የሕወሃትን የመሬት ዘረፋ ሕዝቡ አጠናክሮ በመቃወሙ፣ ግንባሩ በተላላኪው ኦሕዴድ አማካይነት “አቁሜዋለሁ” ማለቱ፣ የፈሰሰው የዜጎቻችን ደም ከንቱ ሆኖ እንዲቀር ያስባልን?

14 Jan

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ከሕወሃት በተሠጠው መመሪያ መሠረት ከሶስት ቀናት ስብሰባ በኋላ፣ ማስተር ፕላኑን አቁመነዋል ማለቱን መግለጹ፣ በስሙ የሚነግደውን ሕዝብ ድኅንነት ማረጋገጥ ቀርቶ አስደብዳቢና ገዳይ ሆኖ ከርሞ ሳለ፣ አሁን በኦሮሞ ሕዝብ ስም ከዚህ በኋላ ምን እደሚደረግና እንደማይደረግ ለመናገርና ለማሳመን ምንም ብቃት እንደሌለው ኦሕዴድ በሚገባ አረጋግጧል!

ሌላው ኦሕዴድ ከፖለቲካው ጋር እንዳልሆነ የሚያሳየው፡ አሁንም ስለ አዲስ አበባ ማስተር ፕላን ያወራል። የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ለሕወሃት መሬት ዘረፋዎች ሽፋን በመሆኑ እንጂ፡ የኦሮሞ ተማሪዎችም ሆኑ ገበሬዎች ወላጆቻቸው ከፕላኑ ጋር የሚያላትም ምንም ሌላ ችግር የለባቸውም።

ኦሕዴድም ሆነ ሕወሃት ልብ ሊሉት የሚገባው፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአጠቃላይ የሕወሃት ረገጣና ብልግና ስልችቶታል። ስለሆነም ከእንግዲህ የኦሮሞ ሕዝብ የተነሳበትም የጭቆና የማራገፍ ጥያቄ የኢትዮጵያ ሕዝብም ጥያቂ ሆኖ እንደተፋፋመ እንዲቀጥል ሁሉም በየፊናው የድርሻውን ቢያበረክት፡ በኢትዮጵያ የነጻነትና የዲሞክራሲ ዘመን እንዲቀርብ ያደርጋል!

ስለሆነም፣ ጥር 13 ኦሕዴድ በሠጠው መግለጫ ማስተር ፕላኑን እንደሚተወው ቢያሰማም፡ አስተባባሪ አመራር በሌለበት ሁኔታ በሕዝቡ ምሬት፣ በቃኝ ባይነትና መጎልበት በሚገባው የሌሎች ኢትዮጵያውያን ድጋፍ የተነዳው የኦሮሞ ወጣቶች ትግል እስካሁን ምን ያህል በትክክለኛ መሥመር ላይ መሆኑን አመላካች ነው። በዚህም ረገድ፣ ታህሳስ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. የትላንቱና የዛሬው የኦሮሞ ኅብረተሰብ ትግል የኦሮሞች ብቻ ወይንስ የመላው ኢትዮጵያ? በሚል ርዕስ ካሠፈርኳቸው ሃሣቦች ውስጥ አንዳንድ ነገሮችን
እንደገና ለመዳሰስ ተገድጃለሁ።

ለዚህም በሃገራችን ላይ የተንሠራፋው ውጥረትና በአንዳንድ መልኩ የ1974 አብዮት ዋዜማን የተመሳሰለው የኦሮሞች ትግል ለወደፊቱ ተስፋ የሰጠ በመሆኑ፣ አንዳንድ ሃሣቦችን መጋራት ጠቃሚ መሆኑን በማመን ከመሠንዘር ባሻገር፡ ታህሳስ 31 ቀን 2015 በማዕደ ኢሣት “የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ” የሚለውን በመምዘዝ፣ እንደ ኢሣት ዜና ማሠራጫ ሠራተኛነታቸው ባሻገር፡ አንድንዶች “እሥረኞች ይፈቱ፤ ለተጎዱት ካሣ ይከፈል…” የሚሉት ሃሣቦች መሠንዘራቸው እንደ ወንጀል ተቆጥሮባቸው መተቸታቸው፡ ባለንበት የትግል ደረጃ ጠቃሚነታቸውን ካለማመዛዘን የመጣ ይመስለኛል። ኢሣት መረጃ ባለፈ በጥቅሉ – እንደ ኢሕአፓ ሁሉ የትግል ስትራቴጂ ነዳፊ ይመስል– እነዚህን ተመሳሳይ ሃሣቦች በሠነዘሩት ግለሰቦች ላይ በአግድሞሽ የተቃጣው ጠረባ አላስፈላጊና የወረደ መሆኑ ስለተሰማኝ ጭምር ነው ይህንን የማነሳው።

እኔም በአሁኑ ወቅት ምን መደረግ ይገባል በሚል ከአንድ ወር በፊት አንዳንድ ሃሣቦችን ስሰነዝር አንድ መንደርደሪያ ያስቀመጥኩት ነጥብ የሚከተለው ነበር፡-

“ከታሪክ እንደሚታየው፣ የፖለቲካ ውጥረት በተጠናከረበት ወቅት ሁሉ፣ በዓላማ በተቆራኙ መካከል ሁነታው ራሱ ለአመራር መፈጠር ተገቢውን አመራር የመፍጠር ግፊት እንደሚኖረው መገንዝብ ያስፈልጋል። ለዚህም በዘር መከፋፈል የሕወሃት የበኩር ልጅ መሆኑን አበክሮ በመገንዘብ፡ ያለፈው ላይ ብቻ ከማተኮር ተሻግሮ፡ ግልጽነት ያለበት በአዲስ አስተሳስብ የተባበረች ኢትዮጵያን በመፍጠር ዘረኞችን ከምድራችን ላይ ለመጥረግ መቻቻል ያስፈልጋል።”

በነገራችን ላይ፣ ዶ/ር ታደሰ ብሩም ጥር 13/2015 ሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ከጠየቋቸው ነገሮች መካከል – እኔን የምስማማባቸው – የማዕደ ኢሣት ሙያተኞች በሚገባ ያላመነዠጉት ከላይ ያነሳኋቸው ጉዳዮች – ይገኙበታል – ክዚህ በታች ባለው የኢሣት ኦዲዮ ላይ እንደተቀመጠው፡፡

ዶ/ር ታደሰ ብሩ የኦሕዴድን መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ዝሕብ ድል ነው በማለት ያሠፈሩት ትክክለኛ ግንዛቤ ነው። ይህ ድልም የተገኘው – ምንም እንኳ ሕወሃት የኦሮሞ ወጣቶች “በጠባቦችና በጸረ-ሕዝቦች እየተመሩ ልማታችንን በመቀልበስ ላይ ናቸው” እያለ ሲወንጅል ቢከርምም፣ ከላይ እንደጠቀስኩት፣ ሕዝቡ በቁጣው ተገፋፍቶ የወሰደው እርምጃ ነው።

ይህ ረገጣው ያስከተለው ቁጣ ደግሞ በኦሮሞች ላይ ብቻ የተወሰነ ባለመሆኑ፡ ሁላችንም – ማበረታቻዎችን እየተጠቀምን – ትግሉ ወደፊት የሚራመድበት ላይ ልናተኵር እንደሚገባን እኔም ይሰማኛል። ብዙ ዜጎች በዚህ ረገድ እንቱ የሚባል አስተዋጾ በማድረግ ላይ ይገኛሉ!

ከላይ በጠቀስኩት ጽሁፍ፣ ወደዚህ ደረጃ እንደምንደርስ ስለተሰማኝ አሥራ አንድ እርምጃዎችን ከ(ሀ) እስከ (ቸ) ሕዝቡ እንዲወስድ በወቅቱ ዘርዘርያለሁ። እነዚህም ከነመንደርደሪያቸው የሚከተሉት ናቸው፦

  “ለአፉ ለከት የሌለው ጌታቸው ረዳ እንኳ በዛሬው ውይይት ላይ “ጠባብ አመለካከት ያለቸው ወገኖች ለኦሆዴድ ዕውቅና ባለመስጠት የራሳቸውን ዓላማ ለመዘርጋት እንደሚንቀሳቀሱ” አድርጎ አቅርቦታል –የራሱ ወገን የመሬት ዘረፋ ከመሆን ይልቅ!

  በሌላ በኩል ደግሞ በዚህም ምክንያት ከዛሬው ምክክሩ ሕወሃት ማድረግ ያሰበው “ለሰሞነኛው ሁከት አንደ አዲስ መቀስቀስ አንዱ በቅርቡ ጨፌው ያፀደቀው የከተሞች ልማት አዋጅ በመሆኑ በቀጣይ ሠፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እንደሚሠራ እና በአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙሪያ የተቀናጀ ልማት ረቂቅ ዕቅድ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ነው።”

  በነገራችን ላይ፡ ሕወሃት/ኦሕዴድ በሚዲያ ምክክራቸው እንዳበቃ፣ የሕወሃት ተሳታፊዎች ያደረጉት ነገር ቢኖር፡፣ ሕወሃት የኦሕዴድን የሴቶች ሊግ ጉርሻ እየሰጡና እያስፈራሩም፡ “በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች ሰሞኑን የተቀሰቀሰውን ሁከትና ብጥብጥ አጥብቀው እንደሚቃወሙ” ገለፁ ሲል በሚድያው ላይ ፈንጭቶበታል።

  ይህ ግን ደረታቸውንና ሕይወታቸውን ለመሠዋት የተዘጋጁትን ወጣቶች ከቆሙለት ዓላማ ካለፈው ዓመት ግድያ ተሸጋግረው እንደገና በዚህም ዓመት ለመጋተር መቁረጣቸው ሲታይ።

  ስለሆነም፣ በእርግጥ ሕወሃት ዛሬ ኢትዮጵያ የገባችበትን ውጥረት ማርገብ የሚሻ ከሆነ፣ በአስቸኳይ በአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የሚከተሉትን እርምጃዎች ሊወስድ ይገባል፦

  (ሀ) በ24 ሰዓት ውስጥ የታሠሩትን የሁለተኛ ደረጃና ይኒቨርሲቲ ተማሪዎችንና መምህራንን መፍታት

  (ለ) በ24 ሰዓት ውስጥ የታሠሩትን ወላጆች፡ የየከተማና ቀበሌ ነዋሪዎች፥ የፖለቲካ ድርጅቶችን አመራሮችና አባላትን መፍታት

  (ሐ) በ24 ሰዓታት ውስጥ በሕወሃት ለተሠውት ዜጎች ቤተሰብች አገዛዙ ይቅርታ እንዲጠይቅና ተገቢውን ካሣ በአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ለመክፈል ቃል አሁኑኑ እንዲገባ

  (መ) በሕዝብ ነብረቶች ላይ ለደረሱት ጉዳቶችና መደምሰሶች ተገቢውን ካሣ እንዲከፍል

  (ሠ) ለሕዝብ መብቶች ሲታገሉ እንደ ወንጀል ተቆጥሮባቸው መቀመቅ የተወረወሩት የፖለቲካ እሥረኞች – ጋዜጠኞችን ጨምሮ – በሶስት ቀናት ጊዜ ውስጥ በነጻ እንዲለቀቁ

  (ረ) በዝርያቸውና ቋንቋቸው ምክንያት የታሠሩ እሥር ቤቶችን ያጣበቡት የኦሮሞ ፖለቲካ እሥረኞች ባስቸኳይ ነጻ እንዲለቅቁና፣ ለተፈጸመባችውም ግፍ ተገቢው ካሣ እንዴከፈላቸው አስፈላጊው የሕግ ሁኔታ እንዲመቻችላቸው

  (ስ) የኢትዮጵያ ሕዝብ ለወደፊቱ የሚያስፈልገውን የአስተዳደር ሁኔታ በነጻ ፍላጎቱ መመሥረት ይችል ዘንድ፡ የፖለቲካ ኃይሎች መሰባሰብና መነጋገር እንዲችሉ ሁኔታውን ለመጠቀም የሚያደርጉት ጥረት በማናቸውም ረገድ እንዳይደናቀፍ መጠንቀቅ

  (ሽ) ለሱዳን ሊሠጥ ቃል የተገባው የኢትዮጵያ መሬት ውል ያላንዳች ማወላወል መሠረዙን ያላንዳች መቀባጠር በማያወላውል መንገድ ግልጽ እንዲድደረግ

  (ቀ) በኢጋድ አማካይነትና በሁለትዮሽ መሰተጋብር ከአፍሪካ ቀንድ ሃገሮች ጋር በስደት ከሃገር የወጡትን ዜጎም የዓለም አቀፍን ሕግ በመጣስ የሚያደርገው አስገድዶ የመመለስ ወይንም የማፈን ተግባር ያላንዳች ማመንታት አስፈላጊውን ሜሞራንደም በመላክ ሕወሃት በዚህ ረገድ ሲያደርግ የነበረው ጥረታና ጎርቤቶችን የማስገደድ ሁኔታ መሠረዙን ማስታወቅ

  (በ) በዚህ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ከፕሮፓጋንዳ ነጻ የሆነ ሚዲያ እንዲኖረው፡ የመናገር፡ የመጻፍ፡ የመሰብሰብ፣ በነጻ የመደራጀትና የእምነት መብቱን ያላንዳች ዕገዳ እንዲጠቀም የተጣሉበት ማቀቦች በሙሉ እንዲነሱ። ይህንንም በሚመለከት የወጡት አዋጆች፡ ሕጎችና ደንጋጌዎች በሙሉ እንዲሻሩ

  (ተ) በአኤአ በ2009 ዓ.ም. የወጡት የጸረ ሽብርና (Proclamation No. 652/2009) መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አሠራር በመመዝገብ ስም ዓላምው ግን የማኅበራዊ ኑሮን ሰብዓዊ መብቶች መከበርን ዕርዳታ ለመግታት የወጣው ሕግ አዋጅ ቁጥር 621/2009 (Proclamation No. 621/2009) በዚሁ በአንደ ወር ውስጥ እንዲሻሩ።

  (ቸ) በአዲስቷ ኢትዮጵያ፡ ለሃገር ደህነነትና ጥበቃ ዋናው ኃይል ሕዝቡ ራሱ እንጂ የሃገር ዳር ድንበር ለሱዳን የሚሸጥ አሰተዳደር አለመሆኑ ግንዛዜ ውስጥ ሊገባ ይገባል። በተመሳሳይ መንገድም ይህም ሕወሃት ከሱዳኑ ዓለም አቀፍ ወጀለኛ አል በሽር ጋር የሚያደርገው ስምምነት – ታህሳስ 4፣ 2013 ካርቱም ላይ የተፈራሙትንና የቀሞዎቹን ከመለስ ዜናዊ ጋር የተደረጉትን ጨምሮ – በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተሽረው ይኸው መረጃ ለሕዝቡ በሕዝብ መገናኛ መሣሪያዎች ሊገለጽለት ይገባል።”

በአሁኗ ሰዓትም፣ የሚካሄደውን የኦሮሞች ትግል በሕዝባዊ ቁጣ መገለጫነቱና ለወደፊትም የኢትዮጵያውያን የነጻነትና የዲሞክራሲ ትግል ፈር ቀዳጅ እንደሚሆን በሙሉ ልብ ሊታመን ይገባል!

አሁንም ደግሜ ደጋግሜ የማሠምርበት፣ የትግሉን መሪ ለመጨበጥ መሽቀዳደም ሳይሆን፡ ይህ ትግል የራሱን የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎትና ጥቅሞች ለማስጨበጥ የሚረዳ አመራር እንዲመሠርት፣ ሃሣቦች ፋታና ጊዜ ልንሰጠው ይገባል። ተማሪዎቹሙ ሆኑ ደጋፊዎቻቸው በነጻነት በእነዚህ ሃሣቦች ላይ የየራሳቸውን ሃሣቦች ሊጨምሩ ሊቃወሙ ይችላሉ። የኢሣት ሥራ መረጃ ማከፋፈል ነው፣ ኢሣት ግለሰቦችን በግልጽም ሆነ በአሽሙር የሚተች ሚዲያ መሆነ የለበትም!

በሌላ አባባል፣ ኢሣት እስካሁን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ያደረገውንና የሚያደርገውን አስተዋጾ ባህሉና መመሪያው አድርጎ ቢንከባከበው፣ አኩሪ ታሪኩን ለመጻፍ ያስቸለዋል።

በተጨማሪም ከዚህ በፊት በሊቢያ የኢትዮጵያውያን ዕርድ ማግሥት የባለ ሶስት ክፍል ትዊተር መልዕክት “እባካችሁ ሕወሃትን የኢትዮጵያ መንግሥት ማለታችሁን አቁሙ” ብዬ እስከመለመን ድረስ ብጠይቅም – ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ጭምር – ምናልባትም ኢሣት አንዱ የሚወደው አባባል ደግሞ ድጋግሞ “የኢትዮጵያ መንግሥት” ማለት እስኪመስልበት ድረስ አባብሶታል!

ለሕዝቡ ከበሬታ የሌለው አስተዳደር መንግሥት ሊባል አይችልም። የመንግሥት ቀደምት ተግባር የዜጎችን ድኅንነት ማረጋገጥና ማበራከት ሲሆን፡ ሕወሃት የሚፈጽመው ተጻራሪውን በመሆኑ መንግሥታዊ ባህሪ ቅንጣቱም የለውም!
 

%d bloggers like this: