አዳማ ከተማ ነዋሪዎች፥ ዩኒቨርሲቲዋ፥ መምህራንና ተማሪዎቹዋ እየታፈሱና እየተደበደቡ በመዋከብ ላይ ናቸው!

21 Mar

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

ባለፈው ምሽት አዳማ በችግር ማሳለፏን ተገንዝበናል፡፡ ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ ብሎክ 347 እና 366 50 ተማሪዎች በአጋዚ ሠራዊት በግፊትና ማንገላታት ተወስደው መታሠራቸው በሶሻል ሚዲያ ተመዝግቧል፡፡

ይህም ቁጥር ባለፈው ሣምንት በተመሳሳይ መንገድ ተውስደው እስከዛሬ ክስ ያልተመሠረተባቸውን ሌሎች 27ቱን የዩኒቨርሲቲው ተማሪዊች እይጨምርም፡፡

አዲስ አድማስ ከሰሞኑ እንደዘገበው፣ በአዳማ ዩኒቨርሲቲ በርካታ አመታት ሲያገለግል የነበረ ጀኔሬተር ፈንድቶ የእሳት ቃጠሎ እንደተነሳና በተለያዩ ክፍሎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ ተናግረዋል፡፡

ኣጋዚ በፈጠረው ሽብርና በከተማዋ በተፈጠረው አለመጋጋት ስጋት እንዳደረባቸው ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፤ ተማሪዎች ተደናግጠው ትምህርት እንደ ተቋረጠና አንዳንዶቹ ግቢውን ለቀው ወደ የመጡበት አካባቢ መሄዳቸውን ለጋዜጣው ገልፀዋል፡፡

የሕወሃቶች ክፋትና ወንጀል በዚህ ብቻ እይቆምም!

ከላይ በተጠቀሱት ክስተቶች ሳቢያ አለመረጋጋትና ስጋት ጋር ተዳምሮ፣ በዩኒቨርሲቲው አቅራቢያ በሚገኘው 10 ቀበሌዎች ተጨማሪ ህገ ወጥ ቤቶችን ለማፍረስ ተወስኗል ብለዋል የአዲስ አድማስ ምንጮች፡፡ በሰባት ቀናት ውስጥ ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው የተናገሩ ነዋሪዎች፤ በሰባተኛው ቀን አፍራሽ ግብረ ሃይል መጥቶ ቤቶችን እንደሚያፈርስ ተነግሮናል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ኩሽነን እና ቀበሌ 03 በተሰኙ ቦታዎች፣ ህገወጥ ናቸው የተባሉ ‘የጨረቃ ቤቶችን’ ለማፍረስ በተጀመረ ዘመቻ፣ ከነዋሪዎች ጋር ግጭት ተፈጥሯል፡፡ ከ250 በላይ ቤቶች እንደፈረሱ ምንጮች የገለፁ ሲሆን፤ ነዋሪዎች ከፖሊስና ከአፍራሽ ግብረ ሃይል አባላት ጋር ተጋጭተው በዜጎች ላይ ጉዳት የደረሰ መሆኑን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

የኦሮሞች አመጽ መቀጣጠል እንደጀመረ – በመደናገጥ ነው መሰል – ሕወሃት መተኪያ መሬትና ቤት ሳልሰጥ ሁለተኛ ዜጎችን አላፈናቅልም ያለውን ቃል በማጠፍ፥ የሰባት ቀን ማስጠንቀቂያ በመስጠት መሄጃ የሌካቸውን ዜጎች በማፈናቀል መኖሪያዎቻቸውን ለራሱ ጎጥ ሰዎች እንዲያለሙት ለመስጠት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያውያን በዚህ የዜግነት መብቶቻችውን በጎጠኛ የወንበዴ ቡድን መገፈፍና ፍትህን በማጣት ምክንያት ጠላታቸውን በማንኛውም መንገድ ለማስወገድ ቢሹ ስህተቱ፥ ጥፋቱ፥ ኃጢአቱና ወንጀሉ ምን ላይ ነው?
 

ተዛማጅ:

https://ethiopiaobservatory.com/2016/01/28/ሕወሃት-መሬት-ዘረፋውን-እንደሚቀጥል-ዛሬ/
 

%d bloggers like this: