ፍትሕ ሚኒስቴር እንዳይፈርስ የሕግ ባለሙያዎች አማራጭ ሐሳባቸውን ለፓርላማ አቀረቡ! ለመሆኑ የሃገራችን ወሳኞቹ ጥያቄዎች የፍትህ ወይንስ የቅርጽና መዋቅሮች?

6 Apr

Editor’s Note:
 

  ይህ የፍትህ ሚኒስቴር መኖር ወይንም በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመተካት ጉዳይ፡ እስከዚህ ድረስ ውስብስብና አወዛጋቢ ሊሆን ባለተገባ ነበር – በተለይም በዓለማችን ውስጥ የብዙ ሃገሮች ልምድ ሊያስተምረን የሚችላቸው በርካታ ትምህርቶች ሊገኙ ስለሚችሉ!

  ስለሆነም ከፍሬ ነገሩ ይልቅ፡ ማለትም ለኅብረተሰቡ ሊሠጥ ከሚገባው ፍትህ አንጻር ሣይሆን ትኩረቱ ገላዊ ጉዳዮች ላይ በመሆኑ፡ ውጤቱ ፍሬያማ ይሆናል የሚል ተስፋ አልሰጠንም። እንዲያውም ሕወሃት መቶ በመቶ በሚቆጣጠረው ፓርላማ ውስጥ ይህንን ውይይት አካሄደ መባሉ የሚያስገኘውን በጎነት ተቋዳሽ እንዳያደርገው እንሠጋለን። ስለተሰብሳቢዎቹ ብዙ ባናውቅም፣ ሕወሃት እንዲህ ያሉ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ግብዣ የሚሠጣቸው የሚተማመንባቸውን ‘የራሱን ሰዎች’ መሆኑም መዘንጋት የለበትም!

  ዕውነቱን ለመናገር ከሆነ፣ ውይይቱ አንኳር ፍሬ ነገሩን በመዘንጋት፥ ቅርጽ ላይ በማተኮሩ – ከማንም እንድልወገኑ ዜጎች – ፍሬያማ የሆነ ውጤት ያስገኛል ብለን ለማመን ተቸግረናል።

  በሌላ አባባል፡ በአሁኑ ወቅት ከሕግ አሠራርና ለኅብረተሰቡ ፍትህን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ዋናው መታየት ያለበት የፍትሕ ሚኒስቴር መኖር ወይንም እርሱን በማፍረስ፡ በምትኩ የአቃቤ ሕግ ውክልና መቁቋም መሆኑ በየጊዜውና በየደረጃው በአሠራር እየታየ ምንጊዜም ሊሻሻልና ሊስተካከል የሚችል ነገር ነው። በዓለም ላይ ሁለቱንም አጣምረው የሚሠሩ፡ ለሕዝባቸው ፍትህን የዜጎች መብትና መንግሥታዊ ግዴታቸው አድርገው የሚኖሩ ዲሞክራሲያዊ የሆኑ ሃገሮች አሉ!

  የኅብረተሰባችን መሠረታዊው ችግር – በተለይም ለፍትህና ለሕግ ተፈጻሚነት ዕንቅፋት የሆነው – የሕወሃት አምባገነንነት በመሆኑ፡ ያ ጥያቄ በሰክነ አዕምሮና የሙያ ብቃት ከኅብረተሰቡ ዘላቂ ጥቅሞች አንጻር ሊታይና ሊገመገም የሚገባው ይመስለናል።

  ለምንደነው ለዚህ ትኩረት የሠጠነው?

  የሕግ የበላይነትና የሁሉም ዜጎች እኩልነት በማይከበርባቱት ሃገር፥ የሁሉም ዜጎች ተጠያቂነት በሕጉ መሠረትና ሥነ ሥርዓት ተፈጻሚነት እስካላገኝ ድረስ – ያላንዳች ዘለልነት – የሕግ ተፈጻሚነት ትርጉም አልባ ይሆናል። የዜጎችንም እምነት አያተርፍም። ለዚህም ዋናው ምክንያት በዘር አሠራር ላይ የተመሠረተው ሕወሃት በሃገራችን እርሱ ከሚፈፈልገው ውጭ ለሆኑት ሕጎችና ተቋሞች እንዲሁም አሠራሮች ተጻራሪ በመሆኑ፡ በዚያው መጠን ኅበረተሰባችንን ሲያጉላላና ፍትህ ሲነሣ ኖሯል!

  ታዲያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዴት ነው የመዋቅር ለውጥ የሕጎችን አሠራርና አፈጻጸም ሊያሻሽል ይችላል የሚል አስተሳሰብ ይዞ ፍትሃዊነትን ወደጎን በገፋ ጉዞ የኅብረተሰቡን አመኔታ መጎናጸፍ የሚቻለው? ይህ ችግር በየቀኑ ቀርቶ በየሰዓቱ ሊታሰብና አስቸኳይ መፍትሄ የሚሻ ይመስለናል።

  የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች፥ የባለሃብትና ንብረት ባለቤትነት በትክክልና በወጥነት በማይከበሩባት የሕወሃት አሠራር በኢትዮጵያ፡ የዜጎች እኩልነት ምኞት ብቻ በሆኑባት፡ የመናገርና የመሰብሰብ ነጻነት በሌለበት ሁኔታ፥ የሕግ ተፈጻሚነት ወገናዊ በሆነበትና እንዲሁም ፍትህ የዜጎች መብት ሣይሆን፡ ጥጋበኛና ቀጣፊ የሕወሃት ካድሬዎች የቀኑ ስሜት መገለጫ ሆኖ፡ ቀደምትነት ሊሠጣቸው የሚገቡ ተግባሮች፡ በዜጎችና በሃገራችን ጉሮሮ ላይ በተሸነቆረው ሕወሃት ምክንያት በእንጥልጥል ቀርተዋል።

  በመሆኑም ከሕጉ መዋቅሮች በፊት ቅድሚያ ሊሠጠው ይገባል ብለን የምናምነው፡ የፍትህ ጉዳይ በመሆኑ፣ በዚህ ረገድ ሕወሃት ፈቃደኝነት እንደሌላው ደጋግሞ ስላሳየ፥ በአስፈላጊው መንገድ መንቅሮ – ብትፈልጉ መንግሎ – ማስወጣቱ ነው!

  ዛሬ በፓርላማ የተሰበሰቡት የሕግ ባለሙያዎች ያስታወሱን ጥንታዊቷ ሮማ ከክርስቶስ ልደት በፊት የገመመችውን ችግሮች ሥርና መሠረቱት አበክረው እንደሚያውቁ አንጠራጠርም። ጎራ በመለየት ለዘመናት በመኳንንቱና (patricians) ተራው ዜጋ (plebeians) ታግለውበት የሮም ሕግ (Roman Law) ሰብዓዊ መብቶችን በየደረጃው ያለፍላጎቱ እንዲቀበል መድረጉንና በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል የነበረው ግልጽና ሥውር ትግል/መከፋፈል ለዓለም የበጀ አስተዋጽኦ አድርጓል።

  አፍሪካ ውስጥ ኢትዮጵያ ቀደምት የሮማን ሕግ ተቀባይ ሃገር ብትሆንም፡ በየዘመኑ የነበሩት መኳንንት/ገዥዎች ጥቅሞቻቸው ላይ በማተኮራቸው መንፈሱም፡ አሠራርም ሆነ በመዋቅር ደረጃ ፍትህን አስፈጻሚ ለመሆን አልበቃም! የሕግና ፍትህ መንፈስ በሃገራችን ሊሠርጽ አልቻለም። በዚህም ምክንያት፡ ዛሬ ሃገራችን ያለችበት ሁኔታ ሮም ከክርስቶስ ልደት በፊት ከነበረችበት ይወዳደራል።

  ሮምም ብትሆን፥ በሕግ አለመኖር በማሳበብ መኳንንቱ ሕግ፡ መዋቅርና ተወካዮቻቸው ላይ በመተማመን የበላይነታቸውን ለብዙ ምዕተ ዓመታት ቢያስችላቸውም – ከታሪክ እንደምነገነዘበው – ይህ ግን የሮምን መጨረሻ አላሳመረውም! በዚህም ምክንያት ነው ታዋቂው የታሪክ ተመራማሪ Edward Gibbon The History of the Decline and Fall Of the Roman Empire በተሠኘው መጽሐፋቸው (Chapter 44) ስለ ቄሣር ሕግጋት ሲተርኩ፡ ስለተፈጻሚነት ድክመት ያነሱትን ከዚህ በታች የሠፈረውን ልብ ብሎ መመርመር ያስፈልጋል፡-

   ” [I]n the possession of legislative power, he [Caesar] borrowed the aid of time and opinion; and his laborious compilations are guarded by the sages and legislature of past times”

  እንግሊዝ ሃገር መንግስትንም በሚገባ ለሕዝብ ተጠያቂ ያደረገው እስከ 17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ የተካሄዱት ትግሎች መሆኑም ይታወቃል። እንዲሁም የፈረንሣይና የአሜሪካ አብዮቶች!

  ስለሆነም፥ ሕወሃትም የሚያደርገው በመዋቅርና በአሠራር በማሳበብ፡ ዜጎች በመብቶችና ነጻነት ዕጦቶች ታፍነው የሚኖሩባት እንድትሆን በመምረጡ፡ የሃገራችን ሁኔታ ዛሬ ካለበት አስከፊ ሁኔታ – በተራ የፖለቲካ ውንብድና ብቻ ወደ ተሻለ ሁኔታ ሊሸጋገር ይችላል ብሎ ማሰቡ አንድም የዋህነት አለያም ዕብደት ነው!

  እኛ እንደውም በአሁኑ ወቅት ሕወሃት የዜጎች ጨፍጫፊ በሆነባት ሃገር ውስጥ፡ ሕወሃት ይህንን አጀንዳ ይዞ የቀረበበት ሁኔታ ራሱን የቻለ ደባ ይኖረው ይሆናል የሚል ጥርጥር አሳድሮብናል! ሌላው ቀርቶ ለምንድነው ለዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን ገፎ አሳሪና ገራፊ የወንበዴ መንግሥት የሆነው?

  ከላይ የተነሳንበትን ዋነኛውን ችግር በሃሣባችን ይዘን፡ ሕገ መንግሥቱ ባለፉት 20 ዓመታት ለኢትዮጵያ ችግሮች ብዙ የሚያስኬድ ሆኗል! ነገር ግን ለምን ሕወሃትን ወደ ሕገ መንግሥታዊ መንግስት አልለወጠውም ለሚለው ጥይቄ መልሱን ማግኘት አልቻልንም!

===============
 

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 

    * የሙስናና የግብር ወንጀሎች ምርመራ ለፖሊስ እንዲተላለፍ መታቀዱ ላይም ጥያቄ ተነስቷል

ፍትሕ ሚኒስቴርን ከአስፈጻሚ አካላት ማቋቋሚያ አዋጅ በመሰረዝ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የማቋቋም እንቅስቃሴ ላይ የፓርላማው የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያዘጋጀው መድረክ ላይ የተገኙ የሕግ ባለሙያዎች፣ ፍትሕ ሚኒስቴር እንዳለ ሆኖ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንዲቋቋም ሐሳባቸውን አቀረቡ፡፡

መጋቢት 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፓርላማ ቀርበው ለቋሚ ኮሚቴው ለዝርዝር ዕይታ ከተመሩት ረቂቅ አዋጆች መካከል የአስፈጻሚ አካላት ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ ላይ የፍትሕ ሚኒስቴርን ማቋቋሚያ መሰረዝ አንዱ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ነው፡፡

ይህ ረቂቅ አዋጅ የተበተኑ የዓቃቤ ሕግ ሥልጣኖችን በአንድ በመሰብሰብ የሚያደራጅና የፍትሕ ሚኒስቴር ሠራተኞችን ለሚያደራጀው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሚያስተላልፍ ነው፡፡ በመሆኑም የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የዓቃቤ ሕግነት ሠራተኞች በሙሉ ወደሚቋቋመው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንዲዛወሩ፣ እንዲሁም የእነዚህ ተቋማት ወንጀል የመመርመር ሥልጣን ወደ ፌዴራል ፖሊስ እንዲተላለፍ በረቂቁ ተካቷል፡፡

በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሕዝባዊ ውይይት መጋቢት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ያደረገው የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፍትሕ ሚኒስቴር እንዳለ ሆኖ እንዲቀጥልና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ራሱን ችሎ የመክሰስ ሥልጣን ኖሮት ብቻ እንዲደራጅ፣ የሕግ ባለሙያ ከሆኑ የውይይቱ ተሳታፊዎች ሐሳብ ቀርቦለታል፡፡

ሐሳባቸውን ካቀረቡ በርካታ ባለሙያዎች መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግና አስተዳደር ጥናቶች ኮሌጅ መምህር የሆኑት አቶ ሲሳይ መንግሥቴ፣ ‹‹የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ የተቋሙ ኃላፊነት ተደርገው የተካተቱት የወንጀል ፖሊሲ ማውጣት፣ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች፣ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ፣ መንግሥትን ማማከርና የመሳሰሉትን ጉዳዮች ከፍትሕ ሚኒስቴር ወስዶ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከመስጠት ይልቅ፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዋነኛ ሥራው መክሰስ ሆኖ ክሱ ላይ አትኩሮ መሥራቱ አይሻልም ወይ?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት አማካሪ ሆኖ ሌሎች ክስ ከመክሰስ ውጪ ያሉ ሠራተኞችን ይዞ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግና አስተዳደር ጥናቶች ኮሌጅ መምህርና ጠበቃ የሆኑት አቶ ስሜነህ ኪሮስ በበኩላቸው በሰጡት ተመሳሳይ ሐሳብ፣ ‹‹ፍትሕ ሚኒስቴር ራሱን ችሎ የመንግሥት የሕግ አማካሪ ሆኖ ቢቆም?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ባለድርሻ አካላት ደግሞ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ ረቂቅ ላይ የሙስናና የግብር ወንጀሎችን የመመርመር ሥልጣን ለፌዴራል ፖሊስ የመስጠቱ አግባብነት ላይ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የምርመራ ክፍል ባልደረባ አቶ ፀጋዬ ወልደ ሩፋኤል በሰጡት አስተያየት፣ ከግብር ጋር የተያያዙ ወንጀሎች ምርመራ የሚጀመረው ከኢንተለጀንስ ቡድኑ በሚመጣ መረጃና በምርመራ ኦዲት በሚመጣ መረጃ መሆኑን ጠቅሰው፣ እነዚህን ቡድኖች ነጥሎ ምርመራውን ለፌዴራል ፖሊስ መስጠት የምርመራው ጥራትና ውጤታማነት ያስተጓጉላል የሚል ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

በተመሳሳይ ሐሳባቸውን የሰጡት የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባልደረባ፣ ሙስናን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ልምዱ በአብዛኛው የሚያሳየው የምርመራ ሥራው ለፀረ ሙስና ተቋም የተተወ መሆኑን ነው ብለዋል፡፡

የሰጡት ምክንያትም የምርመራ ሥራው ከሥራ አስፈጻሚው ገለልተኛ በሆነ ተቋም ሊመረመር ይሻላል በሚል ነው፡፡

በተጨማሪም ፌዴራል ፖሊስ አሁን ባለው ከፍተኛ የወንጀል ምርመራ ሥልጣንና ወንጀል መከላከል ተልዕኮ ላይ የሙስናና የግብር ወንጀሎችን እንዲመረምር መፍቀድ፣ በከፍተኛ ሁኔታ ጉልበታም አያደርገውም ወይ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጡ ለፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ ዕድል የሰጡ ሲሆን፣ ሚኒስትሩ በሰጡት አስተያየት በሌሎች አገሮች ጠቅላይ ዓቃቤን ሕግ ለብቻ፣ ፍትሕ ሚኒስቴርን ለብቻ የሚያደርጉ ቢሆንም ሁለቱንም በአንድ ማደራጀትን ደግሞ አይከለክልም ብለዋል፡፡

‹‹የአደረጃጀት ጉዳይ መንግሥት ወቅታዊ ዓላማውን የሚያስፈጽምበት የታክቲክ ጉዳይ ስለሆነ፣ ሁለቱን አካላት ይበልጥ እንዲናበቡ የሚያደርግ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በዓቃቤ ሕግ ላይ የሚፈጠረው የሥራዎች መደራረብ የተሻለ ውጤት እንዳይመጣ ያደርጋል የሚለው ሥጋት መነሳቱ ችግር እንደሌለው፣ ነገር ግን ለሥጋቱ መሠረታዊና ግልጽ የሆነ አደረጃጀት ይፈጠራል ብለዋል፡፡

ከፀረ ሙስና ኮሚሽንና ከገቢዎችና ጉምሩክ ጋር በተያያዘ የተነሱ ጉዳዮች በዋናነት የሚፈቱት ግንዛቤን በመፍጠር፣ ማለትም ሙስናን የማይሸከም ትውልድና የታክስ ማጭበርበርን የሚጠየፍ ማኅበረሰብ በመፍጠር እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

‹‹ፖሊስ እንዲመረምር የተሰጠውን ሲያልፈሰፍስ ሲገኝ ለምን ብሎ መጠየቅ የሚቻልበት ኃላፊነት ለዓቃቤ ሕግ ይሰጣል፡፡ እስካሁን ድረስ የነበረው አሠራር ግን ተቃራኒ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ዓቃቤ ሕግም በቀረበለት የምርመራ ውጤት በተገቢው መንገድ ተከራክሮ የማያስቀጣ ከሆነ፣ ፖሊስ ዓቃቤ ሕግን አንቆ መያዝ የሚችልበትን አሠራር ለመፍጠር ነው እየሞከርን ያለነው፤›› ብለዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በወቅቱ ከተደረገው ውይይት በርካታ ግብዓቶችን ማግኘቱን ገልጾ፣ በሌሎች መድረኮችም ረቂቅ አዋጁን የማዳበር ሥራ እንደሚያከናውን አሳውቋል፡፡
 
/ሪፖርተር
 

%d bloggers like this: