ሕወሃት ከወዲሁ ኑዛዜ ጀመረ! “የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አመራር መሠረታዊ ስህተቶች”                – የእነርሱው አይጋ ላይ እንዳሠፈሯቸው!

31 Jan

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 

የተዘረዘሩት የኢሕአዴግ መሠረታዊ ስህተቶች ሲጠቃለሉ

  1. በወቅቱ የነበረውንና በሀገር ሀብት ሰልጥኖ የተደራጀውን የመከላከያ ሰራዊት የአሸናፊነት ስሜት በሚፈጥረውና ሚዛኑን ባልጠበቀ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ በተሰጠ ስሜታዊ ውሳኔ አማካኝነት መበተኑ

  2. ኢሕአዴግ የኤርትራ መገንጠልን በእጅጉ ማፋጠኑ ነው፣ የአመራር አርቆ አሳቢና ብልህ ቢሆን ኖሮ በወቅቱ ማድረግ የነበረበት ሸአብያ በጉልበቱ የመሰረተው ጊዜያዊ መንግስት የሽግግሩ መንግስት
  አካል እንዲሆን ለማግባባት ጥረት ከማድረግ ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ በሕዝብ የተመረጠ መንግስት ስልጣን እስኪይዝ (ወደ ስልጣን እስኪመጣ) ድረስ በኤርትራ የተቋቋመውን ጊዜያዊ መንግስት እውቅና በመንፈግ በኤርትራ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ ለማድረግም ሆነ የሕዝበ ውሳኔ ውጤቱን እውቅና ለመስጠት የሚያስችል ፖለቲካዊ ስልጣን እንደሌለውም ጭምር ለሸአብያ እንቅጩን በመንገር የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህንን የጸና አቋሙን አውቆ እንዲደግፍ መስራት ነበረበት፡፡

  3. የአዲሲቷ ኤርትራ መንግስትና በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው የህወሀት/ኢህአዴግ የቁርጥ ቀን ወዳጅ ፓርቲ ሸአብያ “ፍየል ከመድረሷ ቅጠል መበጠሷ” ሆነና ስልጣን ከመያዙ ኤርትራ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያንን እያንገላታና ንብረታቸውንም ያለአግባብ እየቀማ (አንዳንዶች የወርቅ ጥርስ በማስነቀል ጭምር ይሉታል) በግፍ ሲያፈናቅል ሀይ ባይ ከማጣቱም በላይ የመንን፣ ሱዳንንና ጂቡቲን ጎነታትሎ ኢትዮጵያ ላይ ጠንከር ያለ ወታደራዊ ወረራ ፈጸመ፡፡ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም በተለይም ኋላ ላይ ተፈጥሮ የነበረውን ወታደራዊ የበላይነትና ጠንካራ የህዝብ ድጋፍ ግምት ውስጥ በማስገባት አሰብን በመደራደሪያነት ማቅረብና ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዲኖራት ለማድረግ ከመጣር ይልቅ ምክንያታዊ ባልሆነ አኳኋን ህጋዊነታቸውን ካጡ ከስልሳ በላይ የሚሆኑ አመታት ያለፋቸውን የስምምነት ሰነዶች ከያሉበት ቆፍሮ በማውጣት በማስረጃነት ለመጠቀም በመሞከሩ ሳቢያ ብቻ ሳይሆን ለአገራቸው የሚቆረቆሩ የሕግ ምሁራንን ከማሳተፍ ይልቅ በውጭ የህግ ሰዎች ተማምኖ
  ሀላፊነት የጎደለው ክርክር በማድረጉ ምክንያት ለሸአብያ መንግስት ዱላ በማቀበል ጭምር “እባቡ ከእግርህ ዱላው ከእጅህ ምን ትሰራለህ” የማለት አይነት እርምጃ መውሰዱ

  4. የኢሕአዴግ መሪዎች ለአላማቸውና ለመስመራቸው እንኳ ታማኝ አለመሆናቸው ሌላኛው ትልቅ ችግር ነው፣ በመግቢያየ ላይ በግልጽ ለማመላከት እንደሞከርሁት ሁሉ ምርጥ ሊባል የሚችል ሕገ-መንግስት አውጥተው ስራ ላይ አውለዋል፣ ቀደም ሲልም ይዘውት የተነሱት አላማ ቅዱስ እንደሆነ ደጋግመው ሲናገሩ ይደመጣል፣ ሊያሰራ የሚችል ሕዝባዊ መስመር እንዳላቸውም በኩራት መንፈስ ይናገራሉ፣ ከዛም አልፈው ቅድመ ምርመራን የሚያስቀርና የፕሬስ ነጻነትን የሚፈቅድ አዋጅ ከሽግግር ወቅት ጀምሮ በማውጣት ተግባራዊ ለማድረግ ሞክረዋል ወዘተ. ሆኖም እነዚህን መልካም ሁኔታዎች
  በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ሲያደርጓቸው ግን አይታዩም፡፡ በተቃራኒው ሙሰኞችን የሚያበረታታ፣ ሀቀኛ ታጋዮችን አንገት የሚያስደፋና የሕዝብን ስቃይ የሚያባበሱ አድርባዮችን የሚሾምና የሚሸልም እርምጃ ያለምንም ይሉኝታ ሲወስዱ ይታያሉ፡፡ በደርግና በሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች የተፈጸመውን ጅምላ ጭፍጨፋና በሕወሀት ሰራዊት አማካኝነት የተገደለውን የደርግ ወታደርና የኢሕአፓ ሰራዊት ቁጥር ትተን ከሕወሀት ሰራዊት አባላት መካከል ብቻ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት መምጣትና ለሰብአዊ መብት መከበር እንዲሁም ራስን በራስ ለማስተዳደር ሲባል በተደረገ የተራዘመ የትጥቅ ትግል ከ60 ሽ በላይ ወጣቶችን ገብሮ እንደመጣ የሕወሀት አመራር ራሱ በየመድረኩ ደጋግሞ ሲናገር ይደመጥ እንጂ በተግባር ግን የዚህ ሁኔታ ተቃራኒ የሆነ እርምጃ ሲወስድ ይስተዋላል፡፡”

  5. የኢሕአዴግ አመራር ፍትህና መልካም አስተዳደርን ማስፈን አለመቻሉ ደግሞ ሌላኛው መሰረታዊ ችግሩ ነው፣ ድርጅቱ ከመነሻው አብዮት ለማካሄድ የተፈጠረ እንጂ እንዲህ አይነት የተወሳሰበን ጉዳይ ከመሰረቱ ለመፍታት የሚያስችል ህሊናዊ ዝግጁነትም ሆነ ትግስት ያለው አይመስለኝም፡፡ በመሆኑም አከራካሪ ቢሆንም አብዮት ማካሄድ ችሎበት ሊሆን ይችላል፣ አምባገነን መንግስታትን በአብዮት ማስወገድ ይቻል ይሆናል፣ ድህነትንም በአብዮታዊ እርምጃ በታገዙ የልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መቀነስ እንደሚቻል በሌሎች አገሮች ጭምር በተግባር ተሞክሮ ታይቷል፡፡ ፍትህና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ግን አብዮትና በስሜት የሚነዳ የህዝብ ንቅናቄ ብሎ ነገር የትም የሚያደርስ እርምጃ አይደለም፡፡ በተለይም ገለልተኛ ፍርድ ቤትና ብቃት ያለው ሲቪል ሰርቪስ እንዲኖር በማድረግ ለዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት መከበር ብቻ ሳይሆን ለምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት መፋጠን ትልቅ ፋይዳ የሚኖረውን የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የሚጫወተውን ሚና በአግባቡ አለመገንዘብ አንዱ መሰረታዊ ችግር ነው፡፡

 

1. መግቢያ፡-

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የደርግ-ኢሰፓን መንግስት በጦር ሀይል ከስልጣኑ አስወግዶ መንበረ-ስልጣኑን ከተቆጣጠረ ጊዜ ጀምሮ ባለፉት 25 አመታት በርካታ መልካም ነገሮችን የሰራውን ያህል በዚያው መጠን በእኔ ግምት እጅግ የበዙ ሊባሉ የሚችሉ መሰረታዊ ስህተቶችንም ፈጽሟል፣ አሁንም በመፈጸም ላይ ይገኛል፡፡ የፈጸማቸውን መሰረታዊ ስህተቶች በዝርዝር ነቅሰንና በምሳሌ አስደግፈን ጭምር ከማየታችን በፊት ስለመልካም ፍጻሜዎቹ የተወሰኑ ነገሮችን ብለን ማለፉ ተገቢ ይሆናል ብቻ ሳይሆን ምልከታችንንም ሚዛናዊ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡

የመጀመሪያው እንደ መልካም ፍጻሜ ተደርጎ ሊወሰድለት የሚችለው የመንግስትን ስልጣን በጦር ሀይል ተቆጣጥሮ የነበረ አሸናፊ የፖለቲካ ድርጅት ቢሆንም የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ከኢሰፓና ኢሕአፓ በስተቀር ሁሉንም ተቃዋሚ ሀይሎች ጋብዞ የሰላምና የዴሞክራሲ ኮንፈረንስ ማዘጋጀቱና ለሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ትልቅ ቦታ የሚሰጥ እና ለመጀመሪያ ጊዜ ብሔር-ብሔረሰብ ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ የሚፈቅድ የሽግግር ወቅት ቻርተር ጸድቆ ተግባራዊ እንዲሆን ግንባር ቀደም መጫወቱ አንዱ ሲሆን፣ ከአራት አመታት በኋላ ደግሞ ይህንኑ መርህ ይበልጥ የሚያጠናክር ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ የመንግስት አስተዳደር ስርአትን የሚያሰፍን ሕገ-መንግስት ተረቆ በህዝብ በተመረጡ የሕገ-መንግስት ጉባኤ አባላት እንዲጸድቅና ስራ ላይ እንዲውል ማድረጉ ሁለተኛው ነው፡፡

በዚህም ተግባራዊነቱ ላይ በርካታ ቅሬታዎችና ስሞታዎች ቢቀርቡበትም ለሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ሰፊ ሽፋን ሰጥቷል፣ በንድፈ ሀሳብ ደረጃም ቢሆን ዴሞክራሲያዊና ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር እንዲኖር አድርጓል፣ አተገባበሩ ላይ አሁንም አንድ ሽ አንድ ቅሬታዎችና ለቁጥር የሚያዳግቱ ስሞታዎች ቢቀርቡበትም ከነችግሩም ቢሆን የመድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርአትን በሕገ-መንግስት አስደግፎ ተግባራዊ ለማድረግ በመሞከሩ በአስሮች የሚቆጠሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለመፈልፈል በቅተዋል፡፡ አተገባበሩ ላይ አሁንም በርካታ ችግሮች ቢስተዋሉበትም የቅድመ ምርመራ ስርአትን አስወግዶ ሀላፊነቱን ለጸሀፊዎች የሚያሸጋግር ህግ አውጥቶ ስራ ላይ አውሏል፡፡

አሁንም በተግባር ሲፈተሸ የማያፈናፍኑ ችግሮች ቢኖሩበትም የፍርድ ቤት መዋቅርን በኢትዮጵያ የመንግስት አስተዳደር ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊልባል በሚችል ደረጃ እንደ ሶስተኛ የመንግስት አካል ራሱን ችሎ እንዲደራጅ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፣ ወዘተ. ወዘተ. ከዚህም ባሻገር በመሰረተ ልማት ዝርጋታውና በአንዳንድ የልማት መስኮች ላይ የተሳካ ስራ ሰርቷል፣ አሁንም እየሰራ ይገኛል፡፡ ሆኖም ከላይ የተዘረዘሩትን መልካምፍጻሜዎች የሚሸረሽሩና የድርጅቱንም አመራር ሚዛናዊነት፣ ፍትሀዊነት፣ አርቆ አስተዋይነት እና ዴሞካራሲያዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ መሰረታዊ ስህተቶች
እንዳሉበትም ይታመናል፣ በዚህ ጽሁፍ በዝርዝር ለማየት የምሞክረውም እነዚህን መሰረታዊ ጉድለቶች ይሆናል፡፡ መልካም ንባብ!!

2. የኢሕአዴግ አመራር መሰረታዊ ስህተቶች፡-

የኢሕአዴግ አመራር የሀገሪቱን የፖለቲካና የአስተዳደር ስልጣን ሙሉ ለሙሉ ከተቆጣጠረበት ግንቦት 20/1983 ዓ.ም ጀምሮ እጅግ በርካታ ጠቃሚ ተግበራትን በሚያከናውንበት ወቅት በዚያው ልክ የበዙ ስህተቶችን የፈጸመና አሁንም ድረስ እየፈጸመየሚገኝ አመራር ቢሆንም በእኔ ግምት መሰረታዊ የምላቸው ላይ በማተኮር ስህተቶቹን በምሳሌ በማስደገፍ ጭምር አንድ ባንድ ነቅሼ በማውጣት እንደሚከተለው ለማቅረብሞክሬያለሁና አንባቢያንም የራሳችሁን ግምገማ ልታስቀምጡ ትችላላችሁ፡፡

2.1 የመጀመሪያውና ታሪካዊው ስህተት ተብሎ የሚወሰደው በወቅቱ የነበረውንና በሀገር ሀብት ሰልጥኖ የተደራጀውን የመከላከያ ሰራዊት የአሸናፊነት ስሜት በሚፈጥረውና ሚዛኑን ባልጠበቀ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ በተሰጠ ስሜታዊ ውሳኔ አማካኝነት መበተኑ ነው፣ እርግጥ ነው ይህ ሰራዊት የገዥ መደቦችን መሰረታዊ ፍላጎት ለማስፈጸምና የብሔር-ብሔረሰቦችና ህዝቦችን መብት ለማፈን የሰለጠነና በዚሁ ቅኝት የተደራጀ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሆኖም በውስጡ ሀገራቸውንና ህዝባቸውን የሚወዱ፣ ለሀገር ዳር ድንበርና ልኣላዊነት መከበር መስዋዕትነት የከፈሉ፣ በወታደራዊ ሳይንስ ዕውቀት እጅግ በጣም የበለጸጉ፣ የተሻለ የአመራር ልምድ ያካበቱ፣ ሙያዊ ብቃትና ጠንካራ ዲስፕሊን የነበራቸው ወታደሮችና አመራሮች እንደነበሩበትም በማንም ሊታበል የማይችል ሀቅ ነው፡፡ ለዚህም አይነተኛ ማስረጃ ሊሆን የሚችለው እንደዚህ አይነት ባህሪ የነበራቸው ወታደሮች በጦርነቱ ወቅት በኢሕአዴግ ሰራዊት ተማርከው በትግሉ ሁኔታ ላይ የተወሰነ ገለጻና ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ በርካቶች ከኢህአዴግ ጎን ተሰልፈው እንዲታገሉ ሲደረግ መቆየቱም ይህን ሀቅ ይበልጥ ያረጋግጣል፡፡ በዚህ ረገድ የተወሰኑ ታጋዮችን በምሳሌ አንስቼ እንዳስረዳ የግድ ቢለኝ ቀድመው የሚመጡልኝ የኦህዴድ መስራችና አመራር
አባል የሆኑትን የተከበሩ አቶ አባዱላ ገመዳንና ክቡር አቶ ኩማ ደመቅሳን እንዲሁም ከደቡብ ክልል በርካታ አመራሮችን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል፡፡

ሆኖም የኢሕአዴግ አመራር ስሜታዊ እርምጃ ግን ለራሱ ለኢህአዴግ ሰራዊት እርሾ ሆነው ሊያገለግሉ ይችሉ የነበሩትን እነዚህን ሀይሎች እንኳ ግምት ውስጥ ለማስገባት ሳይሞክር ነበር በጅምላ የበተናቸው፡፡ የሚገርመው ነገር በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ለእነዚህ የሰራዊቱ አባላት ጥሪ ማድረጉና የተወሰኑትንም ተቀብሎ ተጠቅሞባቸው ስለነበር የሸአብያን እብሪት ለማስተንፈስ በተደረገው እልህ አስጨራሽ ጦርነት ላይ ተሳትፈው ሁል ጊዜም በታሪክ ሲወሳ የሚኖር የጀግንነት ተግባር መፈጸማቸው በግልጽ የሚታወቅና የኢህአዴግ አመራርም የማይክደው እውነት ነው፡፡

2.2 ሌላኛውና ሁለተኛው መሰረታዊ ስህተት ብዬ የማነሳው ደግሞ የኤርትራ መገንጠልን በእጅጉ ማፋጠኑ ነው፣ የኢሕአዴግ አመራር አርቆ አሳቢና ብልህ ቢሆን ኖሮ በወቅቱ ማድረግ የነበረበት ሸአብያ በጉልበቱ የመሰረተው ጊዜያዊ መንግስት የሽግግሩ መንግስት አካል እንዲሆን ለማግባባት ጥረት ከማድረግ ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ በህዝብ የተመረጠ መንግስት ስልጣን እስኪይዝ (ወደ ስልጣን እስኪመጣ) ድረስ በኤርትራ የተቋቋመውን ጊዜያዊ መንግስት እውቅና በመንፈግ በኤርትራ ውስጥ ህዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ ለማድረግም ሆነ የህዝበ ውሳኔ ውጤቱን እውቅና ለመስጠት የሚያስችል ፖለቲካዊ ስልጣን እንደሌለውም ጭምር ለሸአብያ እንቅጩን በመንገር የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህንን የጸና አቋሙን አውቆ እንዲደግፍ መስራት ነበረበት፡፡ ሆኖም በወቅቱ የሆነው ነገር የዚህ አይነት አስተዋይ እርምጃ ተቃራኒ ስለነበር ውጤቱም ለበርካታ አሰርት አመታት በሀገሪቱ ሀብት በአግባቡ ተደራጅቶ የነበረውን የሀገሪቱን የመከላከያ ሰራዊት በጥላቻ ስሜት ላይ በመመልከት ብቻ በመበተኑ ምክንያት በእጅጉ ሲከፋና ሲቆጭ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ገና ከጅምሩ በኢህአዴግ ላይ የጥርጣሬ ስሜቱን አጠናክሮ በግልጽ ማንጸባረቅ ጀመረ፡፡ ከዚሁ መሰረታዊ ስህተት ጋር ተያይዞ በግዴለሽነት ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታጣ በማድረጉ የሕዝቡ ቁጣ ይበልጥ ገንፍሎ ወጣ፣ እናም የተቃውሞ ሀሳቡን የተለያዩ አጋጣሚዎችንና መድረኮችን በመጠቀም ማንጸባረቁን አጠናክሮ ቀጠለበት፡፡

ይሁን እንጂ የኢሕአዴግ አመራር ይህንን የህዝብ ጥያቄና እውነተኛ ፍላጎት ግምት ውስጥ በማስገባት በአንድ በኩል በህዝብ የተመረጠ መንግስት ስልጣኑን እስኪረከብ ድረስ ምንም አይነት ድጋፍ ለማድረግና እውቅናም ለመስጠት እንደሚቸገር እያሳወቀ በሌላ በኩል ሀገሪቱ የባህር በር እንዲኖራት ዲፕሎማሲያዊ ስራውን አጠናክሮ ቢሰራ ኖሮ የኢትዮጵያን ህዝብ ድጋፍ በአስተማማኝ ሁኔታ ያገኝ የነበረ ከመሆኑም በላይ ሸአብያም ቢሆን ዕውቅና ለማግኘት ከነበረው ጠንካራ ፍላጎትና እጅግ የበዛ ጉጉት የተነሳ አሰብን ለኢትዮጵያ አሳልፎ ከመስጠት ወደ ኋላ የማይልበት ሁኔታ ይፈጠር ስለነበር ኢህአዴግም ሆነ አገሪቱ ከዚሁ አስተዋይነት ከተሞላበት ፖለቲካዊ እርምጃ ይበልጥ ትጠቀም እንደነበር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

2.3 የባሰው ስህተት ደግሞ ኋላ ላይ የተገኘውን ወርቃማ ዕድል በአግባቡ መጠቀም ያአለመቻልና ከስህተትም ለመማር የአለመቻሉ ነው፣ የአዲሲቷ ኤርትራ መንግስትና በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው የሕወሀት/ኢህአዴግ የቁርጥ ቀን ወዳጅ ፓርቲ ሸአብያ “ፍየል ከመድረሷ ቅጠል መበጠሷ” ሆነና ስልጣን ከመያዙ ኤርትራ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያንን እያንገላታና ንብረታቸውንም ያለአግባብ እየቀማ (አንዳንዶች የወርቅ ጥርስ በማስነቀል ጭምር ይሉታል) በግፍ ሲያፈናቅል ሀይ ባይ ከማጣቱም በላይ የመንን፣ ሱዳንንና ጂቡቲን ጎነታትሎ ኢትዮጵያ ላይ ጠንከር ያለ ወታደራዊ ወረራ
ፈጸመ፡፡

ይህን አጋጣሚ በመጠቀም በተለይም ኋላ ላይ ተፈጥሮ የነበረውን ወታደራዊ የበላይነትና ጠንካራ የህዝብ ድጋፍ ግምት ውስጥ በማስገባት አሰብን በመደራደሪያነት ማቅረብና ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት ለማድረግ ከመጣር ይልቅ ምክንያታዊ ባልሆነ አኳኋን ህጋዊነታቸውን ካጡ ከስልሳ በላይ የሚሆኑ አመታት ያለፋቸውን የስምምነት ሰነዶች ከያሉበት ቆፍሮ በማውጣት በማስረጃነት ለመጠቀም በመሞከሩ ሳቢያ ብቻ ሳይሆን ለአገራቸው የሚቆረቆሩ የህግ ምሁራንን ከማሳተፍ ይልቅ በውጭ የሕግ ሰዎች ተማምኖ ሀላፊነት የጎደለው ክርክር በማድረጉ ምክንያት ለሸአብያ መንግስት ዱላ በማቀበል ጭምር “እባቡ ከእግርህ ዱላው ከእጅህ ምን ትሰራለህ” የማለት አይነት እርምጃ ወሰደ፡፡

እነዚህ የስምምነት ሰነዶች ደግሞ በመሰረቱ በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት መፍረሳቸው የአደባባይ ምስጢር መሆኑ እየታወቀ ህልውና እንዳላቸውና ተከብረው የቆዩ አለምአቀፍ ስምምነቶች እንደሆኑ አድርጎ በማስረጃነት አቅርቦ በመከራከሪያነት ለመጠቀም ያደረገው ጥረት ሲታይ አንድም ሁል ጊዜም ቢሆን “የልብስ ሰፊነት” ሚና በመጫወት ላይ የሚገኙት የህግ አማካሪዎቻቸው በደንብ አልነገሯቸውም አሊያም የኢሕአዴግ መሪዎች በወቅቱ የዚህ አይነቱን ሞያዊ ምክር ለመስማት ዝግጁ ስላልነበሩ ሁሉም ነገር በስሜት እንዲነዱ አድርጓቸዋል፡፡

ለነገሩ በኢሕአዴግ ቤት የሕግን ጨምሮ ማንኛውንም አይነት አማካሪ ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ወይም ወደ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት የሚያስገባው አንድም ለማቆያነት አሊያም ለጥቅማጥቅም ማሟያነት ሲባል ካልሆነ በስተቀር መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል የማማከር ስራ በጥናትና ምርምር ላይ ተመስርቶ እንዲሰራ እንዲሁም ለውጥ በሚያመጣ መልኩ እንዲያማክር ብዙም ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ይህም ሆኖ አሁንም ቢሆን የተፈጠረውን ክፍተት ማለትም የአልጀርሱ ስምምነት በኤርትራ መንግስት አለመከበሩን (25 ኪሎ ሜትር ወደ ውስጥ ገብቶ ወታደሩን እንዲያሰፍርና የተባበሩት መንግስታት ታዛቢዎች እንዲቆጣጠሩት የሚለውን ስምምነት መጣሱንና የካሳ ኮሚሽን ሸአብያ ለኢትዮጵያ እንዲከፍል የወሰነበትን የገንዘብ መጠን ለኢትዮጵያ በወቅቱ
አለመክፈሉን) ታሳቢ በማድረግ የአልጀርሱን ስምምነት ውድቅ ማድረግ ይቻላል፡፡

ይህን ተከትሎም አዲስ የድርድር ሀሳብ ይዞ በመቅረብ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ማረጋገጥና የአለም አቀፉን ማህበረሰብ በማሳመን ጭምር የኤርትራ መንግስት ላይ ጠንከር ያለ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ከማሳደር ጀምሮ ለሁለቱም ጎረቤት ሀገሮችና ወንድም ህዝቦች ዘላቂ ሰላም ሊያስገኝና መልካም ግንኙነትን ሊፈጥር የሚችል አካሄድን መከተልም እንደ አንድ የተሻለ አማራጭ መታየት ይኖርበታል፡፡ በእርግጥ በኢህአዴግ የሚመራው የኢፌዴሪ መንግስት ዘግይቶም ቢሆን ባለአምስት ነጥብ የሰላም ሀሳብ በሚል መልኩ ያቀረበውንና የአለም ማህበረሰብም ግምት ውስጥ ያስገባውን አማራጭ የሸአብያ መሪዎች አለመቀበላቸውም ከላይ በዋናነት የቀረቡትን ምክንያቶች ሊያጠናክር ስለሚችል ይህንም ታሳቢ አድርጎ ሀሳቡን እንደገና ማንሳት የሚቻልበት አጋጣሚ አለ፡፡

2.4 የኢሕአዴግ መሪዎች ለአላማቸውና ለመስመራቸው እንኳ ታማኝ አለመሆናቸው ሌላኛው ትልቅ ችግር ነው፣ በመግቢያየ ላይ በግልጽ ለማመላከት እንደሞከርሁት ሁሉ ምርጥ ሊባል የሚችል ህገ-መንግስት አውጥተው ስራ ላይ አውለዋል፣ ቀደም ሲልም ይዘውት የተነሱት አላማ ቅዱስ እንደሆነ ደጋግመው ሲናገሩ ይደመጣል፣ ሊያሰራ የሚችል ህዝባዊ መስመር እንዳላቸውም በኩራት መንፈስ ይናገራሉ፣ ከዛም አልፈው ቅድመ ምርመራን የሚያስቀርና የፕሬስ ነጻነትን የሚፈቅድ አዋጅ ከሽግግር ወቅት ጀምሮ በማውጣት ተግባራዊ ለማድረግ ሞክረዋል ወዘተ. ሆኖም እነዚህን መልካም ሁኔታዎች በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ሲያደርጓቸው ግን አይታዩም፡፡ በተቃራኒው ሙሰኞችን የሚያበረታታ፣ ሀቀኛ ታጋዮችን አንገት የሚያስደፋና የህዝብን ስቃይ የሚያባበሱ አድርባዮችን የሚሾምና የሚሸልም እርምጃ ያለምንም ይሉኝታ ሲወስዱ ይታያሉ፡፡ በደርግና በሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች የተፈጸመውን ጅምላ ጭፍጨፋና በሕወሀት ሰራዊት አማካኝነት የተገደለውን የደርግ ወታደርና የኢህአፓ ሰራዊት ቁጥር ትተን ከህወሀት ሰራዊት አባላት መካከል ብቻ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት መምጣትና ለሰብአዊ መብት መከበር እንዲሁም ራስን በራስ ለማስተዳደር ሲባል በተደረገ የተራዘመ የትጥቅ ትግል ከ60 ሽ በላይ ወጣቶችን ገብሮ እንደመጣ የህወሀት አመራር ራሱ በየመድረኩ ደጋግሞ ሲናገር ይደመጥ እንጂ በተግባር ግን የዚህ ሁኔታ ተቃራኒ የሆነ እርምጃ ሲወስድ ይስተዋላል፡፡

በሌላ አነጋገር የኢሕአዴግ መሪዎች ለአላማቸውም ሆነ ለህገ-መንግስታዊ መርሆች እንዲሁም እንታገልለታለን ለሚሉት ህዝባዊ መስመር እንኳ ተገዥና ታማኝ ሊሆኑ አልቻሉም፣ ይልቁንም በተቃራኒው ለጠባብ የድርጅት፣ የቡድንና የግል ፍላጎት ቅድሚያ ሲሰጡና የህዝብን አደራ ወደ ጎን ትተው ቃላቸውን ሲበሉ ይታያሉ፡፡ ለዚህም ነው በብዙዎች የህግና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ዘንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ህገ-መንግስት እንጂ ህገ-መንግስታዊነት የለም፣ ህግ ይወጣል እንጂ የህግ የበላይነት አይከበርም እንዲሁም ፍርድ ቤት በሕገ-መንግስት አማካኝነት በነጻነት ተቋቁሟል ይባል እንጂ ነጻ ሆኖ እንዲሰራ አይፈለግም የሚባለው፡፡

2.5 የኢሕአዴግ አመራር ፍትህና መልካም አስተዳደርን ማስፈን አለመቻሉ ደግሞ ሌላኛው መሰረታዊ ችግሩ ነው፣ ይህም በእኔ ግምት ከድርጅቱ መሰረታዊ ተፈጥሮ የመጣ ይመስለኛል፣ ምክንያቱም ድርጅቱ ከመነሻው አብዮት ለማካሄድ የተፈጠረ እንጂ እንዲህ አይነት የተወሳሰበን ጉዳይ ከመሰረቱ ለመፍታት የሚያስችል ህሊናዊ ዝግጁነትም ሆነ ትግስት ያለው አይመስለኝም፡፡ በመሆኑም አከራካሪ ቢሆንም አብዮት ማካሄድ ችሎበት ሊሆን ይችላል፣ አምባገነን መንግስታትን በአብዮት ማስወገድ ይቻል ይሆናል፣ ድህነትንም በአብዮታዊ እርምጃ በታገዙ የልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መቀነስ እንደሚቻል በሌሎች አገሮች ጭምር በተግባር ተሞክሮ ታይቷል፡፡ ፍትህና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ግን አብዮትና በስሜት የሚነዳ የህዝብ ንቅናቄ ብሎ ነገር የትም የሚያደርስ እርምጃ አይደለም፡፡ በተለይም ገለልተኛ ፍርድ ቤትና ብቃት ያለው ሲቪል ሰርቪስ እንዲኖር በማድረግ ለዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት መከበር ብቻ ሳይሆን ለምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት መፋጠን ትልቅ ፋይዳ የሚኖረውን የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የሚጫወተውን ሚና በአግባቡ አለመገንዘብ አንዱ መሰረታዊ ችግር ነው፡፡

ከዛም አልፎ ፍትህና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የህግ ማዕቀፉን በሰከነ መልኩ መፈተሸንና ማስተካከልን፣ የሕዝቡን መሰረታዊ ችግር በጥልቅ ጥናት ላይ ተመስርቶ መለየትን፣ የፍትህ አካላቱን አደረጃጀትና የሰው ሀይል ስምሪት ማስተካከልን፣ የስራ ሁኔታዎችን ማሻሻልንና ለፍትህ አካላቱ ባለሞያዎች ተገቢ ዕውቅና ሰጥቶ የሚገባቸውንም ጥቅማጥቅም በወቅቱ ማሟላትን ይጠይቃል፡፡ እንዲሁም ፍርድ ቤት በእርግጥም ገለልተኛ ሆኖ የሚሰራ መሆኑ ሊረጋገጥ ይገባል፣ ይህ ሲሆን ነው የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሀብት እርግጠኛ ሆኖ መዋዕለ ንዋዩን የሚያፈሰው፣ በሰው ህይወት፣ ነጻነትና ንብረት ላይ የሚወስን ዳኛ በየስርቻው በሚገኙ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶችና ኮንዶምኒየሞች ውስጥ እየኖረና ታክሲዎችን ጨምሮ በህዝብ ትራንስፖርት እየተጋፋ በሚሄድበት ሁኔታ የሽብር ፈጣሪዎችንና የሙሰኞችን ጉዳይ የሚመረምርና የሚወስን የፍትህ አካላት ባሞያ ተገቢ ጥበቃና ዋስትና ባላገኘበት አገር በአጠቃላይም ተቋማዊም ሆነ ግለሰባዊ የዳኝነት ነጻነት ጉዳይ ብዙ ጥያቄ እያስነሳ ባለበት ሁኔታ እንዴት ተብሎ ነው የተፋጠነ፣ ሚዛናዊና የህዝብን የፍትህ ጥማት ሊያረካ የሚችል ስራ በፍትህ አካላት አማካኝነት ሊሰራ የሚችለው? በተቃራኒው በየደረጃው በአስፈጻሚው መስሪያ ቤት ውስጥ ተሹሞ ወይም ተመድቦ የሚሰራ ፖለቲከኛ ሻል ያለ የመኖሪያ ቤት እስከሚገኝለት ድረስ ጊዮን አሊያም ኢትዮጵያ ሆቴል በቀን አንድ ሸ ብርና ከዛ በላይ ለአልጋ እየተከፈለለትና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ
የወጣበት አዲስ ተሸከርካሪም በወቅቱ እየቀረበለት ባለበት ሁኔታ ሶስተኛ የመንግስት አካል ለሆነውና በአቻነት መታየት ለነበረበት ፍርድ ቤት የታችኞቹን ትተን በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኝነት ደረጃ የሚሾሙት የህግ ባለሞያዎች ሳይቀሩ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ያለስጋት የሚያሳርፉበት ቤት ለማግኘት እንኳ አመታትን መጠበቃቸው ብቻ ሳይሆን ከክልል ለሚመጡ ዳኞች ለጊዜው እንኳ የሚያርፉበት የመኖሪያ ቤት አለመኖሩ ሲታይ የኢህአዴግ አመራር በእርግጥም እሱ ለሚተማመንበትና “የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጠበቃ ነው ብሎ ለሚያምነው” ለአስፈጻሚው አካል አመራሮች እንጂ ለፍትህ መዋቅሩ ባለሞያዎች ደህንነት፣ ጥቅምና የስራ ሁኔታ ያን ያህል ደንታ የሌለው መሆኑን ነው፡፡

3 ማጠቃለያ፡-

የኢሕአዴግ አመራር ባለፉት 24 አመታት የፈጸማቸው መልካም ተግባራትና መሰረታዊ ስህተቶች ከላይ የተጠቀሱት ብቻ ናቸው እያልሁ እንዳልሆነ ግን ግንዛቤ ይያዝልኝ፣ ይሁን እንጂ መገለጫቸው ይለያይ ካልሆነ በስተቀር ብዙዎቹ በእነዚህ ዙሪያ የሚሽከረከሩ መሆናቸው አይቀርም ብየ አምናለሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ከአንድ ሶስተኛ በላይ የሚሆነው ክፍሉን ለሰብአዊና ዴሚክራሲያዊ መብቶች መከበር የሰጠ ሕገ-መንግስት እንዲኖር ማድረጉና በተግባር መፈጸሙ ላይ የሚታይ ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ዙሪያና በማህበራዊ አገልግሎቶች አካባቢ የሰራው አበረታች ስራ በራሱ በአዎንታዊ ጎንነት ሊታይ የሚገባው ቢሆንም ህገ-መንግስቱን አክብሮ በማስከበር፣ መልካም አስተዳደርን በማስፈንና በዚህች አገር ላይ ማህበራዊ ፍትህን በማንገስ ረገድ ግን አልተሳካለትም ብቻ ሳይሆን ብዙ ሊባሉለት የሚችሉ መሰረታዊ ስህተቶች ያሉበት አመራር መሆኑ የሚያከራክር ጉዳይ አይመስለኝም፡፡

ምክንያቱም ይነስም ይብዛ የኢሕአዴግ አመራር ራሱ በየጉባኤዎቹ ላይ በመልካም አስተዳደርና በፍትህ ዙሪያ በልማቱ ያስመዘገብሁትን ያህል ውጤት ስላላመጣሁ ይህን ችግሬን ፈጥኜ ማስተካከል አለብኝ ሲል ይደመጣል፡፡ በሌላ አነጋገር ልክ እንደ ልማቱ ሁሉ በፍትህና በመልካም አስተዳደር ማስፈን ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ያሰበውን ያህል ባይሳካለትም ከአመታት በፊት ጀምሮ “እመርታ በመልካም አስተዳደር” የሚል መሪ መፈክር አውጥቶ እስከመንቀሳቀስ ደርሶ እንደነበር ይታወቃል፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ ከሌሎች ልማታዊ መንግስታት (በዋነኛነት ደቡብ ኮሪያና ታይዋን) እኔን የሚለየኝ ልማታዊ ብቻ ሳልሆን ዴሞክራሲያዊም ሆኜ ነው ልማቱን ማፋጠን የምችለው ቢልም በተግባር ግን የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚያጣብብ እርምጃ ሲወስድና ፍትህን ሲያዛባ ይስተዋላል፡፡ በመሆኑም የኢሕአዴግ አመራር ይህን ሁኔታ ተገንዝቦና ከራሱ ጠባብ ፍላጎት ወጣ በማለት ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም የሚቆምና ስህተቶቹን በጊዜ አርሞ ትክክለኛውን መስመር በመከተል የጋራ መግባባትን ሊያመጣ የሚችል ስራ ለመስራት ከልቡ ዝግጁ ሆኖ ከተንቀሳቀሰ አሁንም ጊዜው የመሸበት
አይመስለኝምና በሚገባ ቢያስብበት መልካም ነው የሚለው ምክረ-ሀሳብ የመጨረሻው መልዕክቴ ይሆናል፡፡

እውነቱ ዘለቀ
ከአዲስ አበባ 01-28″
 

/aigaforum

 

%d bloggers like this: