ከእንግዲህ ሕወሃትን ለማንኮታኮት አምስት ነገሮች ላይ ትኩረት በማድረግ የወደፊቱ ትግል ምን እንደሚመስል ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከአርበኞች ግንቦት7 ዕይታ አንጻር አቅጣጫ አመላከተ

1 Feb

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

78.28 ደቂቃዎች በፈጀ ንግግር የአርበኞች ግንቦት7 መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ትኩረት በሳበ ንግግር እሁድ ጥር 31/2016 ድርጅቱ ባለበት ደረጃ “በተለያዩ መስኮች በሁለንተናዊ መልኩ መታገል የሚችል ጠንካራ ዘመናዊ ደርጅት መገንባት ችለናል!” ማለቱ አዳራሹን በጭብጨባ አድምቆታል።

“ከልቤ ልናገር” በማለት የድርጅቱ ጥንካሬ መለኪያ ተደርጎ በሚወሰድ መልኩ፡ ፕሮፌሰሩ “ሕዝባዊ እምቢተኝነትን በሃገር ውስጥ ለማካሄድ – ጊዘው ሲደርስ – ከማንም ያልተናነሰ ጠንክራ ድርጅት ሃገር ውስጥ አለን! – [የወያኔን] የሰለላ ኃይሉንና የጦር ኃይሉን ማዳከም ዋናው ሥራችን ነው…!” ብሏል።

እኔ እስከማውቀው ደረስ፣ አርበኞች ግንቦት7 አርበኞች ግንቦት7 እንዲህ ያለ በትግል መፈርጠምን የሚያሳይ መልዕክት ሲያስተላልፍ የመጀመሪያው ሲሆን፣ ምንም እንኳ በንግግሩ ላይ ባይነሳም፡ የነሞላ አስገዶም ወደ ሕወሃት ጉያ መፈርጠጥ በድርጅቱ ላይ እምብዛም ጎጂ ተጽዕኖ እንዳላሳደረበት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

እንዲሁም፡ ይህ የሚያሳየው፡ በተደጋጋሚ ዶ/ብርሃኑ በንግግሩ ወቀት በሙሉ መዘናጋት እንዳይፈጠር በማለት በቅድሚያ በመግቢያው ካሰማው የመቆጠብ (restraint) ፍላጎት ፈንጠር እንዳደረገው ተሰተውሏል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በፕሮፌሰሩ ላይ ከጣለው አመኔታ አንጻር፡ በተለይም ግለሰቡን በወዳጅነት እንደሚያውቀው ግለሰብ፣ ዶ/ር ብርሃኑም ሆነ ግንቦት 7 ይህንን እንደ ሕወሃት በፈጠራና ለፕሮፓጋንዳ ዓላማ በማሰብ ያደርጋሉ ብዬ ለማመን እጅጉን እቸገራለሁ።

በሌላ በኩል ደግሞ ይህ መባሉ በትግል ሜዳ ለተሠማሩት የሚያበረታታ ከመሆኑ ባሻገር፣ በሃገር ውስጥም ይሁን በውጭ ካሉ ዜጎች ፍላጎት አንጻር ይህ አባባል የሚጠበቅ፣ የሚፈለግና የሚደገፍ መሆኑ አያጠራጥርም።

ሆኖም ዛሬ ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ ሲታይ፡ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ልበ ሙሉ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም፣ በዚህ ንግግር ውስጥ ስሜቱ ተቆጥቦና በዚህ ትውልድ ላይ ያለበትን ኅላፊነትና ነገን በመመልከት ከተናገራቸው ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል ይገኝበታል፡– “ወያኔን በሥልጣን ላይ ለማቆየት የሚይዙት ነገሮች እየተዳከሙ መምጣታቸውና የለውጥ ፖሲቢሊቲ ረል (real possibility) መሆኑን ማየት ማለት ተግባራዊ ከሆነ ዲሲፕሊንድ (disciplined) ከሆነ ሥራ ውጭ ያ ለውጥ ይመጣል ማለት እንዳልሆነ በደንብ መገንዘብ አለብን!” ማለቱ ከላይ የተነሳውን ቁጥብ የመሆኑነ ፍላጎት ምንጭ ያመላክታል።


ንግግሩ ሠፋ ያለ ቢሆንም፡ በአምስት ነጥቦች ላይ ያተኮረ ነበር፦

    ሀ. በዘረፋ፣ በድርቅ፣ ርሃብና የፖሊሲ ብልሹነት በመንኮታኮት ላይ ያለው የወያኔ ኤኮኖሚ ለወደፊቱ ጠንቅ ጥሎ የሚሄድ በመሆኑ፣ በሚገባ ሊታሰብበት እንደሚገባ አሥምሮበታል። ርሃብ የዴሞክራሲ ዕጦት ምልክት እንጂ የድህነት ውጤት አለመሆኑን ታዊቂውን ሕንዳዊ ኤኮኖሚስት የAmartya Sen ቻይናንና የሕንድን ርሃቦች ጉዳቶች በማወዳደር የጻፈውን በማስታወስ፣ ዴሞክራሲ ባልነበረባትና በኬለባት ቻይና ውስጥ ብዙ ሚሊዮን ሕዝብ ሲሞት፣ ዴሞክራሲያዊት ሕንድ ውስጥ አንድም ሰው አለመሞቱን ጠቅሷል። ወያኔ እንደ ሥርዓትና ኃይማኖት የያዘው ዘረፋን በመሆኑ፣ መንግሥታዊነቱም ለዚህ የተቋቋመ አንዳሰመሰለውና መደበኛ ሥራው እንዳደረገው፥ ፕሮፌሰር ብርሃኑ በኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ላይ በሠነዘራቸው ጉልህ ነጥቦች አንስቷል። የኤኮኖሚ ፖሊሲ ብልሹነቱና ዘረፋ መጠናከሩ የውጭ ምንዛሪ እንኳ በመጥፋቱ፡ የተጀመሩ ፕሮጄክቶች በቁም እንዲቀሩ እስከመድረስ መቻሉ ምን ያህል ኤኮኖሚው እንደተንኮታኮተ እንደማስረጃ ተጠቅሞበታል።

ለ. በዝርያ ላይ የተመሠረተውና ሕጋዊነት የሌለው የወያኔ ፖለቲካና ሃገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ወያኔን እራሱን እየነከሰው መሆኑ፥ የዘረፋው ቅርጫ በመካከላቸው የፈጠረው የፖለቲካ ችግር አንዲሁም በመካከል የቀረው ‘ድርሻዩ አነሰ ባዩ’ የፈጠሩት ከሌሎች ጋር ተዳምሮ ወያኔ ላይ ያስከተሏቸው ችግሮች፤ እንዲሁም የውጭ ደጋፊዎቻቸው በተለይም በሰላማዊ ኦሮሞ ትግል ምክንያት የሃገሪቱ ሁኔታ አሳሳቢ/አጠራጣሪ እየሆነባቸው መምጣቱንና የአማራጭ ፍለጋ ላይ መሆናቸውን ግንቦት 7 እንደ ሌሎች ሁሉ መገንዘቡንና ለሁኔታው ዲሲፕሊንድ ቲንኪንግ (disciplined thinking –) ጠንካራ አስተሳሰብ እንደሚያስፈልግ ዶ/ር ብርሃኑ በሠፊው ተንትኗል። ወያኔ ብሔራዊ ስሜት የጎደለው በመሆኑ፣ ካለው የአውሬነት ባህሪ በመነሳት፣ ውድቀቱ እየተቃረበ ሲሄድ ሃገሪቱን በግድየለሽነት ወደማነኳኮት ሊሂድ ስለሚችልና ይህም አደጋ ከመሆኑና በተረካቢዎች ላይ የግንባታው ሥራ ከባድ እንደሚሆን ግንዛቤ ውስጥ እንዲገባ የአርበኞች ግንቦት7 መሪ አሳስቧል።

ሐ. በኦሮሚያ የተካሄደውና የሚካሄደው የትግል እንቅስቃሴና የየአርበኞች ግንቦት7 አመለካከት ከማንነት ጥያቄ ባሻገር ሃገሪቱ የወደፊት ደህንነቷንና የሕዝቡን ዲሞክራሲያዊ ነገነት፣ ራስን የማሰተዳደር ጥያቄንም ሆነ የመሬት ባለቤትነት በተመለከተ እንደ ሕዝብ ጥያቄ በመመልከት አሰፈላጊ ስለሆኑት ነገሮች በግልጽ በሕዝብ ደረጃ ውይይት እንደሚያስፈልግ፤ ለዚህም እንዲረዳ ግንቦት7 ለሠፊ ሃገራዊ ትግል ሁኔታ ዕድል በመፈጠሩ ወደ እውነተኛ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትኩረት መዘንጋት እንደሌለበት ገልጿል። ለዚህም እንዲረዳ ከኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመታገል በስትራቴጂ ደረጃ ስምምነት ያለው የጋራ ትግሉን መጀመር አንደሚያስፈልግ በመቀበል – የሃገር ጉዳይ በመሆኑ ከሌሎች ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው የኦሮሞ ድርጅቶች ጋር ውይይቶች መጀመሩን ገልጿል። በዘውግ ዙርያ ለሚነሱት ጥያቄዎች በቀደምትነት መልስ የመስጠቱን አስፈላጊነት ፕሮፌሰሩ ነካክቶታል።

መ. አርበኞች ግንቦት ሰባት ምን እያደረገ ነው? የትግሉ ዓላማ ያለውን “የዘራፊዎች አምባገነን ሥርዓት አስወግደን እውነተኛ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመሥረት ነው! ስትራጂውም “ወያኔ የቆመበትን ምሶሶ በተቀናጀ ትግልና ሥርዓት ማፈራረስ አለብን – ወታደራዊ ኃይሉንና የስለላ ድርጅቶቹንና የገንዘብ ምንጮችና የውጭ ደጋፉን ማድረቅ በሁለንተናዊ ትግል…”

ሰ. ያጋጠሙና የተገኙ ተግዳሮቶች: በዚህ ጉዳይ ትኩረት የተሠጠው አርበኞች ግንቦት ሰባትን አሁንም ምሁራን፡ በንግድና በሌሎች መስኮች ከድርጅቱ ጋር አያሌ የተማሩ ዜጎች የመቀላቀላቸው አስፈላጊነት ጉዳይ ነው። የእነዚህ ዜጎች መሳተፍ በጋራ እንድትመሠረት ለምንፈልጋት ዴሞክራሲያዊት ሃገር ስኬት ከፍተኛ አስተዋጾ እንደሚሆን ፕሮፌሰር ብርሃኑ አስገንዝቧል።

*Updated to upload better video.

%d bloggers like this: