ሕዝባዊ አመጹ እየተፋፋመ ሳለ የሕወሃትና ቅጥረኞቹ የፕሮፓጋንዳ ስካር መሬት ላይ የሚታየውን የሕዝብ አልገዛም ባይነትና መነሳሳት ሊገታው እንዳልቻለ ሊገነዘቡ አልቻሉም!

19 Feb

በከፍያለው ገብረመድኅን The Ethiopia Observatory (TEO)
 

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም ኦሮሚያ ውስጥ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አመጽ በየደቂቃው ተለዋዋጭ። ነገር ግን የማይለዋወጠው ሕዝቡ መቁረጡንና በተለይም ወጣቱና ገበሬዎች ሕይወታቸውን ለነጻነትና ዲሞክራቲክ መብቶቻቸው መከበር መሥዋዕትነቱን ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸው በግልጽ እያሳዩ ነው።

በዚህ በያዝነው ሣምንት ውስጥ ትልቁ የነውጥ ማዕከል ምዕራብ አርሲና የሻሸመኔ አካባቢዎች ናቸው። ይህ ማለት ሌሎቹ አካባቢውች ዘንድ – ሕወሃት እንደሚቀዣብረው – ሰላም ወርዷል ማለት አይደለም።

 
በቅድሚያ በኦሮሚያ ኔትዎርክ ሚዲያ በኩል የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ሰባት ሰዎች በትላንትናው ዕለት ተገድለዋል፤ አካባቢውም ለሕወሃት አንገዛም ባይነቱን በግልጽ እያሳየ ነው። በኢሣት በኩል የተገኘውም ዜና ይህንኑ አረጋግጧል።

ከግማሽ ሰዓት በፊት የተገኘ ሌላ መረጃ እንደሚያሳየው የሕወሃት አጋዚ ጦር ወጣቶችና ገበሬዎች ላይ ክፍተኛ ጭካኔ በተሞላው መንገድ አፈናው፡ በተናጠልና በቡድን ግድያና ርሸናው ቀጥሏል። በዚህም መሠረት አምቦም አካባቢ በጥይት የተመታው የሶስተኛ ክፍል ተማሪ ኤልያስ አራርሳ እህት፣ ናጋሴ አራርሳ ወንድሟ መመታቱንና መውደቁን አይታ ወደርሱ ስትሮጥ እርሷንም የአጋዚ ጥይት በልቷታል።

በሁሉ8ም አቅጣጫ ዝግ የሆነው የቦቆጂ መንገድhttps://www.facebook.com/Jawarmd/posts/10102133526587413

በሁሉም አቅጣጫ ዝግ የሆነው የቦቆጂ መንገድ https://www.facebook.com/Jawarmd/posts/10102133526587413

ለማንኛውም ሕወሃት ይህንን ሁሉ ግድያ እየፈጸመና ትግሉ እየተፋፋመ ሳለ፡ “በሻሸመኔና አከባቢዋ በፖለቲካ ሽፋን ሕዝብን ለማቃረን የሚፈልጉ ኃይሎች ጥረት በሕዝቡና በፀጥታ ኃይሉ የተቀናጀ ሥራ” ከስሟል ሲል የካቲት 10/2008 መግለጫ ሠጥቷል

ኦሕዴድም በዛሬው ዕለት አለቃው ሕወሃትን ተከትሎ፡ በሚያሳፍር ሁኔታ “ሰሞኑን በምዕራብ አርሲ ዞን በተወሰኑ ወረዳዎች የተፈጠረው ሁከትን አስመልክቱ…ጥፋት ሀይሎች እምነትን ከእምነት እና ብሄርን ከብሄር የሚያጋጭ አጀንዳ ለመጠቀም እየተሯሯጡ እንዳሉ ተጨባጭ የሆነ ምልክት” ታይቷል ይላል። በዚሁ መግለጫውም ለሕዝብ አሳቢና ተቆርቋሪ ይመስል፡ ኦሕዴድ “የሕዝቦች የመዋደድና ተቻችሎ አብሮ የመኖር ባህል ተጠናክሮ ሊቀጥል” እንደሚገባ ተረት ተረቱን ማሰማቱ ጅቡ ከሄደ በኋላ እንደሚጮኸው ውሻ አስመስሎታል።

በሌላ በኩል ደግሞ በሃገሪቱ በአጠቃላይ በአመራር ደረጃ ከፍተኛ ግራ መጋባት ይታያል። ሌላው ቀርቶ ይህ ሁሉ ሕዝባዊ ቁጣ በየአካባቢው እየተካሄደ፡ 41ኛ ዓመቱን ለማክበር የሚዘጋጀው ሕወሃት የካቲት 10/2008 በሠጠው መግለጫ – በፕሮፖጋንዳ ስካር ይመስላል – በሕወሃት ምክንያት የዛሬይቷ ኢትዮጵያ፡ “ብዘሃነትን የተቀበለች ሁሉም ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች እኩል ሃገሬ የሚሏት ኢትዮጵያን በትግላቸውና ድምጻቸው ያቋቋሙት ሥርዓት መፈጠሩን” አሥምሮበታል!

ታዲያ እንዲህ እያለ ሕዝባችንን ከሚጨፈጭፍ ቡድን ምንስ የተሻለ ነገር ይጠበቃል?፣ የሚለው እውነት ክሆነ፣ ቆም ብሎ እንኳ ይህ ሕዝብ በቃኝ ብሎ ለምን ከዳር እስከ ዳር አክ እንትፍ እንደሚለው እንዴት አይጠይቅም!

ሕውሃቶች አበክረው ሊያስቡበት የሚገባው ነገር ሕዝቡን ከመጨፍጨፍ፣ ሃገሪቱን ከማናጋትና ለዘመናት አብሮ የኖረውን የዜጎች ቤተሰባዊነት ለማፍፈርስ ከሞመክርና ደም ከማፋሰስ እንዲቆጠቡ ነው!
 
*Updated.
 

%d bloggers like this: