በሻሸመኔ ከተማ መጸዳጃ ቤት ላይ የተሠራው ቤተ አምልኮ ተደርምሶ የ10 ሰዎች ሕይውት አለፈ – ሕወሃት መንግሥት መሆን አቅቶት ዘረፋው ላይ ሲያተኩር፥ በሃገሪቱ ስታንዳርድ ጠፍቶ የዜጎች ሕይወት በከንቱ እየተቀጠፈ ነው!

11 Apr

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 3፣ 2008 (ኤፍ ቢ ሲ) በሻሸመኔ ከተማ ቀበሌ 10 አካባቢ ለመጸዳጃ ቤት የተቆፈረ እና በላዩ ላይ ለአምልኮ ስፍራነት የሚውል አዳራሽ የተገነባበት ጉድጓድ ተደርምሶ የ10 ሰዎች ሕይዎት አለፈ።

ትናንት ማምሻውን በደረሰው አደጋ ፀሎት ላይ የነበሩ 18 ሰዎች ሲሰምጡ፥ የ10ሩ ሕይዎት ወዲያውኑ አልፏል። ቀሪዎቹ 8 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል።

አማኞቹ ሕያው የእግዚአብሄር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የቃል ፕሮግራም ላይ እያሉ፥ በአዳራሹ ውስጥ ቀደም ብሎ ተቆፍሮ የነበረውና አሁን የአምልኮ ቦታ የተሰራበት ጉድጓድ ተደርምሷል።

በወቅቱ በሶስት ረድፍ የነበሩት የሃይማኖቱ ተከታዮች ሲሰምጡ፥ የአካባቢውና የፌደራል ፖሊስ አባላት ወደ ስፍራው በማምራትና ጉድጓዱን በኤክስካቫተር በመቆፈር ስምንቱን በሕይዎት ማውጣት ችለዋል።

ከሟቾቹ መካከል የ1 ዓመት ልጇን እንዳቀፈች ሕይዎቷ ያለፈው እናት ትገኝበታለች።

የከተማው ፖሊስ መምሪያ ምክትል ኢንስፔክተር ታምራት አበበ፥ የጉድጓዱ ርዝመት 7 ሜትር በመሆኑ ከምሸቱ 11:30 እስከ ሌሊቱ 7 ሰዓት ድረስ የሕይዎት ማዳን ስራው መከናወኑን ተናግረዋል።

ከጉድጓዱ በሕይዎት የተረፉት በመልካ ወዲያ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን፥ 5ቱ ላይ ከባድ የሚባል አደጋ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል።

ለመፀዳጃ ቤት ተቆፍሮ የነበረው ጉድጓድ ሙሉ በሙሉ በአፈር ሳይሞላ ከላይ ብቻ ተደልድሎ አዳራሹ መሰራቱ ለአደጋው መድረስ ምክንያት መሆኑም ነው የተነገረው።
 

ተዛማጅ:

  በስድስት ወር ውስጥ 41 ሰዎች በመንገድ ጉድጓዶችና ኩሬዎች ውስጥ ገብተው ሞተዋል

  የአንድ ት/ቤት አጥር ተደርምሶ 11 ተማሪዎች ላይ ጉዳት ደረሰ

  በዘመናችን ከሚታዩት መንግሥታዊነት ብቃት ማነስ የተከሰቱ የአስተዳደር ጉድለቶችና ለሕይወትና ንብረት ተጠያቂነት አለመኖር ተጠቃሽ መሆን ከሚገባቸው የአዲስ አበባ ምሣሌዎች መካከል

  በአዲስ አበባ ቡልጋሪያ አካባቢ ለህንፃ ግንባታ የተቆፈረ ጉድጓድ ተደርምሶ በ6 ሰዎች ላይ ጉዳት አደረሰ

  የፋብሪካዎች ዝቃጭ በአካባቢና በማኀበረሰብ ደህንነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ነው

  Ethiopia Among Worst in Traffic Safety – Addis Fortune

%d bloggers like this: