የኤርሚያስ አመልጋ እሥርና የአክሰስ ጉዳይ ሕወሃትን ትዕዝብት ላይ ቢጥለውም፣ የባሰው ግን ‘ወንጀለኛ ባለሥልጣኖች ለምን አይታሠሩም?’ የሚለው 25 ዓመታት ያስቆጠረው ጥያቄ ነው!

3 Feb

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

በዚህ ሣምንት Addis Fortune Access’ Drama Continues (Feb 1/2016) በሚል ርዕስ ያወጣው ጽሁፍ ወደኋላ መለስ ብዬ ሰለአቶ ኤርምያስ አመልጋ አንዳንድ ነገሮችን እንዳስታውስ አድርጎኛል።

በግለሰብ አቶ ኤርምያስ አመልጋን ባላውቀውም፣ በተለይም በአክሰስ ሪል ስቴት/አክሰስ ካፒታል/ሌሎችም ድርጅቶች መሥራችነቱ የተማረና እጅግ ዘመናዊ ግለሰብ፣ ካፒታሊዝም ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት ከአሜሪካ ባንከርነቱ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ፣ ከፈጸማቸው አሰገራሚ እንቅስቃሴዎቹ አንጻርና ውጤቶቹ አሁን ደግሞ በወንጀል መጠየቁ (እኔ የሕግ ችግሮቹን ባላውቃቸውም) ሕግና የሰው ልጅ በማይከበርበት ሃገር የረቀቀ ካፒታሊስትነቱ የጎዳው ሰው ይመስለኛል።

ይህም ማለት፡ አቶ ኤርምያስ ለግለሰቦች የገባውን ኮንትራት ለመፈጸም ካልቻለ፡ በሕግ መጠየቅ የለበትም የሚል ሃሣብ ማራመድ አይደልም የዚህ ጽሁፍ ዓላማ! የጽሁፉ ትኩረት ኤርምያስ አመልጋ ብቻ ነው ሃሣበ ብዙ ግን ተግባረ ለሆሳስ የሆነው፡ ወይንስ የሕወሃት አስተዳደር ማፊዮዞዎችም በስውር የተጫወቱት ሚና አለ ወይ የሚለውን ጥያቄም ያስተናገደ ነው።

ጥር 23፣ 2008 የሕወሃት የዜና ምንጮች እንደዘገቡት፣ አቶ ኤርምያስ የታሠረበት ምክንያት “የ2,500 ቤት ገዥዎችን ገንዘብ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የተረከቡ ቢሆንም ለአንዳቸውም ቤት ማስረከብ” ባለመቻሉ ነው ይላሉ።

ሁለት ሣምንት ከዚያ ቀድም ብሎ ደግሞ፣ ማለትም ጥር 9፣ 2008 የፍትህ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ እንደሚሉት፥ አቶ ኤርሚያስ ሶስት አበይት ጉዳዮችን በማቅረብ ነበር በዱባይ ከሁለት ዓመታት ከሕግ ፊት ሽሽት/ግዞት በኋላ (fugitive from justice) ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ስምምነት ያደረገው። እነዚህም:-

  (ሀ) ከውጭ ሀገር ከሚመጡ ባለሃብቶች ጋር በጥምረት አልያም በሀገር ውስጥ አቅም ያላቸውን ባለሃብቶች በማሳተፍ በእርሱ መሄድ ምክንያት ሥራቸው የቆመውን የመኖሪያ ቤቶች ግንባታዎች ለማንቀሳቀስ፣

  (ለ) አክሰስ ለሶስተኛ ወገኖች የሰጠውና ያልተሰበሰበ ከ300 ሚሊየን ብር በላይ አለ ስላለ ይህንን ሊያሰባስብ፣

  (ሐ) ከሶስተኛ ወገኖች ጋር ያሉትን ጉዳዮች አቶ ኤርምያስ እንደሜጨርስ – አክሰስ ጋር የገቡት ኮንትራክት ያልተፈጸመላቸው ግለስቦች – መሆናችውን አመልክተዋል።

በየቦታው እንደሚነገረው ሳይሆን፣ “አቶ ኤርሚያስ ወደ ሀገር ቤት ሲመጡ ያለመታሰር ዋስትና አልተሰጣቸውም፤ ከአጠቃላይ የወንጀል ተጠያቂነትም ነፃ ይሆናሉ የሚል ቃል የለም” ይላሉ የፍትህ ሚኒስትሩ። እኔም መንግሥት ነኝ የሚል አካል እንዲህ ያለ የፈርመህ ውሰደው ነጻ ቼክ ይሰጣል ብየ ባልገምትም፡ ነገሩ ለምን እንዲህ እንደተቆላለፈ ግን ሊገባኝ አልቻለም፤ በተለይም አቶ ኤርምያስ ከተመለሰ ጀምሮ የነበረው ግኝት በሚገባ ተለክቶ መሆኑን በመጠራጠር! ይሁንና ለተባለው ግኝት መለኪያው ጊዜ ነው ወይንስ የዘለቄታው ውጤት የሚለውም አነጋጋሪ ነው።

የጊዜ ገደብን በተመለከተ፣ “በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ አክሰስ ሪል ስቴት እንዲያንሰራራ አደርገዋለሁ” የሚል ዕቅድ አቶ ኤርምያስ ለመንግሥት አቅርቦ ነበር ሲሉ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ይህ ባለመሆኑ ነው በሚያሰኝ መልኩ ነው ተቋርጠው የነበሩ አሁን ከ80 በላይ ክሶች አግጠውበት አቶ ኤርምያስ ወደ እሥር ቤት የተሸኘው!

ነገር ግን፥ በሌላ በኩል ደግሞ ከላይ በሚኒስትሩ እንደተጠቀስው ሳይሆን – ከሕጉ መንፈስ ይልቅ ብዙ ጊዜ የካድሬነቱ አቶ ጌታቸው አምባዬን ተጠናውቷቸው ስለሚታይ – ከሁለት ዓመታት የዱባይ ቆይታ በኋላ ከመንግሥት ጋር በተደረገ ድርድር ቃል ተገብቶለት መምጣቱን በአቶ ኤርምያስ ዙሪያ እንደሚሰማና እንዲሁም በሚድያ ምክንያቱን በሪፖተር እንደተገለጸው:-

  “[ኤርሚያስ] has been dealing with government officials in order to secure a risk-free return. Finally, the government agreed to give Ermais legal protection – officially signed from the Ministry of Justice – and that he would not be incarcerated upon his return.”

ማስረጃ ሳያይ ሪፖርተር ይህንን ፈጥሮ ወይንም በተባለ ላይ ተመሥርቶ የሚጽፍ አይመስለኝም። ስለሆነም፡ አቶ ኤርምያስ ነጻነቱ እንደሚከበር፣ ደኅንነቱ እንደሚጠበቅ ሕወሃት ቃል ተገብቶለት መጥቶ አደረሰ የሚባለውን ችግር ፈቶ በሰላም ሃገሩ ውስጥ ሠርቶ መኖሩን እንዲቀጥል (ከፈለገ) ተነግሮት ሲመለስ፡ ለምን ችግሮቹን መፍታት አቃተው የሚለው ጥያቄ በብዙ ሰዎች ጭንቅላት ከመንከባለል አልፎ መወያያም እየሆነ ነው። መንግሥትስ የተጎዱት ግለሰቦች ሃብት የውሃ ሽታ ሆኖ እንዳይቀር ምን ዕርዳታ አደረገለት የሚለው ጥያቄም እስከዛሬ መልስ አላገኘም!

አቶ ኤርምያስስ የተገባለት ቃል ላይ ተማምኖ፣ እርሱም ቃሉን አክብሮ አክሰስን እንደገና አንቀሳቅሶ ለግለሰቦቹ ድርሻቸውን ሊመልስ ካልቻለ፣ ለመታሰር ብቻ ይመጣል ወይ የሚለው ጥያቄም ሌላው መልስ ያላገኘ ጉዳይ ነው።

ፎርቹትን እንደ ዘገበው ከሆነ ደግሞ ችግሩ የመንግሥት ወይንም በመንግሥት ዙሪያ ያሉ ከበድ ያሉ ግለሰቦች እጅ ንጹህ አለመሆናቸውን በተዘዋዋሪ መንገድ ያነሳል። ለዚህም በምሣሌነት በተለያዩ አንደበቶች ኤርምያስ በሌለበት 45 ይደርሱ የነበሩ ንብረቶቹ የአክሰስ ቦርድ እንኳ ሳያውቀው፣ በስተጀርባ ተሻሽጠው የቀሩት ንብረቶች 19 ብቻ መሆናቸው ይነገራል።

‘ማናቸውም ነገር ከእኔ ዐይን ውጭ አይደለም’ ብሎ የሚፎክረው የኢትዮጵያ ደኅንነት መ/ቤት (ሌሎቹየመንግሥት መ/ቤቶች እያሉም) ይህ እንዴት ቢሆን ነው፣ ገንዘባቸው ሽታው ለጠፋው ግለስቦች ክፍያ እንዲሆን ሁነታዎችን ከማመቻቸት ይልቅ፣ ይህን ችላ ብሎ መንግሥት ንብረቶቹ እጅ የለወጡበትን ሁኔታ ሳይገልጽ ግለሰቡን ወደ ማሠር የተሸጋገረው?

እነዚህኑ ንብረቶች አስመልክቶ የከተማና ቤቶች ሚኒስትር መኩሪያ ኃይሌ፥ በዚህ ጉዳይ ላይ የተቋቋመው ሚኒስትራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ፥ ለሚዲያ እንዲህ ሲሉ መናገራቸውን – እንደ አዲስ ፎርቹን ሁሉ – ሪፖርተር ጥር 16/2016 ባወጣው የእንግሊዝኛ እትሙ ላይ ጠምዘዝ ባለመልኩ አትቷል፦

  “…There are 41 plots in various parts of the city associated with Access, some of them are purchased illegally from individuals and companies, while some are secured with a joint venture arrangement with other real estate developers…But there is no plot acquired illegally by the company.”

ይህ ግልጽነት የጎደለው አጥንት የጎረሰ ጅብ አባባልና አሠራር ለራሳቸው የሕውሃት ሰዎችም አይበጃቸውም!

ከዚህ በተጨማሪም፡ በግልጽ ሕወሃትም የሰማቸው በባህሪው ምክንያት የሚያውቃቸውም ጉዳዮችና ስሞታዎች አሉ። እንግዲህ ‘የመንግሥት ጥድፊያውና እሩጫው’ ገንዘባቸውን ውሃ የበላባቸው ግለሰቦች በአብዛኛው ትግሬዎችና የሕወሃት አባሎች በመሆናቸው ነው ይባላል! ስለሆነም፥ ከዚህ ውስጥ ለውስጥ የሚርመሰመሰውን፥ አንዱ ሲገልጥ ሌላው ችግሩ ላይ ሠፌድ የሚደፋበት ሁኔታ ውስጥ የሕወሃትን አስተዳደር የኤርምያስ ችግሮች አካል አድርጎታል!

በተለይም በአሁኑ ወቅት አቶ ኤርምያስ ‘ለምን ታሠረ?’ የሚለውን ጥያቄ ኅብረተሰባችን እንዲያነሳ አስገዳጅ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። በአጠቃላይ በኅብረተሰባችን አስተሳሰብ መንግሥትን ችግር ፈቺ አድርጎ ስለሚመለከት፥ ጥያቄው መንግሥት እንደ መንግሥት ለምን ወደ እሥር አመራ? ለምንስ ቃሉን ማክበር አልቻለም? ይህንንም ለመገንዘብ ገንዘባችን ገደል ገባ ባዪ ወገኖች በኩል አንድ ክፍፍል ወይንም ልዩ ጥቅም ያለው ቡድን መኖሩን ግምት ውስጥ ማስገባትን ይጋብዛል – ምንስ ያስገርማል እንዲህ የሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ቢኖሩ በአንድ በኩል ልባቸው የሚመለሰውን ገንዘብ አከፋፋይ ስለሚሆኑ (ከተገኘ)፥ በሌላ ደግሞ ሕዝቡን እኔ አውቅልሃለሁ የሚል መንግሥት ባለበት ሃገር የዚያ ግርፍ መሆናቸው ግምት ውስጥ ሊገባ የሚገባ ይመስለኛል።

ከላይ ለተነሱት ጥያቄዎች ምናልባትም ፋና ወጊ በሆነ መልኩ፥ ፎርቹን ሪፖርት እንዳደረገው ከሆነ ደግሞ፣ ገንዘባችንን ማግኘት እንፈልጋለን የሚሉት ሰዎች በመንግሥት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር መቻላቸው በተዘዋዋሪ መንገድ ራሱ ለችግሩ መፈታት እንቅፋት አድርጎ እንደሚከተለው ያቀርባቸዋል፦

  “But not everyone filed a lawsuit. Angry homebuyers formed a series of committees in order to organise their efforts. These were able to apply enough pressure to warrant the creation of two special government [committees?] in July 2014, empowered by Prime Minister Hailemariam Desalegn to take legal, administrative and political measures to resolve the problems faced by both homebuyers and shareholders.”

የፍትህ ሚኒስትሩ ኅብረተሰቡና ሚዲያው የሚለውን መካዳቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፥ አሁንም ኤርምያስ መታሰር አለበት ብሎ ለመወሰን መንግሥት ምንን መለክያ አደረገ? ተጠያቂው ግለሰብ ላከሠርኳቸው ሰዎች የማደርግላቸው ነገር የለም ብሎ እራሱ ተጠያቂነቱን ለሕግ አረጋገጠ ወይ? ወይንም በተወሰነ የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ ለመሞከር ቃል የገባውን ለማድረግ ራሱ እንዳልቻለ ተቀብሎ የተሰጠው የጊዜ ገደብ አለቀበት ወይ? ትክክለኛ ቅበላ ነው ማለቴ ባይሆንም፡ ይህ ካልሆነ ሕወሃቶች ሲዘርፉና ሲገድሉ ኖረው – ኤርምያስ እንደ እነርሱ ዘራፊ ነው ብለን ብንቀበል እንኳ – ሌላውን አታድርግ ማለትስ መብቱ አላቸው ወይ?

ግልጽ ነው የሕወሃት ሰዎች ይዘርፋሉ! ምናልባትም ዘርፎ ሕዝብን ወደ መሳደብ እንደ ዐባይ ፀሐዬ ዐይነቱስ በዐይን አውጣነት መሄዱ ከዚህ ውስብስብ ሁኔታ በምን ይለያል? ጥጋበኛው ዐባይ ፀሐዬ የስኳር ፕሮጄክትን ገንዘብ ተንደላቀቀበት! ዋናው ኦዲተር በበጀት ሳይሆን፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር ቋት ወጥቶ የተሠጠውና (ለሌሎች መ/ቤቶች የማይደረገው) የት እንደ ደረሰ ሰለማይታወቀው ብር 418,803,484.57 ለፓርላማ ሚያዝያ 2007 ማሳወቃቸውና ነገሩ ግን ለጊዜው መረሳቱን አንብበናል። የሚገርመው የፕሮጀክቱን ሥራ ማስፈጸም ስላልተቻለ፣ ሃገሪቱ በድምሩ ከቻይና በስኳር ፕሮጀክትና የባቡር ሥራ ስም $700 ሚሊዮን መበደሯ ነው። ይህ በሃገርና በሕዝብ ሃብት ላይ የተፈጸመ ውንብድና በመሆኑ፡ ለምን በወንጀሉ የተጠረጠረው ግለስብ ተጠያቂ አልተደረገም?

Ermias Amelga (Addis Fortune)

Ermias Amelga (Addis Fortune)


 
ሃገርን ዘረፋና ፖሊሲ የሥራ መመሪያ ሳይሆን ጥቅማ ጥቅሞችን ማስጠበቂያ በሆነባት ሃገር፡ የአቶ ኤርምያስን ጥረት አላደነቅሁም ማለት አልችልም። በፈለገው መስክ ኢንቬስት ቢያደርግ ምንም ችግር አልነበረኝም። ጎበዝም በመሆኑ በወቅቱ ሕጉ በፈቀደለት ቀዳዳ ሁሉ፡ በሃገርም ውስጥ እንደ ሕወሃት ሰዎች ሁሉ ነዋሪዎቿ በተገፉባት ጋምቤላ ውስጥ ሳይቀር 5,000 ሄክታር መሬት ወስዶ ማልማት ጀምሮ ነበር። በሌላ የተለያዩ መስኮችም ስሙ ይጠራ ነበር። ይህም ችሎታ ይጠይቃል፣ በተለይም ሥልጣን ይዘው ተጠያቂነት የሌለባቸው ባለሥልጣኖች የአምስት ዓመት ዕቅድ እያወጡ አንዱም ነገር ግቡን ሳይመታ በቀረበት ዘመን!

የአቶ ኤርምያስን ፈተናዎች በተመለከተ፣ ፎርቹንም እንደኔው አንዳንድ የእውነት እንጭፍጫፊዎችን ከማንጠባጠብ ባለፈ፥ መልስ መስጠት የማይችልባቸው ጉዳዮች ላይ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ጥያቄዎችን ያነሳና የሕወሃት ባለሥልጣኖች ላይ የሚሰሙት ሃሜታዎች ያሉበትንም አካባቢ በጨረፍታ ነካ በማድረግ፣ መዋቅራዊም ሆነ አስተዳደራዊ ተሃድሶ ለዚህ ብቃት ያለው መልስ እንደማያስገኝና ሁሉም ነገር አስቸጋሪ እንደሆነበት እንደሚከተለው የችግሩን ክብደት ያጎላውል:-

  “Lives have been shattered, life savings have been lost, retirees have been effectively and ironically rendered homeless. What seems clear is that Ermias has run out of options to avoid recourse in law. But what are the factors that could have turned what initially seemed like a good investment into the nightmare that investment in Access Real Estate seems to have become for homebuyers? And they are not the only ones who have suffered losses. The reasons seem to go beyond the personal, to the political, social and poor institutional governance.”

ከላይ የተጠቀሰው፡ ሥርዓቱ ራሱን አሻሽሎ ወደፊት ይቀጥላል የሚል እምነት ባለበት አካባቢ ምናልባትም የፎርቹን ጥረት ሌሎች ስዎች እንዳይጎዱ ቢሆንም፡ ይህ ምክር የሚሰጠው ግን መጽሔቱ ባላሰባሰበው የሕግ መረጃና ውክልና በኬለው ጉዳይ በተዘዋዋሪ መንገድ ግለሰቡን መወንጀል ሆኖ እንዳይታይበት ሠጋለሁ።
 

የኔና የኤርሚያስ መንገድ የተገናኙበት አጋጣሚ

እንደማስታውሰው ከብዙ የኤርምያስ ጥረቶች መካከል ኢትዮጵያ ውስጥ በዐይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ዳታ አሰባስቦ ትንተና የሚያዘጋጅና በኤኮኖሚው ላይ ምልከታ መሥጠት የሚችል ግለሰብና ለዚህም የሚረዳ ክፍል አቋቁሞ ነበር። በዚህም አማካይነት ከ2009 ጀምሮ Ethiopia: Macroeconomic Handbook 2009: 2010 እና2011 እየታተመ መውጣት ጀምሮ ነበር።

ያኔ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ እርሱ በዚያ መስኲ እኔ በብሎገርነቴ በዓመታዊ ሥርጭቱ አማካይነት ያወቅሁት።

እንደ ማስታውሰው አድናቆቴንም ቶሎ ወደ ቅያሜ የወሰደው ይኸው የልፋቱ ውጤት የሆነው የምርምር ሥርጭቱ ነበር። የ2011-2012 Macroeconomic Handbook ባወጣበት ጊዜ ነበር። የግንኝነታችንም ምክንያት ያ እትም በውስጡ የያዛቸው ነገሮች ለሃገሪቱ አስፈሪና አስደንጋጭ ሰለሆኑብኝ፣ ተቃውሞዬን ጥር 12/2012 Access Capital adds its own to the on-going debate on Ethiopia’s economic performance ገለጽኩ፤ ብዙ ሰው ወደደው፣ አነበበው፤ እስከዛሬም አልፎ አልፎ በአንዳንድ ጽሁፎች ሲጠቀስ አያለሁ።

ድርጅቱ በመዘጋቱ/ክፍት ባለመሆኑ፡ እነዚህን ጥናቶቹን በኢንተርኔት እንኳ ዛሬ ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ ላይ ነን – አጥፊዎች ዘወትር ውሃውን በማደፍረስ ብቻ በሚያምኑበትና ታሪክን በሚሠርዙበት ባሀሪያቸው ምክንያት ማለት ነው!

ከአክሰስ ጋር የነበረኝ ትልቁ ጠብ አንደኛውን የአምስቱን ዓመት ፕላን (2011-2015) ተግባራዊ ለማድረግ ለሚያስፈልገው ገንዘብ፡ መንግሥት በእጁ የሚገኙትን ኩባንያዎች በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድን፡ ቴሌኮሙኒኬሽንን፣ መብራት ኃይልን፥ ‘ሙታንታውን’ ጭምር ወዘተ በሃራጅ እንዲሸጥ የሚመክር ነበር። እዛ ውስጥ አብሮ የታየኝ አቶ ኤርምያስ ምን ያህል ሊያላምጥ ከሚችለው በላይ ለመጉረስ እንደ ተዘጋጀ ነበር።

ምናልባትም ከዘመናዊ ካፒታሊስት ቢዝነስ አሠራር አንጻር ትክክለኛ ሊሆን ይችላል፡ በተለይም ቢዝነሱና ትርፉ አስተማማኝ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ!

በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሽያጭ ጉዳይ አልተዋጠልኝም ነበር።

በጥቅሉ በወቅቱ የሠነዘርኩት አስተያየት የሚከተለው ነበር፦

  “As a company that is in the process of expanding itself in so many areas at the same time, at least no less than 15 companies under it at present, clearly Access is hungry for growth more for its own sake than benefitting from the country’s wholesome development. For instance, while I like the five recommendations it has made in respect of smallholder agriculture, even then there are indications that the intention is not at all to address rural Ethiopia’s accelerated agro-technological transformation, as it claims, but to make gains for itself as an investment firm. There is also the nationalization proposal, to which it has failed to make serious case.

  What Access and the government share in common is self-interest. When they are focussed on what they need, they both ignore many prerequisites and essentials. A case in point is the plight of those citizens in the food insecure districts. Access believes that their situation is incapable of limiting or stopping growth. To that end, it takes the government’s figure of more than 4.6 million “food-insecure individuals” and drops them out of existence, stating their situation “does not contradict expectation of strong overall agricultural growth figures, which reflect output in food-producing and food-surplus regions of the country.” This is hard to take since it is also detached from the country’s ugly realities that need changing.”

በአምስቱ ዓመት የልማት ዕቅድ መሠረት ሃገሪቱ በ2015 በምግብ ራሷን ትችላለች ተብሎ ስንጓዝ ከርመን፣ የረባ የኤኮኖሚ ዕድገት እንኳ ሳናይ፣ ዛሬም ከረሃብ መላቀቅ ባለመቻላችን፣ ኤርሚያስም የያኔው ችግር ትኩረታችንን አይሳበው ሲል (የዛሬውን ሶስት ዕጥፍ ምን እንደሚለው አላውቅም)፡ በአሁኑ ወቅት ከ18-20 ሚሊዮን የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በችጋር እየተጠበሰ ነው!

ነገር ግን የዚህ ዐይነቱ የሃሣብ ልዩነት፥ አቶ ኤርምያስን እንደ ጠላት እኔን የተሻለ አያደርገንም። እንዲያውም የዚህ ዐይነቱ የተለያዩ አመለካከቶች ግጭቶች የአንድን ሃገር ዕድገትና የፖለቲካ ኤኮኖሚው ጤንነት ከሁሉም አቅጣጫ እንዲታይ ዕድል ይከፍታል። ችግሩ ያ አለመሆኑ ማስረጃውም አክሰስ በወቅቱ ካቀረበው ሃሣብ ይበልጥ፡ ሃገሪቱን እየጎዳ ያለው ዛሬ የኢርሚያስ አመልጋ አሣሪዎች፣ በሚስቶቻቸውና በልጆቻቸው አማክይነት ዶላርና ወርቅ በሻንጣ እየጫኑ ባህር ማዶ ማሻገራቸው አይደል እንዴ?

እስካሁን ባለን መረጃ፣ ኤርምያስ ይህንን ማድረጉን አናውቅም። አቶ ኤርምያስ የፈለገው መንግሥትን ከቢዝነስ አስወጥቶ፡ የግሉ ሴክተር ቢዝነሱን እንዲያካሄድ – በተለይም የእርሱ ኩባንያ የሚችለውን ያህል ውጦ እንዲከብር ነበር! ይህ ወንጀል አይደለም፤ ይህ መደረግ ያለበት ሥነ ሥርዓት ባለው ግልጽ የፖሊሲ አቅጣጫ እንጂ – ሕወሃት እንደሚያደርገው – ሃገሪቱን የሕወሃት-ስብሃት-ነጋ ኩባንያ በሚያደርጋትም መንገድ መሆን የለበትም!

አቶ ኤርምያስ ያተኮረባቸው ዋና ዋና የመንግሥት ተቋሞች (ለምሣሌ አየር መንገድ) ያንን ፕላን ተግባራዊ ቢደረግ ኖሮ፥ ዛሬ ሃገራችን አጨብጭባ ባዶ እጇን ትቀር ነበር!

አሁን እንደምናየው ከሆነ፡ ትግሉ ሕወሃት የሃገሪቱን ኤኮኖሚ ኪሡ በማድረጉ፣ ሕዝቡ ይህንን አልወደደለትም። ፖለቲካውን እፍን አድርጎ ይዞ፣ ዘረፋውን እያጧጧፈ በመሆኑ፡ እንደ አቶ ኤርምያስ ዐይነት እሳት የላሰ ካፒታሊስት ሲመጣ ደግሞ በኤኮኖሚው መስክ አንድ እርምጃ እየቀደማቸው፡ ሊያዩት ሊያስቡት በማይችሉበት መስኮችና ፍጥነት ጥቅም ሲያሰባስብ፣ ኤኮኖሚያዊ ምቀኝነት ተጠናወታቸው። ቆም ብለው ሲያስቡትም፣ ነገ በፖለቲካው መስክም ክፉ ተቀናቃኝ እንደሚሆናቸው የተሰማቸው ይመስለኛል።

ለነገሩ አቶ ኤርምያስ የዚህ ዐይነት ዕጣ ፈንታ ሲደርሰው የመጀመሪያው ሰው አይደለም። ብዙ እንደርሱ የማያንጸባርቁና በየዋህነት ኢትዮጵያ ውስጥ ወደፊታቸውን መፈጠር የተመኙ ሁሉ ውጭ ያላቸውን ቋጥረው መጥተው ጉድ የሆኑትን የብዙ ዜጎቻችንን ሁኔታ አንብበናል። ነገር ግን በአንድ በኲል ‘ገዥ ካልሆኑት’ የተለያዩ የዘር ግንዶች በመምጣታቸው በሕወሃት ወንበዴዎች (በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚስትና ቤተስቦች ጭምር) ቢዝነሶቻቸውን ተነጥቀው ቀድመው ወደ ተሰደዱባቸው ሃገሮች ተመልሰው ጀማሪ መደረጋቸውና ‘ለሃበሻ ሽሙጥ’ መጋለጣቸውን በየጊዜው ስናነብ የከረምናቸው ነገሮች ናቸው።

ይህም በውቅቱ በደኅንነቱ ጭምር የተደገፈ ተራ ማጅራት መምታት በመሆኑ፣ እነ መለስ ዜናዊ ደግሞ ታክስን እንደ ምክንያት ደጋግሞ በመጠቀምና ሌሎቹን በማሠር ንብረቶቻቸውን በመዝረፍ የተሸኙትን ቤቶቻቸው ይቁጠሯቸው። አሁን ሕወሃትም የዚህን ዐይነቱን የተራ ካድሬዎቹ ዘረፋ የራሱን ቱባና ካብ የሚያህሉ ፕሮጅከት ዘራፊዎችና ጉበኞችን ‘እንጀራ እየነሳ’ በመምጣቱ አልወደዱላቸውምና የዚህ ዐይነት ከፊል ሰዓት የደኅንነት ሠራተኞች አፋኝነት (part-time intelligence operatives) ጋብ እንዲል ተደርጓል። ይህም ሆኖ ሃገሪቱ በሕግ የተደገፈ የውንብድና ሃገር መሆኗን አላስቀረውም፡ ገና ገሃድ ወጥቶ ዓለም ካለማንበቡ በስተቀር!

አንደኛው የአምስት ዓመት ዕቅድ ሲያልቅ፡ ሃገሪቱ ከነበረችበት ወርዳ – በተለያዩ ጽሁፎቼ እንደገለጽኩት – ተጠያቂነት የሌለባቸው ግለስቦች መክበሪያቸው አድርገዋታል። ሕወሃት በትግራይ ተሃድሶ ኮርፖሬሽን ስም (EFFORT) ለዐባይ ግድብ ያለጨረታ ሲሚንቶ ለማቅረብ ተቋራጭ ሆኖ የሃገራችንን አጥንት ሲግጥ ከርሟል። የትራንስፖርት ኩባንያው ብቸኛ ዕቃዎች ተሸካሚና አቅራቢ ሆኖ እየሠራ ነው። ከኦርኪድ ጋር በተያያዘ፡ የመለስ ዜናዊ ቤተሰብም እንዲሁ ከጀርመን ኩባንያ ጋር በመሥራት ዘረፋ ሲያካሂድ ቆይቷል። መስፍን ኢንጂነሪንግም እንዲሁ ከብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ጋር በበጀት በተያዙ ፕሮጂከቶችም ከዚያ ውጭ ተቋራጭነት እየተሰጣቸው ሕወሃትን ሲያከብሩ መኖራቸውን በተለያዩ ጽሁፎቼ አቅርቢያለሁ። ሱር የመንገድ ሥራ ድርጅታቸው እንዲሁም የሕወሃት የዜና ምንጭች ጭምር ሁሉም በየፊናቸው በየቀኑ እንደጎረሱ ናቸው!

ባለቻቸው ውሱን ቀዳዳ እንኳ፣ የሃገሪቱ ዋና ኦዲተር ጄኔራል ገመቹ ዲቢሶ ማይክሮስኮፒክ በሆነ መንገድ ባለፈው ሣምንት ፓርላማ ውስጥ በማዕድን ዘርፍ “ሃገሪቱ እየተዘረፈች ነው!” ብለው መጮሃቸውን – ትዊት ባደርገውም – ሰለደነዘዝን ብዙ ላይሰማን ይችል ይሆናል፡ በሃገሪቱ ላይ ግን ጥፋቱ እየተበራከተ ነው!

አሁንም እንደገና የሕወሃት ሰዎች ‘እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይበቀል በሚለው አህያዊ አስተሳሰባቸው፡ ለራሳቸው የሚዝቁትን ሲያዘጋጁ፡ ሁለተኛው የአምስት ዓመት ፕላን (2016-2020) ያለፈው ሐምሌ ላይ ታውጇል።

ይህንንም የመሬት መዝረፍያ ፕላን (ኢንዱስትሪ ፓርክና የኤኮኖሚ ዞን) በጸደቀ ማግሥት በለቀቅሁት የቲዊተር አስተያየት ‘ሳይተገበር የሞተው’ (dead on arrival) ማለቴ በመፈብረክ መስክ በመጀመሪያው ዓመት የስድስት ወር በተገኘው ውጤት ትክክል መሆኑን ተገንዝቤያለሁ።

በየቦታውም እራሱን ለመትከል ሌሎች የማይደፍሩበት ቦታ ሁሉ ኢንቬስተር በመሆን፣ አዳዲስ ሃሣቦችንና አሠራሮችን በማፍለቅ ኤርምያስ አመልጋ ብዙ መንቀሳቀሱ የችገሩ ምንጭ ሆኖበታል የሚል ጠንካራ ስሜት አድሮብኛል – ድክመቱንም በደንብ የተገነዘብኩትን ያህል!

በሙስና መጨማለቅ የሚታወቁት ጄኔራል ክንፈ ዳኘው – የቺፍ ኦፍ ስታፍ ሳሞራ ዩኑስ በትዳር ቤተስብነታቸው የሚነገርላቸው – ባለፈው ታህሳስ ወር በተቀረጸላቸው ቪዲዮ አማካይነት ዐይናቸውን ወደ ሰማይ ከፍ አድርገው ኦሮሞች እየተጨፈጭፉባት ባሉባት ሃገር ስለ ሕገ መንግሥቱ ቅዱስነት ምሥክረነት ሲሰጡ መስማቱ የበሉ ሕወሃቶች ምን ያህል የሚያሳፍሩ ሰዎች መሆናቸውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አስረግጦልኛል!

ከዚህ ጋር በተያያዘ ልናስብ የሚገባን፥ ኤርምያስ ወደ ሃገሩ በሰላም እንዲመለስ ከእርሱ ጋር የተደራደረው ኮሚቴ በሕወሃት አስተዳደር ሕወሃታዊ ትግሬ ላልሆነ ሰው ዲፕሎማሲያዊ የመፍትሄ ሃሣብ አቅርቧል – ከላይ እንደተገለጸው በሁኔታዎች አስገዳጅነት።

ይህ ግን በሁሉም መስክ ለዘበርጋም ሆነ ሃጎስ ሆነ ለደባላም ሆነ የኔነህ፥ ለአጊሎና አብዱላሂ፥ ለዓለምነሽና አመኔ ወዘተ፥ – ባጠቃላይ ለሁሉም ዜጎች – በሁሉም መስክ የሰላማዊ የዜጎችን ሰብዓዊነት፥ ክብርና መብቶቻቸውን ያከበረ ጥረቶችን ማድረግ ጠቃሚነት አሰምርበታለሁ። ይህ ብዙ ብቃትና ችሎታ ያላቸው ዜጎች ወደ ሃገራቸው መመለስና በሰላምና በሃገራቸው ከለላ ሥር ማሰባሰብ እንጦርጦሮስ የወረደውን የዕውቀት ደረጃ፥ የኢትዮጵያን ሰብዓዊ ልማት (human development) ለማዳበርና የሃገሪቱን የወደፊት ግስጋሴ እንዲፋጠንና የዜጎቻችን ሕይወት እንዲለወጥ ይረዳል!

ይህም የሃሰት የልማት ቁጥር ከመደርደር ይሻላል – ሕወሃት እስካለ ድረስ የማይታሰብ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም!
 

%d bloggers like this: