በዘመናችን ከሚታዩት መንግሥታዊነት ብቃት ማነስ የተከሰቱ የአስተዳደር ጉድለቶችና ለሕይወትና ንብረት ተጠያቂነት አለመኖር ተጠቃሽ መሆን ከሚገባቸው የአዲስ አበባ ምሣሌዎች መካከል

17 Jan

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

አዲስ አበባ ፣ ጥር 8 ፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በአዲስ አበባ በሚገኙ ዋና ዋና የቀለበት መንገዶች ላይ 132 የንብረት ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሰልጣን አሰታወቀ።

ባለስልጣኑ ለጣቢያችን እንደገለጸው በቀለበት መንገድ መከላከያ ብረቶች ላይና ግንቦች ላይ ነው 132ቱ የግጭት አደጋዎች የደረሱት።

Addis Abeba Ring Road (Foto Fana)

Addis Abeba Ring Road (Foto Fana)

በተጨማሪም ከቀለበት መንገድ ውጭ ሌሎች መንገዶች ላይም 134 የንብረት አደጋ መድረሱን አስታውቋል።

ይህን ተከትሎም የጉዳት ካሳ እንዲፈጸም በጠየቀው መሰረት ከ2 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ መከፈሉ ተገልጿል።

የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፈቃዱ ሀይሌ የጉዳት ካሳው ባለስልጣኑ ለጥገና ካወጣው ወጪ አንፃር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይ ጉዳት የደረሰባቸውን ንብረቶች ተከታትሎ ተገቢውን ካሳ ማስፈፀም ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡም ቢሆን ለንብረቶቹ የሚደረገውን ጥንቃቄ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።
 

በአዲስ አበባ ቡልጋሪያ አካባቢ ለህንፃ ግንባታ የተቆፈረ ጉድጓድ ተደርምሶ በ6 ሰዎች ላይ ጉዳት አደረሰ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ቡልጋሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለህንፃ ግንባታ በተቆፈረ ጉድጓድ በደረሰ የመደርመስ አደጋ ስድስት ሰዎች ቀላልና ከባድ ጉዳት ደረሰባቸው።

አፍሪካ ህብረት ፊት ለፊት በሚገኝ ስፍራ ለህንጻ ግንባታ እየተቆፈረ በነበረው ከ12 ሜትር ጥልቀት ባለው ጉድጓድ ውስጥ ስራ ላይ የነበሩ ሰራተኞች ናቸው በመደርመስ አደጋው ጉዳት የደረሰባቸው።

በአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ባለስልጣን የቂርቆስ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ኒቆዲሞስ ቡጬ ለጣቢያችን እንደገለፁት፥ የመደርመስ አደጋው የደረሰው ዛሬ ጠዋት 4 ሰዓት ከ20 ላይ ነው።

በግንባታው ስፍራ ከነበሩት አጠቃላይ ሰራተኞች መካከል በስድስቱ ላይ ከደረሰው ቀላልና ከባድ ጉዳት በተጨማሪ የአንደኛው ሰራተኛ ደብዛ በመጥፋቱ የመፈለጉ ስራ መቀጠሉንም አቶ ኒቆዲሞስ ተናግረዋል።

በአካባቢው ያለው አፈር ልል በመሆኑና ትናንት የጣለው ዝናብ በቀላሉ እንዲደረመስ ስላደረገው ነው አደጋው የደረሰው ተብሏል።

ተጎጂዎቹም በዘውዲቱና የካቲት 12 ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል።
 

በአዲስ አበባ ከተተከሉ አምስት የአደባባይ ላይ ስክሪኖች መካከል አራቱ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 18 ፣ 2008 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከ28 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ወቶባቸው ከተተከሉት አምስት የአደባባይ ላይ ስክሪኖች መካከል አራቱ አገልግሎት መስጠት አቁመዋል።

ስክሪኖቹ በአራዳ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ንፋስ ስልክ፣ የካና ኮልፌ ክፍለ ከተሞች የተተከሉ ናቸው።

ክፍለ ከተሞቹ አልያም የከተማው አስተዳደር በማንኛውም ዘርፎች ላይ ያከናወኗቸውን የልማት ተግባራት እንዲሁም ወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮችን ለአካባቢው ህብረተሰብ እንዲያደርሱ ታስበው የተተከሉ ናቸው።

ሙስና ያሳወረው ስክሪን አደባባይ Corruption-Blinded Square Screen (Foto Fana)

ሙስና ያሳወረው ስክሪን አደባባይ Corruption-Blinded Square Screen (Foto Fana)

ይሁን እንጂ እነዚህ ስክሪኖች የታሰበላቸውን አላማ ሳያደርሱ አገልግሎት መስጠት አቁመዋል።

ለዚህ ደግሞ ተገቢውን ጥበቃ እና ክትትል የሚያደርግ አካል አለመኖሩ ስክሪኖቹ ለታሰበላቸው አላማ እንዳይውሉ እና ለብክነት እንዲዳረጉ ማድረጉን ነው ነዋሪዎቹ የሚናገሩት።

ከፍተኛ ወጭ ወጥቶባቸው የተተከሉት እነዚህ መገልገያዎች ያለ አገልግሎት መቀመጣቸው አግባብ እንዳልሆነም ያነሳሉ።

እነዚህ ንብረቶች በአያያዝ ጉድለትና በባለሙያ እጥረት ሳቢያ በተገቢው መልኩ አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን የሚናገሩት ደግሞ የየክፍለ ከተሞቹ የስራ ሃላፊዎች ናቸው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ፥ ክፍተቱ መኖሩን አምኖ በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታተ የሚያስችል አሰራረ እየዘረጋሁ ነው ብሏል።

በቀጣይ የታዩትን ክፍተቶች በመሙላትና የተበላሹትን በመጠገን ወደ አገልግሎቱ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል።

ከዚህ ባሻገርም ከማዕከል መቆጣጠር የሚያስችልና ስርጭቶችን ማድረስ የሚያስችል አሰራር ለመተግበር እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።
 

የፋብሪካዎች ዝቃጭ በአካባቢና በማኀበረሰብ ደህንነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ነው

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 14 ፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ፋብሪካዎች ዝቃጭ በአካባቢና በማኀበረሰብ ደህንነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑ ተገለጸ።

የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

የደን ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ከበደ ይማም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከሚገኙ ነዋሪዎች የተሰበሰበውን ቅሬታ በውይይቱ ወቅት አቅርበዋል።

ከአካባቢ ብክለት ጋር ተያይዞ በሚመለከተው አካል የሚወጣውን ህግ ፋብሪካዎቹ ቢቀበሉም ተፈጻሚ በማድረግ ረገድ ክፍተት መኖሩን ገልጸዋል።

የአደገኛ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድን በተመለከተ አዋጅ አለመውጣቱ ለችግሩ መባባስ ምክንያት ሆኗል ያሉት ነዋሪዎቹ በአፈር፣ በውሃና በአየር ንብረት ደህንነት ላይ ተጽእኖ እያሳደሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

የቅንጅታዊ አሰራር ጉድለትና የማስፈጸም አቅም ክፍተት፥ ፋብሪካዎች ከችግሮቹ ጋር ሥራቸውን እንዲያከናወኑ መንገድ መክፈቱንም ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት።

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደባሱ ባይለየኝ በበኩላቸው፥ አንዳንድ ፋብሪካዎች የልቀት መጠንን የሚቀንሱ መሳሪያዎች ቢገዙም በአግባቡ ጥቅም ላይ እንደማያውሉት ተናግረዋል።

ፋብሪካዎቹ ዝቃጫቸውን እንዲቀንሱ ለማድረግ ሚኒስቴሩ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ ድጋፍ የሚሹትን በመደገፍ የሚፈጥሩትን ተጽዕኖ እንዲቀንሱ እንደሚደረግና መዘጋት ያለባቸው ፋብሪካዎችም ይዘጋሉ ብለዋል።
 

%d bloggers like this: