ለኢቢሲ 50ኛ ዓመት በዓል የተመደበው ዘጠኝ ሚሊየን ብር ወደ ሶስት ሚሊዮን ተቀነሰ!                           – ፀረ ሙስና ኮሚሽን አልሰማሁም አለ!

12 Dec

የአዘጋጁ አስተያየት፦

  ሃገራችንን እግዚአብሄር በተአምሩ ይታደጋት እንጂ – የግብዣ ነገር ሲነሳ – አንድ ያስገረመኝ ነገር ሕዝቡ በሚሊዮኖች በርሃብ እየተቆላ፡ ብአዴን የብር 300 ሚሊዮን ደግሶ መምነሽነሹ ነበር!

  የአማራ ክልል አስተዳዳሪ ገዱ አንዳርጋቸው (ፎቶ ፋና)

  የአማራ ክልል አስተዳዳሪ ገዱ አንዳርጋቸው (ፎቶ ፋና)

  ታዲያ ብአዴን ሠርግና ድግሱን በጨረሰ ማግሥት ኅዳር 26፣ 2008 በአስተዳዳሪው በገዱ አንዳርጋቸው አማካይነት 2.2 ሚልዮን ሕዝብ ለክፉ ርሃብና ችግር ተጋልጧል በማለት ማወጁን ፋና ዘግቦለታል!

  በሃገራችን አዲስ የተያዘው ፈሊጥ፡ ግብዣ፡ ጮማ መቁረጥና ከዳንኪርታው ባሻገር፡ በዚህ መልክ የሚዘረፈው ገንዘብ ብዛትና መጠነ ነው። የፖለቲካ ድርጅቶቹ ተመሰጣጥረው ደጋሽም እነርሱ፡ ዕቃ አቅራቢም እነርሱ በመሆናቸው፡ የበዓል አከባበር ብዛትና ወጭያቸው የሚያመልክተው፣ ለዘረፋ ያላቸውን ርሃብና ጥማት ነው! ለዚህ ግንባር ቀደሞቹ የሕወሃት ሰዎች መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቀዋል፣ ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት እነርሱ ከየካቲት እስከ ግንቦት ያደረጉትን ብአዴኖችም በአጭር ጊዜ በመከወን ካለቆቻውም ብሰው ቢገኙም!

  ስለዚሁ የግብዣዎች መብዛትና የወጭው ስፋትን የሚመለከት ጥያቄ ለጠቅላይ ሚኒስተር ተብየው አቅርበውለት የሠጠውን የሚከተለውን የተለመደውን የቅጥፈት መልሱን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይዳኘው፡፟

  ጥያቄ፦ ይህ ድርቅ ባለበት ወቅት ሰሞኑን ብአዴን 35ኛ ዓመቱን በተለያዩ ዝግጅት ሲያከብር ነበር፡፡ ለዚህም ዝግጅት በርካታ ገንዘብ ወጥቷል ተብሎ ይገመታል፡፡ አሁንም የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን ለማክበር በዝግጅት ላይ ናችሁ፡፡ እንደሚታወሰው በንጉሡ ጊዜ በተከሰተው ድርቅ ንጉሡ ለልደታቸው ኬክ ያወጡት ወጪ ከፍተኛ ነበር ብለው ተተችተዋል፡፡ በተመሳሳይም ደርግ በአገሪቷ ውስጥ ድርቅ እያለ ለአብዮቱ 10ኛው ዓመት በዓል ከፍተኛ ወጪ ማውጣቱ አስተችቶታል፡፡ መንግሥቶት ለእነዚህ በዓላት ያወጣውን ወጪ ከቀድሞው መንግሥታት በድርቅ ጊዜ ካወጡት ወጪ ጋ ተመሳሳይነት አለው በማለት የሚተቹ ወገኖች አሉ፡፡ ይህ ከሞራል አኳያም ተገቢ አይደለም ይላሉ፡፡ ለዚህ ምላሾት ምንድነው?

  መልስ፦ በመጀመሪያ ደረጃ በዓሎቻችን እንደ ማንኛውም ሥራ አንድ የሥራ አካል ናቸው ብለን ነው የምናምነው፡፡ በዓሎቻችን የፈንጠዝያና የዳንስ በዓላት አይደሉም፡፡ እንደምታውቁት ትልቁ የዚህ አገር ሀብት የሕዝብ አዕምሮ፣ የሕዝብ አስተሳሰብ፣ የሕዝብ አመለካከት መቅረጽ ነው፡፡ አመለካከቱና ተነሳሽነቱ ካለ ተራራ መናድ እንችላለን፡፡ ስለዚህ በዓሎቻችን የልደት በዓላት አይደሉም፡፡ የድሮ መንግሥታት የልደት በዓሎቻቸውን ነበር ሲያካሂዱ የነበሩት፤ የግለሰብ በዓሎች ነበሩ፡፡ ይሄ ግን የሕዝብ በዓል ነው፡፡ ይህን በዓል ስናከብብር ሕዝቡ የበለጠ ለልማት እንዲነሳሳ፣ የበለጠ ወደፊት እንዲገሰግስ፣ የበለጠ አንድነቱን እንዲያጠናክር፣ የበለጠ ግንኙነቱን እንዲያሰፋ የሚያደርግ ነው፡፡ በአንድ በኩል በዓሎቻችን ሥራ ናቸው፡፡ አንድ ትልቅ ሥራ፣ ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠርባቸው ናቸው፡፡ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ሥራ አይደለም ተብሎ ከተወሰደ ይሄ ስህተት ነው፡፡ እስካሁን ድረስ አገሪቷ ያጣችው ነገር ቢኖር ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ዙሪያ ነው፡፡ የጋራ አስተሳሰብ በመያዝ ዙሪያ ያለ ጉድለት ነው፡፡ እናንተም የሚዲያ ተቋማት የምትለፉት የእናንተም ሥራ ላይሆን ነው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የሕዝብ አዕምሮ ነው የምትቀርጹት፡፡ የሕዝብ አዕምሮ መቅረጽ ሥራ አይደለም ከተባለ ትክክል አይደለም፡፡

  ሁለተኛው ለእነዚህ በዓላት የወጣው ወጪ ምንድን ነው? ለእነዚህ በዓላት ሕዝቡ እንደማንኛውም ጊዜ ከቤቱ መጥቶ በዓሉን ተካፍሎ ይሄዳል እንጂ እኛ ውስኪ አንራጭም፡፡ ቢበዛ ውኃ ነው የምንጠጣው፡፡ ስለዚህ በዓሎቻችን በጣም በትንሹ ወጪ የሚወጣባቸው ናቸው፡፡ ከድሮ ሥርዓቶች ጋር ሊወዳደር አይችልም፡፡ በዓሎቻችን የሕዝብ በዓላት ናቸው፡፡ እኛ ገንዘብ አናወጣም፤ ሕዝቡ ነው ከየቤቱ ወጥቶ ስብሰባ የምናካሂደው፡፡ ስብሰባ ለማካሄድ ወጪ አናወጣም፡፡ የብአዴን 35ኛ በዓል በየከተሞቹ ስብሰባ በማካሄድ ነው የተደረገው፡፡ በዚህ ስብሰባ ቢበዛ ሰው ትንሽ ውኃ ጠጥቶ ተመልሶ ይሄዳል፡፡ ይሄን ያህል ወጪ አልወጣም፡፡

  በዓሎቻችን ወጪያቸው እጅግ ዝቅተኛ የሆነ ሕዝቡ ራሱ የሚሳተፍበት እንጂ በመንግሥትም ሆነ በድርጅት ወጪ እየወጣ አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ የብአዴን አባሎች በሒደትም የኢሕአዴግ አባላት በሙሉ ከኪሳቸው አውጥተው ለዚህ ድርቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በዚህ አኳያ ብአዴን 30 ሚሊዮን ብር ከአባላቱ መዋጮ አውጥቶ ለድርቅ ሰጥቷል፡፡ ማሳየት የፈለገው ምንድን ነው አባላት የበለጠ ያወጣሉ እንጂ ተጨማሪ ወጪ እያወጡ አይደለም፤ ለድርቅ የበለጠ እያዋጣን ነው የሚለውን ለሕዝቡ እያሳወቀ ነው፡፡

  የብሔር ብሔረሰቦችንም ቀን ስናከብር እኛ የምንጠቀምበት ያንን አካባቢ በተለይም ታዳጊ ክልሎች በሚሆኑበት ጊዜ ክልሎቹ ይሄንን አጋጣሚ ተጠቅመው፣ ሌሎችም ደግፈዋቸው የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን እንዲገነቡ ነው፡፡ ለምሳሌ የአሁኑን የጋምቤላን በዓል ብንወስድ የጋምቤላ ከተማ ውኃ በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ አሁን የጋምቤላ ከተማ ውኃ ሙሉ በሙሉ ጥሩ የውኃ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል ፕሮግራም ቀርጸን ተግባራዊ አድርገናል፡፡ የጋምቤላ ከተማ መንገዶች ብዙ አስፋልቶች አልነበሩም፤ ይህን በዓል መሠረት አድርገን አስፋልት መንገድ ሠርተናል፡፡ የጋምቤላ ስታዲዮምም በጣም ደካማ ነበር፤ በመሆኑም በዓሉን መሠረት አድርገን ጥሩ ስታዲዮም እንዲገነባ ተደርጓል፡፡ ስለዚህ በዓሎቻችን ዘላቂ ልማትንና የኅብረተሰብ የጋራ መግባቢያ መፍጠሪያ ናቸው፡፡ እነዚህ በዓሎች ብሔሮች፣ ብሔር ብሐረሰቦችና ሕዝቦች በአንድ ላይ ተሰባስበው ባህላቸውን የሚለዋወጡበትና አንድነታቸውን የሚያጐለብቱባቸው ናቸው፡፡ ለእኛ የጋራ ኢኮኖሚያዊ፣ የጋራ ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ መፍጠር ትልቅ ስለሆነ ነው በዓሉ የሚከበረው፡፡ ስለዚህ ትርጉሙም ትልቅ ነው፤ ወጪው ግን ትንሽ ነው፡፡ ስለዚህ በዓሎቻችን ከድርቅ ጋር ማገናኘት አያስፈልግም፡፡”
  ====00====
   

  በሕወሃትም ሆነ በብአዴን ግብዥ ላይ ተጋብዘው የበሉ የጠጡ ሰዎች በየገዜው እንዳስረዱት ከሆነ፡ የጮማው ስባትና የውስኪው መትረፍረፍ፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው ከሚነፋው የተለየ ነው። ግለሰቡም ከእውነት ተናጋሪነቱ፡ ሃሰትን በመቅደድ የጊነስ ሬኮርዱ ውስጥ በሥልጣን ላይ ያለ ዕውቅ ዋሾ ተብሎ እስካሁን አለመግባቱ፣ የመረጃ ችግር ሳይሆን ጊኔስ የዚህ ዐይነት ሪኮርድ እስካሁን አለመያዙ ብቻ ነው!

  በነገራችን ላይ የሕወሃት/ኢሕአዴግ አፍቅሮተ ግብዣ ጉዳይ ክፉኛ ሕዝቡን የሚከነክነው የሚያበግነው በመሆኑ፡ ኢትዮጵያዊ ፖለቲካ ቀልደኝነት ወፍጮ ውስጥ ገብቶ፣ ወብሸት ታደለ የመንግሥት መዋቅር ማሻሻያ ሃሣብ ሲለ ባቀረበው ኮሜዲ ውስጥ፡ በደመቀ መኮንን ሚኒስትራዊ አስተናባሪነት የድግስና ስብሰባ ሚኒስቴር እንዲቋቋም መጠቆሙ ይታወሳል!

  ሲያብራራም እንዲህ ይላል፦

  “ይህ መስሪያ ቤት ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የአገሪቱን መደበኛ በጀት የሚያስተዳድር ሲሆን ከዘረፋ ሚኒስቴር ጋር በትብብር ይሰራል፡፡ ትልልቅ ድግሶችን በማዘጋጀት አገራችን በጭፈራና ዕልልታ የተሞላች ለማድረግ የሚንቀሳቀስ ሲሆን የቲ-ሸርቶችንና ኮፍያዎችን እንዲሁም ተዛማጅ የድግስ ወጭዎችን በመሸፈን ለዘራፊዎቹ የገቢ ምንጭ ያመቻቻል፡፡ ከመያዶች የሚመጣውን ዕርዳታ ተከትሎ ስብሰባዎችን በማዘጋጀት ለተባባሪ አካላት አበልን ተደራሽ ያደርጋል፡፡ ሴቶችና ህፃናት፣ ሰራተኛና ማህበራዊ፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ኤች አይ ቪ መከላከያ ሴክሬታሪያት፣ ወዘተ. በዚህ ሚኒስቴር ውስጥ ተጠቃለው ስብሰባና ድግስ እንዲያፋፍሙ ይደረጋል፡፡ ከብሄር ብሄረሰቦች ቀን፣ ከባንዲራ ቀን፣ ከከተሞች ቀን፣ ከህወኣት ልደት፣ ከብአዴን ልደት፣ ወዘተ ልምድ በመቅሰም ትልልቅ ድግሶችን የሚያከናውን ይሆናል፡፡ “
  ===00===

 

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

ሰራዊት ፍቅሬ (ፎቶ አዲስ አድማስ)

ሰራዊት ፍቅሬ (ፎቶ አዲስ አድማስ)

ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) 50ኛ ዓመት በዓል ማድመቂያ የተመደበው 9 ሚሊዮን ብር፤ ሰሞኑን በትችት ሲያወዛግብ የሰነበተ ሲሆን፤ ገንዘቡ ወደ 3 ሚሊዮን ብር መቀነሱ ታወቀ፡፡

ከኢቢሲ ጋር የ9 ሚ. ብር ውል የተፈራረመው የአቶ ሰራዊት ፍቅሬ ድርጅት (“ሰራዊት መልቲሚዲያ”፤ “የበዓሉን ዝግጅቶች እንዳይሰራ በፀረ ሙስና ታግዷል” የሚሉ መረጃዎች ተሰራጭቷል፡፡ መረጃውን ለማጣራት አዲስ አድማስ ላቀረበው ጥያቄ፤ ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ “ጉዳዩ እኔ ጋ አልደረሰም” የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

“ሰራዊት መልቲሚዲያ”፣ የበዓሉን ዝግጅቶች እንዳይሰራ ባይታገድም፤ የዝግጅቶቹ ብዛትና የገንዘቡ መጠን ተቀንሶበታል፡፡ ምንጮች እንደገለፁት፤ ከረሀቡ አደጋ ጋር በተያያዘ ለበዓል ማድመቂያ ተብሎ በየጊዜው የሚወጣ ገንዘብ ላይ የሚሰነዘሩ ጠንካራ ትችቶች እየተበራከቱ በመምጣታቸው፤ ኢቢሲ ወጪውን እንዲቀንስ አስገድደውታል፡፡

”ኢቢሲ በዓሉን ለማክበር ባወጣው ጨረታ ላይ እንድንሳተፍ በደብዳቤ ስለደረሰን ነው የመወዳደሪያ ሃሳብ ያቀረብነው ያሉ አቶ ሰራዊት ፍቅሬ፤ ተቀባይነት አግኝተን ሰኔ ወር ከኢቢሲ ጋር ውል ተፈራርመናል ብለዋል፡፡
“ታግዷል የሚል ወሬ እኔም ሰምቻለሁ፤ ግን የታገደ ነገር የለም” ብለዋል አቶ ሰራዊት፡፡ ሆኖም የተለወጠ ነገር መኖሩን ገልፀዋል፡፡

“በቅርቡ ኢቢሲ ውሉን እንድናሻሽል ጠይቆናል” ያሉት አቶ ሰራዊት፤ የማጠቃለያ ድግሶችና መሰል ዝግጅቶች፤ በተለያዩ ምክንያቶች አስፈላጊ ሆነው ባለመገኘታቸው ከውሉ ላይ ተቀንሰዋል ብለዋል፡፡ ማስታወቂያዎችን ራሱ ኢቢሲ ሊሰራቸው እንደወሰነ አቶ ሰራዊት ገልፀው፤ አሁን እኛ የምናዘጋጀው ኤግዚቢሽኑን እንዲሁም ለስጦታ ከውጪ የታዘዙን ነገሮች ማፋጠንና መሰል ስራዎችን ነው፤ ወጪውም ከ9 ሚሊየን ብር ወደ 2.9 ሚሊዮን ብር ተቀንሷል ብለዋል፡፡
 
/አዲስ አድማስ
 

%d bloggers like this: