የሕወሃት ጸረ ሽብር ግብረ ኃይል የኦሮሞ የመብት ታጋዮች ነውጥ “አድማስ ወደ ከተሞችና ወደ ተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት መስፋፋቱን” አመነ፤ ግድያውና ጅምላ እሥሩን እንደሚያጠናክር ገልጿል!

15 Dec

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

በአብዛኛው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና የዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች የተቀሰቀሰውና ገበሬዎችና የከተሞች ነዋሪዎች የተቀላቀሉበት ሕዝባዊ አመጽ፣ የሕወሃት የመሬት ቅርምት መነሻ ያደረገ ቢሆንም፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉንም የኢትዮጵያውያን ብሶቶች፣ የመብቶች ጥያቂዎችንና የአስተዳደሩን ጸረ ሕዝብና ጸረ ኢትዮጵያዊነት በመቃወም የተጠናከረ ትግሉን አስተዳደሩ ባልጠበቀው መጠን ተስፋፍቶ መቀጠሉ ይታወቃል።

ለመጀመሪያ ጊዜ፡ ሕወሃትም ይህንን በማመን፣ በጸረ ሽብር ግብረ ኃይሉ አማክይነት እሰከዛሬ የገደላቸው ወደ መቶ የተቃረቡ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ታጋዮች፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ቁስለኞችና አሥር ሺህ እሥረኞች አልበቃ ብለውት፣ በዛሬው ምሽት በአጋዚና በአጠቃላይ የመከላከያ ኃይሉ አማካይነት የጀመረውን የኢትዮጵያውያን ግድያ አንደሚያጠናክር አስታውቋል

ለኅብረተስብ ነጻነት፡ የፖለቲካና ኤኮኖሚያዊ መብቶች የሚታገሉትን ወጣቶ ሽብርተኞች በማስመሰል፡ እየተወሰደ ያለው የኅብረተሰብ ጠላትነት እርምጃ፣ የኢትዮጵያንም ሆነ የዓለም አቀፍ ሕግን የሚጻረር የመንግሥታዊ ሽብርተኝነት እርምጃ ነው።

በሕዝቡ ቁጣና መነሳሳት ሕወሃት በመደናገጡ፣ ይህንን የሕዝብ አመጽ ለማፈን ያደረገው ዝግጅት በባህሪውና አደረጃጀቱ – ማለትም በግብረ ኃይልና በተለያዩ ኮማንድ ፖስቶች አማካይነት እየተካሄደ መሆኑ – በ1997 ዓ.ም. ሕወሃት የዘረፈው ምርጫ ማግሥት በአዲስ አበባና በመላው ሃገሪቱ የተፈጸመውን የሕዝብ ጭፍጨፋ ስልትና ድርጅታዊ አሠራር ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ብዙ ዜጎችን ለመግደል የተደረገ ዝግጅት መሆኑ አያጠራጥርም!

የታሣሪዎቹ ብዛት እንዲህ ከፍ ሊል የቻለው በሁለት ምክንያቶች ነው። አንደኛ በምርጫ 97 እንደታየው ሕወሃት ወጣት የሆነውን ሁሉ ጠላቱ አድርጎ በመቁጠርና በማሠር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በመግለጫው ላይ እንዳስቀመጠው፡ ስላዮቹና ቅጥረኞቹ በሰበሱት መረጃ መሠረት ጠቁሙ እያለ እያስፈራራና ገንዘብ እየከፈለ ለመሆኑ ያለፈው ባህሪው ብቻ ሳይሆን እርሱም እንዲህ ሲል ያስቀምጠዋል

“በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሚገኙ የከፍተኛና ሁለተኛ ደረጃ የሚማሩ ተማሪዎች በርካቶቹ ሂደቱን በመቃወምና በመኮነን ትምህርታቸውን እየቀጠሉ የሚገኙ ከመሆኑም በላይ መደበኛ ትምህርቱን ወደጎን በመተው የሽብርና የአመፅ ሃይሉ ሰለባ የሆኑ ተማሪዎችን አጋልጦ በመስጠትና የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊ ለማድረግ አይነተኛ ሚና ተጫወቷል” በማለት የተለመደውን የመከፋፋል ሥራ ለምሥራት ይሞክራል።

ሕዝቡም ላይ የሽብር ስሜት ለመፍጠር፡ “በገጠርም ሆነ በከተማ የሚኖረው ሕዝብ አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት በትምህርት ተቋማትም ሆነ ከትምህርት ተቋማት ውጭ የሚገኙትን ልጆቹንና መላ ቤተሰቡን የሰው ሕይወት እንዳይጠፋና ንብረት እንዳይወድም፣ ዘረፋ እንዳይስፋፋ፣ የሽብር የአመጽ አቀጣጣዩች ሰለባ እንዳይሆን በማድረግ የበኩሉን ሚና እንዲጫውት” ግብረ ኃይሉ ጥሪ በማድረግ ሕወሃት ስሞኑን ከታየው ጭፍጨፋ በከፋ መንገድ የኢትዮጵያ ወጣቶ በየመንደሩና በየጥሻው ለማረድ ተዘጋጅቷል!

የዓለም ኅበረተሰብ ይህንን ወንጀል በቸልታ መመልከት የለበትም!

*Updated.

%d bloggers like this: