አርበኞች ግንቦት7 ከሕወሃት ጦር ጋር ዋልድባና አዲ አርካኢ ላይ ፍልሚያ እያካሄደ አያሌ ወታደሮች ሲገድል፣ የራሱም 6 መማረካቸውን በታማኝነት አረጋግጧል! – ለምን ይህ ጽሁፍ?

17 Dec

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

ታህሳስ 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ትግራይ ኦንላይን ላይ የትግራይ ፖሊሶች ሰባት የኤርትራን አሸባሪዎች አዲ አርካኢ መንደር አካባቢ ማረኩ በሚል ርዕስ ያወጣውን ዜና የተለመደ የሕወሃት ቱልቱላ ነው ብዬ ፊቴን ከሃተታው አዙሬ ነበር። ለነገሩ ብዙ እውነት በእነርሱ ጎን ሳለ፡ አሁንም የልማድ ነገር ሆኖ፣ ትንሽ መበጥረቃቸው አልቀረም!

አንደኛ፡ የተማረኩት – የዜናው አርዕስት ላይ እንደተገለጸው – የኢርትራ ወታደሮች ሳይሆኑ የግንቦት ሰባት አባላት ናቸው። በተጨማሪም የራሳቸው የሕወሃት ፎቶ አንሺ ካፕሽኑ ላይ የግንቦት7 አባል መሆናቸውን መዝግቧል።

ሁለተኛ ቁጥራቸው ሰባት ሳይሆን ከፎቶውም ላይ እንደሚታየው፥ ግልጽ ባይሆንም አምስት ይመስላሉ፤ ግን ግንቦት7 ስድስት ተማርከውብኛል – “ፎቶው ላይ የሚታዩት ስድስት የኔ” ተዋጊዎች ናቸው – ብሏል።

የእነርሱን ቁጥር እቀበላለሁ ከሕወሃት ይልቅ – ሰባቱን ስድስት በማድረጋቸው የሚጠቀሙት ነገር ስለማይታየኝ። ክሁሉም ደግሞ አዲስ ድርጅት ሆኖ በጦር ግንባር  ሳለ የፈጸመውን ሽፍጥ እስካሁን አልሰማንም! አናውቅምም! የተለመደ ነገር ሆኖ፣ ትንሽ ውሸትና መቀዣበርም ካለ በሕወሃት ሰዎች በኩል ነው!

ተማራኪ የአርበኞች ግንቦት7 አባላት (ፎቶ ትግራይ ኦንላይን)

ተማራኪ የአርበኞች ግንቦት7 አባላት (ፎቶ ትግራይ ኦንላይን)

ኢሣት በዜና ፕሮግራሙ የግንቦት7ን ቃል አቀባይ በማቅረብ በድምጽ እንደሰማነው ከሆነ፡ የተባሉት ስድስት – በታጋይ ቡድኑ አጠራር– ቃኝ አባሎች – ተማርከውበታል።

በዚሁ የቃል መግለጫ፡ የአርበኞች ግንቦት7 ቃል አቀባይ “ከተከዜ ወደ መሃል አገር እየገሰገስን መሆኑን መንግስት ራሱ የለቀቀው መረጃ ያመለክታል…መተማ አካባቢ በሚገኙ የገጠር አካባቢዎች አሁንም ድረስ ትግል በመካሄድ ላይ” መሆኑን ገልጿል።

በድምሩ አርበኞች ግንቦት7 48 የሕወሃት ወታደሮችን ሲገድል (29 አድርቃይና 19 ዘባጭ ውሃ አካባቢ)፣ 20 ደግሞ አቁስሎ በሸዲ ሆስፒታል በሕክምና ላይ እንደሚገኙ ተግልጿል።

በራሱ ወገን በኰል ስለተገደሉበት ግን ቃል አቀባዩ የገለጸው ነገር የለም!

ጦርነት አስከፊ ነውና ገና ብዙ ልንሰማ እንችላለን! ትግሉ በአንድ በኲል ሥልጣንና ያሰከተለቻቸውን ጥቅሞች በሚንከባከቡና ለዜጎች መብቶች፣ እኩልነትና ለሃገር ነጻነት እንታገላለን በሚሉ መካከል ስለሆነ – ለጊዜው በምናየውና በምንሰማው ብቻ በመመራት፣ ጦርነቶች ሁሉ በአጥፊነት ባህሪያቸው ብቻ መፈረድ የለባቸውም የሚለው ተስፋ ይሰጠናል!

የዛሬዎችን የአርበኞች ግንቦት7 ተዋጊዎችን ሳይሆን – ፋታ የማይሰጥ ከፍተኛ የሃገር ጥሪ ላይ ናቸውና – ምናልባትም የነገ ወይንም የተነጎዲያዎቹን የሚፈታተን ነገር ይከሰት ይሆናል። በዚህም ምክንያት የኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ጥቅምት 28፣ 1973 ሂነሪ ኪሲንጀርን ጠቅሶ የጻፈው ትዝ ስላለኝ ላስታውሳቸው መረጥኩ: “Lesser known variant: Power is the great aphrodisiac.”

ምንም ለሥጋ ማድላት ሰብዓዊ መሆኑ ቢታወቅም፡ ከመጣም ብልሽታችው ከሕወሃቶች የከፋ እንደማይሆን ቅንጣት አልጠራጠርም!

ይህችን ትንሽ ጽሁፍ ለማቅረብ የፈለኩበት ምክንያት፣ አዲስ መረጃ ነው በማለት አይደለም። አርበኞች ግንቦት7 ሳይገፋፋ፣ ሣይሸፍጥም፣ የተማረኩት ስድስቱ የኔ ተዋጊዎች ናቸው በማለት እውነትን በመናገሩ፡ እውነት እንደ ክረምት ፀሐይ ለሩብ ምዕተ ዓመት በተሠወረችባት ኢትዮጵያ የተሰማኝን ደስታ ለመግለጽ ነው።

ኪሲንጀር ያለው ፈተና ባይቀርም፡ ይኸው እውነት ተናጋሪነቱን ይልመድባችሁ እላለሁ!

እንዲሁም አርበኞች ግንቦት7፣ የነገይቱ ነፃይቷ ኢትዮጵያ አመራር አካል ለመሆን ከበቃችሁ፡ በጦር ግንባር ብቻ ሣይሆን፣ በሰላምም ጊዜ ለምታሳዩት ታማኝነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ይወዳችኋል፤ ያከብራችኋል። ከናንተ ጋር በደጉም በክፉም አብሮአችሁ ይቆማል የሚለውን ባስታውሳችሁ፣ ምናልባት ከሕወሃት የተሻላችሁ መሆናችሁን ያጠናክረዋል የሚል ግላዊ ፍላጎቴንና እምነቴን ለማስረገጥ ነው!

ግልጽ ካልሆንኩ፣ አንገታችሁን ቀና አድርጉና በኢትዮጵያውያን ዐይንና ግምት ሕወሃት ያዘቀዘቀዘበትን እንጥርጦሮስ ተመልከቱት! አስቡት!

%d bloggers like this: