ሕወሃት መሬት ዘረፋውን እንደሚቀጥል ዛሬ ሲያረጋግጥ፣ ከማፍረሱ በፊት ግን ካሣ ክፍያና ምትክ ቤቶች በቅድሚያ አዘጋጃለሁ ይላል                         –የኦሮሞ ትግል ትሩፋት ለመላ ኢትዮጵያውያን?

28 Jan

የአዘጋጁ አስተያየት:
ለነገሩ ዜናው አዲስ አደለም።

ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ሪፖርተር በመልሶ ማልማት ፕሮግራም 360 ሔክታር መሬት ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች ሊነሱ ነው በሚል ርዕስ ዜናውን ቢያወጣውም፡ ዋናው መልዕክቱ ግን – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በቅርቡ የተሾሙት አቶ ዘብረ ያይሎም ለሪፖርተር እንደገለጹት – አዲስ አበባ ውስጥ 1,430 ሄክታር መሬት ከሕዝብ እንደሚወስድና ካሣም እንደሚከፈል፡ ተፈናቃዩ ሕዝብም የሚሠፍርበት ቦታ እንደሚዘጋጅ ገልጸዋል!

የሕወሃት አስተዳደር፡ ላለፉት ዓመታት ሕጻናት፡ አረጋውያን፡ በሽተኞችና ነፍሰ ጡሮች እተኙበት ላይ ቤታቸውን ሲያፈርስና ያለካሣ መንገድ ላይ ሲጥላቸው ከርሞ፡ አሁን ማምሻው ላይ የዚህ ዐይነት እርምጃ መውስዱ፡ የአስተሳስብና የአመለካከቱን ለውጥ ሳይሆን፡ ቆም ብሎ ጡጫው ሲበዛበት የተቆጣ ሕዝብም መብቱን ለማስከበር ለመራገጥ እንደሚገደድ ትንሽ ትምህርት እንዳሰጠው አመላካች ነው።

ሰለፖሊሲ ለውጡ ሪፖርተር ባቀረበው ዜና ላይ በመመሥረት ይህ ድህረ ገጽ ጥር 21 ቀን 2016 ባወጣው ጽሁፍ – አዲስ አበባ ውስጥ በመልሶ ማልማት ፕሮግራም ስም 360 ሔክታር መሬት ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች ሊነሱ መሆኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ ዘብረ ያይሎም ገለጹ! በከተማዋ በዚህ መልክ ለሚነሱት ብር 270 በነፍስ ወከፍ ካሣ ተመድቧል! በመሬቱ እነማን ይከብሩበት ይሆን? – በማለት ያለውን ጥርጥርና በተለይም የካሣውን ናሙናነትና ዘራፊዎቹ ምን ያህል እንደሚከብሩበት በመገመት ጥያቄውን አንከባሏል!

ለዚህም የቁጣው ምንጭ እስከዛሬ በዜጎቻችን ስብዕና ላይ የተፈጸመው በደል ብቻ ሳይሆን፥ ገንዘባቸውን ተዘርፈው ‘መኳንንቱ’ ከባለ ሃብት የአሜሪካና አውሮፓ ቱሪስቶች ጋር ‘በፓራዳይዝ ደሴት የሚዝናኑበትን መጠንና እንዲሁም የወጭያቸውን ብዛት ጭምር በመገመት ነው! ይህም – አንድ የውጭ ምንጭ ትዕዝብቱን ለሌላው እንዳካፈለው – ከአርብ እስከ እሁድ የሣምንት መጨረሻቸውን – ሴይሼል ለሚያሳልፉት አንዳንድ የግንባሩ ባለሥልጣኖች ተጨማሪ ድጎማና በተለይም ከዋና ከተማዋ ቪክቶሪያ (ማሄ) ቻርተር በረራ ወስደው ወደ ታዋቂዋ ፕራስሊን ደሴት (Praslin) ለሚበሩት በቂ ምቾት መሥጠት የሚችል ገቢ በመሆኑ ነው!

ሪፖርተር ከዋና ሥራ አስኪያጅ ዘብረ ያይሎም ጋር ከተነጋገረና መረጃዎችን ከመረመረ በኋላ እንደገለጸው ከሆነ፡ በከተማዋ ውስጥ 1,430 ሄክታር መሬት ባለሥልጣኖቹ ጉያቸው ውስጥ ሲያስገቡ፡ የሚያፈናቅሉት ሕዝብ ብዛትም 23,000 ያህል እንደሚደርስ ተምነዋል።

ወጭያቸውንም አስልተው ብር 6.2 ቢሊዮን በክሣ መልክ ለማከፋፈል ቋታቸው ውስጥ ይዘዋል። በተጨማሪም ለሚፈናቀሉት ግለሰቦት 404 ሄክታር መሬት ምትክ እንደሚሠጣቸው ሪፖርተር በተጠቀሰው ዜና ውስጥ ጠቁሟል።

1,430 ሄክታር መሬት ያጣ 23,000 ተፈናቃይ በተተኪነት የሚያገኝው መኖሪያው 404 ሄክታር ብቻ ሲሆን፡ በፍሰ ወከፍ ድርሻው 0.017 ሄክታር ይሆናል ማለት ነው – ሠፌድ ላይ ካረፈ አፍ ማሙሻ መብለጧን አጠራጣሪ ያደርገዋል።

ይባስ ብሎ ለ23,000 ተፈናቃይ የተያዘው የካሣ ድርሻ በነፍስ ወከፍ ብር 270 ሺህ መሆኑ፣ ምን ያህል ባልሥልጣኖቹ የራሰ ወገን እሴታቸውን ሲያበራክቱ የከተማ ነዋሪውን ግን እንዳመናመኑት ያሳያል።

ምናልባትም በአስተዳደሩ በኩል፣ ከተጓዘበት በ300 ዓመታት ኋላ ቀር ከሆነው መንግሥታዊ አሠራር አንጻር፣ ለሕዝቡ ብዙ አደረግሁ ብሎ ሊመጻደቅ ይዳዳው ይሆናል። መታወቅ ያለበት ነገር ግን፡ በዘርና በወገንና የትውልድ ቀበሌ መፈላለግና መደጋገፍ የሚያምን በመሆኑ፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዐይነት ጥሩ ሕግ ቢወጣ፡ ፍቱን መዋቅር ቢተከል፡ መላዕክት የፖሊሲ አተረጉጎሙን እንዲያስፈጽሙ ቢወከሉ፣ ሕወሃት እስካለ ድረስ ምንም ዐይነት መሻሻልና ሰብዓዊ ዕድገት በኢትዮጵያ አይኖርም!

በሃገራችን ዛሬ ካለው የማቴሪያል ድህነት ይልቅ – ትልቁ ጠላታችን – የአዕምሮና የአስተሳሰብ ድህነት በመሆኑ፡ የምትከተላቸው ፖሊሲዎችም እጅግ የተራቆቱ ናቸው!

በዚህም ምክንያት፡ ይህ አስተዳደር ለወደፊት የሚገጥመውን የሕዝብ ትግል ምን ያህል እያጠናከረውና የሃገሪቱን የወደፊት ሕልውና አሳሳቢ እንዳደረገው መገመት ብዙም ዕውቀት አይጠይቅም!

 

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
አዲስ አበባ ፣ ጥር 18 ፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በመልሶ ማልማት የሚነሱ አከባቢዎች ወጥ በሆነ መንገድ ፈርሰው ወደ ልማት የሚገቡበትን አዲስ የአሰራር ስርአት መዘርጋቱን የከተማዋ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ አስታወቀ።

የመልሶ ማልማት ስራ ውስጥ ወጥ የሆነ አሰራር አለመኖሩን የሚያሳዩ ክፍተቶች የሚስተዋሉ ሲሆን፥ አንዱ ቤት ፈርሶ አንዱ የሚቀርበት ሁኔታም ስራው በእቅድ የመስራት ክፍተት እንዳለበት የሚያሳይ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ገልፀውልናል።

አዲሱ አሰራር ግን ቀደም ሲል በመልሶ ማልማት ላይ ይታይ የነበረውን ይህን ወጣ ገባ አሰራርና ተያይዘው የሚከሰቱ በርካታ ችግሮችን ይፈታል ተብሏል።

በቀጣይም በከተማዋ 360 ሄክታር መሬት በመልሶ ማልማት የሚፈርስ ሲሆን፥ ይህም በአዲሱ የመልሶ ማልማት መርሃ ግብር ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን የኤጀንሲው ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ግርማ ብርሃኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግርዋል።

በእነዚህም አከባቢዎች የማፍረስ ስራዎች ከመጀመራቸው በፊት የአስተዳደራዊ ስራዎች፣ የካሳና ምትክ ቤቶችን የማዘጋጀት ስራዎች ተጀምረዋል።

በዚህም በቦሌ ቡልቡላ የሚገኙ 5 ሺህ ቤቶች በመልሶ ማልማት ለሚነሱ ሰዎች በምትክነት ለመስጠት ተዘጋጅተዋል።

የኮንደሚንየም ቤት ለመውሰድ አቅም ለሌላቸው ደግሞ መንግስት ለኪራይ የሚሆኑ ቤቶችን ለመገንባት በዝግጅት ላይ ነው ተብሏል።

እነዚህም ሲጠናቀቁ በአሁኑ ወቅት የሚስተዋሉት ችግሮች በአዲሶቹ የመልሶ ማልማት አከባቢዎች ላይ እንዳይደገሙ ያግዛል ብለዋል።

በከተማዋ 4 ክፍለ ከተሞች ላይ 186 ሄክታር መሬት ላይ የሚገኙ የመኖርያና የንግድ ቤቶች በመልሶ ማልማት ምክንያት በመፍረስ ላይ ናቸው።

ከነዚህም መካከል ተክለሃይምኖት ፣ ካዛንቺስ፣ ዋቢ ሸበሌ፣በተለምዶ አሜሪካን ጊቢ በሚባለው አካባቢ እንዲሁም፣ ደጃች ውቤና ሌሎች አከባቢዎች ይገኙበታል።

*Updated.

 

 

%d bloggers like this: