የአባገዳና የሕወሃት ድርድር እስከ ምን ድረስ? ሕወሃት እያዳመጠ፣ወይንስ ጊዜ እየገዛ?

23 Mar

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)
 

ሕወሃት በየጊዜው ራሱን ጻድቅ አድርጎ መቀባጠሩን እንዲያቆምና የኦሮሞ አባገዳ ምክር ቤት የሠጠው የየካቲቱን ማስጠንቀቂያ (Ultimatum) ተግባራዊ እንዲያደርግ፥ ይህ ገጽ የካቲት 26/2016 ዓ.ም.ያወጣው መግለጫ ይታወሳል። በወቅቱ ያለተመለከቱት እንዲመለከቱት ጽሁፉን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

አባገዳ የካቲት 25/2016 ባቀረባቸው ጥያቄዎች መካከል በሕወሃት ሠራዊት በተለይም በአጋዚ የሚፈጸመው የኦሮሞች ግድያ፡ አፈናና ማሠቃየቱ እንዲቆም፣ ካሣም ለሞቱትና ለተደመሰሱት ንብረቶች እንዲከፈል የሚሉት ይገኙበት እንደነበር ተዘግቧል። ከሰሞኑ ደግሞ የካሣ ክፍያው ጉዳይ የሕወሃት ማደናገሪያ እንጂ ከመጅመሪያውም አልነበረበትም በማለት ከመጀመሪያው ዘግበው የነበሩ ግለሰቦችም መጻፍ ጀምረዋል።

ጥይቄዎቹ ላይ ተመሥርቶ ይህንን ለሕወሃት ለማሳሰብ ይህ ገጽ የፈለገበት ምክንያት ዝርዝር ጥያቄዎቻቸውን በማወቅ ሳይሆን፡ ለኦሮሞ ኅብረተሰብ ካለባቸው ኃላፊነት በመነሳት በመሆኑ፡ እነዚህ ተግባራዊ ቢሆኑ፡ ሃገሪቷ ከተዘፈቀችበት የፖለቲካ፡ የኤኮኖሚ፡ ድርቅና እንዲሁም ስብዓዊ ችግሮች ብዙ ጉዳቶች ከመድረሳቸው በፊት ለመላቀቅ፥ ይልቁንስ ግንባሩ እንዚህን ተግባራዊ ቢያደርግ ተመራጭ መሆኑን በመገንዘብ ነው።

በጥር ወር 2016 የአባ ገዳ አባሎች በኦሮሚያ የተከሰተው ደም ማፍሰስ አሳስቧቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየውን ለማነጋገር ቢጠይቁም፡ በሩ እንደተዘጋባቸው ልብ ሊባል ይገባል። ምናልባትም ተወካያቸው ከሕወሃት ፈቃድ ስላላገኘ ሊሆን ይችላል። ሕወሃትም – አልሆነለትም እንጂ – በጀብደኝነት ችግሩን በጠብ መንጃ አስተነፍሰዋለሁ ብሎ በስህተት ገምቶም ሊሆን ይችላል!

እምቢታውም በወቅቱ እንደዘገብነው፡ ተመልሰው ሄደው መተኛት ሳይሆን አባገዳ በኦሮሚያ የሚፈጸውን ወጀል አውግዘው፡ የኦሮሞ ፖለቲካ እሥረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱና የሕውሃት ወራሪ ጦርም ከአካባቢው እንዲወጣ ጠይቀው ነበር።

ለማንኛውም፡ የኦሮሚያ ችግር አሁን እንደሚታየው በተለያየ መልኩ መቀጠል ብቻ ሳይሆን፡ ታፍነው፡ ተርግጠው ለሚዘረፉት ኢትዮጵያውያን ሁሉ መነቃቃት እየፈጠረ በመምጣቱ፡ ጉዳዩ በሕወሃቶችም ዘንድ ሊዘለል የማይችልና ትኩረት የተሠጠው በመሆኑ፣ መጋቢት 21/2016 ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው እንዲቀበላቸውና እንዲያነጋግራቸው ተደርጓል።

በአሁኑ ወቅት ውይይቱ የተካሄደው በሕወሃት ጠያቂነት መሆኑ ይነገራል። ፎተግራፉ ራሱ እንደሚመስክረው፡ የሕወሃት ግንባር ከዲፕሎማቶች ጋር እንኳ በሥነ ሥርዓት ኮቱን ቆልፍ ታይቶ አያውቅም። አባገዳ በኢትዮጵያ ውስጥም የአብዛኛው ሕዝብ ተወካይ ተቋም በመሆኑ ለግለሰቦቹ፥ የተሠጠው ከበሬታ ሲያንሳቸው እንጂ አይበዛባቸውም!

በዚህም ወቅት “ሁሉም የሚኖረው ሰላም ሲኖር ነው” ያሉት የቱለማ አባገዳ እና የኦሮሚያ አባገዳ አንድነት ሰብሳቢ አቶ በየነ ሰንበቱ፡ ቀዳሚው የመንግሥት ተግባር በግጭቱ ለሞቱ ሰዎች ካሳ እንዲሰጥ፣ ንጹህ ሆነው የታሰሩ ልጆች እንዲፈቱና ለጠፋ ንብረት ካሳ እንዲሰጥ ጥያቄ ማቅረባቸውን ለጋዜጠኞች ገልጸዋል

ምንም እንኳ የሕወሃቶች ቃል ምነነቱም የማይታመን ቢሆንም፡ ይህም ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ መታየት ያለበት ጉዳይ ቢሆንም፣ በቃል ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየውም “በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱ ግጭቶችን በውይይት ለመፍታት የገዳ ሥርዓት እሴቶች በማህበረሰብ ውስጥ ማጠናከር እንደሚገባ” መግለጹን ኢዜአ በመክፈቻ ዐረፍተ ነገሩ ላይ አስቀምጦታል።

ውይይቱ እንደ ወትሮው የሕወሃት ሰዎች እንደሚያሳዩት ዐይነት ‘እግዚአብሔር የመሆን” አዝማሚያ ያልታየበት ከመሆኑም በላይ፡ አባ ገዳም ከመንግሥት ጋር በመተባበር ሰላም እንዲወርድ ጥረት እደሚያደርጉ፣ በተለይም አሳሳቢ የሆነውን የትምህርት መቋረጥ አስመልክቶ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ከዩኒቨርስቲዎችና ከትምህርት ቤቶች ጋር በጋራ እንሰራለን ብለዋል።

ይህ ማለት ግን ሕወሃት እነደተለመደው እንደፈለገው የሚዘርፈውና የሚሸመጥጥው የጫካ ፍሬ ሳይሆን፡ አባገዳዎችም ጥይቄዎች (demands) ይዘው መቅረባቸውን ማስታወስ ይገባል።

ለመሆኑ ዝርዝር የአባገዳ ጥያቄዎች (demands) – ማለትም እንዲተገበሩ የፈለጓችው ጉዳዮች ምንድናቸው?

በሶሻል ሚዲያ ላይ እንደሠፈረው ክሆነ፡ አባገዳዎች ያቀረቧቸው ጥያቄዎች አሥር ናቸው። ከእነዚህም መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፦

    1) የታሠሩት የኦሮሞ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፡ በስም ከተጠቀሱት መካከል በቀለ ገርባና ወጣት ደጀኔ ጣፋ ይገኙበታል፡

    2) ነፍስ ያጠፉ የሕወሃት ሲቪልና ወታደራዊ ተወካዮች ለፍርድ እንዲቀርቡና ለዚህም ተፈጻሚነት ነጻ የሆነ አካል እንዴመሠረት፡ እንዲሁም በዚህ የፍርድና ፍትህ ፍለጋና አሰጣጥ ሂደት ውስጥ አባገዳ ተሳታፊ እንዲሆን፡

    3) ከገበሬዎች የተዘረፈው መሬት ያላንዳች መዘገየት ለባለቤቶቹ እንዴዲመለሱና፡ የዚህ ዐይነቱ የመሬት ዘረፋ በኢትዮጵያ እንዳይደገም፤

    4) የሕወሃት ወታደሮች ኦሮሚያን ለቀው እንዲወጡ የሚሉ ይገኙበታል።

===============
 

አሁንም ኦሮሚያ ውስጥ ሰላም የለም

ሕወሃትና ቅጥረኞቹ ሰሞኑን እንደሚያስወሩት፣ ኦሮሚያ ውስጥ ስላም ወርዷል የሚለው የቁም ቅዠት ነው። ለምሳሌም ያህል፣ በየቦታው በተለይም በሃረርጌ፡ ወለጋና ሸዋ በየቦታው እሳቱ እንደጋየ ነው። ትምህርት ቤቶች ብዙ ቦታዎች ዝግ ናቸው። ኢሉባቦርም ትግሉ ውስጥ በዚህ ሣምንት መግባቱ ይነገራል። አያሌ ወጣቶችም በአውቶቡስ እየተጫኑ ወዳልታወቁ ሥፍራዎች መወዳቸው ተዘግቧል።

ግድያውና አፈናው (በተለይም የምሁራን ታፍኖ መወሰድ) ተባሷል። የዩኒቨርሲቲ ተማሬዎችም – ለምሳሌ ያህል ነቀምትና ናዝሬት – መደብደብና መረገጥ፡ የጥይት ራት መሆን ብቻ ሳይሆን – ፍርድና ፍትህ የሌለበት እስራት (denial of due process) ቀጥሏል። ባለፈው ሣምንት ናዝሬት ዩኒቨርሲቲ 75 ተማሪዎችን ለተለያዩ እሥር ቤቶች ዳርጋለች።

ባለፉት ሁለት ሣምንታት ብቻ፡ 719 ወጣት ታሳሪዎች ከምዕራብ አርሲ፥ 537 ደግሞ ከምዕራብ ሸዋ ወደ ጦሌ ወታደራዊ ካምፕ መወሰዳቸው ይነገራል። በድምሩ በጦሌ ብቻ ከ3,000 በላይ የኦሮሞ የፖለቲካ እሥረኞች መግባታቸው ሲታሰብ ሃገራችን ፊት የተጋረጠው ችግርና መፍትሄ ለማምጣት ፍላጎት የሌለው አስተዳደር፡ የኢትዮጵያ ማሽቆሎቆል ላይ ያልተደላደለ ‘ሃገር ግዥውን ማካሄዱ እብደት መሆኑን ይመሰክራል!

ምዕራብ ወለጋ ውስጥ መንዲ በተባለ ሥፍራ የገበያ ሥፍራ በሕወሃት ወታደሮች መቃጠሉ ይነገራል። ለዚህም ምክንያቱ ባለሃብቶች ተቃዋሚዎችን በገንዘብ መደገፍ ጀምረዋል ተብሎ በመወራቱ ነጋዴዎቹን ለመጉዳት የታቀደ የሕወሃት ደባ ነው ይባላል።

ንብረት እያወደመ ሰላም ፈልጋግለሁ የሚል አስተዳደር፡ ቤተ ኃይማኖቶችና ትምህርት ቤቶች ውስጥ ቦምብ እየወረወረ ለሃገርና ለሕዝብ አስባለሁ ማለት የተምታታ የናዚ ስልት በመሆኑ፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕውሃትን ከመፈንገሉ በፊት ሰላም፡ ነጻነትና እኩልነት ይኖራል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።