አዲስ አባባ ቦምብ መፈንዳቱን ፋናና የውጭ ዜና ማሠራጫዎች አሰሙ! ማን አፈነዳው ለሚለው ሁሉም ከታሪከ በመነሳትና ከአጻጻፋቸው ሕወሃት መሆኑ የሚጠፋቸው አይመስልም!

11 Dec

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

ላለፈው አንድ ወር ያህል የኦሮሞ ተማሪዎች፣ ወላጆቻቸውና መንደርተኛው ሁሉ በአዲስ አበባ ከተማ ልማት ስም የሕወሃትን የመሬት ወረራ በመቃወም እየተጠናከረ የመጣ ሰላማዊ ሠልፍ ሲያካሄዱ፡ በተለምዶ ከሕወሃት አፍ የማይወርደው “ሽብርተኛ” የሚለው ቃል ጠፍቶ ነበር። በምትኩ የሕወሃትና ጀሌዎቻቸው ተተኪ ስድብና ዛቻ ሲገለጽ የከረመው በተዛማጅ ቃላት፣ ማለትም ለምሣሌ አይጋ ፎረም “ጠባቦች”፣ “ትምክህተኞች”፣ “ኪራይ ሰብሳቢዎች” በመሳሰሉት በማቅራራት ሲሆን፣ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ደግሞ “ጸረ-ሰላም ኃይሎች” በሚሉት ከሰሞኑ በተቃራኒ ሃሣቦች መካከል የሚይዘውን የሚጨብጠውን አጥቶ ሲንከላወት ፌዴሬሽን ይህ ከህነ በአፍንጫየ ይውጣ የሚል ይመስል ነበር።

በተለይም ሁለት ጊዜ በከፍተኛ ባልሥልጣኖቹ አማክይነት ማስፈራራትንና ማግባትን የሞከረው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት “የክልሉ ወጣትም ከሁከቱ ጀርባ ያለውን አፍራሽ ዓላማ ተረድቶ” ራሱን የእነዚህ የፀረ ሰላም ሀይሎች ተልዕኮ ማስፈፀሚያ ከመሆን እንዲጠብቅ” አልሆነላቸውም እንጂ ለማሳሰብ ሞክረውም ነበር።

በሌላ በኲል ደግሞ የኦሮሚያ ክልል አሰተዳደር በፍጹም ቅጥፈት “በሁከቱ ውስጥም ተሳትፎ የሚያደርጉ ጦር መሳሪያ ሁሉ የታጠቁ አካላት መኖራቸው መረጋገጡን” የክልልሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ፋና ላይ ገልጿል። ይህ ከሆነ ለምን አለተያዙም ለሚለው መልስ የላቸውም!

ዋናው ነጥብ ግን ሕወሃትም ሆነ የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ያሰቡት ሁሉ፣ ኃይልን መጠቀማቸው ጭምር የፈለጉትን ለማግኘት ስላላስቻላቸው፣ ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ ዙር ኦሮሞ ተማሪዎችን መጨፍጨፍ ላይ ከተሠማራ በኋላ ሕወሃት እንደዳደረገው፡ ያሉ የሌሉትን እንደ አባዱላ ገመዳ ዐይነት ሕወሃታዊ አሮሞች አማካይነት በየዩኒቨርሲቲዎች ቢልክም፣ ራሳቸውን እንኳ ማክበር ከማይቹሉ ሰዎች ጋር መነጋገር እንደማይሹ በመግለጽ፣ ተማሪዎቹ እነ ወርቅነህ ገበየሁን ዐይናቹ ለአፈር ይሁን ብለው አባረዋቸዋል!

የሕወሃት ችግሩ፡ አንድን ነገር ደጋግሞ በማድረጉ ብቻ እርሱ የሚጠብቀውን ወይንም የተሻለ ውጤት የሚያገኝ ይመስለዋል! ችግሩ ግን ይህ ደግሞ ለተመልካች ወይንም በጠረጴዛ ዙሪያ ለሚገጥመው ምን ዐይነት የዞረበት ነው የሚያሰኘውን ትዝብት ብቻ ያተርፍለታል!

የተማሪዎቹ ጥያቄ ግልጽ ነው! በከተማ ልማት ስም ከዚሀ በፊት እነ አያት ዐይነት ሪል ስቴት ደርጅቶች ሃገር ውስጥ አስገብቶና፡ አቋቁሞና አደራጅቶ ግልጽ የሆነ የመሬት ወረራ ከ1997 ጀምሮ በማካሄድ የፈጸመው ሕዝብ የማራቆትን ወንጀል የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚገብ ተገንዝቦታል፡፡ በዚህም ምክንያት ሕወሃትን ከእርሱ በኋላ የቆሙትን ፊታውራሪዎቹን፡ ጦሩንና ደኅነነቱን አንቅሮ ተፍቷቸዋል!

ሙክታር ከድር በመልዕክተኝነት ዛሬ አርብ ታህሳስ 1 ቀን ያሰማው ሃሣብ፣ ከርሱ የፈለቀ ሣይሆን በል የተባለውን ከማሰማት ባሻገርም፣ ለመደራደር እንኳ ውክልና በሌለው ጉዳይ ላይ “በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተቀናጀ የጋራ እቅድ ጋር ተያይዞ ሁከት መነሳቱን” አስታውሶ፣ “ይህ ሊከሰት የቻለውም እቅዱን ግልጽ ለማድረግ ውስንነት በመኖሩ ነው” ብሏል።

ይህ ከሆነ ታዲያ ለምንድነው እርሱ የሚመራው አስተዳደር ተወካይ የሆነው የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መብታቸው እንዲከበር የጠየቁትን ተማሪዎች “ባልተገባ መንገድ [ሕዝቡን] በማነሳሳት ለአመፅ እና ብጥብጥ እየዳረጉ ነው” በማለት ለመወንጀል የደፈረው? በአጭር አባባል ብዙ አብረው የማይሄዱ ብቻ ሳይሆን፡ እርስ በእርስ ሰለሚቃረኑ ነገሮች ላይ ሁሉም የሚዘባትሉት?

ይባስ ብሎ በሕወሃት የተለያዩ ተቃርኖዎች እየተገረምንና፡ የእነርሱንም ዛቻዎች በስሌት ውስጥ በማስገባት መቼ ነው ለመብታቸው የሚታገሉትን ግለሰቦችና የጎሣ ስብስቦች ሕወሃት ማረድ የሚጀምረው ብለን ስንጠባበቅ፣ ለጊዜው አሁን በአንድ ቦምብ ፍንዳታ የሚቀጥለው ትዕይንት መድረክ የተከፈተ ይመስላል!

The Great Anwar Mosque
ሕወሃትን በታሪኩ እንደምናውቀው፡ ከሃውዜን ጀምሮ እስከ አዲስ አበባ ተደጋጋሚ የቦምብ ፍንዳታ የፈጸመ ረ-ሕዝብ፣ ጸረ-እኩልነት፣ ጸረ-ዴሞክራሲ በመሆኑ፣ አሁንም የዛሬው ቦምብ መስጊድ ወስጥ መፈንዳቱ ማንንነቱን የሚያረጋግጥ የአሸባሪነቱ ምልክት ነው!

በ2006 ዓ.ም. ዊኪሊክስ እንደዘገበው፡ የሕወሃት ደኅንነቶች ሶስት ስዎች (ኦሮሞች) አስረው ከገረፉና ካቆሳሰሏቸው በኋላ፣ ቦምብ ለማፈንዳት ሲዘጋጁ ተይዘው ነው በማለት ለሚዲያ የሠጠው መረጃ እንደዛሬው ሁሉ ሃስተኛ መሆኑን የማይጠራጠር ያልተነካ ባለድሎት ብቻ ነው! በወቅቱ የአሜሪካ ኤምባሲ ተወካይ የነበሩት ሃድለስቶን (Vicky HUDDLESTON) የሚከተለውን መረጃ ለስቴት ዲፓርትመንት አስተላልፈው ነበር፦

    “Clandestine reporting indicates that the bombs did not explode inside the structure, but rather appear to have been placed outside and detonated.”

ዛሬም የቦንብ ፍንዳታው ሲዘገብ፡ ፋና ባቀረበው ዜና ፍንዳታው የነበረው “አዲስ አበባ አንዋር መስጅድ አካባቢ” እንጂ መስጊድ ውስጥ እንዳልሆነ ነው። ብሉምበርግ ከሁሉም ቀድሞ ወደ ቀትር ላይ ባቀረበው ዜና በአርዕስቱ ላይ Explosion hits mosque in Addis Ababa, after weeks that saw protests rock Ethiopia over city’s expansion ይላል።

የዜና ምንጩ በዚሁ ዘገባው “The explosion struck Anwar Mosque in the city’s Mercato market area as worshipers left Friday prayers at about 1:30 p.m.” ቀጥሎም ሲዘግብ፦ “The grenade attack came as Ethiopia’s capital, which has been generally secure in recent years, also saw the Ethiopian opposition claiming that about 10 university students have been killed in the past three weeks by Ethiopian police.”

ፋና በስለላና ደኅንነት ድርጅቱ ብዙ ጊዜ ሙሉ መረጃ የሚሠጠው ሆኖ ሳለ፡ የቦንቡን ፍንዳታ እንዴት አድርጎ ነው ከመስጊዱ አጠገብ ፈነዳ ብሎ የዘገበው – መስጊዱ ውስጥ መፈንዳቱ እየታወቀ? ይህ ብዙ ያነጋግራል በተለይ የሕወሃትን ማንነት ጠንቀቅ አድርገው በሚያውቁ ዲፕሎማቶች፣ የመንግሥት ባለሙያዎች፡ ግለስቦችና ምሁራን በኩል።

ነገሩ የኦሮሞ ተማሪዎችን መራር ተቃውሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ውስጥ ለውስጥ ከሚተንገተገው የእስላሞት ቁጭና ምሬት ጋር ለማያያዝ ከሆነ፡ ለአንድ ብዙ ገንዘብ የሚፈስለት ሙሉ በሙሉ ትግራዊ ለሆነ የስለላ ድርጅት ይህ ግዙፍ ውደቅትና ውርደት ነው!

ይህ ዝቃጭ፡ የወሮ በላ የውንብድና ሥራ፡ ከአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤትና ባለሥልጣን አይታሰብም!

ትክከለኛውን የኢትዮጵያውያንን የመብቶች ትግል አያግተውም፡ እንዲሁም የሕዝባችንን የሕወሃትን ጀርባ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማየት መጓጓት ከቀን ቀን እየጨመረ በመሄድ ዕድሜውን ያሳጥረዋል!

%d bloggers like this: