ሕወሃት መሬታቸውን የዘረፋቸውን ገበሬዎች እንደገና ሐሙስ በስብሰባ ሲያወናብድ ውሎ ከፋና ሃሰተኛ ዘገባ ጋር ተጋለጠ!

2 Apr

በከፍያለው ገብረመድኅን —The Ethiopia Observatory (TEO)
 

መጋቢት 23/2008 (ኢሳት ዜና):- ከነባር እራሻ መሬታቸው የተፈናቀሉ አርሶአደሮች በቂ ያልሆነ ካሳ ሳይከፈላቸው ከቀያቸው በመነሳታቸው ሳቢያ በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ላይ የደርሰባቸውን አስከፊ ሰቆቃ የአዲስ አበባ መስተዳድር በጠራው ስብሰባ ላይ በምሬት ተናግረዋል።

መንግስት ትንሽ ቦታ እንኳን ሳይሰጣቸው ከይዞታቸውን እንዲነሱ በመደረጋቸው ለአስከፊ ሕይወት መዳረጋቸውንና ለወደፊቱም ልጆቻችንን ምን እናብላቸው? እንደ እቃ ሜዳ ላይ ተጥለናል ሲሉ ተፈናቃይ አርሶ አደሮቹ ያጋጠማቸውን የሕይወት ተግዳሮቶች በስብሰባው ላይ አሰምተዋል።

ለአስር ዓመታት ተብሎ የተሰጣቸው ካሳ አግባብ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ ከአስር ዓመታት በኋላስ ገበሬ በምድር ላይ የለም ወይ እባካችሁ መፍትሔ ስጡን? ሲሉ አንድ አርሶአደር ብሶታቸውን ገልፀዋል።

አንድ ካሬ ቦታ በ29 ብር ሒሳብ ተተምኖ የተሰጣቸው ክፍያ አግባብ አለመሆኑን ከአንድ ኪሎ ምስር ባነሰ ዋጋ መሬታቸውን መነጠቃቸውንና እንጀራ ስንበላ የነበረው ዛሬ ቆሎ ለመብላት የማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ብለዋል። የማዘጋጃ ቤት ኃላፊዎች የያዛችሁት ይዞታ ትርፍ ነው መሬት ነዳጅ ነው ለገበሬ ልጅ አታስቡ። መባላቸውንና ችግራቸውን ሰሚ አካል ማጣቸውንም ተፈናቃይ አርሶአደሮቹ አክለው ተናግረዋል። ዘገባውን በቅድሚያ ያቀረበው ሸገር ሬዲዮ ነው፡፡
===========
 

 

ይኽው ተመሳሳይ ስብሰባ ላይ የተካሄድውን ‘ውይይት’ አስመልክቶ ፋና የዘገበው ቅጥፈት እንደሚከተለው ነበር፦

በአዲስ አበባ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚሰሩ ሁለት ፅህፈት ቤቶች ሊቋቋሙ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን፣ አቅመ ደካሞችንና አረጋውያንን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚሰሩ ፅህፈት ቤቶች ሊቋቋሙ ነው።

ለውይይት የቀረቡት ሁለት ረቂቅ ደንቦች ሁለት ቋማትን ለማቋቋም የተዘጋጁ ናቸው።

ተቋማቱም በፅህፈት ቤት ደረጃ የሚቋቋሙ ሆነው የራሳቸው ተልእኮ እና ተግባር አላቸው።

አንደኛው የልማት ተነሺ አርሷ አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ሲሆን፥ ካሁን ቀደም በልማት ምክንያት ከይዞታቸው የተነሱና የተሰጣቸውንም ካሳ አሟጠው ተጠቅመው ለችግር የተጋለጡ አርሷ አደሮችን በጥናት የመለየት እንዲሁም መልሶ የማቋቋም ኃላፊነት ይኖረዋል።

የማህበራዊ ዋስትና ፈንድ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ለማህበራዊ ችግር የተጋለጡ የከተማዋ ነዋሪዎችን ከችግራቸው የመታደግ ሚናን እንደሚጫወት በውይይቱ ላይ በቀረበው ረቂቅ ደንብ ተጠቅሷል።

ውይይቱ በሁለቱ ረቂቅ ደንቦች ላይ ከህዝብ ጋር ለመምከር ቢዘጋጅም ዋና መወያየ ሆኖ የዋለውና ሰፊ ኃሳብ የተሰነዘረበት በልማት የተነሱ አርሷ አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ነው።

በውይይቱ የተካፈሉ የአርሷ አደር ተወካዮች የካሳ ክፍያውን ከተቀበሉ በኋላ በዘላቂነት ህይወታቸውን ሊመሩበት የሚችል ስራ ላይ አላዋልነውም ሲሉ ተደምጠዋል።

እኛ ዘር እንጂ ብር የማስቀመጥ ልምዱ አልነበረንምና በእውቀትም የሚደግፈን አካል ባለመኖሩ ገንዘቡ በጥቂት ግዜ ውስጥ ሊያልቅ ቻለ ያሉም ነበሩ።

ሌላው የልማት ተነሺ አርሷ አደሩን ለችግር ዳርጓል ተብሎ የተቀመጠው ምክንያትም የካሳ ክፍያ መጠን በቂ ያለመሆን ነው።

በመሆኑም የካሳ ክፍያን መንግስት በሚያቀርባቸው አማራጭ የገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ በማዋል በዘላቂነት ህይወታቸውን ለመቀየር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ሰራተኛ እና ማሀበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ግዛው እንደሚናገሩት፥ የፕሮጀክት ፅህፈት ቤቱ አላማ በተለያዩ የልማት ተነሺ ሆነው በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ አርሶ አደሮችን በጥናት የመለየትና መልሶ ማቋቋም ነው።

ለችግር የተጋለጡ አርሷ አደሮችን ለመለየት የሚያችል መረጃ መኖሩንና በጥብቅ ክትትል እንደሚሰራም ነው ሃላፊው የተናገሩት።

በከተማ አስተዳደሩ በጀት የሚንቀሳቀሰው የልማት ተነሺ አርሷ አደር መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጄክት ፅህፈት ቤት ካሁን ቀደም ለችግር ለተዳረጉ አርሷ አደሮች ቋሚና ዘላቂ የገቢ ምንጭ ማስገኛ ፕሮጀክቶችን እውን ከማድረግ ባለፈ ከዚህ በኋላ ለተመሳሳይ እክል እንዳይጋለጡ የሚያስችሉ የጥናት ሀሳቦችንም ያቀርባል።

ከዚህ በኋላ ለልማት ተነሺ አርሷ አደር የሚከፈለው ካሳ ወቅታዊውን የኢኮኖሚ ሁኔታ እና ዋጋ ያገናዘበ እንዲሆን ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን ይሰራል የሚል ነው።

ረቂቅ ደንቦቹ ከመፅደቃቸው በፊት የህዝቡን ፍላጎት ያማከሉና ጥያቄዎችንም የመለሱ እንዲሆኑ ለማስቻልም ሌሎች ሰፊ ውይይቶች እንደሚደረጉባቸው ነው አቶ ኤፍሬም የገለፁት።

በዳዊት መስፍን (ለፋና)
============
 
በሸገር የተዘገበው ሳናዳምጥ፣ አርብ ማምሻውን ብሎጋችን (TEO) የሚከተለውን ጽሁፍ ወዲያውኑ አወጣ፦
መሬታቸው የተመዘበረባቸን ገበሬዎች ሕውሃት ራሳቸውን ወንጀለኛ አደረጋቸው – ከታሪክና ፍርድ ለማምለጥ ወይንስ የዘረፋው አልበቃኝም ምልክት?

ዛሬ በተለቀቀ ዜና መሠረት፡ የሕወሃት አስተዳደር በኦሮሚያ ያጋጠመውን እምቢተኝናትና ሕዝባዊ አመጽ ለማስተንፈስ ኃይል በመጠቀም አያሌ ዜጎችን ገድሏል፤ በሕይወት ያሉትን ሌአያሌዎችን ክፉኛ ጎድቷል።

በዚህ ሁኔታ ውስጥም ሃገራችን ወደ ሰላም ጎዳና ለመመለስ ተአምር የሚጠይቅባት ሁነታ ላይ ትገኛለች።

ኃላፊነት በጎደለው ሥነ ምግባር፥ ምዕራባውያን ሃገሮችም ችግሩን አቃለው እንደሚመለከቱት ሳይሆን፡ እንዲያውም በእነርሱ ድጋፍና አይዞህ ባይነት ሕወሃት በሚወስዳቸው ዜጋዊ ኃላፊነት በጎደለው እርምጃዎች ምክንያት፡ የሕወሃት አስተዳደር ሃገራችንን ወደ አደገኛ አቅጣጫ እንዲወስዳት እያበረታቱት ነው።

ለምሣሌ በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ፥ የሃገራችን ችግሮች ክፉኛ መከርፋት ሲጀምሩ፣ ሕወሃት በከተሞችና በገጠር ድሆች መበራካታችውና የተለየ የነፍስ አድን ዕርዳታ እንደ ሚያስፈልጋቸው ደጋግሞ አሰምቷል። አያሌ የከተማዋ ነዋሪዎች አንዴ ራሳቸውን ለመመገብ የማይችሉ ድሆች መሆናቸውን ነግሮናል። የብዙዎቹን መደኸየትም አስመልክቶ እንዲህ እያደረኩ ነው በማለት መለከት ደጋግሞ ነፍቷል – ምናልባትም በሴፍቲ ኔት ስም ሌላ መቶ ሚሊኖች ገቢ ለማሰባበስብ ያሰላው ነገር ይኖር ይሆናል።

የከተማ ልማትና ቤቶች ግንባታ ሚኒስቴር በ2014 ባወጣው ጥናታዊ ሪፖርት ከ15-24 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ዜጎች 16 ከመቶ ሥራ አጥ በሆኑባት አዲስ አበባ፡ ቤት የሚወሰድ ክፍያ ከእጅ ወደ አፍ ለመድረስ ባቃተበት ሁኔታ የወጣት ሥራ አጡ ቁጥር 25 ከመቶ እንደደረሰ አመልክቶ ነበር። ይህም በዚያን ወቅት ከድህነት ወለል ሥር ናቸው ከተባሉት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር ተመጣጣኝ መሆኑ ተጠቁሟል።

እንዲህ በተናጋው መሠረት ላይ፥ በሕገ ወጥ መንገድ በሕወሃቶች ትዕዛዝና በሰዎችቸው ተጠቃሚነት በከተማ ቤቶች ማፈራረስና በገጠር ደግሞ ቀጥተኛው የመሬት ዘረፋ የጠለቁት ችግሮች ምንጮች መሆናቸውን ተጠቃሚው ካልሆነ በስተቀር፡ ጤነኝ አዕምሮ ያለው ዜጋ አይስተውም! ይሀ ለዓመታት የተጠራቀመው ሕዝብን የማህደኸየት እርምጃ፡ ጉልበት ያላቸውን ወደ ኩሊነት፣ ሴቶቹን ደግሞ ለሴተ አዳሪነት መዳረጉ ችግሩን በቅርብ ከተከታተሉት ለመገንዘብ ትችሏል።
===============

ሁኔታው እንዲህ ሆኖ ሳለ፡ ዛሬ በአዲስ አበባና በዙርያዋ መሬታቸውን “በልማት ስም” በእሳተ በላ የሕወሃት ሰዎችና ደላሎቻቸው ተደልለው ‘የተነጠቁትን’ “ገበሬዎችና አቅመ ደካሞችንና አረጋውያንን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚሠሩ ፅሕፈት ቤቶች ሊቋቋሙ ነው” ብሏል የሕወሃት አስተዳደር።

እጅግ የሚያሳዘነው ግን ያ ሁሉ የዜጎች ሕይወት ተለይ በኦሮሚያ በአጋዚ በከንቱ ከተቀጠፈ በኋላና በዚህች ወቅትም እየተቀጨ ባለበት፥ ሕወሃት ጥፋተኝነቱን በዜጎች ላይ እየረጨባቸው ነው – ከአሽሙረኛ የፓርላማ ይቅርታ ጥየቃውም በኋላ!

ለችግራቸው ምንጩ የሕወሃቶች የመሬት ዘረፋ መሆኑ እየታወቀ፣ ዛሬ ሕወሃት የእነዚህን ሁለት ተቋሞችን መቋቋም አስመልክቶ በሠጠው ማብራሪያ፡ የልማት ተነሺ አርሷ አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት “በልማት ምክንያት ከይዞታቸው የተነሱና የተሰጣቸውንም ካሳ አሟጠው ተጠቅመው ለችግር የተጋለጡ አርሷ አደሮችን በጥናት የመለየት እንዲሁም መልሶ የማቋቋም ኃላፊነት ይኖረዋል” ይላል።

ለዚያውም ቅንጣት ለገበሬዎቹ ክፍለው፣ እነርሱ ወደ ቢሊዮን ሲቀይሩት፥ ያቺንም ቅንጣት – ካሣ ብሎ ዛሬ ከመተርጎም ባሻገር፡ ገንዘቡን በሚገባ አልተጠቅሙበትም በማለት ወደ ወቀሳ ለማምራት ደፍረዋል።

ይህንን በምክንያትነት አቅርቦ በድህነት በመሠቃየት ላይ ያሉትን ዜጎች ኃላፊነት የጎደላቸው በማስመሰል እነርሱን ማሳጣት፡ እንደተለመደው ሕወሃት የራሱን ብልግና ለመሸፋፈን የሚያደረገው የኅሊና ቢስ ባህሪው መገለጫ ነው።

ግለሰቦቹ ወደ ድህነት አዘቅት የወረዱት፡ ከላይ እንደተገለጸው፡ የሕወሃት አልጠግብ ባዮች ተመጣጣኝ ዋጋ ሳይከፍሉ፡ እስከ ሁለት መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኦሮሞችን ከአዲስ አበባ ዙሪያና ሌሎች አቅም ደካማ ኢትዮጵያውያንን በጉልበት አፈናቅለው ሜዳ ላይ በመወርወራቸው መሆኑ ከማንም ኢትዮጵያዊ የተሠውረ አይደለም።

ሕወሃት ይህ ጠፍቶበት ሳይሆን፡ ለሕዝብ ያለው ንቀት መለኪያው ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ከውጭ በእነዚህ ድሆች ስም ፕሮጀከት እየተዘጋጀ – እንደ ገጠሬው 10 ሚልዮን ያህሉ – መለመኛ እየተደረገ ነው። በዚህም ረገድ በ11 ከተሞች 600,000 ድሆችን መልሶ ለማቋቋም በሚል የ$450 ሚሊዮን ፕሮጄክት (Urban productive Safety Net Project – UPSNP) ተዘጋጅቶ፣ ከዚህ ውስጥ $300 ሚሊዮኑን የዓለም ባንክ ባለፈው ጥር 12 ቀን 2016 ዓ.ም. በገንዘብ ሚኒስትሩ አብዱላዚዝ መሃመድና በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ተወካይ ካሮላይን ተርክ መካከል የመጀመሪያው አምስት ዓመት የከተማ ተመጽዎቾችን መርጃ ፕሮጄክት ተፈርሟል።

ይህ የብድር ገንዘብ፡ ለሕወሃቶች ሃላፊነት ሳይሆን ከሰማይ የወረደላቸው ሲሳይ ነው!

በሃገር ደረጃ የዚህ ሁኔታ አሳሳቢነት ምንም አያጠርጥርም። አሜሪካ፡ እንግሊዝና ሱዳን ምንም ያህል ዕርዳታና ድጋፍ ለወዳጃቸው ቢያሠልፉም፡ ከሕዝብ ጥላቻ፣ አመጽና አልገዛም ባይነት በኦሮሚያ፣ ጎንደር፣ ደቡብ ኦሞ፡ ጋምቤላና ወዘተ ልቡ ከሸፈተው የኢትዮጵያ ወጣቶች ጋር ተዳምሮ ያ በቂ መከታ ሊሆነው እንደማይችል ሕወሃት ሊገነዘብ ይገባል።

ሌላው የዛሬው ዜና ያሳዘነኝ አንዱ ነገር፡ ሕወሃት ከረጂዎቹ ጋርና ከመሬት ተዘራፊዎቹ ገበሬዎች ጋር ተወያይቻለሁ ማለቱ ነው። ያለፉት 25 ዓመታት ስለ ሕወሃትና ስብሰባ ያስተማረን ነገር ቢኖር፡ የራሱን ሰዎች በስብሰባ አዳራሽ በመስግሰግ እርሱ የጋታቸውን ሕዝቡ ላይ አውርደውበት፡ ያንን ሕዝበ ውሳኔ የማድረግ ስታሊናዊ አሠራር ነው። የዛሬውም ከዚያ የተለየ አይሆንም!

የኦሮሞች ተቃውሞ ኅዳርና ታህሣስ 2015 ላይ መጋም ሲጀምር፡ ሩቅ ሳንሄድ፡ የሴቶች ድርጅቶች፡ የዚያ ድርጅቶች፡ የአባቶችና አያቶች ስብሰባ ተቃወሟቸው አወገዟችው በማለት ብዙ ለማምታት ተሞክሯል። ያን ጊዜም ሕወሃት የተጥቀመው ይህንን ያረጀ ያፈጀ የማጨበርበሪያ ዘዴውን ነው – በጊዘው ሁኔታውን በመዘገብም ኢትዮጵያውያንም ሆኑ የውጭው ዓለም እንዲያውቀው ለማድረግ ተሞክሯል!

ዛሬ በዜና እንደተነገረው፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይቱ በሁለቱ ረቂቅ ደንቦች ላይ ከህዝብ ጋር ለመምከር ቢዘጋጅም ዋና መወያየ ሆኖ የዋለውና ሰፊ ኃሳብ የተሰነዘረበት በልማት የተነሱ አርሷ አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ነው ተብሏል።

በውይይቱ የተካፈሉ የአርሷ አደር ተወካዮች የካሳ ክፍያውን ከተቀበሉ በኋላ በዘላቂነት ህይወታቸውን ሊመሩበት የሚችል ስራ ላይ አላዋልነውም ሲሉ ተደምጠዋል። እዚህ ላይ እንደሚታየው በራሳቸው አንደበት መሬታቸውን የተዘረፉት ገበሬዎች ስብሰባው ላይ እራሳቸውን ወንጀለኛ እንዳደረጉ ሕወሃት ለወደፊት ታሪኩ ዛሬ ላይ ውንብድና ሲፈጽም ነው የሚታየው።

“እኛ ዘር እንጂ ብር የማስቀመጥ ልምዱ አልነበረንምና በእውቀትም የሚደግፈን አካል ባለመኖሩ ገንዘቡ በጥቂት ግዜ ውስጥ ሊያልቅ ቻለ” ያሉም ነበሩ – ፋና እንደዘገበው!
================

ሰለ ሴፍቲ ኔት (Productive -safety Net (PSNP) እስከተነሳ ድረስ፣ እንኳን የከተማውን እጅግ ውስብስብ የሆነውን፣ ሕወሃትና የዓለም ባንክ የሚሠሩትን እንደማላምን ከዓመታት በፊት አሳውቄያሁ። ያ እኮ የሚሠራ ቢሆን ኖሮ፥ በምግብ ራስን ለመቻል ሁኔታዎችን ገና ድሮ በማመቻቸት በረዳ ነበር።

ለነሩ ሴፍቲ ኔትን ምዕራባዉያን ይወዱታል። በአንድ በኩል፥ ምንም አልሠራም ተብሎ ወዳጃቸው የሕዝብ ተቃውሞ እንዳይጠናከርበት እንዳያድግ ወይንም እንዳይሞት የሚረዳ መሥፈርት የሌለበት ሕዝቡን በሥፍር እህል ለሕወሃት ተገዥ የሚያደርገው ወጥምድ ነው!

ስለሆነም፡ ሴፍቲ ኔት ትንሽ ምግብና ገንዘብ እየተሰጠው ሕዝቡን ጸጥ በማድረግ መንግሥትን ያጠናክራል።

በሌላ በኩል ደግሞ የPSNP ወጭ በተረጂ $53 ሲሆን፡ በባህላዊው ሰብዓዊ ዕርዳታ ማቅረብ መንገድ ወጭው በነፍሰ ወከፍ $169 መሆኑን የሚያመለክት ለእንግሊዝ ፓርላማ ኮሚቴ መቅረቡን ዘግቤ ነበር የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ!
 

ተዛማጅ:

  በምርጫ ማግሥት: ሕገወጥ መሬት ባለይዞታዎች ሕጋዊ ካርታ ተሰጣቸው – የሕወሃት ሰዎች ከ97 ጀምሮ በሕገ ወጥነት፥ ተንኮልና ነጠቃ የያዟቸውን እንደሚጨምር ታውቋል፤ እሪ በይ ኢትዮጵያ!

  State engineered land grab & corruption are alive and well in Ethiopia
  Addis Abeba continues homes demolition & land grab to make way for five-star hotels

  TPLF greed at its worst: Ethiopia’s ethnic minority regime members & families own 98% of investments in land in South Omo Valley – official thievery becoming cause for nation’s instability

  Hawassa aflame: TPLF land grab lust lurks behind big fire disasters in Ethiopia

  Addis Abeba in the throes of transformation: Anways, whose capital city is it? Part II

 

%d bloggers like this: