“ማስተር ፕላኑ መሰረዝ ያለበት በፓርቲ ውሳኔ አይደለም” – ፓርቲዎች ተቃዋሚዎች

16 Jan

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

    “ማስተር ፕላኑን ህዝቡ እንደማይቀበለው ተረጋግጧል” – ኦሕዴድ

ማስተር ፕላኑ ተግባራዊ እንዳይሆን የተሰረዘው ሕዝቡ እንደማይቀበለው በውይይት በመረጋገጡ መሆኑን የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅ/ቤት የገለፀ ሲሆን ተቃዋሚዎች በበኩላቸው፤ ማስተር ፕላኑ መሰረዝ ያለበት በም/ቤት እንጂ በፓርቲ ውሳኔ አይደለም ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልልን የሚያስተዳድረው የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሰሞኑን ለ3 ቀናት በአዳማ ከተማ ባደረገው ስብሰባ፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲያወዛግብ የከረመው የአዲስ አበባና ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን ሙሉ ለሙሉ እንዲቀር ውሳኔ አስተላልፏል። የፓርቲውን ውሳኔ በተመለከተ የተጠየቁት የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ፤ በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ከአርሶ አደሩ፣ ከወጣቱና በየደረጃው ከሚገኝ የህብረተሰብ ክፍል ጋር በተደረገ ውይይት ማስተር ፕላኑን ሕዝቡ እንደማይቀበለው አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

ኦሕዴድም የህዝቡን ፍላጎት መሰረት አድርጎ ማስተር ፕላኑ ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ መወሰኑን የገለፁት አቶ ዳባ፤ ሕዝቡ በውይይቱ ወቅት የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ማንሳቱንም ጠቅሰዋል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች በበኩላቸው፤ ማስተር ፕላኑ ቀርቷል የሚለው ምላሽ የተሰጠው አሳማኝ ባልሆነ መልኩ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡

በኦሮምያ ክልል ማስተር ፕላኑን መነሻ በማድረግ የተነሳውን ተቃውሞና ግጭት ተከትሎ ተቀዳሚ ም/ፕሬዚዳንቱ አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ከ500 በላይ አመራርና አባሎቹ እንደታሰሩበት የገለፀው የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ “ማስተር ፕላኑን መሰረዝ ያለበት ፓርቲ ሳይሆን ምክር ቤቱ ነው” ብሏል፡፡

“ለሕዝቡ ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ በቂ አይደለም” ያሉት የኦፌኮ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ጥያቄው የአዲስ አበባ መስፋፋት ብቻ ሳይሆን የሚፈናቀለው ገበሬ የካሳና ዋስትና ጉዳይን በዋናነት የያዘ በመሆኑ ማስተር ፕላኑ ተሰርዟል ብቻ ብሎ ማለፍ በቂ መልስ አይሆንም ብለዋል፡፡

“ሁለት ወር ሙሉ ብዙ ሰብአዊ ቀውስ ሲፈጠር ኦህዴድ የት ቆይቶ ነው ሰሞኑን በአስቸኳይ ስብሰባ ይሄን ውሳኔ ያስተላለፈው?” ሲሉ የጠየቁት ዶ/ር መረራ፤ በግጭቱና ተቃውሞው ሳቢያ የሞቱና የታሰሩ ሰዎች ጉዳይ በዝምታ መታለፉንም ነቅፈዋል።

“የኛ ክርክር አዲስ አበባ ባዶ መሬት ላይ አትስፋፋ የሚል አይደለም” ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ዋናው ጥያቄ ገበሬው ከመሬቱ መፈናቀል የለበትም የሚል ሲሆን የግድ ከሆነም ቀሪ እድሜውን ሊያኖረው የሚችል ካሳ ተከፍሎት ሊነሳ ይገባል የሚል ነው” ብለዋል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ኦህዴድን እየሰማው አይደለም ያሉት ዶ/ር መረራ፤ ድርጅቱ ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቆ ስልጣን መልቀቅ አለበት ብለዋል፡፡

የመድረክ ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፤ “እኛ እስከምናውቀው ማስተር ፕላኑ በምክር ቤት አዋጅ የፀደቀ በመሆኑ መሻር ያለበትም በአዋጅ ብቻ ነው” ብለዋል፡፡ መንግስት፤ አዋጁ ገና በረቂቅ ደረጃ ያለና ለሕዝብ ውይይት በሰፊው ያልቀረበ መሆኑን በመጥቀስ እንደፀደቀ ተደርጎ የሚነገረው ትክክል አለመሆኑን በተደጋጋሚ መግለፁ ይታወሳል፡፡ ፕ/ር በየነ ግን አይቀበሉትም። “እኛ እስከምናውቀው ፀድቋል ተብሎ ነው ቢሮ ተደራጅቶለት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የተገባው” ይላሉ፡፡

“የዲሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብትና የሕግ የበላይነትን እየጠየቀ ላለ ሕዝብ ማስተር ፕላኑ እንዲቆም ተወስኗል ማለት ብቻ በቂ መልስ አይደለም ያሉት የኢዴፓ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንደሰን ተሾመ በበኩላቸው፤ ኦህዴድ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የህዝቡ ጥያቄ እየሰፋ ሄዶ ከማስተር ፕላኑ በላይ ፖለቲካዊ ይዘት ከተላበሰ በኋላ ኦሕዴድ መግለጫ መስጠቱ ብዙ ለውጥ ያመጣል ብዬ አላምንም ያሉት አቶ ወንደሰን፤ ማስተር ፕላኑ ተሰርዟል የሚለው ውሳኔ ለሕዝቡ በቂ ምላሽ አይደለም ብለዋል፡፡

የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ በበኩላቸው፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ድርጅቱም ሆነ መንግስትም ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች የአፈፃፀም ችግሮችን በመቅረፍ ተግባራዊ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡

የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በበኩሉ፤ የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ማስተር ፕላኑ እንዲቆም መወሰኑ እየተገነባ ያለው ዲሞክራሲያዊ ስርአት በሕዝብ ሉአላዊ የስልጣን ባለቤትነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አረጋግጧል ብሏል – ትናንት ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ፡፡

“የሕዝቦች ውሳኔ የተከበረበት ህገ መንግስታዊ ስርአት በጠንካራ መሰረት ላይ እየተገነባ ነው” ያለው መግለጫው፤ የክለሉ መንግስትና ህዝብ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም ሆነ የልማት ጉዳዮችን በውይይትና ምክክር ለመፍታት መዘጋጀታቸውን አመልክቷል፡፡

የሕዝብን ጥያቄ በመጥለፍ ሁከትና ብጥብጥ ሲፈጥሩ የቆዩ አካላት ከዚህ ውሳኔ ሊማሩ ይገባል ያለው ጽ/ቤቱ፤ እኒህ ወገኖች ወደ ህዝብ መድረኮች በመምጣት የሰለጠነ የሃሳብ ክርክር እንዲያደርጉ መክሯል፡፡
/አዲስ አድማስ
 

ተዛማጅ ዜና:

    የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች መሰረታቸው የህዝብ ጥያቄዎች ናቸው- አቶ ዳባ ደበሌ

 

%d bloggers like this: