የዛሬውንና ነገ የሚከተለውን ኢትዮጵያውያን ለሕወሃት አባሎች ባርነትና ግርድና ከወዲሁ ለማቆም፥ ዜጎች በጋራ ለክብራቸውና ነፃነታችው ትግላቸውን ማፋፋም ይገባቸዋል!

22 Dec

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

ሪፖርተር በእሁዱ ታህሳስ 20/2015 እትሙ ላይ “ሁሉንም ችግር የውጭ ኃይሎች ያመጡት ነው የሚል ክርክር በመንግሥት በኩል የለም” በሚል ርዕስ የሕወሃት አስተዳደር ኮሚኒኬሽን ኃላፊ ጌታቸው ረዳ በሠጠው ቃለ መጠይቅ፡ አንዳንድ የተለመዱ የሕወሃትን ሸፍጥቶችና ቅጥፈቶቹን በሕዝቡ ላይ ረጭቷል፡፡

በተለይም፡ ከኦሮሚያ መነሻውን አድርጎ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አመጽ የሕወሃትን ሰዎች ላብ በላብ አድርጎ ስለነበር፡ የእርሱንም ሃሣብ እንዲሁ በማዝፈቁ፣ የሪፖርተር ጋዜጠኛ ለሚያቀርብለት ጥይቄ ተገቢውን መልስ ከመስጠት ይልቅ – ለአንድ ወር ያህል በሃገራችን በመካሄድ ላይ ያለውን በይዘቱ ከ1973-74 ዓ.ም. ጋር ተቀራራቢና በ25 ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያው የሆነውን ሕዝባዊ አመጽ ጥልቀትና የኢትዮጵያን ሕዝብ ብሶት ማንጸባረቁን – አልተሳካለትም እንጂ – ለማጣጣል ሞክሯል።

ሆኖም ሃቁ፥ ቃል አቀባዩ እንደሚለው ሣይሆን፣ እነዚህ 25 ዓመታት ለኢትዮጵያውያን የሰቆቃና የሥቃይ ዘመን በመሆናቸው፥ ሥልጣንና ምቾት ከእንግዲህ ከእጁ እንዳይወጡ – የፈሪ ጅብ አህያ ነክሶ ደርቆ እንደሚቀር – ሕወሃትም ሕዝቡን በጥርሱ (በአንድ ለአምስት፥ በደኅንነቱና ጦሩ)) ነክሶ፥ እየተባባሰ በሄደው የግንባሩ አባላት ዘረኛነትና በመደባዊ የበላይነት ተገዥ የማድረጉ ድርጅታዊ ሩጫቸውና መነሻ ዓላማቸው መሆኑን በውስጣችው ይዘው፡ ሌሎች ዜጎችም ሕወሃት ሃገሪቱ ከመያዙ በፊት የጠረጠሩት ተግባራዊ በመሆኑና በመታለላቸው ላለፈው እራሳቸውን በመውቀስ ሁኔታውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቀየር የነፃነት ትግሎ ተጀምሯል!

የታወቀው ጸረ-ኢትዮጵያው የስብሃት ነጋ የገራው የሕወሃት አፈ ቀላጤ ሚኒስትር ጌታቸውም የዚህን ተግባራዊነት ለማረጋገጥ፡፥ ሕዝቡን ለማሳሳት፣ ብሎም ለማዘናጋትና ለመከፋፈል የሞከረው ሕዝቡን ያስቆጡትን ጉዳዮች ወደጎን በመግፋት ልበ ወለድ ታሪክ ለመድረስ ሲታገል ታይቷል። በእርሱ አባባል አሁን ገዳዮም፡ ንብረት ዘራፊውም ሕይወት አጥፊውም ያልታጠቀው መረገጥና መግደል ያንገሸገሸው ወጣትና ሕዝቡ ሆኖ አረፈው!

ከሁሉም እጅግ የከፋው ደግሞ፡ ሕግ አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ተማርኩ የሚለው ጌታቸው ረዳ፣ በሕዝባዊ አመጹ ግንባር ቀደም የሆኑትን የኦሮሞ አክቲቪስቶችና ዜጎች፣ እንዲሁም ሌሎችም ለኢትዮጵያ ክብር መንሠራራትና ለዜጎቿ ሁሉ ደህንነት የሚታገሉትን – ለዚያውም በሕጋዊ ፍርድ ቤት ጥፋተኝነት ሳይፈረድባቸው ወንጀለኛ አድርጎ ስማቸውንና ስብዕናቸውን ለማንቋሸሽ ደጋግሞ መሞከሩ ነው! እንዲሁም በስሜታዊነቱና ለከት በሌለው አነጋገሩ የኢትዮጵያውያን ዜጎችን ስብዕነት በመካድ “በአጋንንትነት” መመሰሉ ይገኝበታል

ይህም ከሕግ ተማሪነቱ ይልቅ፣ አስተሳሰቡ መንደራዊ መሆኑን ያመለክታል። የሚያሳዝነው፡ ጌታቸው ረዳ በዝርያና በደም ግንኙነቱ የተቆናጠጠው ሥልጣን፡ የትግራይን ሕዝብ ማንነት ለሚያቆሽሽውና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሆድና ጀርባ እያደረገው የሚገኘው ድርጅት ዋና መስካሪና ቃል አቀባይ ሆኖ፣ ከተራ መንገደኛ ባነሰ መንገድ የሕገ መንግሥቱን አንቀጾች 20 ና 22 ተግፍቷል።

ይህንንም የምልበት ምክንያት፣ በሕወሃት የፖለቲካና የጥቅም መከላከል መነጽር ብቻ የተወነጀሉትን ግለሰቦች – ተገቢው ሕጋዊ አካል እንዲመሠርትባቸው ብሎ እንኳ ሳይወስን፥ – ‘ዐይናችን እያየ ስብዕናችንን አናዋርድም፡ የቤተሰቦቻችን ክብር ሲረገጥና ንብረታቸው ሲዘረፍ፣ የዘራፊው የሕወሃት ዱላና ጥይት ፀጥ አያሰኘንም’ ያሉትን ኢትዮጵያውያን የመብት ተፋላሚ ግለስቦችንና ትግላቸውን ከጋኔንና አጋንንት ጋር ማመሳሰሉ ከእርሱ የሚጠበቅ አልነበረም። ፡ ይህም እርሱ ለተማረበት የአሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ከቁጥር ባይሆንም፣ አሳፋሪ ነጥብ መሆኑም አይካድም።

በተጨማሪም፡ Fritz Pappenheim: The Alienation of Modern Man – An Interpretation Based on Marx And Tönnies ከተሰኘው የ1959 መጽሐፉ ቃል አቀባዩ (ወይንም ከተጠቃሽ ምንጭ) የወሰደውን ታዋቂውንና ጥንታዊውን የጀርመን ባህላዊ አባባል (‘The spirits that I summoned I cannot now dismiss’ – ገጽ 43)፣ የሚለውን Pappenheim ባላሰበው መንገድ ተጠቅሞበታል።

ደራሲው ይህንን ጥንታዊ የጀርመን አባባል የተጠቀመው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ምክንያት የሚፈጠረውን የኅብረተሰብ አባላት መገለልና (alienation) ተገዥነት ሥር መውደቅ ሲሆን፣ ዛሬ በሃገራችን ተለኩሶ በሃገድና በሥውር የሚምቦገቦገውን በመጥፎ አስተዳደር ላይ የተነሳውን የሕዝብ ቁጣ – ጌታቸው እንደሞከረው ለማዳፈን አልነበረም።

ስለሆነም፣ የጥቅሱ ዓላማ ዛሬ በሃገራችን ውስጥ ለመብቶችና እኩልነት ታጋዮችን፥ እንዲሁም ከኅብረተሰብ ፍሬዎች የእኩል ተቋዳሽነትን ከሚጠይቁ፣ መሬታቸውን በሕወሃት እየተነጠቁ የሚገለሉትን ኦሮሞችን በፖለቲካ ሽፍጠኝነትና በዐይን አውጣ ቅጥፈት በሚኒስትር ጌታቸው ለማዛመድ እንደደፈረው ለማንቋሸሽ አልነበረም!
=========000=========
ምናልባትም፡ አቶ ጌታቸው ለሕወሃት ባለው ቀናዒነት (የራሱም የዛሬው ምቾትና የነገው ተስፋው ታሳቢ ሆኖ)፡ ሁሉን አደነባብሮና አጣፍቶ፥ ጥረቱ የግንባሩን ዘረኛ ዓላማ ተግባራዊ ለማደረግ ከሆነ፣ ዛሬ አልተሳካለትም! – ከሕዝቡ ወገን ሆኜ ሳየው ነገም አይሳካለትም!

አንደኛ፥ አሸናፊው የፖለቲካ ተልዕኮ ቀናዒነትን የሚቀስቅስ ሃቀኛነት፣ በሰው ልጅ ክብር፡ ደህንነት እኩልነት ላይ የማይናውጥ የእምነት የተመሠረተ መሆን እንዳለበት ታዋቂው የሶሲኦሎጂ አባት ማክስ ዌበር (Max Weber) ብዛት ተጠቃሽ በሆነው የ1919 የሙኒክ ዩኒቨርሲቲ ሌክቸሩ – Politics As A Vocation ውስጥ ያሠምርበታል።

ሁለተኛ፥ መልዕክተኛው እውነትን እስከያዘና የኃላፊነት ስሜቱ ከፍተኛ ከሆነ፣ እንዲሁም በሁሉም ነገር መጠንን (sense of proportion) ማወቅ እስከቻለ ድረስ የዚህ ዐይነቱ ግለሰብ/ቡድን የሕይወት ጥሪው ኅብረተሰብን ማገልገል የሚያስችል ብቃትና ጥራት እንዳለው በአስተማማኝነት መመስከር ይቻላል ይላል።

ከላይ የተነሱትን ጉዳዮች በኅብረተሰብ መነጽር ስንመለከት፡ አንዳንድ ነገሮች ግልጽ ይሆኑልናል። አንደኛ፣ ሰሞኑን አቶ ጌታችው ረዳ ካሰማን ዘለፋና ሕዝብን ማንቋሸሽ ስንነሳ፣ እውነት የሚባል ነገር በሕወሃት መንደር እንደሌለና በየጊዘውና በየደረጃው ለእነርሱ አሳሳቢ የሆኑ ችግሮችን ለማለፍ ወይንም የእለያዩ ጥቅሞችን ለማግኘት እስካስቻላቸው ድረስ ውሸትና ዐይን ያወጣ ቅጥፈት መሣሪያችው እንደሆኑ ደግመን ደጋግመን ተመልክተናል – ሰሞኑን ብቻ ሳይሆን ባሉፉት 25 ዓመታት!

በአጭር አባባል፡ ከቪድዮው የምናዳምጠው፡ ሥልጣንን በእጁ የያዘ ወገን አጥቂና አስገባሪ በመምሰል የባዶ እምነትና ጅምላ ክህደት ነው።

ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ፣ አሁንም የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ረቂቅ ነው ብሎ ራሱ የፈበረከውን ለሕወሃት የሚጠቅመውን ባዶ ክርክሩን (false argument) የኅብረተሰብ እውነት ለማድረግ፣ ሲፈልግ ሕወሃት ለኅብረተሰብ አሳቢ እንደሆነና ለሕዝቡ ጥቅም እንደቆመ አስመስሎ በማቅረብ የቡድኑን አመለካከት በሕዝቡ ለማሠረጽ ሲሞክር ነው የሚታየው!

    “የተጀመረውን የተቀናጀ ማስተር ፕላን በተመለከተ ማብራሪያ በመስጠት በኩል በክፊልም፣ በፌዴራል መንግሥትም ባለሥልጣናት መዘግየት ነበር፡፡ ማስተር ፕላኑን በሚመለከት በኅብረተሰቡ ዘንድ በቂ ግንዛቤ ለመስጠት የሚያስችል ሥራ ያልተሠራው ረቂቅ ስለሆነ ነው፡፡ በጥናት ደረጃ ባለሙያዎች አጥንተውት፣ ባለድርሻ አካላትን አነጋግረው፣ ሕዝቡንም አወያይተው የመጨረሻ ቅርፅ የያዘ አልነበረም፡፡”

በሌላ በኩል ደግሞ በማስተር ፕላኑ ዙሪያ ኃላፊነት አለብኝ ብሎ አባይ ፀሃዬም “ሕዝቡ ተወያይቶ” አጽድቆታል፤ የኦሮሚያ አስተዳደር ተግባራዊ ባያደርገው “ልክ ይገባታል” ብሎ ባለፈው የካቲት ወር አሣፋሪ በሆነ መንገድ – በስካር መንፈስ ሳይሆንም አይቀርም – በአደባባይ መደንፋቱ ይታወሳል። ለማስታወስ የሚከተለውን የራሱን የአባይ ፀሃዬን ድምጽ ያዳምጡ፦

አባይ ፀሃዬ “ልክ ይገባታል!” “‘ልክ  – ክህደቱ ሲመጣ ደግሞ "እናስገባችዋለን!" የተባለች ቃል ከየት እንደተወሰደች አላቃትም!”

አባይ ፀሃዬ “ልክ ይገባታል!” “‘ልክ – ክህደቱ ሲመጣ ደግሞ “እናስገባችዋለን!” የተባለች ቃል ከየት እንደተወሰደች አላቃትም!”

ቪድዮው ላይ ሲክድ ፊቱን ላየው ሰው፣ የሕወሃት አመራሮች ሃሰት መናገርን ምን ያህል ያላንዳች ዕፍረት እንደሚጠቀሙበት እንደሚያሳይ፡ የአባይ ፀሃዬ ድርቅ ብሎ በራሱ ድምጽ የቀረበውን ሃዋሳ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የደነፋበትን ሣምንት ባልሞላ ጊዜ “‘ልክ እናስገባችዋለን’ የተባለች ቃል ከየት እንደተወሰደች አላቃትም!” በማለት ክዷል። ለዚያውም ‘የሌባ ዐይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ’ እንደሚባለው፡ የእርሱን ኦዲዮ መረጃ እንደሚለቅ አሰምቶ ነበር – እስካሁን ኤዲት ያደረገውን እንኳ የእርሱን ሃሰት ሕዝቡ ብትዕዝብት እንዲሰማው እንኳ ለመልቀቅ አልደፈረም – የሚያምነው እንደማይኖር በማወቁ!

ኢትዮጵያ በሕግና እኩልነት የምትተዳደር ብትሆን ኖሮ፡ ሕግ አስፈፃሚው የወከለው ወገን ምርመራ አካሂዶ እርምጃ በተወሰደ ነበር! የችግሮቻችንም ምንጭ፡ ዛሬ ኢትዮጵያውያን በሕግ ፊት እኩል አለመሆናቸው ነው!

ነገሩን ዐባይ ፀሃዬና ጓዶቹ እንደቀልድ ቢወስዱትም፡ ሰኞ ታህሳስ 21 ለኢሣት በኦዲዮና ቪዲዮ በደረሰው መረጃ መሠረት ምን ያህል የጥጋብና የብልግና ንግግሩ ኦሮሚያ ውስጥ በሕዝብ ደረጃ እንኳ ሕወሃት ክልሉን ለቆ እንዲወጣ አንገቱን ደፍቶ የኖረው የኦፒዲኦ አመራርም ግልጽ ጥያቄ አቅርቧል። በተጨማሪም የሕወሃት አረመኔ ሠራዊት በሕዝቡ ላይ ላደረሰው ጭፍጨፋ ተገቢው ተጠያቂነት እንዲኖር ጠንከር ያለ ድምጽ አሰምቷል።

ሆኖም፣ በክልሉ ውስጥ የተፈጸመው ወንጀል መልክ መያዝ የሚለካው ኦፒዲኦ በሚወስደው የፖለቲካ አቋም ሣይሆን፣ በኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። ለነገሩ የኦፒዲኦ ሰዎችም እሰከዛሬ የኦሮሞ ሕዝብ እንዲመታ ለሠጡት ድጋፍና ትብብር አመራራቸው ከተጠያቂነት አያመልጥም።

ከዚህ በታች ከHornAffairs የተገኘውን ቪዲዮ ወደ ኦዲዮ የቀየርነው የሃዋሳውን እንዲህ ያለ ባህሪ የለኝ ብሎ የካደውን ከዚህ በታች ማደመጥ ይቻላል፦

ለእኔ ግልጽ ያልሆነልኝ ለምን በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ዋናው የፖለቲካ ችግር ሆኖ መታየቱ ነው!

የኦሮሞ ወጣቶችና ቤተሰቦች ጠባቸው ከማስተር ፕላን – የፕሮጀክት ማስፈጸሚያ መሣሪያ ወይም ማስፈጸሚያ – ጋር ሳይሆን፡ ከእርሱ በስተጀርባ ካለው የመሬት ዘረፋ ዕቅድ ጋር ነው! በእኔ እምነት ዛሬ መንግሥታዊ መዋቅሮች በከሠረውና የዘረፋ መሣሪያ ናሆነው የሃገሪቱ አመራር ፖለቲካ ፓርቲ በተሠለቡበት ሁኔታና የሕግ አስተዳደርና ተከባሪነትና ተፈጻሚነት በሌለባት ኢትዮጵያ፣ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ብቻ ሳይሆን፣ የኢኮኖሚ ዞን ተብለው ለማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ በዋና ዋና ከተሞች ከአዲስ አናባ እስከ መቀሌ፡ ከሃዋሣ እስከ ኮሞብልቻ፡ ከድሬዳዋ፡ ከአዳማ እስከ ባህር ዳር፥ ወዘተ ሃገሪቱ ከውጭ እየተበደረች ዛሬ የምታቋቋሟቸው የኤኮኖሚ ዞኖች (የኢንዱስትሪ ዞኖች) የነገዎቹ ተጠቃሚዎች የሕወሃት ሰዎችና ኩባንያዎቻቸው ናቸው።

በዚህ ላይ ምንም ጥርጥር የለኝም!

ለእነዚህ ኩባንያዎች የሕወሃት ሰዎች ከውጭ በግልም በሕወሃት ባለሥልጣኖች አግባቢነት (ደላላነት) ለሕወሃት አባሎች የውጭ ኮንሰርኖች ብድር ይሠጣሉ ወይንም ሽርክና ይገባሉ። ነገ በአንድ ዜዴ የውጭው ኩባንያ ሲለቅ፡ መሬቱንም ንብረቱም ወራሾቹ ወያኔዎቹ ናቸው።

ከዚያ አንጻር፡ መታወስ ያለበት፥ የመሬትን ኩባንያው ያረፈበት ሥፍራ ባለቤቶቹ ተደብድበውና ተገፍተው፣ ዕድለኛ ከሆኑ በየዘመዱ መጠጊያ ያገኛሉ፤ አለያም ጎዳና ተዳዳሪ ይሆናሉ/ሆነዋልም!

በቴሌቪዥን ጭምር እንደታየው፣ ቤቶቻቸው ላያቸው ላይ ፈርሰውባቸው አያሌ ዜጎቻችን ንብረቶቻቸውን አስረክበው ተገቢው ካሣ እንኳ ሳይከፈላቸው፣ ባዶ እጆቻቸውን ቀርተዋል!

ከጥቂት ዓመታት በኋላም፡ ይህ በዝርያ ሕወሃታዊ ባልሆነ የነገው ትውልድ ላይ – በዛሬዎቹ ላይ እንደሆነው ይደገማል። መንግሥት የመንግሥትን ንብረት ሲሸጥ ሁለት ዋና ዋና ቡድኖች ነበሩ። አንደኛው አላሙዲ ነበር በቀደምት ዓመታት። እርሱም ስድቡና ጥላቻው ሲበዛበት ያለኝን ልብላና ላግሣ ብሎ ከዚያ ዐይነት ቅርምት ወጥቷል።

አሁንም ሆነ ነገ፡ እንደቁራ በየቦታው እየዞሩና እያደቡ የመሬት፡ የመንግሥት በጀትን በኮንትራት ሥራዎች (መንገድ፡ ውሃ፡ ሕንጻ፡ መብራት፡ ትራንፖርት፡ ኢንዱስትሪ ኢንፍራስትራክቸር ወዘተ)፣ በፕሮጅክት ሥራዎች ግንባታና አፈጻጸም፣ ሃገሪቷን አጥንቷን ጭምር የሚግጧት ምህረት የሌላቸው የሕወሃት ጅቦች ናቸው!

ወደፊት ማስተር ፕላኑ ትሮጃን ፈረስ ሆኖ ከኋላው የሕወሃትን ሰዎች የመሬት ዘረፋና የበላይነት ዓላማ ይዞ የመጣ መሆኑን ቃል አቀባዩና የሚወክለው መንግሥት እየካዱ ስለሆነ፡ ይህ ችግር ወደፊት በስላም ይፈታል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ያም ማለት ሕውሃት ከዚህ በፊት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንዳደረገው፣ ካድሬዎቹን ደርድሮ አሁን በቅርቡም በሁለተኛው የአምስት ዓመት ፕላን (GTP II) እንዳደረገው፡ ስድስት ሺህ ሰዎች ስብስቦ፣ በፍራቻ ሰዎች ተገቢውን ጥያቄ ነጻ በሆነ መንገድ መነጋገር በማይችሉበት ሁኔታ፡ ሕዝቡ ፕላኑነ አጸደቀው ተብሎ በሚዲያ ይነገራል።

ብዙውን ጊዜም ያልሆነውን ሆነ በማለት ወይንም ግለሰቦችን በመግዛት (ገንዘብ/ ሹመት) ወይንም፣ ሕወሃት – አልበጀውም እንጂ – በማስፈራራት ወይንም ጠቅላላ ኅብረተሰቡን በመሸወድ ሊያደርገው አይልችም ማለት አይደለም። GTP IIን በተመለከተ፣ እኔም በቲዊተር “Dead on arrival” መሆኑን ጠቅሼ ጽፌ ነበር።
የማይሆነውና የማይሳካውን “አይሆንም” ማለት ጸረ-ልማትነት ሣይሆን፣ በአንደኛው የአምስት ዓመት ዘመን የኢትዮጵያ ፕሮጄክቶችና የመንግሥት በጀት የሕወሃት ድርጅቶችና ማክበሪያ ስለነበር፣ ያ አሁን እንዳይደገም በማሰብ ነው።

ደግነቱ፥ ባለፈው ሣምንት ሕወሃትም ገንዘብ ማግኘት ስላልቻለ እንዲሁም – በድርቁ ምክንያት ጭምርም – GTP IIን ሥጋቱን ማሳክት የመቻሉን ጥርጥር ቢያሰማም፥ አስተባባሪው አረከበ ዕቁባይ ከሃገር ልማት ይልቅ በግል ራሱን ፕሮሞት እያደረገበት መሆኑ ይታያል!
=========000=========
የሕወሃት ሰዎች ሥልጣን ላይ መቆናጠጣቸውን ካረጋገጡ በኋላ፡ የሃብት ማካበት ርሃባቸው – በተለይም የመሬትና ቤቶች ጥማታቸው እየተባባሰ በመምጣቱ – መለስም ዜናዊም የፖለቲካ ሕይወቱን ለማራዘም፣ ይህንን ማርካት እንዳለበት በመገንዘብ፡ በተለያየ ዘዴ ሕጉን ለእነርሱ ብሎ እንዲለወጥ አደረገ እንዳይባል፣ ሰበብ አስባብ እየፈለገ፡ ከ2011 ጀምሮ ፓርላማ በቀረበ ቁጥር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ገሚስ ሰበብ ገሚስ ያለሕግ በሥውር የሚካሄደውን የመሬት ዘረፋ እነማን እንደሚያካሄዱት ዳር ዳር ማለት ጀመረ።

እንደውም መጋቢት 2011 ላይ ፓርላማ ውስጥ ባደረገው ንግግር ደርግ ያወጣው የመሬት አዋጅ፡ የውርስ መብት አለማረጋገጥ፡ በሥውር የመሬት ንግድ እንዲካሄድ አድርጓል ብሎ ችግሩን መሬትን የመግንሥትና የሕዝብ ንብረት ባደረገው አዋጅ ላይ ረበረበበት ይህም ሕጉ እንደሚቀየር ኅብረተሰቡን ያዘጋጀበት አንዱ መንገድ ነበር – ምንም እንኳ እንደ እውነቱ ከሆነ በማዘጋጃ ቤት ስብሰባዎች ላይ የተነሳውን መራኮት ላስታወሰ ሁሉ!።

‘የ1975 የመሬት አዋጅ’ – አለ መለስ:

    “…does open the way for transfer of lease right which could lead then into the speculation in urban land. The intention of the law was not to encourage speculation in terms of urban land ownership.”

በዚህ ጉዳይ ላይ መለስ ለሃገርና ለልማት የተቆረቆረ በማስመሰል፡ ሁኔታውን ለራሱና ለሕወሃት ሰዎች ሲያመቻች መሆኑን የሚጠቁሙ ጠቃሚ እየወጡ ነው።። ሆኖም ከተፈጸሙትና እየተፈጸሙ ካሉት የዘረፋ ተግባሮች አንጻር ሲታይ፡ መለስ የራሱን (የሕወሃትን) ዓላማ እየተገበረ ነው እንዳይባል ነው የሚከተለውን ንግግር በፓርላማ ያደረገው፦

    “There are two actors; on the one hand the private sector developers who were effectively engaged in grabbing the land that does not belong to them in any legal sense and misusing the land lease rights that they were given for personal profits and speculation and there were government officials who facilitated such activities or at least turn a blind eye while such activities were taking place.”

በሌላ በኩል ድግሞ፡ እንወርስና መሬቶቻችንን በግልጽ እንሸጥውና ሌላ ሃብት እናፈራበታለን ብለው የቋመጡት ሃሣቡን ደገፉት። ነገር ግን ለመለስም ሆነ በውቅቱ የአዲስ አበባ ከንቲባ ለነበረው ኩማ ደመቅሳና መኩሪያ ኃይሌ ተቃውሞው እጅግ አስደንጋጭ ነበር – ለመለስ ዜናዊም ጭምር።

እንደ ተለመደው በካድሬዎቻቸው አምታችነትና በአንዳንድ ሃብታም ነጋዴዎች የአምባሳደርነት ሹመት ፍንጭ በመስጠት (እንደተሰማው – ስም አልጠቅስም ፟ በኋላ ነገሩ ሲሳካላችው ሕወሃቶችም አፍንጫችሁን ላሱ ነው ያሉዋቸው) አዋቂ ሆነው መሃል በመግባት በተለይ በመኩሪያ ኃይሌ አስተባባሪነት የሕዝቡ የሕጉ ተቃውሞ ላይ ውሃ አፍሰውበታል። በመጨረሻም መኩሪያ ኃይሌ ነው ከአባ ዱላ ጋር በመተባበር ፓርላማ አባላት ኮረም በሌለበት ወቅት አዋጁ ጥቅምት 12፣ 2011 እንዲያልፍ የተደረገው።

The Ethiopia Observatory (TEO) የካቲት 8፣ 2012 ሥጋቱንና ቅሬታውን አቀረበ።

በተመሣሣይ መንገድ፣ በፓርላማ የተደረገውን ማምታት አስመልክቶ፡ Addis Fortune የሚከተለውን ትዕዝብት አሠፈረ፦

    “Critics are proved right. Little debate prevails in the EPRDF dominated parliament than protocol. It all runs dry. Party loyalty overshadows reasoned representation and interest based deliberation remains a pipe dream. Legislations are serving to put governmental intent into laws.”

የ1975 የከተማ መሬት አዋጅን ለመልከት እዚህ ይጫኑ

ክላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት፡ ከእንግዲህ የኢትዮጵያ ከተሞችና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በኤኮኖሚ ልማት ስም በሕወሃት ዘረፊዎች ምክንያት ለሃብት ንብረቱ ዋስትና የለውም – ያለው ሁኔታ በዜጎች ለሃገራቸው ፍትሃዊ አስተዳደርና ለራሳቸው ደህንነት የበላይ ተቆጣጣሪነቱን እስካልተያዙና መንግሥት የሚባለውን አካል ለሕዝብ ተጠሪነቱን ማጠናከር እስካልተቻለ ድረስ! በየሥፍራው የኤኮኖሚ ዞኖች እየተባሉ ቤቶች እየፈረሱ፡ ገበሬው መሬቱን እየተነጠቀ የሚደረገው ዘረፋ በልዩ ትኩረት ሊታይ ይገባል።

እ.አ.አ. ከ1975 ዓ.ም. ጀምሮ ፊውዳላዊ የሆነውን የመሬት ይዞታ በአዋጅ በሕዝብና በመንግሥት ቂጥጥር ሥር በማድረግ፣ በወቅቱ በሃገሪቱ ሠፍኖ የነበረው የፊውዳል አገዛዝ ለመስበር አስችሏል፤ ሕወሃትም ከመጣ በኋላ ሕጉ ዛሬ የሚታየውን የመሬት ስግብግብነት አፍኖ ለመያዝ አስችሎ ነበር – መለስ ለጓዶቹ በሩን ባይበረግድላቸው ኖሮ!

በዚያ ምክንያት ነው መለስ ሕጊ እንዲወጣ የተጠቀመበት ዘዴ ቅጥፈት መጠቀሙን ያሳያል። ለዚህም ማረጃዎቹ፦

አንደኛ አብዛኞቹ በመሬት ሥውር ንግድና ልውውጥ የተሠማሩት በአብዛኛው የሕወሃት አባሎች ናቸው። ሕወሃትም የአዲስ አበባን መሬት በቁጥጥሩር ሥር ለማድረግ ባሠረጋቸውና ባቋቋማችው የሬል ስቴት ኤጀሲዎች አማካይነትና የአባይ ፀሃየ ደላላነት ነበር – ኤርሚያስ ለገሠ እንደመሰከረው!

ሁለተኛ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በዘር ልዩነት ገንዘብ እያፈሰሰላቸው ተጠቃሚ የሆኑት እነዚሁ የአንድ ብሔረስብ የግል ድርጅቶች ናቸው። አብዛኛውንም የአዲስ አበባን መሬት በመቆጣጠር ላይ ያለው ሕወሃት ሆኖአል።

በ1975 ዓ.ም. የወጡት የከተማና የገጠር መሬት ሕጎች በተግባራዊ መንገድ መሬትን የሕዝብና የመንግሥት ማድረጋቸው የማያጠራጥር ነበር። ክ2011 ጀምሮ በወጡት አዋጆች ግን፡ ሕወሃት የኢትዮጵያን ሕዝብ ከመሬት ባለቤትነት አስወግዶ፡ የሃገሪቱ መሬት ባለቤት ከሆነ ሰንበት ብሏል።

የኢትዮጵያ ሕዝግብ ከዚህ የዘራፊዎችና የደም መጣጮች ሥርዓት ለመላቀቅ ለራሱና ለልጅ ልጆቹ ሲል ትግሉን ካላፋፋመ፡ ልጆቹ በገዛ ሃገራቸው ከባርነትና ከግርድና ውጭ ምንም እንደማይቀራቸው ሊገነዘግቡት ይገባል!

%d bloggers like this: