Image

የትላንቱና የዛሬው የኦሮሞ ኅብረተሰብ ትግል የኦሮሞች ብቻ ወይንስ የመላው ኢትዮጵያ?

13 Dec

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

ጥጋበኛና ዘረኛው የሕወሃት አስተዳደር ቅዳሜ ታህሳስ 2 ቀን 2008 ዓ.ም. “በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ዕቅድ ላይ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች ዛሬ ውይይት ተካሄደ” በማለት በራሱ ዜና ማሠራጫ አሰምቷል። ውይይቱ በማንና እነ በእነማን መካከል እንደተካሄደ የተገለጸ ነገር የለም።

የተባሉትም ውይይቶች በአዳማ፣ ቡራዩና ጅማ ከተሞች የተካሄዱ ሲሆን፥ “የውይይቱ ተሳታፊዎች በተቀናጀው የጋራ ዕቅድ ላይ ላለው ብዠታና ጥያቄ በሰላም መልስ መግኛት እየተቻለ አንዳንድ ወገኖች ይህንን ሽፋን ባደረጉ የጥፋት ሃይሎች መጠቀሚያ መሆናቸው አግባብ አይደለም” የሚለውን ጭፍን ሃሣባቸውን ከማነብነብ አልገታቸውም። እንዲሁም እነዚህ ውይይቶች ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ደረጃ በደረጃ የሚቀጥሉ መሆናቸውም ተገልጿል።

ለመሆኑ ይህ ጠብ ያለሽ በዳቦ ብሎ ሕወሃት የጀመረው የመሬት ነጠቃና ዘረፋ ዕቅድ መሬት ላይ ወርዶ፣ ኅብረተሰብን ቅጥቅጣና ግድያ እንዳተጠበቀና እስከ አሁን 25 የሁለተኛ ደረጃና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተገደሉበት፣ ቁጥራቸው ወደ 700 የሚጠጋ ቆስለው ባሉበትና እጅግ ከፍተኝ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች በእሥር ላይ ሳሉ፣ እንዴት ነው አሁን “ሰላም የማምጣት” እየተባለ የሚያስተጋባለት ምኞታዊ ውጤት ሰላም ያሰገኛል ብሎ ተስፋ ማድረግ የሚቻለው?

የሕወሃት የፈለገውን ወንጀል በዜጎች ላይ መለጠፍ የፖለቲካ ባህሉና ልምዱ ያደረገ አስተዳደር እንደመሆኑ፣ ዜጎች በሰላማዊ መንገድ ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ሲጠይቁ፡ ጥያቄዎቻቸውን በማጣመም “የጸረ-ሰላም ኃይሎች ቅንብር” በማስመሰል የሚያደርገው ውንጀላ፡ ካለፈው ስህተቶቹ ሕወሃት ምንም እንዳልተማረና ለዜጎችም ደኅንነትና ሕይወት ደንታ የሌለውና በሃገርም ላይ ገና ብዙ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ዕኩይ ድርጅት መሆኑ ላፍታ እንኳ ሊዘነጋ አይገባም።

አስቂኙ ነገር ግን፡ ከላይ የተጠቀሱት የኦሮሞ ከተሞች ውስጥ ተካሄዱ የተባሉትን ‘ውይይቶች’አስመልክቶ ሕወሃት ከቀባጥራቸው ጉዳዮች መካከል “በምክክር መድረኮቹ የተገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ማንኛዉም በክልሉ የሚተገበር የልማት እቅድ ህዝቡ አውቆት ተሳተፊ ሳይሆንበት ወደ ትግበራ እንደማይገባ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል ብለዋል” ይላል።

ለዚህም ‘ክቡር አቶ ሙክታር ከዲር’ የሠጡትን ‘መሪ ቃል’፣ ማለትም በረቄቅ ደረጃ የሚገኘው [የማስተር ፕላኑ] መሪ ዕቅድ ሕዝቡ ሳይስማማበት እንደማይተገበር ማስታወቃቸውን” ይጠቅሳል። ለመሆኑ፡ ሙክታር ከዲር የነዐባይ ጸሃዬ ተላላኪ፡ አናቱ ላይ መፈንጫና ማላገጫ ከመሆን አልፎ እንዴትና ምን ጊዜ ነው የኦሮሞ ሕዝቦችን ጥቅም አስከብሮ የሚያውቀውና በማስተር ፕላኑስ ላይ ሊደራደር የሚችለው የሚለው ጥያቄ በሁሉም ዘንድ አስገዳጅነቱን መጋፋት አይቻልም!

ታዲያ በምክክር አማኒ መስሎ የሚቀርበው ሕወሃት፣ ይህን ለመገንዘብ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራልዚምን ለሃያ ዓመታት ቢሰብክም፣ በመሬት ዘረፋ ጥቅሙ ላይ የተማሪዎቹ ቁጣና ብሎም የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጣና ጥላቻ መነሳሳት ሲመጣበት መሆን አለበትን ይህንን መርህ ዛሬ ለማስታውስ የሚገደደው፣ ወይንስ አበው እንደሚሉት “ዶሮን ሲደልሏት በመጫኝ…” ህኖበት፤ እርሱ ንቁ ሆኖ ሌሎችን በማጅራታቸው ሊያርዳቸው ሲዘጋጅ ይሆን?

በችግር ጊዜ አዝናኝ የፕለቲካ ቧልቶች ችግሮችን ለመፍታትና ውጥረትን ለማላላት የሚረዱ ቢሆኑም፡ በመፍትሄዎቹ ዙርያ የአሁኑ የዚህ ዐይነቱ የሕወሃት ቀልድ ግን ደም አፍይ ከመሆን አያልፍም!

በአጋጣሚ ምናልባት የኦሮሞ ተማሪዎች የተቃውሞ መንስዔ ለሕወሃት ሰዎች ግልጽ አልሆነላቸው እንደሆን፡ የችግሩ ምንጭ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን አስፈላጊነት ሳይሆን፡ ከዚያ በስተጀርባ ያለው የሕወሃት የራሱን ብኄረስብ አባሎች በመሬት ዘረፋ አበልጽጎ፡ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን – በተለይም በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉትን ኦሮሞች – በማራቆት በኢትዮጵያ ላይ የበላይነቱን ለማሥረጽ የሚፈጽመው ውንብድና ነው።

በአንዳንድ የተቃዋሚ ወገኖች ለነገሩ ትኩረት ባለመሥጠት የማስተር ፕላን ተቃውሞ አስመስሎ ለማቅረብ የሚደረገው ጥረት መታረም ይኖርበታል። አሁን እንደሚደረገው ከሆነ፣ ሕወሃት እንኳ ይህንን እንደመንጠላጠያ ቆጥሮ፣ አንዴ ተቃዋሚዎቹን በፖለቲካ፣ በኤኮኖሚና በስብዓዊ መብቶች ዙሪያ ተቃዋሚነት ሳይሆን፡ በልማት ተቃዋሚነት ሲወነጅላቸው ይሰማል

አቶ ዳባ ደበሌ የኦሆዴድና ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚና የኦሆዴድ ማእከላዊ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት ሃላፊ፣ አቶ ድሪባ ኩማ የኦሆዴድና ኢህአዴግ የስራ አሰፈፃሚ አባል እና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አንዲሁም አቶ ጌታቸው ረዳ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒሰትር ናቸው በውይይቱ የተሳተፉት (ፎቶ ፋና)

አቶ ዳባ ደበሌ የኦሆዴድና ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚና የኦሆዴድ ማእከላዊ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት ሃላፊ፣ አቶ ድሪባ ኩማ የኦሆዴድና ኢህአዴግ የስራ አሰፈፃሚ አባል እና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አንዲሁም አቶ ጌታቸው ረዳ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒሰትር ናቸው በውይይቱ የተሳተፉት (ፎቶ ፋና)

ለአፉ ለከት የሌለው ጌታቸው ረዳ[foto: Fana] እንኳ በዛሬው ውይይት ላይ “ጠባብ አመለካከት ያለቸው ወገኖች ለኦሆዴድ ዕውቅና ባለመስጠት የራሳቸውን ዓላማ ለመዘርጋት እንደሚንቀሳቀሱ” አድርጎ አቅርቦታል  –የራሱ ወገን የመሬት ዘረፋ ከመሆን ይልቅ!

በሌላ በኩል ደግሞ በዚህም ምክንያት ከዛሬው ምክክሩ ሕወሃት ማድረግ ያሰበው “ለሰሞነኛው ሁከት አንደ አዲስ መቀስቀስ አንዱ በቅርቡ ጨፌው ያፀደቀው የከተሞች ልማት አዋጅ በመሆኑ በቀጣይ ሠፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እንደሚሠራ እና በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ የተቀናጀ ልማት ረቂቅ ዕቅድ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ነው።”

"የኦህዲድ ሴቶች ሊግ አባላትና ደጋፊዎች" (ፎት ፋና)

“የኦህዲድ ሴቶች ሊግ አባላትና ደጋፊዎች –የሊጉ አባላት በክልሉ ከተሞችና ገጠር አከባቢዎች እየተመዘገበ ያለው ፈጣን ልማትና ዕድገት የህብረተሰቡን ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ሆኖ ሳለ የኦሮሞ ህዝብ ምንም ጥቅም እንዳላገኘ ተደርጎ የተነዛው አሉባልታ ርካሽ የፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ነው ብለዋል፡፡ (ፎት ፋና)

በነገራችን ላይ፡ ሕወሃት/ኦሕዴድ በሚዲያ ምክክራቸው እንዳበቃ፣ የሕወሃት ተሳታፊዎች ያደረጉት ነገር ቢኖር፡፣ ሕወሃት የኦሕዴድን የሴቶች ሊግ ጉርሻ እየሰጡና እያስፈራሩም፡ “በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች ሰሞኑን የተቀሰቀሰውን ሁከትና ብጥብጥ አጥብቀው እንደሚቃወሙ” ገለፁ ሲል በሚድያው ላይ ፈንጭቶበታል።

ይህ ግን ደረታቸውንና ሕይወታቸውን ለመሠዋት የተዘጋጁትን ወጣቶች ከቆሙለት ዓላማ ካለፈው ዓመት ግድያ ተሸጋግረው እንደገና በዚህም ዓመት ለመጋተር መቁረጣቸው ሲታይ።

ስለሆነም፣ በእርግጥ ሕወሃት ዛሬ ኢትዮጵያ የገባችበትን ውጥረት ማርገብ የሚሻ ከሆነ፣ በአስቸኳይ በአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የሚከተሉትን እርምጃዎች ሊወስድ ይገባል፦

  (ሀ) በ24 ሰዓት ውስጥ የታሠሩትን የሁለተኛ ደረጃና ይኒቨርሲቲ ተማሪዎችንና መምህራንን መፍታት

  (ለ) በ24 ሰዓት ውስጥ የታሠሩትን ወላጆች፡ የየከተማና ቀበሌ ነዋሪዎች፥ የፖለቲካ ድርጅቶችን አመራሮችና አባላትን መፍታት

  (ሐ) በ24 ሰዓታት ውስጥ በሕወሃት ለተሠውት ዜጎች ቤተሰብች አገዛዙ ይቅርታ እንዲጠይቅና ተገቢውን ካሣ በአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ለመክፈል ቃል አሁኑኑ እንዲገባ

  (መ) በሕዝብ ነብረቶች ላይ ለደረሱት ጉዳቶችና መደምሰሶች ተገቢውን ካሣ እንዲከፍል

  (ሠ) ለሕዝብ መብቶች ሲታገሉ እንደ ወንጀል ተቆጥሮባቸው መቀመቅ የተወረወሩት የፖለቲካ እሥረኞች – ጋዜጠኞችን ጨምሮ – በሶስት ቀናት ጊዜ ውስጥ በነጻ እንዲለቀቁ

  (ረ) በዝርያቸውና ቋንቋቸው ምክንያት የታሠሩ እሥር ቤቶችን ያጣበቡት የኦሮሞ ፖለቲካ እሥረኞች ባስቸኳይ ነጻ እንዲለቅቁና፣ ለተፈጸመባችውም ግፍ ተገቢው ካሣ እንዴከፈላቸው አስፈላጊው የሕግ ሁኔታ እንዲመቻችላቸው

  (ስ) የኢትዮጵያ ሕዝብ ለወደፊቱ የሚያስፈልገውን የአስተዳደር ሁኔታ በነጻ ፍላጎቱ መመሥረት ይችል ዘንድ፡ የፖለቲካ ኃይሎች መሰባሰብና መነጋገር እንዲችሉ ሁኔታውን ለመጠቀም የሚያደርጉትን ጥረት በማናቸውም

  (ሽ) ለሱዳን ሊሠጥ ቃል የተገባው የኢትዮጵያ መሬት ውል ያላንዳች ማወላወል መሠረዙን ያላንዳች መቀባጠር በማያወላውል መንገድ ግልጽ እንዲድደረግ

  (ቀ) በኢጋድ አማካይነትና በሁለትዮሽ መሰተጋብር ከአፍሪካ ቀንድ ሃገሮች ጋር በስደት ከሃገር የወጡትን ዜጎም የዓለም አቀፍን ሕግ በመጣስ የሚያደርገው አስገድዶ የመመለስ ወይንም የማፈን ተግባር ያላንዳች ማመንታት አስፈላጊውን ሜሞራንደም በመላክ ሕወሃት በዚህ ረገድ ሲያደርግ የነበረው ጥረታና ጎርቤቶችን የማስገደድ ሁኔታ መሠረዙን ማስታወቅ

  (በ) በዚህ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ከፕሮፓጋንዳ ነጻ የሆነ ሚዲያ እንዲኖረው፡ የመናገር፡ የመጻፍ፡ የመሰብሰብ፣ በነጻ የመደራጀትና የእምነት መብቱን ያላንዳች ዕገዳ እንዲጠቀም የተጣሉበት ማቀቦች በሙሉ እንዲነሱ። ይህንንም በሚመለከት የወጡት አዋጆች፡ ሕጎችና ደንጋጌዎች በሙሉ እንዲሻሩ

  (ተ) በአኤአ በ2009 ዓ.ም. የወጡት የጸረ ሽብርና (Proclamation No. 652/2009) መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አሠራር በመመዝገብ ስም ዓላምው ግን የማኅበራዊ ኑሮን ሰብዓዊ መብቶች መከበርን ዕርዳታ ለመግታት የወጣው ሕግ አዋጅ ቁጥር 621/2009 (Proclamation No. 621/2009) በዚሁ በአንደ ወር ውስጥ እንዲሻሩ።

  (ቸ) በአዲስቷ ኢትዮጵያ፡ ለሃገር ደህነነትና ጥበቃ ዋናው ኃይል ሕዝቡ ራሱ እንጂ የሃገር ዳር ድንበር ለሱዳን የሚሸጥ አሰተዳደር አለመሆኑ ግንዛዜ ውስጥ ሊገባ ይገባል። በተመሳሳይ መንገድም ይህም ሕወሃት ከሱዳኑ ዓለም አቀፍ ወጀለኛ አል በሽር ጋር የሚያደርገው ስምምነት – ታህሳስ 4፣ 2013 ካርቱም ላይ የተፈራሙትንና የቀሞዎቹን ከመለስ ዜናዊ ጋር የተደረጉትን ጨምሮ – በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተሽረው ይኸው መረጃ ለሕዝቡ በሕዝብ መገናኛ መሣሪያዎች ሊገለጽለት ይገባል።

በመጨረሻም፡ ዛሬ በኢትዮጵያውያን በጋራ ተመዞ ያለው ሠይፍ በነሙክታር ከዴር፡ አባዷላ ገመዳና ወርቅነህ ገበየሁ አግባቢነትና አታላይነት ወደ አፎቱ ቢመለስ፡ ነገ የሚጎዳው ዛሬ በመንገድ ላይ ደረቱን ለመብቱና ነጻነቱ አሳልፎ የሠጠው ወጣት መሆኑ በደንቡ ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ ይገባል። ሕወሃት መረጋጋት ሲመለስለት መጀመሪያ ከትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች የሚያባርራቸው እነዚሁኑ የመብት ታጋዮች ነው! ካለፉት እርምጃዎቹ በመነሳት ስንመለከት፡ የወደፊትም የሥራ ዕድል ከሚነፈጉት መካከል እነዚህ ወጣቶች ግንባር ቀደሞቹ ናቸው።

harmomaya students
 
ጥያቄው ሥራ ኖረ አልኖረ፣ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ይሁኑ፣ ሃገራቸው ሙያቸውን ዕውቀታቸውን ትፈልግ አትፈልግ አይደለም! ሕወሃት ቀንም ሆነ ሌሊት የሚያስበውና የሚያተኩረው የራሱ የፖለቲካና ኤኮኖሚያዊ ጥቅሞች ላይ ብቻ በመሆኑ፡ ለሰብ ዓዊ መብቶችና እኩልነት በመታገላቸው ብቻ የሃገር ጠላት አድርጎ ይፈርዳቸዋል – እርሱ ራሱ ግንባር ቀደም የሃገር ጠላት ሆኖ ሳለ!

ካለፈው ምርጫ እንኳ በመነሳት የተፈጸሙትን ወንጀሎች ስንመለከት፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሃገሪቱ ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኖረው ለሥልጣን መወዳደራቸው ሕጋዊ መሆኑ ቢደነገግም፡ የሕወሃት ሰዎች መቶ በመቶ የፓርላማውን ወንበር ይዘውም ከምርጫው ማለቅ ሁለት ወራት በኋላ ጭምር ለተቃዋሚዎች መርጣችኋል ተብለው የእርሻ መሬቶቻቸውን የተነጠቁ ገበሬዎች፡ የንግድ ተቋሞች የተዘጉባቸው ባለሃብቶች ብዛት፡ ከትምህርት ቤቶችና ሥራ የተባረሩት ተማሪዎች ቁጥርን በማስታወስ፡ በዚህ አስተዳደር ዘንድ ክተጀመረው ትግል በተላላነት ወደ ኋላ ማፈግፈግ ለሕውሃት የአጥፋኝን በትር በተላላነት የማቅረብ ያህል መሆኑ ልብ ሊሉ ይገባል!

በማጠቃለልም፡ መንገድ ሕወሃት እንዳያደናቅፍ፤ ይህንን ቢያደርግ ሕዝቡ በቅድሚያ የሕወሃት አመራሮችንና አባሎችን እያደነ ለፍርድ የሚያቅርብበት ላይ እንዲያተኩር ማድረግ

ከታሪክ እንደሚታየው፣ የፖለቲካ ውጥረት በተጠናከረበት ወቅት ሁሉ፣ በዓላማ በተቆራኙ መካከል ሁነታው ራሱ ለአመራር መፈጠር ተገቢውን አመራር የመፍጠር ግፊት እንደሚኖረው መገንዝብ ያስፈልጋል። ለዚህም በዘር መከፋፈል የሕወሃት የበኩር ልጅ መሆኑን አበክሮ በመገንዘብ፡ ያለፈው ላይ ብቻ ከማተኮር ተሻግሮ፡ ግልጽነት ያለበት በአዲስ አስተሳስብ የተባበረች ኢትዮጵያን በመፍጠር ዘረኞችን ከምድራችን ላይ ለመጥረግ መቻቻል ያስፈልጋል።

አዲሱም አሰተሳሰብና አመራር በሁሉም ኢትዮጵያውያን እኩለነት፡ ነጻነትና ዲሞክራሲያዊነት ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል።

አዲሲቷ ኢትዮጵያ ዜጎቿን ከፍርሃት፡ ከሰቀንና ረሃብ፤ ፍርድ ቤቶቿ የዜጎቿ ነጻነት አሰክባሪዎች እንጂ የዘራፊዊቿ አለመሆኗን ነገ ሳይሆን፡ ዛሬውን መሆን ይኖርበታል – የዛሬውን የተግማማ ሂትለራዊ አገዛዝ የፖለቲካ፡ የዝርያና የኤኮኖሚያዊ ብልግና በማጋለጥ!

*Updated.

ተዛማጅ ጽሁፎች

Oromo students trying to end TPLF’s land grab widen their protests; parents & residents throughout region involved; student casualty stands at 15; many injured & over 500 imprisoned by int’l Human Rights Day, Dec 10!

የትላንቱና የዛሬው የኦሮሞ ኅብረተሰብ ትግል የኦሮሞች ብቻ ወይንስ የመላው ኢትዮጵያ?

በማስተር ፕላኑ ላይ በተነሳው ተቃውሞ፣ በመብት ጥያቄዎችና በመንግሥት ምላሽ ላይ የተጠናቀረውን ዝርዝር ዘገባ ለመመልከት እዚህ ላይ ይጫኑ ወይም በ ፖለቲካ ገጽ ይመልከቱ፡፡

 

%d bloggers like this: