የፖሊስ ኮሚሽንን ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው ማድረጉ የሕወሃት ዓላማ የ2005ን ጭፍጨፋ በመድገም ለተቆጣ ሕዝብ ማስፈራሪያነት መሆኑ አያጠራጥርም

22 Mar

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)

የሕወሃት ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነት ለጊዜው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ መቅረቡን ፋና በዛሬው ዕለት ዘግቦታል። የዚህም ዓላም አንድና አንድ ብቻ ነው:

ዲክታተር መለስ ዜናዊም በ2005 ሕወሃት ባጭበረበረው ምርጫ ማግሥት ያደረገውም ይኽው ስለነበር ያንኑ ‘የድል ፈለግ’ ለመከተል የተወሰደ እርምጃ ነው። ወንድ ሴት ሳይባል አያሌ ወገኖቻችንን አጋዚ በብሩህ ጸሃይ መረሸኑና መጭፍጨፉ ይታወሳል!

አሁንም በኦሮሚያ ሕወሃት ያሠማራው ኮማንድ ፖስት ሲካሄድ የከረመውን ተቃውሞና ሕዝባዊ አመጽ ሊያኮላሸው ስላልቻለና ተቃውሞው መቀጠሉ ብቻ ሳይሆን፡ ወደ ሌሎችም አካባቢዎች በመዛመቱ፡ ሕወሃት ግልጽ በሆነ መንገድ ይህንን የተቀጣጠለበትን ተቃውሞ ለማብረድ አያሌ ወገኖቻችን ለማረድ መዘገጀቱን አመላካች እርምጃ ነው!

ኢትዮጵያውያን በሊቢያ የታረዱትን ወንድሞቻቸውን በማሰብ ባደረጉት ሠልፍ ላይ የአጋዚ ራምቦ የሕወሃትን ዘላለማዊነት ለማረጋገጥ በዜጎች ላይ ጥቃት ሲፈጽም(Foto Negere Ethiopia).

ኢትዮጵያውያን በሊቢያ የታረዱትን ወንድሞቻቸውን በማሰብ ባደረጉት ሠልፍ ላይ የአጋዚ ራምቦ የሕወሃትን ዘላለማዊነት ለማረጋገጥ በዜጎች ላይ ጥቃት ሲፈጽም(Foto Negere Ethiopia).

ዓላማው ይህ መሆኑ እንዳይታወቅበትም፥ በጥናት ላይ ተመስርቶ እስከሚወሰን ድረስ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆን ዜናው ለፓርላማው የቀረበው ረቂቅ አዋጁ ያመለክታል ይላል።

ይህ ዕውነት ከሆነ፡ ጥናቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ የፖሊስ ኮሚሽን ባለበት ለጥቂት ወራት መቆየቱ ለምንም አማራጭ አልሆነም? ችግሩ ምንድነው? ከላይ እንደተጠቀስው፥ የዚህ ጥድፊያ ኢትዮጵያውያን በተለይም በኦሮሚያ፡ ኦሞ ሸለቆና ጎንደር ውስጥ የሕዝብ ቁጣና አመፍጽ በመጠናከሩ፡ እንደተለመደው ዜጎችን ለማረድ መሆኑን ማንም ሊጠራጠር አይገባውም!

ከታሪክ እንደምንማረው – ነገር ግን ሕወሃት ሊገነዘብ ያልቻለው ነገር – በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዘረኛው ወገን ረግጬ ገዛሃለሁ፣ ንብረትህንም እንደፈለግሁት ዘርፍሃለሁ ሲል እሽ ያላለውን ሁሉ አርዳለሁ ማለቱ ስለሆነ፣ ዓለም አቀፍ ኅብረተሰብም የኢትዮጵያን ሕዝብ ሊታደግ ግዴታ አለበት!

ኃይል ግን ለእንደዚህ ዐይነቱ ሕዝባዊ ተቃውሞ መፍትሄ ሊያስገኝ እንደማይችል ሕወሃትም ሆነ መጋቢዎቹ ሊገነዘቡ ይገባል!
===========
 

የሕወሃት የመረጃ ምንጭ የሆነው ፋና ዛሬ እንደዘገበው፡ ሙሉውን ዜና ከዚህ በታች ይመልከቱ፦

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነት ለጊዜው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን ረቂቅ አዋጅ ቀረበ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 13 ፣ 2008 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል አስፈጻሚ አካላት ማቋቋሚያ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።

ረቂቅ አዋጁ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ተጠሪነታቸው ከፌደራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳይ ሚኒስቴር ስር እንዲወጣ የሚያደርግ ነው።

በጥናት ላይ ተመስርቶ እስከሚወሰን ድረስ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆን በረቂቅ አዋጁ ተገልጿል።

የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ራሱን ችሎ በፌደራል ደረጃ እንዲቋቋም የሚያደርግም ነው።

ይህም በአዋጅ ለፍትህ ሚኒስቴር ተሰጥቶት የነበረውን በአንቀጽ 16 የተጠቀሰው ስልጣንና ተግባርም ለሚቋቋመው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ እንዲሆን ያደርጋል።

የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽንም ተጠሪነቱ በቀጣይ ለሚቋቋመው የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ እንደሚሆን ነው በረቂቅ አዋጁ የተገለጸው።

በክልሎች አካባቢ እንዲሁም በሃይማኖት ተቋማት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ጨምሮ የሚከሰቱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የፌደራል እና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ተግባራት ናቸው።

ይሁን እንጅ የፌደራል ፖሊስ እና የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ተጠሪነታቸው ለሚኒስቴሩ የተሰጠ ነበር።

ከዚህ አንጻር ተቋማቱ የሚያከናውኑት ተግባር እና ከሚኒስቴሩ ጋር ያላቸው የተግባር ትስስር የጠበቀ ባለመሆኑ፥ ሁለቱ ተቋማት ተጠሪነታቸው አግባብነት ላለው አስፈጻሚ አካል ወይም ተቋም እንዲተላለፍ በመንግስት ታምኖበታል።

ይህን ተከትሎም በዛሬው እለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌደራል አስፈጻሚ አካላትን ለማቋቋም የተዘጋጀውን ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅን ጨምሮ ተዛማጅነት ያላቸው አራት ረቂቅ አዋጆችን ተመልከቷል።

የፌደራል ፖሊስም የሃገርን ደህንነት በማስጠበቅ የሽብር ወንጀልን እየተከላከለ በመሆኑ እያከናወነ ያለው ተግባር ተጠንቶ እስከሚወሰን ድረስ ተጠሪነቱ እንዲቀየር ተደርጓል።

የተቋማቱ ተጠሪነታቸው መቀየር እየተሰራ ያለውን ስራ ለማቀላጠፍ እንደሚያግዝ ነው የተገለጸው።

ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጆቹ ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር እይታ ለህግ ፍትህ እና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።
 

%d bloggers like this: