ስለነገይቱ ዴሞክራሲያዊቷ ኢትዮጵያ የተለያዩ የፖሊሲ ጥያቄዎች ላይ ፕርፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተጨማሪ ማብራሪያ ሠጠ!

19 Feb

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

የካቲት መጀመሪያ ላይ ከ78 ደቂቃ በላይ በፈጀ ገለጻና የጥያቄዎችና መልስ ወቅት፣ አርበኞች ግንቦት7 ኢትዮጵያንና ሕዝብቿን ከሕወሃት ተረክቦ ዲሞክራሲያዊት ሃገር ለመገንባት፥ በጥንቃቄና በሰላም ለማስተዳደር፥ ለማገልገል ስለሚቻልበት ሁኔታ አንኳር በሆኑ ጉዳዮች ላይ ዘርዘር ያለ ማብራሪያ በፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ መሠጠቱ ይታወሳል።

ይህንን በሜሪላንድ አሜሪካ ውስጥ የተካሄደውን ስብሰባ፡ ያልተከታተሉ ዜጎች ቪዲዎውን እዚህ በመጫን ሊያይት ይችላሉ።

የፕሮፌሰሩ ንግግር፡ በተለይም በፖሊሲ ላይ ተመሥርቶ ኅብረ ብሔራዊ በሆነች ሃገር ውስጥ በዲሞክራሲና በእኩልነት ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ጥረት መደረግ አለበት የሚለው አቋም ብዙዎችን የማስደሰቱን ያህል፣ በተወሰኑ ወገኖች ለሥልጣን የሚደረግ ውድድር ተደርጎ አላስፈላጊ አስተያየትን እስከ መሠንዘርና ጥርጥሮችን የመዝራት ሁኔታ ታይቷል።


 
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የፕሮፌሰሩ ንግግር ለሕወሃት ሰዎች መብረቅነቱ የታየው፡ ሃሣቡን ከመዋጋት ይልቅ፣ እጅግ አሳፋሪ በሆነ መንገድ ኤርትራ ውስጥ የበረሃ ኑሮ አልመች ስላለው ከትግሉ ሸሽቶ አሜሪካ ተመልሷል ማለታቸው ነው። እዚያ ላይ ቢያቆሙ ደግሞ ድግ ነበር። እነርሱ ከዚያም ዘልቀው ከምድረ አሜሪካ የትርፍ ሰዓት ትግል ለማካሄድና ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት እየተዘጋጀ ነው ብለው ማሾፋቸው አይዘነጋም!

ደግነቱ ከኢሣት እንደተሰማው ፕሮፌሰር ብርሃኑ የካቲት 10/2008 ከኤርትራ ውጭ ያሉትን ጉዳዮቹን አጠናቆ ወደ በረሃ መመለሱን ተነግሯል። ለነገሩ ትግሎን ከበረሃ ሳይሆን ከአሜሪካ ሊያካሄድ ነው ብለው የተገረሙም ብዙዎች ሊሆኑ ይችላሉ! የመረጃም ጉዳይ ሊሆን ስለሚችል፡ የዚህ አስከፊነት ወይንም አሳፋሪነት አይታየኝም።

የወደፊቱን በሚመለከት፡ እዚህ ኦዲዮ ላይ እንደሚደመጠው፡ በሥልጣን አፋፍ ላይ ሆኖ ዶ/ር ብርሃኑ የዜጎች መብቶች መከበር ጉዳይ ላይ ብዙ ትኩረት የሠጠና የሚሠጥ መሆኑን – ቀደም ሲል እርሱን እንደሚያውቀው ግለሰብ – የሜሪላንድ ንግግሩ፡ ቀጥሎም በኢሣት ቃለ መጠይቁ ማብራራቱ ለኔ ስለነገይቱ ኢትዮጵያ የእኩልነትና ዴሞክራሲያዊ ተስፋ ተጨማሪ እፎይታ ሠጥቶኛል።

በተጨማሪም ፕሮፌሰር ብርሃኑ በደንብ የተማረ ግለሰብ ብቻ ሣይሆን፡ ለወደፊት ኃላፊነቱ ራሱን በደንብ ያዘጋጀ መሆኑና በዚህም ብዙ ሊያድግና ሊጐለብት እንደሚችል አልጠራጠርም። የሜሪላንድ ንግግሩና የሃሣብ ልውውጡ፥ የወደፊቷ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ልትመሠርትበት ስለምትችልበት ሁኔታ አቅጣጫ ጠቋሚና ግለሰቡም ምን ያህል ራሱን ያዘጋጀለት መሆኑን በሚገባ አመላክቷል!

ምናልባትም ኢትዮጵያውያን ራሳችንን ማዘጋጀት ያለብን፣ የኢትዮጵያን ዲሞክራሲ ለመገንባት ዝግጁ ነን የሚሉንን ሰዎች ወደ በትረ ሥልጣኑ መምጣታቸውን መጠባበቅ ብቻ ሳይሆን፡ ትግሉን ከማገዝ ባሻገር፡ ከእንግዲህ ኢትዮጵያውያኖች ደፋር ጥያቄዎችን በሥልጣን ላይ ላሉት/ለሚመጡት ግለሰቦች ማንሳት – ዋጋ የሚያስከፍል ከሆነም ለመክፈል ከሆነ መዘጋጀት ይገባናል። ስላለፉት 42/43 ዓመታት አሰከፊነት መደስኮሩ ዛሬ በደረስንበት ደረጃ ምክንያት ፋይዳ ቢስ ሆኖአል። ሰለሆነም፥ ዛሬም ሆነ ነገ፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን ዛሬውን ማዘጋጀት ያለብን ከባድ ያሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ነው – ምንም እንኳ ከአሁኑ ምን ያህል ብዙ ለእርሱ እናውቅልሃለን በሚሉ ግለሰቦች ቢከበብም!

ለምንድነው ይህንን ያነሳሁት?

ከወታደራዊ መንግሥት እስከ ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ አስተዳደር ሥር ያለፉ ዜጎች ተጠራጣሪ ቢሆኑ ብዙ ሊያስገርም አይገባም። ደርግም “ኢትዮጵያ ትቅደም ያላንዳች ደም” ብሎ ቢቀርብም፡ በኤርትራ ግንባር፡ ሕወሃትና የኢሕአፓ የከተማ ሽብርና የሶማሌ ወረራ በፈጠሩት ግፊቶችና ተጠራጣሪነት ምክንያት፥ ዜጎች በመንግሥት ደረጃ የሚሠነዘርባቸውን ጥቃቶች የመከላከል አቅማቸው ክፉኛ ተሰልቧል። ባለፉት 25 ዓመታትም፡ የሕወሃት ወንበዴዎችም ካለፈው በከፋ ሁኔታ እያንዳንዱን ዜጋ እንደ ቤት አሸከርና ገረድ ወደ ሚያስተዳድሩበት ደረጃ ደርሰናል – በዚህ የተወሰንኩት ከሰሞኑ ጭካኔ የተሞላ የአጋዚ ጭፍጨፋ ወዲህ ብዙም ስለ እሥራት፡ ግርፋትና ሞት ላለማንሳት ፈልጌ ነው!

በዚህም ምክንያት – በታሪካችን እንዳየነው፣ በግል ሕይወቶቻችንም እንደመሰከርነው – ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት ሁሉን ተጋፎቶ – አንድ ግለሰብ ወይንም ጥቂቶች ሽርከኞች ብቻቸውን – ከፍተኛ ባለሥልጣን የመሆኑ ዝንባሌ ጠንካራ በመሆኑ፡ ባለሥልጣኖች መንግሥት የእነርሱን ጥቅምና ምቾት ብቻ ተንከባካቢ ተደርጎ መወሰዱ፣ ወደ ፊትም በዘመነ አርበኞች ግንቦት 7 እንዳይደገም ብዙ ሊታሰብበት ይገባል!

ፕሮፌሰር ብርሃኑ በአሁኑ ንግግሩ በዜጎች መብቶች ላይ ማተኮሩን የወደድኩለት በዚህም ምክንያት ነው!

ፕሮፈሰር ብርሃኑ የሕዝቡ በመሆኑ፡ የሕዝብ ሆኖ እንዲቀጥል ይጠብቅበታል። ሆኖም ይህንን ማረጋገጥ የሚቻለው፥ በፊውዳል ኢትዮጵያ ባህል ውስጥ ከሥልጣንና ከባለሥልጣኖች ጋር የነበረንና ያለን ግንኝነት ወደፊት እንድትመሠርት ለምንፈልጋት ነጻይቷ ኢትዮጵያ መሠናክል ሊሆን የሚችለው፥ ፕሮፌሰር ብርሃኑን ቀስ በቀስ መጀመሪያ በደህንነት ስም ቀጥሎ በፕሮቶኮል ተሸክፎ ከሕዝቡ እንዲርቅ ሲደረግ ነው። ከፕሮፌሰርነቱ፥ ባለቤቱንና ልጆቹን ተለይቶ ለትግል ወደ በረሃ መውረዱ ሲታሰብ እርሱ የዚህ ዐይነት ዓላማም ሆነ ፍላጎት የሌለው መሆኑ ገሃድ ነው!

ዶ/ር ብርሃኑ የሚኖርበት የደህንነት ጥንቃቄ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ፡ ተንከባካቢዎቹ – ጋዜጠኞችን ጨምሮ – በተለያየ መልኩ ከዝሕቡ እንዳያርቁት እሠጋለሁ! ከላይ እንደጠቀስኩት፥ የኢትዮጵያ መንግሥታዊ አስተዳደር ባህል መሪውን ከጠላት ብቻ ሳይሆን ከንፋስና ከፀሐይ ጭምር የመከላከሉ አዝማሚያ ወደዚያ አስከፊ ሁኔታ መሸጋገሪያ እንዳይሆን በሩቅ ለመያዝ ከወዲሁ ለማስታወስ ነው።

ሰዎች ሰዎችን መልዓክ ወይንም ሠይጣን የማድረግ ችሎታ አንዳለን በማስታወስ፥ ጥቂቶች ለራሳቸው ሰሜት መርካት፡ ይህንን የኢትዮጵያን ተስፋ በታሪካችን እንዳየናቸውና እንዳወቅናቸው መሪዎች እንዳያወርዱት ከወዲሁ ማየትና መጠንቀቅ አስፈላጊ ነው!
 

%d bloggers like this: