በአንድ ጀምበር ሚሊየነር የሚሆኑ ግለሰቦችን ጉዳይ በማንሳት የፓርላማው አባላት የፀረ ሙስና ኮሚሽን ክስ ያለመመሥረት ዳተኝነት ላይ የሰላ ትችት ሰነዘሩ – ሪፖርተር

7 Feb

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

“ቀማኛ በምክር አይመለስም” ሲሉ ተችተዋል

በአንድ ጀምበር ሚሊየነር የሚሆኑ ግለሰቦችን ጉዳይ አንስተዋል

የፓርላማው አባላትና የሕግ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሰላ ትችታቸውን በፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ላይ ሰነዘሩ፡፡
አባላቱ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትና የሥራ ኃላፊዎች በግዥ ሰበብና በተለያዩ መንገዶች የሕዝብና የአገር ጥቅም ለመዝረፍ ረዥም ርቀት መሄዳቸውን ኮሚሽኑ ቢያረጋግጥም፣ በምክር እያለፋቸው የምክር አገልግሎት መስጠት ላይ አዘንብሏል በማለት ተችተዋል፡፡

የሕግ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ፣ ኮሚሽኑ መንግሥት የጀመረውን የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ መደገፍ በሚያስችለው አደረጃጀት ላይ አይደለም በማለት ተችቷል፡፡
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነርና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች የተቋሙን የ2008 ዓ.ም. የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ለፓርላማው ጥር 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ባቀረቡበት ወቅት ነው ይህ ትችት የገጠማቸው፡፡

ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ ወዶ አጦ ከፍተኛ ትችት የገጠማቸው ባቀረቡት ሪፖርት ‹‹አስቸኳይ የመከላከል ሥራዎች›› በሚለው የሪፖርቱ ይዘት ላይ ነው፡፡

ሪፖርቱ፣ “አስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ በተቋማት ውስጥ በሒደት ላይ ያሉ ጉዳዮች፣ በተለይም ጐላ ጐላ ያሉ የግዥ ተግባራትን ግልጽነት በጐደለው፣ ሕግን ባልተከተለና በተሳሳተ መልኩ እየፈጸመ መሆኑን የሚጠቁም መረጃ ሲደርስ፣ ጉዳዩን የማጣራት ሥራ በማከናወን ተገቢው የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወሰድ፣ እንዲሁም ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው ፍትሐዊ አሠራር እንዲሰፍን ማድረግ ነው፤” ይላል፡፡

በዚሁ መሠረት ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅራቢ ድርጅት የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ለመፈጸም ባካሄደው ጨረታ መመርያን ያልተከተሉ አሠራሮች መኖራቸው ታውቆ፣ መንግሥት ሊያጣው ይችል የነበረ 55 ሚሊዮን ብር መዳኑን ምክትል ኮሚሽነሩ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡ በፊንጫ ስኳር ፋብሪካ የሠራተኞች ደንብ ልብስ ግዥን በሚመለከት የስምንት ሚሊዮን ብር ጨረታ ችግር የነበረበት በመሆኑ እንዲሰረዝ መደረጉን አክለዋል፡፡

የአዳማ ዩኒቨርሲቲ የሠራተኞች የደንብ ልብስ ግዥ አፈጻጸም ችግር ከነበረባቸውና በአስቸኳይ የማስተካከል ሥራ መፍትሔ ያገኙ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ ምክትል ኮሚሽነሩ ሪፖርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የምክር ቤቱ አባላት በሪፖርቱ ላይ ጥያቄ እንዲያቀርቡ ዕድል ተሰጥቷል፡፡

በዚሁ መሠረት የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ዳባ፣ በአስቸኳይ የሙስና መከላከል ተግባር በሚል ኮሚሽኑ እያቀረበ ያለው ሪፖርት ተገቢ ያልሆነና ውጤት የሌለው መሆኑን በመጥቀስ ወደ ክስ እንዲገባ አሳስበዋል፡፡

“ኮሚሽኑ ባለፈው ዓመት ባቀረበው ሪፖርት የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የእሳት አደጋ መከላከያ ለመግዛት ባካሄደው ጨረታ ችግር እንዳለበት ተጠቁሞ ኮሚሽኑ 5.2 ሚሊዮን ብር የመንግሥት ሀብት ማዳኑ መገለጹን፣ ዛሬም በሪፖርቱ ይኸው ተቋም የቀረጥ ነፃ መብት የተሰጣቸው ድርጅቶች አያያዝን በተመለከተ ምክር እንደተለገሰው ሪፖርቱ ይገልጻል፤” ብለዋል፡፡

በአዳማ ዩኒቨርሲቲ በ2007 ዓ.ም. ከምግብ ግዥ ጋር በተያያዘ መንግሥት ላይ ሊደርስ የነበረ የ16.2 ሚሊዮን ብር ጉዳት መታደጉን በሪፖርቱ የገለጸው ኮሚሽኑ፣ ዛሬም ለአዳማ ዩኒቨርሲቲ ምክር መለገሱን በመጥቀስ አቶ ተስፋዬ ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

በተጨማሪነት ያነሱት ማሳያ ደግሞ የስኳር ኮርፖሬሽን በ2007 ዓ.ም. 30 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ነጭ ስኳር ለመግዛት ባወጣው ጨረታ ያልተገባ አሠራር እንዲከሽፍ ማድረጉን በሪፖርቱ መግለጹን፣ ዛሬም በዚህ ኮርፖሬሽን ሥር ባሉት ተንዳሆና ፊንጫ ስኳር ፋብሪካዎች ሕግን ያልተከተለ ግዥ በምክር ማለፉን ጠቁመዋል፡፡

“መንግሥታችንና መሪ ድርጅታችን የመልካም አስተዳደር ችግር መቅረፍ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው ብሎ ከሕዝብ ጋር ንቅናቄ በፈጠረበት በአሁኑ ወቅት፣ የሙስና ወንጀል እየታየ በሕግ የማይኬደው ለምንድነው? ይህንን ወርቃማ ዕድል የማትጠቀሙበት ለምንድነው?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ይህንን የሚሉበት ምክንያት የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 27 ማንኛውም ሰው ወንጀል ለመፈጸም ጀምሮ ወንጀሉን ባይፈጽምም ወይም ውጤቱን ባያይም መሞከሩ ብቻ ጥፋተኛ የሚያደርገው በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ይህንን ድንጋጌ ለምንድነው ከፍተኛ ወንጀል በሆነው ሙስና ላይ የማትጠቀሙት ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

“በዚህ ፍጥነት ኮሚሽኑ የሚቀጥል ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትራችን እንዳሉት ጣት እንቆርጣለን ሳይሆን ምክር እንሰጣለን ወደሚል የምትለውጡት ይመስለኛል፤” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አቶ ብርሃኑ አበበ የተባሉ የምክር ቤቱ አባልም የአቶ ተስፋዬን ሐሳብ ደግፈዋል፡፡ ሌላው የምክር ቤቱ አባል ዶ/ር አድሃነ ኃይሌም አቶ ተስፋዬ በመረጃ ላይ ተመሥርተው ያነሱትን ጥያቄ ተገቢነት ደግፈዋል፡፡

“ሕዝብን ማስተማር ይቻላል፡፡ ዜጐችን በአጠቃላይ ማስተማር ይቻላል፡፡ ቀማኞችን ግን ማስተማር አይቻልም፤” ብለዋል፡፡

በመሆኑም አቶ ተስፋዬ እንዳነሱት የመከላከል እንቅስቃሴ ተደርጐም የሚደገም ከሆነ የሚደገምበት ምክንያት አለ ማለት በመሆኑ፣ ኮሚሽኑ በቅጣት ማረም መጀመር አለበት ብለዋል፡፡

አቶ ዓለሙ አሰፋ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል በበኩላቸው፣ በአገሪቱ ውስጥ በአንድ ጀንበር ሚሊየነር የሚሆኑ ግለሰቦችን ጉዳይ ኮሚሽኑ እንዴት እየተከታተለው እንደሆነ ጠይቀዋል፡፡

ባለሥልጣናት ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ መደረግ ከተጀመረ በኋላ የማሸሽና በሌላ መልክ የመደበቅ ዝንባሌ መታየቱን፣ ይህም በአንድ ጀንበር የሚፈጠሩ ሀብታሞችን እያሳየ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ከእነዚህ የአንድ ጀንበር ባለፀጐች ጀርባ ያለውን የሙስና ኔትወርክ ኮሚሽኑ እየተከታተለው እንደሆነ ጠይቀዋል፡፡ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ምክትል ኮሚሽነሩ አቶ ወዶ አጦ ሀብት የማዳንና የልማት ሥራው እንዳይስተጓጐል ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

“ይህ ማለት ግን ወደ ምርመራ የገቡ የለም ማለት አይደለም፡፡ ምክር ሰጥተን ያልተስተካከሉትን ወደ ምርመራ እናስገባለን፡፡ በምክር ብቻ አይደለም የምንሠራው፤” ብለዋል፡፡
በአንድ ጀንበር ሚሊየነር የሚሆኑትን ወይም ከሀብት በላይ የሚኖሩትን በተመለከተ ጥናት ማድረግ እንደሚጀምሩ ገልጸዋል፡፡

ዘንድሮ በፀደቀው የፓርላማው የአሠራርና ሥነ ሥርዓት ደንብ መሠረት የሥራ አስፈጻሚው አካላት ለሚቀርብላቸው ጥያቄ የሚመልሱት መልስ አላረካኝም የሚል አባል በድጋሚ መጠየቅ የሚችልበትን አሠራር ፈጥሯል፡፡ በዚሁ መሠረት በቅድሚያ እጃቸውን ያወጡ አንድ አባል የቀረበው ጥያቄ ይዘት ትምህርት አታስተምሩ የሚል እንዳልሆነ፣ በተደጋጋሚ ለምን በትምህርት ይታለፋል የሚል ይዘት ያለው መሆኑን በመጠቆም በዚህ መልኩ ጥያቄው እንዲመለስ ጠይቀዋል፡፡

በድጋሚ ዕድል ያገኙት አቶ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው፣ “በሕግ ትምህርት ቤቶች ዘንድ የሚታወቅ አንድ አባባል አለ፡፡ ‘ሕግ አስፈጻሚው ከሕግ አውጪው የበለጠ ሩህሩህ ሊሆን አይችልም’ የሚል፤” በማለት ‹‹ፓርላማው ያፀደቀውን ሕግ ተግብሩ፡፡ ምክር አሁን ከተጀመረው ንቅናቄ ጋር አብሮ አይሄድም፤” ብለዋል፡፡

“ወንጀልን መሞከርና መፈጸም ተመሳሳይ ነው ብሎ ይህ ምክር ቤት ሕግ አውጥቶ ሰጥቷችኋል፡፡ መክሰስ እየቻላችሁ ወደ ምክር የምትወስዱትን ነገር አንቀበልም፡፡ የሞት ሽረት ጉዳይ ማለት ይህ ነው፤” ሲሉም አክለዋል፡፡

በድጋሚ ምላሽ የሰጡት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ “በምርመራ ላይ ያለውን ጉዳይ ለምክር ቤቱ አላቀረብንም እንጂ በምክር የነበሩ ወደ ምርመራ የገቡ አሉ፤” ብለዋል፡፡

“ይህንን የመሰለ የምክር ቤት ድጋፍ እያለና ኅብረተሰቡ ከታች እየደገፈ እያለ ዕርምጃ አለመውሰድ ማለት ሌላ ነገር አለ ማለት ነው፤” በማለት በምክር ማለፉ እንዳለ ሆኖ ዕርምጃ እንደሚወሰድ በመግለጽ በድጋሚ ተቋማቸውን ተከላክለዋል፡፡

የማጠቃለያ አስተያየት የሰጠው ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ ኮሚሽኑ የመልካም አስተዳደር ንቅናቄውን እደግፋለሁ ቢልም፣ የፀረ ሙስና መኮንኖች በየተቋሙ እየተመናመኑ መሆኑን ገልጿል፡፡ “የሚነቃነቅ ሰው ሳይኖር የምን ንቅናቄ አለ?” በማለት ኮሚሽኑ ከምክር ቤቱ የተነሱ ሥጋቶችን እንዲቀርፉ አሳስቧል፡፡
 

/ሪፖርተር
 

ተዛማጅ ዜናዎች:

  ኮሚሽኑ የተሿሚዎችን ሀብት ለሕዝብ ለማሳወቅ የሶፍት ዌር ስምምነት ፈረመ – ለመሆኑ በምኑ ይፋ ለማደርረግ ነበር ለታህሳስ 2012 ቃል የገባው?

  ኮሚሽኑ የተሿሚዎችን ሀብት ለሕዝብ ለማሳወቅ የሶፍት ዌር ስምምነት ፈረመ – ለመሆኑ በምኑ ይፋ ለማደርረግ ነበር ለታህሳስ 2012 ቃል የገባው?India firm to develop Ethiopia’s wealth registration software

  TPLF-led corruption fells big tree: Are investigators making inroads into Meles Zenawi’s inner sanctum – Ringleaders – Azeb & Associates?

  ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የማለበት የባልሥልጣኖች ሃብት ምዝገባ ውጤት ሲገፋበት፡ አዲስ ባለ11-ነጥብ ‘ማኅበራዊ እሴቶች’ ማደናገሪያ ይዞ ሊቀርብ ነው

  የሕወሃት፡ የጸረ-ሙስና ኮምሺንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ለዛ ቢስ ጨዋታ

  ታህሳስ ላይ የባለሥልጣናት ሀብት ከወር በኋላ ይፋ ይሆናል ቢሉም፤ ሶስተኛ ወሩ አልፎም የሪፖርቱ ደብዛ እስካሁን የለም

  State engineered land grab & corruption are alive and well in Ethiopia

  መሬትና መሬት ነክ ቋሚ ንብረቶችን ለመመዝገብ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ – ማንን ለመጥቀም / ለማዘናጋት?

  Benefits of Ethiopia’g growth are passed to corruption, not the poor

  ተንቀሳቃሽ ያልሆኑ ንብረቶችን አዲስ አበባ ዛሬ መመዝገብ ትጀምራለች – ዓላማው መሬት ለዘረፉት በዚሀ ለማዘናጋት? ወይስ የ2015 ሥራ ብዙነት?

  Land ownership draft law being tossed around, perhaps waiting for land grabbers to finish

  US slashes HIV/aids funding to Ethiopia by 79%: Could corruption be the reason?

  Ethiopia’s defense outfits tainted by corruption – secrecy, ethnicity & political loyalty serving as the grease

 

%d bloggers like this: