በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአናብስት ቁጥር መጨመሩን አቶ ካህሳይ ገብረትንሳኤ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አስታወቁ

6 Feb
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በማኦኮሞ ወረዳ በቁጥርም ከፍተኛ የዱር እንስሳት ሃብት መኖሩ በቅርቡ በተደረገ ጥናት ተረጋግጧል (ኢዜአ)

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በማኦኮሞ ወረዳ በቁጥርም ከፍተኛ የዱር እንስሳት ሃብት መኖሩ በቅርቡ በተደረገ ጥናት ተረጋግጧል (ኢዜአ)

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 
(አዲስ አበባ ኢዜአ ጥር 27/2008) በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአናብስት ቁጥር ማደጉን በጥናት ማረጋገጡን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የባለሥልጣኑ ሠራተኞች አናብስቱ በብዛት የሚገኙት በክልሉ ማኦኮሞ ወረዳ መሆኑን በጥናት አረጋግጠዋል።

ሠራተኞቹ በዓይን በሚታይ ርቀት በአንድ ጊዜ 53 አናብስት ተመልክተዋል።

በባለስልጣኑ የዱር እንስሳት ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ ካህሳይ ገብረትንሳኤ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት በማኦኮሞ ወረዳ በቁጥርም ከፍተኛ የዱር እንስሳት ሃብት መኖሩ በቅርቡ በተደረገ ጥናት ተረጋግጧል።

ምንም እንኳን አካባቢው ጥቅጥቅ ባለ እጽዋት የተሞላና በዓይን ለማየት አስቸጋሪ ቢሆንም፤ የባለሥልጣኑ ባለሙያዎች በርካታ ቁጥር ያላቸው አናብስትና ሌሎች የእንስሳት ዝርያዎች በአካባቢው ለመመልከት ችለዋል።

ቀይ ጦጣ፣ ጉሬዛ፣ ድኩላ፣ አቦሸማኔ፣ እንዲሁም በአካል ባይታይም ዝርያው ጠፍቷል ተብሎ የሚታመነው አውራሪስም በስፍራው ሊኖሩ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ሥፍራው ካለው የ2ሺ 304 ስኩዬር ኪሎ ሜትር ስፋት አንጻር በተለይ በአይን የታዩት አናብስት ቁጥር በእጅጉ ሊበዛ እንደሚችል ተገምቷል።

ዳይሬክተሩ እንደገለጹት አካባቢው ከኦሮሚያና አማራ ክልሎች እንዲሁም ከሱዳን ድንበሮች ጋር ይዋሰናል፤ ብዙ የሰዎች ንክኪ የሌለበት መሆኑም ለዱር እንስሳቱ መኖር አመቺ አድርጎታል።

በመሆኑም የእንስሳት ስርጭት መጠኑንና ቁጥሩን ለማወቅ በመሬት ተደራሽ ያልሆኑትን አካባቢዎች በአየር ቆጠራ በማካለል በቀጣይ “ማኦኮሞ ብሔራዊ ፓርክ” በሚል ለመከለል በዕጩ ፓርክነት መያዙን አስታውቀዋል።

በአካባቢው ድንበር ዘለል የእንስሳት ጥበቃ ስርዓት ለመዘርጋትም እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ መሆኑን አቶ ካህሳይ አስረድተዋል።

ሰሞኑን በተለያዩ የውጭ መገናኛ ብዙኃን አላጣሽ በተሰኘው ብሔራዊ ፓርክ ተገኙ የተባሉት አናብስት አስመልከቶ የተሰራጨው ዘገባ የተዛባ መሆኑን አስታውቀዋል።

አናብስቱ ከዚህ በፊትም በፓርኩ ይኖሩ እንደነበር እንደሚታወቅም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በማኦኮሞ ዕጩ ፓርክ ውስጥ ከዱር እንስሳት በተጨማሪ የተፈጥሮ ፍል ውሃና ሐይቅ እንደሚገኝ የባለሥልጣኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
 

%d bloggers like this: