ሕወሃት በጋምቤላ የግብርና ኢኮኖሚ ዞን ማቋቋም ስላቀደ፥ ከተወላጆቹ ተነጥቆ ለሕዋታዊ የመሬት ዘራፊዎች የተሠጡት መሬቶችን መወሰድ በመቃወም 31 ግለሰቦች አቤቱታ አሰሙ! የተወላጆቹንስ ቤት ንብረታቸው መፍረስ አቤቱታ ሠሚ ማን ይሆን?

6 Mar

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

  ይሄማ ቅጽበታዊ ፍትህ ነው የሚባለው!

  መለስ ዜናዊ መቃብሩ አይመቸውና፣ ከንፈሩን እያጣመመ ነበር በኢትዮጵያ መሬት ዘረፋ የለም ሲል በሕንድ ITMN ቴሌቪዥን ላይ በሰኔ ወር 2011 ከVickram Bahl ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ የተውረገረገው! ይህንን የወቀሱ ግለሰቦችን – የዚህን ዓምድ አዘጋጅ ጭምር – ብዙ ሊያውቁ ሲገባቸው፡ ምንም ሳይውቁ የቀሩ ብሎን እንደተቸን አስታውሳለሁ! ደግነቱ እኛ ልክ ሆን!

  እርሱ ከነስህተቱ እንጦርጦሮስ ወረደ!

  ይኸው ዛሬ እንደምናየው፣ አንዳንዶቹ የሕወሃት ጋምቤላ ሠፋሪዎች እንደ ተመኙት ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ገፍትረው አልከበሩም። ሰዓቱንና ደቂቃዋን ቆጥራ ፍትህ እነርሱ በዘረፋ ለመክበር ያደረጉትን ጥረት ክርፋት ደፍታበት – ሕወሃት ሃሣቡን ሲቀይር ለግለሰቦች ንብረት ኃላፊነት ሳይሰማው – ዛሬ የትናንትናዎቹ ዘራፊዎች በራሱ በሕወሃት ተዘራፊ ለመሆን በቅተዋል! ለዚያውም እነርሱ በቀደምቱ መሬት ባለቤቶች ላይ የተፈጸመው ወንጀልና ግፍ አልደረሰባቸውም!

  ለነገሩ ሕወሃት ለራሱ አስተዳደር በኤክኖሚና ፖለቲካ መጠናከር ያስላው ባዕዳንና የራሱን ሰዎች ብድርና ሌሎችም ዕርዳታ እየሰጠ የገነባው የቅኝ ገዥነት ሠፈራ ነበር፤ ዛሬም አሉ እነርሱም እንዳለፉት ናቸው – የቀደምት ተዘራፊዎቹ ጥይቄ መልስ እስካላገኘ ድረስ!

  በወቅቱ በዚህ ጉዳይ ላይ መለስን ራሱን በመጥቀስ ያሠፈርኩት ባለሶስት ክፍል አርቲክል በተለይም ዲክቴተሩ “No land grab in Ethiopia — Not today, not tomorrow!” ያለበት አመለካከቱን በትክክል የዘገብኩበትና በኋላም በአጥፌነቱ ብዙ ተጠቃሽ የሆኑት አመለካከቶቹ: Part I, Part II እና Part IIIእነዚህ ውስጥ ይገኛሉ፡፡


   

  ታዲያ እነ አቶ ጌታቸው ጀንበሩና ኪሮስ በርሔ እነርሱ ከቀደምቱ የመሬቱ ባለቤቶች በተለየና የበለጠ መብት ያላቸው ይመስል፣ 31 መሬት ተዘረፍን ባዮችን በመወከል ያቀረቡት አቤቱታ ማተኮር ያለበት በመንግሥት የፖሊሲ ብልሹነት ላይ ነው። ይህን ካደረጉ፡ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ ተጨማሪ ግፍ እንዳይፈጸም ለመከላከል ይረዳሉ።

  ከሕግ አንጻር፣ መንግሥት ለኅብረተሰብ ጥቅም የተያዘ መሬትን ከነግንባታው ተገቢውን የገበያ ዋጋ ከፍሎ ባለይዞታቸውን ሊያስነሳ ይችላል – ይህ ሕግ አባዛኛው ሃገሮች ውስጥ ተፈጻሚነት ያለው The Law of Eminent Domain ይባላል፡፡ ሕግ ባለባቸው ሃገሮች ለመንግሥታትም ቢሆን ይህ ካዲላካቸው እንደልብ የሚነዱበት አውራ ጎዳና አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

  መጸሐፉ እንደሚለው ዛሬ አቶ ኪሮስ በርሔና አቶ ጌታቸው ጀንነበሩ በራሳቸው ላይ እንዳይደርግ የማይፈልጉትን በሌሎች ላይ ሲፈጸሙ ትከሻቸውን ግማሽ እስክስታ ገፍትረው ማለፍ እንደማይችሉ ሊገነዘቡ ይገባል!

  ዛሬ እነርሱ እንደፈለጉ ቢሆንላቸውም፣ በሕወሃት አስተዳደር ላይ ቂም ያለው ሁሉ የሚሰማውን ሊያደርግ ይችላል። ሌሎች ደግሞ ሕግነ መከታ በማድረግ እነርሱ ዓለም ሰላም ነው ብለው መዝናናት ሲጀመሩ፡ ወንጀለኝነታቸውን መዞ ሊያወጣው ይችላል! ለዚህ ነው ዛሬ በዘር ፖለቲካ መሳከርና በጥጋብ ካለኛ በስተቀር የለም የሚሉ ሁሉ መግቢያ ቀዳዳ የሚያጡበት ቀን ሊመጣ ይችላል!

  ለነገሩ ለወደፊቱም፡ የሕወሃት አስተዳደር ስግብግብነት በየትኛውም ጀምበር ሕግን ከመስበር እንደሚያግደው አልጠራጠርም!

  ለዚህ ነው እነአርከበ ዕቁባይ ለመሬት ዘረፋቸው አንዴ የኢኮኖሚ ዞን ሌላ ጊዜ ደግሞ – ጋምቤላ እንደተደረገው – ልዩ የኤኮኖሚ ዞን፣ እንዲሁም ኢንዱስትሪያል ፓርክ በማለት ለሕዝቡ መብት ደንታ ሳይሰጣቸው፡ ሕግን በጣሰ መንገድ፡ ባሕር ዳር፡ ሃዋሣ፡ መቀሌና ወዘተ ለማስፋፋት መንፈራገጣቸውን አጥብቀን የምንቃወመው፡፡

  በጽንሰ ሃሣብ ደረጃ፡ እነዚህ እርምጃዎች ጠቃሚ መሆናቸውን በጠቅላላ አንቅረን በመትፋት ሳይሆን፣ ሕወሃት በሚወስዳቸው ማናቸውም እርምጃዎች ላይ አመኔታ ስለሌን መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል!

=============
 

በጋምቤላ ክልል የሚያለሙት የእርሻ መሬት የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ለመገንባት ላቀደው የኢኮኖሚ ዞን እንዲለቁ የተወሰነባቸው ኢንቨስተሮች፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አቤቱታ አቀረቡ

የክልሎችን ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች በውክልና ተረክቦ እንዲያስተዳድር የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን የሰጠው የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ በአገሪቱ የተለያዩ አግሮ ኢኮሎጂ አካባቢዎች የግብርና ኢኮኖሚ ዞን የማቋቋም ዕቅድ አለው፡፡

ሚኒስቴሩ በሚያቋቁመው ኢኮኖሚ ዞን ሰፋፊ ሜካናይዝድ እርሻዎችን ለሚያካሂዱ ግዙፍ ኢንቨስተሮች መሬት በሊዝ የማከፋፈል ዕቅድ ይዟል፡፡ የኢኮኖሚ ዞኑ የመስኖ ግድቦች፣ መንገዶች፣ የኤሌክትሪክና የቴሌኮም አውታሮች ተሟልተውለት ለኢንቨስተሮች የሚቀርብ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በዚህ መነሻ በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ አኩላ ቀበሌና ጎግ ወረዳዎች ውስጥ ከአኩላ ወንዝ እስከ ኪሎ ወንዝ ድረስ የሚገኝ 1.2 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የማልማት ዕቅድ ተይዟል፡፡

ነገር ግን ይህ ዕቅድ ተግባራዊ በሚሆንበት መሬት ላይ ቀደም ብለው የእርሻ ሥራ ውስጥ የገቡ ወደ መቶ የሚጠጉ ኢንቨስተሮች እንዲነሱ ተወስኗል፡፡

በተለይ በአኩላ ቀበሌ የሚፈናቀሉ 31 ኢንቨስተሮች በተወካዮቻቸው አማካይነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት አቤቱታ፣ አሠራሩ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና ሕገወጥ መሆኑን በመግለጽ ቅሬታቸውን በጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

“31 በላይ የምንሆን ባለሀብቶች የመንግሥት ፖሊሲና ጥሪ በመቀበል በጋምቤላ ክልል በአኙዋ ዞን በዲማ ወረዳ አኩላ ቀበሌ፣ የክልሉን የኢንቨስትመንት መሥፈርቶች አሟልተን በዲማ ወረዳ ኢንቨስትመንት ቦርድ ሦስት ወራት የፈጀ ጥናት አድርጎ፣ ቦታዎቹ ከማንኛውም ይዞታ ነፃ የሆኑና በክልል ደረጃ ሊለሙ የሚችሉ መሆኑን አረጋግጦ፣ ታኅሳስ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. መሬቱን አስረክቦናል፤›› በማለት የኢንቨስተሮቹ አቤቱታ ይገልጻል፡፡ ‹‹በዚህ መሠረት ክልሉ ጋር ለ50 ዓመታት የሚቆይ ሕጋዊ ውል በማሰር የመሬት ግብር አስቀድመን በመክፈል በፍትሕ ቢሮ በማፀደቅ ሕጋዊ ካርታ በመውሰድ ወደ ሥራ ገብተናል፤›› በማለት የሚተነትነው የቅሬታ አቅራቢዎች ደብዳቤ 65 ኪሎ ሜትር መንገድ በመጥረግ፣ የአኩላ ወንዝ ላይ 20 ሜትር ርዝመት ያለው ድልድይ በመገንባትና ካምፕ በመቆርቆር የእርሻ መሬት ዝግጅት መከናወኑን ይገልጻል፡፡

ለእነዚህ ሥራዎች በርካታ ሚሊዮን ብሮች ማውጣታቸውን ኢንቨስተሮቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስገቡት ደብዳቤ ያመለክታል፡፡

ነገር ግን የዲማ ወረዳ አስተዳደር በጻፈላቸው ደብዳቤ የተሰጣቸው መሬት የፌዴራል ኢኮኖሚ ዞን ክልል በመሆኑ፣ ከተሰጣቸው መሬት ላይ እንዲነሱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ለተነሽዎቹ ተለዋጭ ቦታ እንደሚሰጣቸው ወረዳው የጻፈው ደብዳቤ ጨምሮ ገልጿል፡፡

ለጎግ ወረዳ ኢንቨስተሮችም ተመሳሳይ ደብዳቤ ባለፈው የካቲት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. መጻፉ ተገልጿል፡፡ የ31 ተፈናቃዮች ተወካይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ጀንበሩና አቶ ኪሮስ በርሔ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በእርሻ መሬታቸው ላይ በርካታ ገንዘብ አውጥተዋል፡፡ መንግሥትን አምነው ያፈሰሱት ሀብት መና ሊቀር እንደማይገባ፣ በኢኮኖሚ ዞኑ ሊመረት የሚችለውን ምርት ማምረት የሚችሉ በመሆኑ መንግሥት ጉዳዩን በአንክሮ እንዲመለከተው ጠይቀዋል፡፡

“ለ50 ዓመታት በሕግ የያዝነውን መሬት በወረዳ አስተዳደር ደብዳቤ እንድንለቅ መደረጉ ፈጽሞ ሕገወጥ ከመሆኑም ባሻገር፣ የአገሪቱን የኢንቨስትመንት ሕግና የፍትሐ ብሔር ሕጎች ያላገናዘበ፣ ከክልሉ ጋር ከተዋዋልነው ውል ጋር ፈጽሞ ተቃራኒ የሆነ፣ የሞራል ክስረትን ግምት ውስጥ ያላስገባ ከፍተኛ ግፍ ነው፤” በማለት ባለሀብቶቹ ባቀረቡት የቅሬታ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍትሕ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል፡፡

ነገር ግን ባለሀብቶቹ ለልማት እያዘጋጁት ያለው መሬት ቀደም ሲል በፌዴራል መንግሥት ለኢኮኖሚ ዞን የተከለለ ሆኖ ሳለ፣ በስህተት የክልሉ መንግሥት እንደሰጣቸው የፌዴራል መንግሥት ምንጮች ይናገራሉ፡፡ በዚህ ስህተት ምክንያት ችግሩ ተፈጥሯል፡፡ ያለው አማራጭ በሚሰጣቸው ተለዋጭ ቦታ ላይ ሥራቸውን መቀጠል ነው ተብሏል፡፡ ባለሀብቶቹ ግን ካፒታላቸውን ያፈሰሱበትን መሬት ካጡ በኋላ፣ እንዴት ሆነው ዳግም ወደ አዲስ ሥራ መመለስ እንደሚችሉ ግራ እንደገባቸው አስረድተዋል፡፡
/ሪፖርተር
 

%d bloggers like this: