በአዲስ አበባ የታክሲዎች የሥራ ማቆም አድማ!                     Addis Abeba taxis strike!

29 Feb

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

 

የሕወሃት አስተዳደር ችግሩን ለማስተንፈስ፡ ታክሲ አሽከርካሪዎችን ያስቆጣውን አዲስ ሕግ ማዘግየቱን ዛሬ ገልጿል። የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ለኢዜአ እንዳስታወቀው የደንቡ ትግበራ የተራዘመው ከአዲስ አበባ ታክሲዎች ማህበራትና ከአሽከርካሪዎች በቀረበ ጥያቄና ያልተሟሉ ጉዳዮች በመኖራቸው ነው።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ኃይለማርያም እንዳስታወቁት ደንቡ ለጊዜው እንዳይተገበር ተወስኗል። የደንቡ ትግበራ የዘገየው ከማህበራቱና የሚመለከታቸው አካላት ጋር በተካሄደ ውይይት ለአሽከርካሪዎች ማብራሪያ መስጠት በማስፈለጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለሥልጣኑም በተለይ በአዲስ አበባ ምቹ ያልሆኑ የታክሲ ማቆሚያ ቦታዎችን እንደሚያስተካክልም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። ደንቡ በአሽከርካሪዎች ጥፋት የሚደርሱ አደጋዎችን ለመቀነስ ሚና እንደሚኖረው የታመነበት ሲሆን፣ በስድስት እርከኖች የተከፋፈሉ የጥፋት ዝርዝሮችን አካቷል።

በእያንዳንዱ እርከን ስር የተዘረዘሩ ጥፋቶች እስከ ሰባት ነጥብ የሚያዝባቸው ሲሆን፣ አሽከርካሪዎች በደንቡ ላይ የተቀመጠውን እስከ 21 የጥፋት ነጥብ ጣሪያ ሲደርሱም ፈቃዳቸው ይሰረዛል።

በደንቡ ፈቃድ የተሰረዘበት አሽከርካሪ ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ አዲስ ፈቃድ እንዲያወጣ ያስገድዳል።

ማህበራቱ ደንቡ በከተማዋ ያለውን የትራፊክ አደጋ በመቀነስ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ቢያምኑበትም፣ የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘቡና መሻሻል ያለባቸው ነጥቦች መኖራቸውን ይናገራሉ። በዚህም ደንቡን ለመተግበር የሚስተካከሉ ጉዳዮች ማየትና የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ማስገባት ይገባል ባይ ናቸው።

ካልሆነ ግን በጥቂት ቀናት ውስጥ በሶሰት ጊዜ ቅጣት ብቻ የቅጣት ጣሪያው ላይ የሚደርሱና መንጃ ፈቃዳቸውን ተነጥቀው ሥራ የሚያቆሙ አሽከርካሪዎች ሊበረክቱ ይችላሉ ይላሉ። ማህበራቱ በተሰጠው ጊዜ የታክሲ አሽከረካሪዎች በአሰራሩ ላይ ግንዛቤ በመያዝ ከጥፋት ታቅበው ለመስራት እንደሚያስችላቸው ሰብሳቢው ተናግረዋል።

በኢፌዴሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው ደንብ 208/2003 የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ደንብ በትራንስፖርት ዘርፍ ባሉት ችግሮች ሳቢያ ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል። ደንቡ ከየካቲት 7/2008 አንስቶ መተግበር ጀምሮ ነበር።

በአገሪቱ ባለፈው በጀት ዓመት 3 ሺህ 800 ያህል ሰዎች ህይወት በትራፊክ አደጋ አልፏል። ከ11 ሺህ በላይ ሰዎች ለከባድና ቀላል አካል ጉዳት የተዳረጉ ሲሆን፣ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረትም መውደሙን መረጃዎች ያመለክታሉ።

===============

ከዚሁ ጋር በተያያዘ፡ የሕወሃት ዜና ምንጭ ፋና እንደዘገበው፡ በአዲስ አበባ ከአሽከርካሪዎች የስነ ምግባር ደንብ ጋር ተያይዞ በተነሱ ቅሬታዎች ትግበራው ለሶስት ወራት እንዲራዘም የተደረገ ቢሆንም አንዳንድ ባለታክሲዎች አገልግሎቱን አቋርጠዋል ይላል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የታክሲ ባለንብረት ማህበራት፥ ደንቡ ወደስራ ሲገባ በርካታ የታክሲ ባለንብረቶች ቅሬታ በማቅረባቸው ጥያቄያችንን ለመንግስት አቅርበን ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 19 2008 በከፊል መፍትሄ አግኝተናል ብለዋል።

መንግስት በደንቡ ላይ ሰፊ ግንዛቤ ለመፍጠር እንዲቻል እና መግባባት ላይ ለመድረስ ደንቡ የትግበራ ጊዜው ለሶስት ወራት እንዲራዘም ማድረጉን ነው ማህበራቱ የገለፁት።

ይሁን እንጂ ዛሬ ጠዋት አንዳንድ የታክሲ ባለንብረቶች የታክሲ ማቆም አድማ በማደረግ አገልግሎት ማቋረጣቸውን አንስተዋል።

የደንቡ ትግበራ ለሶስት ወራት መራዘሙን የሰሙ ባለታክሲዎች ግን ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቅሰው፥ ጥቂት የታክሲ ባለንብረቶች ግን የስራ ማቆም አድማ አድርገዋል፤ ይህም ከእኛ እውቅና ውጭ ነው ብለዋል ማህበራቱ።

ጥቂት ባለታክሲዎች ጠዋት ላይ ወደ ስራ ለመግባት የሞከሩ ባለ ታክሲዎችንም በማስፈራራት እና የተለያዩ ወረቀቶችን በመበተን የታክሲ ማቆም አደማውን እንዲቀላቀሉ ሲያደርጉ እንደነበርና እነዚህን አካላትም ወደሚመለከተው አካል ለማቅረብ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ችግሩን ካስተዋልን በኋላ የታክሲ ባለንብረቶችን በስልክ እና በአካል እየሄድን የደንቡ ትግበራ ለሶስት ወራት መራዘሙን በመንገር ያቋረጡትን አገልግሎት እንዲጀምሩ እያደረግን ነውም ብለዋል።

አገልግሎት በማይሰጡ የታክሲ ባለንብረቶች ላይ ግን እንደየ ማህበራቱ ህግና ደንብ እርምጃ እንደሚወስዱም አመላክተዋል።

ለመንግስት ያቀረብነው ቅሬታ በከፊል ምላሽ አግኝቷል ያሉት የታክሲ ባለንብረት ማህበራቱ፥ ጥያቄዎቻችን በህጋዊ አግባብ እንጂ ስራ በማቆም አይፈታም ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የአዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ በበኩሉ፥ ጥያቄያቸውን ሊያነሱ የሚገባቸው አገልግሎቱን በማቋረጥ ስላልሆነ ከአሁን ጀምሮ ሁሉም ባለታክሲ አገልግሎት ለመስጠት እንዲወጣ አሳስቧል።
 

%d bloggers like this: