳይሬክቶሬትነት ይዋቀራል፡፡ ሚኒስቴሩ የህወአት ባለሃብቶችን ለመፍጠር እንደባቡር፣ ግድብ፣ ወዘተ. ፕሮጀክቶችን እየነደፈ የህወኣት ባለሃብቶች ከቻይና ጋር ዝርፊያውን እንዲያጣድፉት መንገዱን ይጠርጋል፡፡ እንደ አፋር፣ ጋምቤላና ቤንሻንጉል የመሳሰሉትን ክልሎች በመጠቀም ትልልቅ ባለሃብቶችን ይፈጥራል፣ ማዕድኖችን ይቸበችባል፣ መሬት ይቸረችራል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ አገሪቱን የማራቆትና የዘረፋ ስትራቴጅውን የማስፈፀም ስራውን ለማከናወን ብዙ ሰዎችን በዕጩነት ማቅርብ የሚቻል ሲሆን ለጊዜው ወ/ሮ አዜብ መስፍንን በእጩነት እንዲቀርቡ አስተያዬቴን እሰጣለሁ፡፡ ወ/ሮ አዜብ ኤፈርትን በመቆጣጠርና የጫት ንግድን በማጧጧፍ ሰፊ ልምድ ያላቸው ሴት ሲሆኑ ከባላቸው ጀርባ ሆነው ሰፊ የዝርፊያ ተግባራትን ለእናት አገራቸው ሲያከናውኑላት የነበሩ ታታሪ ሰው ናቸው፡፡

በመሆኑም የዘረፋ ሚኒስቴርን ወ/ሮ አዜብ መስፍን ቢመሩት በማለት አስተያዬቴን አቀርባለሁ፡፡
 

4ኛ. ድግስና ስብሰባ ሚኒስቴር፡-

ይህ መስሪያ ቤት ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የአገሪቱን መደበኛ በጀት የሚያስተዳድር ሲሆን ከዘረፋ ሚኒስቴር ጋር በትብብር ይሰራል፡፡ ትልልቅ ድግሶችን በማዘጋጀት አገራችን በጭፈራና ዕልልታ የተሞላች ለማድረግ የሚንቀሳቀስ ሲሆን የቲ-ሸርቶችንና ኮፍያዎችን እንዲሁም ተዛማጅ የድግስ ወጭዎችን በመሸፈን ለዘራፊዎቹ የገቢ ምንጭ ያመቻቻል፡፡ ከመያዶች የሚመጣውን ዕርዳታ ተከትሎ ስብሰባዎችን በማዘጋጀት ለተባባሪ አካላት አበልን ተደራሽ ያደርጋል፡፡ ሴቶችና ህፃናት፣ ሰራተኛና ማህበራዊ፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ኤች አይ ቪ መከላከያ ሴክሬታሪያት፣ ወዘተ. በዚህ ሚኒስቴር ውስጥ ተጠቃለው ስብሰባና ድግስ እንዲያፋፍሙ ይደረጋል፡፡ ከብሄር ብሄረሰቦች ቀን፣ ከባንዲራ ቀን፣ ከከተሞች ቀን፣ ከህወኣት ልደት፣ ከብአዴን ልደት፣ ወዘተ ልምድ በመቅሰም ትልልቅ ድግሶችን የሚያከናውን ይሆናል፡፡ ይህን ሚኒስቴር እንዲመራ በእጩነት ይቀርብልኝ ዘንድ አስተያዬቴን የምሰጠው ለአቶ ደመቀ ግርማ [መኮነን] ነው፡፡ አቶ ደመቀ ለድግስ ካላቸው ቅርበትና በምክትል ጠ/ሚኒስቴርነት ለሆዳቸው ያላቸውን ታታሪነት የገለፁ ቁርጠኛ አመራር ሲሆኑ በንግግራቸው ውስጥ አንድም ፍሬ ሃሳብ ባለማስቀመጥ ስብሰባዎቻችን የታለመላቸውን ሰው የማሰልቸትና የማደንዘዝ ግብ እንዲመቱ ለማድረግ ሲታትሩ የኖሩ መሪ ናቸው፡፡ ለመንገድ ምርቃትም ይሁን ለተማሪ ምርቃት ንግግራቸው የማይለያየው አቶ ደመቀ በንግሮቻቸው ውስጥ “አስተሳስረን… አቀናጅተን…” ወዘተ የሚሉትን ቃላት ብቻ እየቀያየሩ በመጠቀም የስብሰባዎቻችንን ግብ ለማሳካት የቻሉ ሰው ናቸው፡፡

በመሆኑም አቶ ደመቀ ግርማ [መኮነን] የድግስና ስብሰባ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው እንዲሾሙ አስተያዬቴን አቀርባለሁ፡፡

አመሰግናለሁ!

ተዛማጅ ጽሁፍ፡

አንተም ደመቀ መኮንን!
 

%d bloggers like this: