መንግሥታዊ አስተዳደር በሃገራችን አለመኖር!        በአዲስ አበባ የኦዲት ችግር ተስተውሎባቸው እንዲያስተካክሉ ከተነገራቸው 125 መስሪያ ቤቶች ምላሽ የሰጡት 9 ብቻ መሆናቸው ተነገረ!

11 Apr

የአዘጋጁ አስተያየት:
 

    “የዓሣ ግማቱ ከአናቱ” ይሉሻል ይኼ ነው! ለዝርዝሩ የሽፍታ/ወንበዴ መንግሥት በኢትዮጵያ የሚለውን ጽሁፋችንን ይመልከቱ!

=============
 

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 3፣ 2008 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ2002 እስከ 2007 ዓመተ ምህረት በአዲስ አበባ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በኦዲት ወቅት ችግር ተገኝቶባቸው እንዲያስተካክሉ ከተነገራቸው 125 መስሪያ ቤቶች መካከል ምላሽ የሰጡት ዘጠኝ ብቻ ናቸው አለ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት።

ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቱ ከ2002 እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ በተለያየ ጊዜ በከተማው የሚገኙ 125 የመንግስት ተቋማት ላይ የኦዲት ምርመራ አከናውኗል።

በጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም ላይ ነበር በተጠቀሰው ጊዜ ኦዲት ተደርገው ከግዥና ክፍያ ጋር የተያያዙ ችግሮች ታይቶባቸው ችግሮቹን እስከ መጋቢት 30፣ 2008 ድረስ አስተካክለው ወይንም እርምጃ ወስደው እንዲያሳውቁ ያደረገው።

ሆኖም ተቋማቱ በተቀመጠላቸው ገደብ ባለማሳወቃቸው በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ አሁንም በትክክል ምን ላይ እንደዋለ ማወቅ አልተቻለም።

ዋና ኦዲተር ጽጌወይን ካሳ እንደሚናገሩትም 125ቱ ተቋማት ኦዲት ሲደረጉ ከግዥና ከክፍያ አፈጻጸም ጋር የተያያዙ በርካታ ችግሮች የታየባቸው ሲሆን፥ ከእንዚህ መካከል በጨረታ መፈጸም ሲገባቸው ያለ ልዩ ፍቃድ ግዥ መፈፀም አንዱ ነው።

የከተማ አስተዳደሩ የግዥ መመሪያ ልዩ ሁኔታ ካላጋጠመ በስተቀር ግዥ በጨረታ ይፈፀም ቢልም፥ ከ2003 እስከ 2006 ዓ.ም 15 ተቋማት መመሪያውን ጥሰው ያለጨረታ 6 ነጥብ 9 ሚሊየን ብርን ለግዥ አውጥተዋል።

125ቱ መስሪያ ቤቶች በአምስት እና ስድስት አመት ውስጥ ኦዲት ሲደረጉ ካለ ህጋዊ ደረሰኝ 13 በከተማው የሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በአጠቃላይ የ4 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር ግዥ መፈፀማቸው ተመልክቷል፣ ዘጠኝ ተቋማትምየጨረታ አሸናፊ የሆኑ አቅራቢዎች እያሉ ያለበቂ ምክንያት አሸናፊ ካልሆኑ ተቋማት ግዥ ፈፅመዋል።

በሌላ በኩል የዋጋ ማወዳደርያ ሳያደርጉ ግዥ የፈፀሙ መስሪያቤቶችም ቢሆኑ ቁጥራቸው በርካታ ሲሆን፥ ከ2002 እስከ 2006 ዓ.ም ድረስ በዚህ መልክ የ5 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ግዥ በ19 ተቋማት ተፈፅሟል ።

በ2005 አዲስ ከተማ ከፍለ ከተማ ከ697 ሺህ በላይ ብር ቤት ሳይፈርስ የካሳ ክፍያ የተፈፀመ ሲሆን፥ በ2004 ዓ.ም ደግሞ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ለተቋራጭ ክፍያ በማዘግየቱ ምክንያት 7 ሚሊየን ብር ወለድ መክፈሉ ተጠቅሷል።

በተያያዘ 31 የከተማው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከ2002 እስከ 2005 ዓ.ም ገንዘብ አውጥተው አገልግሎት ሳያገኙ የተከፈሉ ቅድመ ክፍያዎችን ማስመለስ ባለመቻሉ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር መሰብሰብ ሲገባው አለመሰብሰቡም ተነግሯል ነው።

በጥቅሉ እነዚህ በርካታ ተቋማት እስከ መጋቢት መጨረሻ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ቢጠበቅም፥ ዘጠኝ ተቋማት ብቻ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ምላሽ ሲሰጡ፣ አንዳንድ ተቋማት አመታት ላስቆጠረ ጉዳይ ቀን ጨምሩልን ሲሉ ተደምጠዋል።

አንድ ተቋም ከ2002 እስከ 2007 የወጣበትን ሪፖርት እስከ አሁን ድረስ አላረመም ወይም አላሳወቀም ማለትም ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑንና ይህ ተግባር በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ በምን ላይ እንደዋለ ለማወቅ እንዳላስቻለ ጠቁመዋል።

ዋና ኦዲተር ጽጌወይን እርምጃን በተመለከተም በዚህ ጉዳይ ላይ “የእኛ ስራ ለሚመለከተው አካል ማስተላለፍ ነው እርምጃ መውሰድ ደግሞ የሌላው አካል ድርሻ ነው” የሚል ምላሽን ነው የሰጡት።

በሪፖርቱ መሰረት ምላሽ ያልሰጡ ተቋማትን አነጋግሮ በቀጣይ ጊዜ ዘገባን ለማቅረብ ፋናብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጥረት ያደርጋል።
 

ተዛማጅ፡

    Accounting standards: Ethiopia’s Achilles heel; country fares poorly by Sub-Saharan Africa standards

 

%d bloggers like this: