ተጠያቂነት ያላስከተለው የሕወሃት ዘረኝነትና የኢትዮጵያ ፖንዚ ፖለቲካዊ ኤኮኖሚው የተለያዩ መገለጫዎች

27 Mar

በከፍያለው ገብረመድኅን – The Ethiopia Observatory (TEO)
 

በስንቱ አንጀታችን በግኖ፥ ስለስንቱ ክፋትና ወጀለኝነት ተተርኮ ይዘለቃል?

አሁንማ ቅዳሜ ሪፖርተር ላይ እንዳነበብኩት፥ የመጥፎ አስተዳደር ሽልማት በኢትዮጵያ ሕዝብ የተበረከተለት ይመስል፥ አባይ ፀሐዬ እርሱው ራሱ የመልካም አስተዳደር ልሂቅና ምሶሶ ሆኖ ከእንግዲህ መወሰድ ስላለባቸው አስቸኳይ እርምጃዎች በከፍተኛ ደረጃ ተቆርቋሪና ተከራካሪ ተደርጎ ስለመቅረቡ ሳነብ፥ አጥፊው ጻድቅ የሚሆንበት የራዕዩ ዘመን መከሰቻ ላይ መድረሳችን ነው የተሰማኝ።

ሌላው ቢቀር፣ በስኳር ፕሮጄክት አባይ ፀሐዬን የተካው ግለሰብ – ቀዳሚው ባልተወለደ አንጀቱ ክፉኛ ያራቆተውን መሥሪያ ቤት አስመልክቶ – ‘እዚህ ቤት ከእንግዲህ ምንም ሊሠራ አይችልም’ አለ መባሉ፥ ከራሱ የሰማሁት ይመስል ጆሮዬ ላይ ተሠንቅሮ ቀርቷል!

ለመሆኑ፥ በከተማ መሬት ስንት ሕዝብ ያስለቀሰው የገፈፋ መሃንዲሱና ቤት ፈርሶ መሬቱ ለሪል ስቴት ኩባንያዎች እንዲሰጥ (በ”ሁከት ይወገድልኝ!” – የኤርምያስ ለገሠ መጽሐፍ) የመጀመሪያውን የመሬት ዘረፋ ሕገ ወጥ ሕግና የአሠራር መንገዱን የከፈተው ባለሥልጣን – ኤርምያስ ለገሠ በመጽሐፉ እንዳሳመነን – አባይ ፀሐዬ አልነበረምን?

ታዲያ እርሱ በየትኛው ብቃቱና ታማኒነቱ ነው አሁን የአስተዳደር ህዳሴን ለመምራት እሽቅድምድሞሽ የያዘው?

በስኳር ፕሮጀከት ውስጥ የነበረው ገንዘብ ብቻ ሳይሆን፡ ፕሮጀክቱ በአባይ ሥር ሆኖ ከገንዘብ ሚኒስቴር ተጭማሪ ከብር 400ሺህ በላይ ተሠጥቶ ደብዛው መጥፋቱን የኢትዮጵያ ኦዲተር ጂኔራል ገመቹ ዱቢሶ – አባይ ጸሐዬን ሳይሆን ፕሮጀክቱን ተጠያቂ ማድረጋቸው፡ በሃገራችን ምን ያህል ሥልጣንና መብት ተደጋጋፊ መሆናቸውን ያስገነዝብናል። በዚህም መሠረት፥ ኦዲተር ጀኔራሉ እስከ 2006 ዓም ማጠናቀቂያ የነበረው የሂሣብ መዛግብት ላይ በ2008 ዓም ለፓርላማ አስተያየታችውን ባቀረቡበት ወቅት እንደሚከተለው አሥፍረውታል፦

  “የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በመልሶ ማበደር ለስኳር ፊብሪካዎች ከሰጠው ብድር ውስጥ እስከ ሰኔ 30/2006 ዓ.ም ድረስ መሰብሰብ የነበረበት ብድር መሰበሰቡን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ ወለድና ቅጣትን ጨምሮ ብር 418,803,484.57 [$20 ሺህ] ያልተሰበሰበ መሆኑ ታውቋል፡፡”

በአባይ ሲመራ የነበረው የስኳር ፕሮጄክት በጀቱንና በብድር ያገኘውን ገንዘብ አውድሞ፣ ለቻይና $700 ሚሊዮን ብድር ሃገሪቱን መዳረግ ብቻ ሳይሆን፣ የስኳር ፕሮጀክትም በተጠበቀው ጊዜ ለመድረስ አለመቻሉ ሳያንስ፡ አሁንም የሕወሃት ሰዎች ቅርምት የሚሰበስቡት ፕሮጄክታቸው ሆኖ ለዓመት ያህል በሚቀጥለው ወር የስኳር ምርት ይጀመራል እየተባለ እንደቀልድ ከዓመት ዓመት ተሸጋግረናል!

ታዲያ በምን ታማኝነቱ ነው አባይ ጸሐዬ ስለመልካም አስተዳደር ትችት መስጠት ቀርቶ፡ ስለፓርቲው ወደፊት አስተያየት መስጠት የቻለው? አንዳቸው ከሌላው መሻላቸውን ባልጠራጠርም፡ በራሱ ሲታይ፥ ትንሽ ተምሯል በሚባልበት መስክ እንኳ ከአፈና ውጭ ምንም ውጤት ያላስገኘው እነደብረ ጽዮንም የሃገሪቷን የኤኮኖሚና ፋይናንስ ዘርፉን መያዝ ሃገራችን በችግሮች ችግር መቀፍደዷን በገሃድ የሚያሳይ ነው!

ታዲያ ሃገሪቱ በዚሁ ሁኔታ ውስጥ በተራ ወራሪዎች በመቀፍደዷ ኢትዮጵያ የወደፊት መንገዷን እንዴት ይሆን ልታገኝ የምትችለው?

ለኔ ይሄ የሚያሳየኝ፥የሽፍታ/ወንበዴ መንግሥት በኢትዮጵያ በተሰኘው ጽሑፌ ግንቦት 6/2015 እንዳሠፈርኩት፣ ሃገራችን ከምን ጊዜውም በከፋ መልኩ አደጋ ላይ ናት!

ሕዝቡም ያለውን ሁኔታ አስከፊነት በመገንዘቡ፥ ባለፉት 25 ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ መልኩና ሁኔታ ቁጣና ጽየፋውን ከመሃልም በአራቱ ማዕዘናትም በመግለጽ ላይ ይገኛል።

አሁን ሕዝቡን በመናቅ የሕወሃት ብልጣ ብልጦች በመልካም አስተዳደር ስም በማስለፍለፍ ለማሸማደድ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው! የአባይ ጸሐዪንም የሰሞኑ ተከታታይ ቲአትሮችንም (የHorn Affairs ክህደቱን ጭምር – (ሀ) እና (ለ)) በዚያ መስመር ነው ያየኋቸው።

ባለፈው ዓመት ከምሣ ሰዓት ውስኪ ጉንጨታ በኋላ ሃዋሣ ስብሰባ ላይ የመሬት ዘረፋውን ‘የሚያደናቅፍበትን’ የኦሮሚያ አመራርን አስመልክቶ፥ አባይ ፀሐዬ “ልክ ይገባታል …” እያለ ካቅራራባት ውድቀቱ በመልካም አስተዳደር ስም አሁን ለመታደስ የሚያደርገው ጥረት ሃገሪቱ ሕግ የሚባል ነገር የሌለባት መሆኑን የሚያረጋግጥ በመሆኑ፣ ወደ ኋላም እየተመለስን ማስታወሱ፥ ሌላው ቢቀር የወደፊቱን በደንብ ለመመልክትና ለመገንዝብ የሚረዳ ይመስለኛል።

ሌላውን ቅጥረኛ እያባረሩ፥ ሕወሃቶች የመተዳደስ ነገር ስለጀመሩ፣ ይህ እንደማይሠራ እንዲገባቸው አንዳንዶቹን የተቀየምንባቸውን ነገሮች ደጋግሞ ለዓለምም ጭምር ማሳወቁ አይጎዳም ባይ ነኝ!
 

የኢትዮጵያ የግዛት ሉዓላዊነት በሕወሃት በተደጋጋሚ መገሰሰ

ኢትዮጵያ ባለፉት 25 ዓመታት ዳር ድንበሯ ጭምር ሲሸራረፍ ቆይቷል። ዛሬ የባህር በር የሌላት ሃገር በመሆኗ፣ በኤኮኖሚው መስክ በተለይም በኋላ በፍብረካና የውጭ ንግድ ረገድ እምብዛም ተጠቃሚ ስለማትሆን፡ የሕዝባችችንን የጫጨ ኑሮ ብቻ ሣይሆን በከተማዎች አካባቢ የሠራተኛውን ከቀን ባለሙያ ያልተሻለ ኑሮ ለምግፋት ስለሚያስገድድ፡ የፖለቲካ ተቃውሞው ይጠናከራል፤ ወንጀሎችና የወጣቶች ሰውነታቸውን ለመሸጥ መገደድ ሕወሃት በኦሞ ሸለቆ እንዳደረገው ሁሉ ተጠቃሚ ሊሆንበት እንጂ ሕየወታቸውን ሊያሻሽል የሚያስችል ፍላጎቱም ሆነ ዓላማው አይኖረውም!

ለችግሮች መፍትሄ በመሻት ረገድ፡ የሕወሃት መሪዎች የሚያውቁት መፍትሄ ኃይልን መጠቀም፡ ወይንም ያለውን አንስቶ መቸብቸብ ነው። በዚህም ረገድ ጥቂቱን ለማስታወስ ያህል፥ በቅርቡ ለሱዳን የተሠጠው ሉዓሏዊ ግዛታችን ወቅታዊ ስለሆነ ሁሉም በሚገባ ያውቀዋል።

በተጨማሪም፥ ኢትዮጵያ በምዕራብና በደቡብ ድንበሮቿ በኩል ከሚኒሊክ ጊዜ ጀምሮ ያስከበረቻቸውን ግዛት ክፍሎች ቀስ በቀስ ማስረከብም ጀምራለች። ለምሣሌም ያህል፥ በእንግሊዞች ሞድ መስመር (Maud Line) ወይንም ቀዩ መስመር (Red Line) ተቀባይነት የሌለው ሆኖባት፥ የባለቤትነት ጥያቄ ያሠመረችበት በመሆኑ፥ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ተቀባይነት አለው፡ ከሌሎች ሁኔታዎች ጋር ተዛምዶ።

በዚህ ረገድ እንኳ ሕወሃቶች ውክልና ሳይኖራቸው፡ ማለትም የሕዝብ ይሁንታ ሳይጠይቁ፡ ከ2014 ጀምሮ ከኬንያ ጋር በተደረገ ምሥጢራዊ ድርድርና በኅዳር 2015 በቴዎድሮስ አድሃኖምና በኬንያ መንግሥት መካከል በተጠናቀቀው ሚሥጥራዊ ስምምነት፥ ሕወሃት እንደገና ሃገራችን ከአጼ ሚኒሊክ ጊዜ ጀምሮ የነበራትን የኢለሚ ትሪያንግል (Ilemi Triangle) የይገባኛል ጥያቄ ያላግባብ ማሰረከባቸው ከወደብ ዕጦታችን ባላነሰ መልኩ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው።

በነገራችን ላይ በጎን እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብም ከበስተጀርባው የተወጋው የደቡብ ሱዳን መንግሥትም ነው – ኢትዮጵያ ዕውቅና የሠጠችው ለኬንያ ነውና! በቅርቡ የደቡብ ሱዳን ጦርነት ወቅትም፡ ኬንያ በኢጋድ አባልነቷ አደራዳሪ ብቻ ሳትሆን፡ በጎን ሪክ ማቻርን ኢሌሚ ትሪያንግል የኬንያ ነው ብሎ ክተስማማ በደቡብ ሱዳን በወታደራዊ ኃይል ጭምር ፕሬዚደንት እንደምታስደርገው ማግባቢያ በመስጠትና ጫና በመፍጥር ብዙ ነገሮች ውስጥ ለውስጥ መካሄዳቸውን በቅርብ ጉዳዩን የሚከታተሉ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ጥረቱ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

ከጎረቤቷ ቅኝ ገዥዋ እንግሊዝ ጋር ባለመስማማትና በድንበር ማካለሉ ኢትዮጵያ በሚኒሊክ ትዕዛዝ ባትሳተፍም፡ እንግሊዝ በራሷ ፍላጎት የግዛት መስመሯን (Maud Line) ወይንም ቀዩ መሥመር (Red Line) ለብቻዋ በ1902/03 ማስመሯ አንድ ግብ ነበረው – አካባቢዋ ላይ ቅኝ ግዛቷን ማጠናከርና ማስፋፋት! ይህንን ዓላማዋንም ያንጸባረቀውን የሞድ መሰመር በመሆኑ፥ የአካባቢው ኢትዮጵያውያ ባለሥልጣኖችና ኢትዮጵያውያን ችካሎቹን በመነቃቀልና በምትኩ – በእንግሊዝኛ ጭምር የሚኒሊክ መሥመር (Menilik Line) መትከላቸውን – ከሌሎች በተጨማሪ – ሱዳናዊው የፖለቲካ ጂኦግራፊ ባለሙያ ጣሃ ሃስን ኑር (Taha Hassan Nur) ለዱርሃም ዩኒቨርሲቲ በ1971 ዓ.ም. ባቀረቡት The Sudan-Ethiopia boundary: a study in political geography በተባለ 273 ገጽ ምሁራዊ ጥናት በዝርዝር ዘግበዋል።

ኢትዮጵያ በየዘመኑ በራሷ ችግር ተውጣ – እንደ ኬንያ – ዐይኗን በግልፅ ኢለሚ ትሪያንግል ላይ የምትጥልበት አቅምና ሁኔታ እንዳልነበራት የታወቀ ቢሆንም (ዕድሜ ለሶማሌው ዚያድ በሬ፥ ኤርትራና ትግራይ የመገንጠል ጦርነቶች) – በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የኢትዮጵያ የኢለሚ ትሪያንግል ይገባኛል ጥያቄ የተነሳበት ሠነድ ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በተባበሩት መንግሥታት የመንግሥታት የትሪቲ Treaty Section ሠነዶች ውስጥ አልተገኝም።

በታቃራኒው፣ ከሚኒልክ ጊዜ ጀምሮ በባለቤትነት የተያዘ ከመሆኑ በተጨማሪ፥ ጣልያን እንኳ ኢትዮጵያን ከወረረች በኋላ በ1936 ኢሌሚ ትሪያንግል በዓለም ዓቀፍ ሕግ መሠረት ኢትዮጵያዊ ነው በማለት ለዓለም ማሳወቋ ይታወሳል

ለዚህም ጣልያን ያቀረበችው ማስረጃ ደሳንቾች ((Dasanech – Geleb) ከብቶቻቸውን የሚያስግጡበት ቦታ በመሆኑ፡ ሕጉ እንደ ነዋሪዎችና ባለቤት ይቀበላቸዋል የሚል ነበር። ነገር ግን ጣልያን አካባቢዋን ይዛ ማስተዳደር አስቸጋሪ ስለሆነባት፡ የአካባቢውን ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰቦች በማስታጠቅ የባለቤትነት ማስረጃ ፖሊሲዋ አድርጋ ብቻ ቀጠለች – የእንግሊዝን እንቅስቃሴ ለመግታት እንዲያስችላት!

ይህ አሠራርም፣ ለተከታታዮች የኢትዮጵያ መንግሥታት ተስማሚ በመሆኑ፡ ሁሉም መሣሪያ በማደል ሕዝቡ ራሱን እንዲከላከልና በልምድም ከብቶቹን ለማስጋጥ ወደ ኢሌሚ ትሪያንግል መመላለሱ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ (symbolically) የኢትዮጵያን ባለቤትነት አጠናክሮ ለማስቀጠል አስችሎ ነበር።

ለኢሌሚ ትሪያንግል ጥንታዊ ኢትዮጵያዊነት ምሥክርነት ከሚሠጡት ማስረጃዎች አንዱ፡ ይህቺ እስከ 14,000 ስኩ ኪሜ ስፋት አላት ተብላ የምትገመተው፣ ኢትዮጵያን፡ ኬንያንና ደቡብ ሱዳንን አቆራኝታ የያዘችው መሬት፡ ስያሜዋ አንዱ ነው። ምንም ተቀናቃኝ ሳይነሳባት፣ ሥፍራዋ እስከዛሬ የምትጠራው በአንያዋ (ጋምቤላ መሪ ቺፍ chief Olemi Akwon መሆኑ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነዳጅና የተለያዩ ማዕድናት አላት መባሉ፥ የአካባቢውን ሃገሮችን ፍልጎት ብቻ ሣይሆን አንዳንድ የተለያዩ ምዕራባውያንን ሃገሮችም ትኩረት ሁሉ እንደቀሰቀስች ብዙ እየተነገረ ነው።

በአጼ ሚኒልክ ዘመነ መንግሥት የተወሰደው እርምጃ ተቃዋሚነቱ ለእንግሊዙ ቀዩ መሥመር ብቻ ቢመስልም፡ በፍጹም ያልተቀበለው አንድ ቁም ነገር አለ። ሕውሃት ዛሬ የሃገራችንን መሬት ለሱዳን ያስረከበበትን የሻለቃ ጉዌንን ክለላ ኢትዮጵያ አለመቀበሏን የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው። ታዲያ ሃቁ ይህ ሆኖ ሳለ፥ ለምንድ ነው ሕውሃት ወረዳ በሆነ መንገድ የሃገር ዳር ድንበር ሽያጭ ውስጥ የገባው – ይሁዳ ክርስቶስን በ30 ብር ለጠላቶቹ አሳልፎ እንደሠጠው ሁሉ (የማቴዎስ ወንጌል 26፡ 14-15)?

መገመት የሚቻለው፡ ይህ እርምጃ ሕወሃቶች በአንድ በኩል ለሱዳን የገቡትን የመሬት ቆርጦ በመስጠት ማስፈጸም ማስቻሉ ሲሆን፣ በሌላ በክሉ ደግሞ ልክ ድሮ አፍሪካውያን መሬቶቻቸውን ለፈረንጅ አረቄና መስተዋቶች አሳልፈው እንደለወጡ ሁሉ፡ ሕወሃትም ዛሬ ያደረገው፡ ኬንያ ለኢትዮጵያ የተ.መ.ድ. ጸጥታ ምክር ቤት አባልነት ተራዋን እንድትለቅላት በመስማማት ነው።

እጅግ በሚያሳፍር መንገድ በቴዎድሮስ አድሃኖም መሪነት ኢትዮጵያን በ2017-2018 የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት አባል የማስደረግ ኃላፊነት ስለተሠጠው፣ ‘ድሉን’ በአጭር መንገድ መጎናጸፍ የፈለጉት።

ከ2012 ጀምራ የምረጡኝ ዘመቻ ስትካሄድ የነበረችውን ሴይሼልስን ኢትዮጵያና ኬንያ ወደ ጎን በመግፋት – በተለይም ኢትዮጵያ በአየር መንገዳችን ሣምታዊ በረራዎች መቀነስ በማስፈራራት፡ የአዲስ አበባንና የናይሮቢ መሪዎችን ጥቅም በማስቀድም መሥዋዕት ስላደረጓት፡ የደሴቷን መንግሥት አዲስ አበባ ላይ ጥር 31/2016 በተደረገው የአፍሪካ አንድነት መሪዎች ስብሰባ ላይ የሃገሪቱ ልዑካን መሪ የውጭ ጉዳይና ትራንስፖርት ሚኒስትር ጆኤል ሞርጋን በከፍተኛ ምሬት ለጉባዔው መናገራቸውና ይኽውም ሁለተኛ እንዳይደገም መጠየቃቸው ይታወሳል።

ሚኒስትሩ በዚያ የሃገራቸውን ቁጣ በሚገባ በገለጸ ንግግራቸወ፡ በተሸፋፈነ ቋንቋ ብልግናን እንደማይቀበሉ አስረግጠው ከተናገሩት መካከል የኬንያና የኢትጵያ ስምምነት በሰነድ ያልተያዘ መሆኑን ጭምር ጠቅሰዋል፡

  “So while we remain firm in our support of the principles of rotation as being sacrosanct to our institution, and that those who have not served before should be given the opportunity to do so, we also recognised the need here for gentlemanly conduct.”

ለምን ይህ ሆነ ለሚለው ጥያቄ፡ የራሴ ግምት አለኝ። ኢትዮጵያን በ1987/88 የጸጥታው ምክር ቤት አባል የማስድረግ ጥረት እንዳስጀመረና እንዳስፈጸመ ባለሙያ፥ በኔ ግምት ለዚህ ውድድር ምክንያት የሆናቸው፥ የግንቦት 2015 ምርጫን ማጭበርበር ከሃገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ሕወሃት ላይ ስላጠላበት፡ ያንን ለማለሳለስና ከውጭ ገጽታን ለማደስ እንዲረዳቸው የታቀደ መንገድ ነው!

ሕወሃት የጸጥታው ምክር ቤት ውስጥ ወንበር ሊያገኝ ይችል ይሆናል። ነገር ግን በኢትዮጵያ ሕዝብ ዐይን ገጽታውን ሊያድስ አይችልም። ችግሩም እንደተባባሰ እንደሚቀጥልና ከኢኮኖሚ ዘረፋ ባህሪው ጋርና ከሕዝቡ የኑሮና የመብቶች አፈና ችግር ጋር ተዳምሮ እንደውም ይበልጥ ሊያዳክመውና ወደ ውድቀቱ ሊያመራው እንደሚችል ይገመታል።

የኢትዮጵያ ሁኔታ ለሕወሃቶች የተለያየ ዐይነት የዘረፋ አስተዳደር እንዲያመቸቻቸውም፥ ተጎራብቶና ተዋልዶ የኖረ ሕዝብ አንዱ በሌላው ላይ በነገድና በሃይማኖት ስም እየተከፋፈለ እርስ በእርሱ እንዲጋጭ ማድረጉን ሥራችን ብለው ተይይዘውታል። ደግነቱ ጨዋ ሕዝብ “ያ የኢትዮጵያውያን መንገድ አይደለም” በሚል – ሰላም እየደፈረሰ ቢመጣም – እስካሁን ሕዝቡ የጋራ አኗኗሩን መርገጥ እንደማይሻ በተደጋጋሚ አሳይቷል።
 

የቁማር ኤኮኖሚው አሳሳቢነት

በዘረፋ ላይ የተመሠረተ ኤኮኖሚ የቁማር ኤኮኖሚ (ፖንዚ ኤኮኖሚ, Ponzi Economy, Ponzi Scheme) በመሆኑ፣ ተጠቃሚዎቹ /አራማጆቹ ናቸው። ሆኖም ማጭበርበር ላይ የተመሠረተ የቁማር ኤኮኖሚ በአንድ በኩል አራማጆቹ የያዙት ሲመስላቸው፥ ሕዝቡ የበይ ተመልካች በመሆኑ፥ በሌላ በኩል ከዕድገት ይልቅ ሲያፈስና ሲያነባ ያገኙታል። ይህ ሁኔታም በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ ውስጥ ከቁጥጥር ያመለጠ 39 ወራት የፈጀው የዋጋ ግሽበት፥ የምርታማነት ዕድገት (productivity growth) በግብርናው ዘርፍ ከሲታ መሆን፣ እንዲሁም በሰው ሃብት ልማት (human resources development) ኢትዮጵያ 14 ከእርሷ የባሰ ድሃ ሃገሮቸን ብቻ በመቅደም ባለችበት በመርገጥ ላይ በመሆኗ፡ የኤኮኖሚ ዕድገቷ ምልክት በዜጎች መካከል የተፈጠረው መተናነስ (inequality) ብቻ ነው።

ከጥቂት ዓመታት በፊት፥ የታዋቂው BigThink አዘጋጅ Robert De Neuville ስለ ፖንዚ ኢኮኖሚ ሲጽፍ፥ በንግዱ ዓለም ሃብት ለማፍራት ሁለት መንገዶች አሉ ይላል።

አንደኛው ገንዝብ ያላቸውን ኢንቬስተሮች ተጠግቶና አግባብቶ ገንዘባቸውን በስምምነት ወስዶ ማትረፍና ተጠቃሚ መሆን የሚያስችለው ዐይነት ነው። ይህ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው የገንዘብ እንቅስቃሴ፣የብድርና ክፍያ ሥርዓቱ በሚፈቅደው መሠረት የሚሠራ በመሆኑ፡ አበዳሪም ተበዳሪም ብሎም መላው ኅብረተሰብ ተጠቃሚ የሚሆንበት አሠራር ነው። ይህ አባባል ትክክለኛነቱ ተቀባይነት የሚኖረው የተጠያቂነትን መኖር፥ የመዋቅሮችን በሚገባ ተልዕኳቸውን በተግባር ማዋል የሚያስችል ነጻነት መኖሩን፥ ፍርድ ቤቶችና ዳኞች በሕግ መሠረት ሥራቸውን ለማከናውን የሚያስችላቸው ሕጋዊነት መኖሩን እንደነባራዊ ሁኔታ በመቀበል ነው።

ሁለተኛው ደግሞ ሕጋዊነትና ተጠያቂነት የሌለበት የኢትዮጵያ ዐይነት አሠራር ነው። ይህም ማለት በአጭር አገላለጽ፡ ተፈጻሚነት የሚኖረው ትክክለኛውና ሕጋዊ የሆነው አሠራርና ባህሪ ሣይሆን፡ የባለሥልጣኖቹ ፍላጎትና እነርሱ ለዘመናት ሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችላቸውን ሁኔታ መፍጠር ነው።

ይህም አሠራር፥ ጥቂቶችን እየጠቀመ ብዙኃኑን የሚሞልጨው፡ ገንዘብን በኢኮኖሚ ውስጥ ሙሉ ዋጋው ተጠብቆ ኢኮኖሚው እንዲዳብርና መላውን ኅብረተሰብ ተጠቃሚ እንዳያደርግ፥ ሕወሃት የሃስት ቁጥር እየደረደረ (ሕጋዊነትና የማክሮ ኢኮኖሚክ ዲሲፕሊን መጥፋት)፥ ኅብረተሰቡ እየተራቆተና እየደየ ሲሄድ ዕድገትና ልማትን ተላበስን ብሎ የሚያስወራለት ዐይነቱ ኤኮኖሚ ነው።

የዚህ ዐይነቱን ኤኮኖሚ ባዶነት በ2007 አሜሪካ ውስጥና ብሎም በዓለም ኤኮኖሚና ፋይናንስ ላይ እስከዛሬ ያስከተለውን ቀውስ ተመልክተናል – ምርት አለ፤ ገበያ አለ፤ ጥቂቶች ቢልየነሮች እየሆኑ ሲሄዱ፡ አብዛኛው ሕዝብ ከድሮው ይበልጥ ቢሠራም ገቢው አያድግም! መሠረቱ ሽባ የሆነው የኢትዮጵያም ኤኮኖሚ ትንሽ መሆኑ ነው እንጂ ዛሬ በሃገራችን ላይ ደርሶ የምናየው ቀውስ – ድርቁን ጨምሮ – ለደሃ ሃገር ቀላል አይደለም!

ለዚህ ባዶነት ትክከለኛ መረጃ ከሚሠጡን ሁኔታዎች መካከል እየተስፋፋ ያለውን ሙሰኝነት፣ ከሃገር የሚሸሸውን እስከ ሶስት ቢሊዮን ዶላር በዓመት መጠን፡ ድርቅ በሌለበት ሁኔታ እስከ 40 ከመቶ የሚሆነው ሕዝባችን በዘላቂነት ርሃብተኛ መሆኑ፣ 40 ከመቶ የነበረው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑት ኢትዮጵያውያን መቀጨጭ ወደ 45 ከመቶ ከፍ ማለት፡ ኢትዮጵያ በሰው ሃብት ልማት (human development index) በዓለም ላይ እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኗ ብቻ ሣይሆን፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አዝቅጣ ከ188 ሃገሮች መካከል ወደ 174ኛ ማሽቆልቆሏ፡ የሕወሃት የኅብረተሰብ ፍትህ ይዞታ ከተለያዩ ሃገሮች ጋር ተወዳድሮ፡ ኢትዮጵያ 98ኛ ሆናለች የሚሉትን አሃዞች ትርጉም በሚገባ ማሣለጡ ትክክለኛውን የሃገሪቷን ሁኔታና አቅጣጫ ያመላክታል።

ሲጠቃለልም: የጥንድ አሃዝ የኤኮኖሚ ዕድገት ያለባት ሃገር እየተባለ ሲደነፋ ተከርሞ፥ ዛሬ ኢትዮጵያ በማንኛው ዓለም አቀፍ መለኪያዎች ከሠሃራ በታች ከሚገኙት ሃገሮች ከመጨረሻዎቹ ጥቂቱ ጋር መሠለፏ የፖለቲካዋን ብልሹነትና ትክክለኛ ይዞታዋን ያንጸባርቃል!

ይህ ማለት፥ በዚህ ፖንዚ ኤኮኖሚ ውስጥ ዕድገት የለም ማለት ሳይሆን – 10 ከመቶና 11 ከመቶ ባይሆንም – ያለው ዕድገት የምርቱና የዕድገቱ ፍሬ ተጠቃሚዎች ጥቂቶች ብቻ መሆናቸው በሕወሃትም ላይ ጥላቻንና ተቃውሞን እያፋፋመበት ነው!

ሌላው፣ ዛሬ በሃገራችን ውስጥ ትልቁ ኪራይ ሰብሳቢ ሕወሃት ነው። የሕወሃት ሰዎች በረሃ ወርደን ነጻ አውጥተናችኋልና ኪራይ ይክፈለን በማለት በኅብረተስብ ውስጥ ግንባር ቀደም ተጠቃሚዎች ሆነዋል። ስለራሳቸው መልሰው የሚያወሩት ነገር፣ ራሳቸውን የግብዝነት ማዕዘን አድርጓቸዋል። ግብዝነቱ የሚመጣው መርሆ አለን ብለው ራሳቸውን ሲክቡ ነው። መርሆ ኖሯቸው በረሃ ከወረዱ፣ አሁን ኅብረተሰቡ ውስጥ ሥራቸው መርሆቸውን ማስረጽ መሆን ሲገባው፥ ኪራይ ለመሰብሰብ ከኅብረተስቡ ጋር መራኮታቸው ነው።

በእነዚህም ምክንያቶች ራሳቸውን የመርህ ተከታይነት ምሣሌዎች ለማድረግ ባለመብቃታቸው፥ በኪራይ ሰብሳቢነታቸው ምክንያት እነርሱን በትክክል እየገለጻቸው ያለው፡ ኅብረተሰቡን ነጋ ጠባ የሚዘልፉበት ራሱ የሕወሃቶች ኪራይ ሰብሳቢነት ነው!

ትራንስፔረንሲ ኢንተርናሽናል (Transparency International) ኢትዮጵያን አስመልክቶ በየዓመቱ ያወጣቸው ሪፖርቶች ጎን ለጎን ሲታዩ፥ በ2015 ኦን ላይን ምልከታው – መንግሥታዊ ዘራፊነትና ኪራይ ስብሳቢ ለመሆን ሕወሃት በየደረጃው ስለወሰዳቸው እርምጃዎች – አንድ አሰደናቂ ሥዕል ይኸው እየገለጽኩት ያለሁት ሥዕል ገሃድ ሆኖአል።

እነዚህም የሚያመላክቱት በኢትዮጵያ የሙስና ሁኔታ መጠናከሩን፣ በከፍተኛ ደረጃ የሚካሄድ (ሕወሃት)፣ በሕገ ወጥነት የሚከናውን ጉዳይ በመሆኑ፡ ዓላማቸውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚፈጽሟቸው ድርጊቶች፡ የሚያወጧቸው ሕጎችና የሚያቋቁሟቸው መዋቅሮችም ሕገ ወጦችና ሕገ ቢሶች መሆናቸውን እንደሚከተለው በገሃድ ያሳያል፡

  (ሀ) ሚዲያውን እንደሚያፍኑ፡

  (ለ) ፍትህ እንዳይኖር እንደሚጥሩ፥

  (ሐ) መራጩን ሕዝብ ድምጽ አልባ አድርገው ሥልጣን በራሳቸው ሥር እንደሚያሰባስቡ፥

  (መ) ገንዘብ ነክ ሚሥጥሮች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር መደረጉ በተለያየ ቀዳዳ ባለሥልጣኖችን ገንዘብ ለማሸሽ እንደሚያስችላቸው፣

  (ሰ) ተጥያቂነት አለምኖርና የሕግ የበላይነት ትርጉመ ቢስ መሆኑ በገሃድ እንደሚታይ፡

በማጠቃለልም፡አንዱ የፖንዚ ኤኮኖሚ ውጤት፥ ሃገሪቱ በየዓመቱ ከሌሎች ሃገሮች ጋር ተወዳዳሪና ተፎካካሪነቷ እያዘቀጠ መምጣቱን ያለፉት ዓመታት ሪፖሮቶች የሣሉት አጠቃላይ ሥዕል አረጋግጧል። ሌሎች ዓለም አቀፍ መለኪያዎችም (international indices) እንዲሁ፡ በተፋጠነ መንገድ የኢትዮጵያን ከሰሃራ በታች ያሉ ሃገሮች ጭራ እየሆነች መምጣት ማሳያ እየሆኑ ናቸው።

ከላይ የተጠቀሰው የፖንዚ ኤኮኖሚ ዋናው ባህሪ ኤኮኖሚው በመላ ተንሳፋፊ በመሆኑ፡ የምርት ውጤቱ ኅብረተሰቡን ከማሻሻል ይልቅ ጥቅሙ ጥርጊያው ለተከፈተላቸው ብቻ የሚያደርግ በመሆኑ፡ ኅብረተሰቡ ውስጥ የብዙኃኑ ድህነትና የጥቂቱ ማን አለብኝነት በተመሳሳይ መጠን እየተስፋፉ ይሄዳሉ።

ኢትዮጵያ ለአያሌ ዓመታት አፍሪካ ውስጥ ከፍተኛውን የለጋሽ ሃገሮች ሃገሮችን ዕርዳታ ተቀባይ ከመሆኗም በላይ፥ በዓመት እስከ አሥር ሚሊዮን የሚደረሰው ሕዝቧ በምዕራባውያን የምግብ ዕርዳታ የሚኖር ቢሆንም፥ ይህ የምጽወታ ፕሮጄክት ከተካሄደባቸው ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ የሕወሃት አስተዳደር ምንም መሻሻል ሳያደርግ ሃገራችን በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ የሕዝባችን ብዛት ወደ 102 ሚሊዮን ከፍ ይላል።

ይህም ስሌት ላይ የተደረሰው፥ የተባበሩት መንግሥታት ያሰላው የ2015 ቁጥር ላይ ማለትም 99.4 ሚሊዮን ላይ የዓመቱ ተጨማሪ ተወላጆች 2.5 ሚሊዮን ሲደመርበት ማለት ነው።

በዚህ በተበላሸ ሥርዓት እንዴት ነው የዚህን ሕዝብ መሠረታዊ ፍካጎቶች ማርካት የሚቻለው?

ሌላው ቀርቶ ሆስፒታል ውስጥ የሚወልዱት እናቶች ቁጥር ከ2006 እስከ 2014 ባለው ጊዜ ውስጥ ከ16 ከመቶ እንዳልዘለለ የተባበሩት መንግሥታት መረጃዎች ያመለክታሉ!

ባዶ ፕሮፓጋንዳ ብቻ ሕውሃት በሚቸረችርባት ኢትዮጵያ፡ በአፍሪካና በዓለም ደረጃ በዚህ ለልጆችና እናቶች በሚሰጥ የሕክምናና የእንክብካቤ አገልግሎት ቁጥር የመጭረሻዋ ሃገር ሆናለች! ኢርትራና ሶማልያ ውስጥ 34 ከመቶ እናቶች ሆስፖታል ይወልዳሉ፤ ደቡብ ሲዳን ከኢትዮጵያ ተሽላ 19 ከመቶ እናቶች ሆስፒታል ሲወልዱ፡ ሱዳን ውስጥም ይህ ቁጥር ከኢትዮጵያ ተሽሎ 23 ከመቶ ነው።
 

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ: የፖንዚ ኤኮኖሚ ትክክለኛው ምሣሌነት

በሃገራችን የሚካሄደው ዘረፋ ዐይነተኛ አስተባባሪና ግንባር ቀደም መሪ ሕወሃት ሲሆን፡ በተለይም የመንግሥት ባንኮች መሣሪያው ከሆኑት መካከል እንደ መሆናቸው፡ ከሥሮ የተዘጋው የግንባታ ባንክ Construction Bank) በምሣሌነት ሊጠቅስ ይችላል። የንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለሕወሃት በሚሠጡት አገልግሎት ግንባር ቀደሞቹ ናቸው።

ምናልባትም ዘላቂና ሕጋዊ መፍትሄ ካልተገኘለት በስተቀር፥ ከእነዚህ ቀድሞ የሚደፋው ቃሬዛ ላይ የሚገኘው በሕወታዊው ኢሣይያስ በርህ ሲመራ የኖረው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ነው።

ፋና ፍቶ

ፋና ፍቶ

መጋቢት 14/2016 አቶ ኢሣይያስ በባንኩ ላይ ለደረሰበት ኪሣራ ለፋና በሠጠው መግለጫ፡ ጥፋቱ የኢንቪስተሮች እንጂ የባንኩ አስተዳደር አይደለም በሚል ማብራሪያ፡ “በወጪ ንግድ ላይ ተሰማርተው የውጭ ምንዛሪን ለማምጣትና ከውጭ የሚገባን ምርት ለመተካት ብድር የሚወስዱ ደንበኞቼ ስራቸው ስኬታማ እስኪሆን የወለድ ምጣኔ ማበረታቻዎችን መስጠት አቆማለሁ” መባሉ እጅግ አስገርሞኝ ነበር።

ይህ አባባል የሚያሳየው ባንኩ የፈለገውን የሚሠራ እንጄ በሕና ደንብ እንደማይመራ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። አንድ የውጭ ኢንቬስተር በገባችሁልኝ ቃል መሠረት መጥቻለሁ፡ በምን ምክንያት ነው ጥይቄየ ተቀባይነት ያጣው የሚለው ጥይቄ መልስ ስለማይኖረው፡ የባለዜጋው ሃገር በዕርዳታም ላይ ቢሆን እንቅፋት መሆን ያስችለዋል – ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ሚና ለትትልቆቱ ሃገሮች ኢምንት ቢሆንም

የዛሬው የልማት ባንክ ገንዘብ አልባነትና የሰሞኑ ነፍስ አድን እርምጃ እምብዛም አልገረመኝም – ዋናው ለዚህም ሕውሃትና ገንዝብ የሚከባበሩ ወዳጆች ባለመሆናችወ ነው። ለምሣሌ፥ በ2013 እኔን በጣም ካስገረመኝ ነገር፡ በኢሣኢያስ በርህ አመራር የመንግሥት ባንክ ከቤተስብና ከድርጅቶች ተሽቀዳድሞ በጉለሌ የመልሰን ፓርክ ለማቋቋም ከፍተኛ ገንዘብ ያላንዳች ውክልና (ከደንቡና ባንኩ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጭ) በእሽቅድምድም መረጨቱ ብዙ ዘረፋ የሚካሄድበት ለመሆኑ ደንበኛ ማሰረጃ ሆኖኝ ነበር።

በዘረፋና ሀቀኛ ልማት መካከል መሠረታዊ ልዩነት በመኖሩ፡ ሕወሃት በልማት ስም ከዜጎች በተዘረፉ መሬቶች ሳቢያ ካሽ መስበሰቢያና መያዣ እንዲሆነው፡ ለራሱ ዞግ አባሎች ብድሮችን እያከፋፈለ እስከዛሬ ዘልቋል። ለነገሩ ኢትዮጵያ ተጠያቂነትና ሕግ ትርጉመ ቢስ የሆኑባት ሃገር በመሆኗ፡ የባንኩ ባለሥልጣኖች የሕወሃቶችን ፍላጉቶች እስካገለገሉ ድረስ የሕዝብ ሃብትና ንብረት መሆኑ፣ የሞኞች ፈሊጥ ብለው ሳይሳለቁበት አልቀሩም!

ከሕወሃት አባሎች በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያ የልማት ባንክ ዋነኛ ተጠቃሚ ዜጎች ሳይሆኑ የውጭ ኢንቬስተሮች መሆናቸው ገሃድ ነው። እነርሱም ቢሆኑ ባለቤት የናቀውን አሞሌ ባለዕዳ አያከብረውም ሆነና፡ የፈለጉትን አደረጉ፥ የዘረፉትን ዘረፉ፥ እስከናካቴው አንዳንዶቹ ከባንኩ የተበደሩትን ገንዘብ እንኳ ሳይከፍሉ ወደ የሃገሮቻቸው መመለሳቸው (የአንዳንድ ዕርዳታ ሠጭ አውሮፓውያን፡ መካከለኛው ምሥራቅ ዜጎች፡ እሥራኤልና ሕንዶች) በተደጋጋሚ ሲጠቀሱ ነበር።

የኢትዮጵያ ሪፖርተርም ባለፈው ረቡዕ እትሙ “የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ካፒታል ለማሳደግ እጅግ አስፈላጊ ቢሆንም፣ የመንግሥት የፋይናንስ አቅም ደግሞ በቂ ስላልሆነ፣” እንደ መንግሥት ዕዳ ተቆጥሮ (የኢትዮጵይ ሕዝብ የሚከፍለው)፣ “ልዩ የመንግሥት ዕዳ ሰነድ ለመሸጥ በአዋጅ እንዲፈቀድለት ተጠየቀ” ይላል።

በሌላ አባባል፥ ሕግን ፍትህ በሌለባት ኢትዮጵያ፡ የኢትዮጵያ ታክስ ከፋዮች ምንም ላልተጠቀሙበት የሕውሃት ሰዎች ዘርፈው ያዘረፉትን ገንዘብ እንዲከፍል ይገደዳል ማለት ነው። ከሁሉም የሚያናድደው፡ አብዛኞቹ የውጭ ኢንቬስተሮች ለሕወሃት ገንዘብ አሸሸዎች በመሆናቸው፡ እነርሱ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የክብር እንግዳ ተደርገው በየወቅቱ እየተመላለሱ የተዘረፈው ገንዘብ ጋር ግንኙነት ያደርጋሉ ማለት ነው።

ውጭ ያለው ገንዘብ፡ ሚስቶቻቸው፡ ልጆቻቸውና ዕቁባቶቻቸው በስማቸው አድርገው ነዋሪ በሆኑባቸው ሃገሮች የንግድ ድርጅቶች – ሲቻልም ሽርክና – ያቋቁሙበታል ማለት ነው። ሃገር ውስጥ ደግሞ ባላቸው ሥልጣን ከለላ ብዙ ነገሮች ከቀረጥ ነጻ በማስገባት (አሁን አዜብ መሥፍን በመለስ ፋውንዴሽን ስም እንደምታደርገው) አኗኗራቸውን ከአንደኛው ዓለም የአኗኗር ዘይቤ አሻሽለውት ከውጭም ወዳጅ ማትረፍያ አድርገውታል!

ዜጎች ከሚገምቱት በላይ ሃገራችን በሕውሃቶች ምክንያት የሌቦችና ዘራፊዎች ሲሳይ ሆናለች። ይህ ካልሆነ 17 ዓመታት በረሃ የክረሙ ‘የትግራይ ነጻ አውጭዎች” ዛሬ ያከበቱትን ሃብት፡ የተደላደለ ኑሮና ጣዕም (taste and style for lief) ከየት አመጡት – ካልዘረፉት በስተቀር?

ሪፖርተር ይህንን እንደሚከተለው ያብራራዋል፦”በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በኩል አልፎ ለፓርላማው ማክሰኞ መጋቢት 13 ቀን 2008 ዓ.ም. የቀረበው ረቂቅ ሰነድ፣ የልማት ባንክን ካፒታል ለማሳደግ የሚውለው ገንዘብ በልዩ የመንግሥት ዕዳ ሰነድ (ቦንድ) እንዲከፈል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ ይህንኑ የሚፈቅድ አዋጅ እንዲታወጅለት ጠይቋል፡፡”

ቦንዱ በአንድ በኩል የባንኩን የገንዘብ ፍላጎትና በኪሣራው ምክንያት የደረሰበትን ክስረት ሲፈወስ፥ በሌላ በኩል ደግሞ እነአርከበ ዕቁባይ በየሣምንቱ መገናኛ ብዙኃን ላይ በመውጣት የሌለውንና የማይኖረውን አለና ይመጣልም እያለ ለተጨማሪ መሬት ዘረፋ የሚጠቀምባቸውን ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማቋቋም በሚል ዘይቤ እንደገና የተስፋፋ ምዝበራ በሁለተኛው የአምስት ዓመት የልማት ዘመን 2016-2020 ለማካሄድ የሚጠቀሙበት ገንዘብ ይሆናል ማለት ነው።

ሪፖርተር እንዳሰባሰበው መረጃ ከሆነ፡-

  የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተከፈለ ካፒታሉ በአሁኑ ወቅት ሦስት ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በመንግሥት የታቀደው ወደ 7.5 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የባንኩን ካፒታል ለማሳደግ የሚያስፈልገውን ገንዘብ በአንድ ጊዜ ለማሟላት የመንግሥት የፋይናንስ አቅም የማይፈቅድ በመሆኑ፣ ካፒታሉን ለማሳደግ የሚያስችል ቦንድ ማውጣት አስፈላጊ እንደሆነ በረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ላይ ተጠቅሷል፡፡

  መንግሥት የልማት ባንክን ካፒታል ወደ 7.5 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ከሚፈለገው 4.5 ቢሊዮን ብር ውስጥ፣ 1.933 ቢሊዮን ብር ያህሉን ከተለያዩ ምንጮች አግኝቶ ለባንኩ ካፒታል እንዲውል አድርጓል፡፡ ቀሪውን 2.57 ቢሊዮን ብር በልዩ የመንግሥት ቦንድ (የዕዳ ሰነድ) በመሰብሰብ ለባንኩ ካፒታል እንዲያውል በአዋጅ እንዲፈቀድለት ነው የጠየቀው፡፡

  በረቂቅ አዋጁ ላይ እንደተገለጸው ልዩ የመንግሥት ዕዳ ሰነዶች ከወጡበት ጊዜ አንስቶ ከአምስት ዓመታት የችሮታ ጊዜ በኋላ በአሥር ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተከፍለው እንደሚጠናቀቁ ተገልጿል፡፡ በዚህ መሠረት የሚወጣው ልዩ የመንግሥት ቦንድ (የዕዳ ሰነድ) ወለድ እንደማይከፈልባቸውም ተገልጿል፡፡

  የተወሰኑ የምክር ቤት አባላት የቦንድ ሽያጩ ከመፈቀዱ በፊት ሽያጩ የሚከናወነው አገር ውስጥ ይሁን ወይስ ከአገር ውጭ እንዲጣራላቸው፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሒሳብ እንዲመረመርላቸው ጠይቀዋል፡፡

  መንግሥት የአጭር ጊዜ የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥመው የግምጃ ቤት ሰነድ ጨረታ በመጠነኛ ወለድ ለፋይናንስ ተቋማት የሚያቀርብ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ መንገድ የሚገኝን ገንዘብ ግፋ ቢል በ365 ቀናት ውስጥ እንዲመልስ ይገደዳል፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት የገንዘብ ፍላጐቱን ለማሟላት በተለምዶ የህዳሴ ግድብ ቦንድ ተብሎ የሚታወቀው (የመንግሥት ቦንድ) ሲሆን፣ በዚህ መንገድ የሚሰበሰብ ገንዘብ በአምስት ዓመት ውስጥ መከፈል አለበት፡፡ ለፓርላማው የቀረበው ልዩ የመንግሥት የዕዳ ሰነድ ረቂቅ አዋጅ በ15 ዓመት ዕዳው እንዲከፈል የሚያደርግ ነው፡፡

 

%d bloggers like this: