በጋምቤላ የተጨፈጨፉትን ወገኖቻችንን በተመለከተ የመከላከያ ሠራዊቱን ገመና የሚያጋልጡ መረጃዎች እየወጡ ነው!

21 Apr

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

ሚያዚያ ፲፫ ቀን ፳፻፰ (ኢሳት ዜና):-በአካባቢው የሰፈረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች የሙርሌ ጎሳ አባላት በተደጋጋሚ የሚፈጽሙትን ጥቃት ለመከላከል አለመቻሉን የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚናገሩ ምሁራን ገልጸዋል።

በደቡብ ሱዳን የሚገኙ የሙርሌ ጎሳ አባላት በኑዌር ኢትዮጵያውያን ላይ ፣ ሚያዚያ 7፣ 2008 ዓም ባደረጉት ጥቃት ከ230 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ140 በላይ ህጻናትና ሴቶች ደግሞ በታጣቂዎቹ ተወስደዋል። መንግስት የተጠለፉት ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ከበባ መጀመሩን ፣ ይሳካል የሚል እምነት እንዳለውም ገልጿል።

በአካባቢው ስላለው የደህንነት ሁኔታ ጥናት ያካሄዱ ምሁራን ፣ የጎሳው አባላት ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ስለሚፈጸሙት ጥቃትና መከላከያ ሰራዊቱ ስለሚሰጠው ምላሽ የሚያውቁትን መረጃ ለኢሳት አካፍለዋል። አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ምሁር፣ ስለ አካባቢው የደህንነት ሁኔታ ለማጥናት በአለም ባንክ ድጋፍ ለበርካታ ጊዜያት ወደ አካባቢው ተመላልሰው ሰርተዋል። “የሙርሌ ጎሳ አባላት በኢትዮጵያም ሆነ በደቡብ ሱዳን ውስጥ በሚገኙ ብሄረሰቦች ላይ እየተንቀሳቀሱ ለምን ጥቃት ይፈጽማሉ ? የኢትዮጵያ መካለከያ ሰራዊትስ ለምን በጋምቤላ የሚኖሩ የአኝዋክና የኑዌር ጎሳ አባላትን ከጥቃት አይከላከልም? “ በማለት የአካባቢውን ህዝብ ማነጋገራቸውን ምሁሩ ይገልጻሉ።

ምሁሩ እንዳሉት፣ ሙረሌዎች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ሰዎችን ሲገድሉና የቤት እንስሳትን ሲወስዱ የሰሞኑ ጥቃት የመጀመሪያ አይደለም። እርሳቸው በአካባቢው በተንቀሳቀሱባቸው 5 አመታት ውስጥ ተመሳሳይ ጥቃቶች በኢትዮጵያውያን ላይ ሲፈጸሙ ተመልክተዋል።

ሙርሌዎች ረጅም ርቀት መጓዝ የሚችሉና ተዋጊዎች ናቸው የሚሉት ምሁሩ፣ በአለም ላይ ያሉት የቀንድ ከብት በሙሉ የእኛ ሃብት ነው ብለው እንደሚያስቡም ያክላሉ ። “ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ ደቡብ ሱዳን ውስጥ የሚኖሩ የሌሎች ብሄረሰቦችን ከብት ሄደው ይዘርፋሉ። ከዚህ ቀደም ወደ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እየገቡ በአንድ ጊዜ እስከ 3 ሺ ከብት ዘርፈው ይመለሳሉ። የአካባቢውን ነዋሪዎችንም ይገድሉ ነበር።” ብለዋል።

ሙርሌዎች ወንዶችን እንጅ ሴቶችንና ህጻናትን እንደማይገድሉ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚናገሩ የገለጹት ምሁሩ፣ ሙርሌዎች ወደ አካባቢው መምጣታቸው ሲታወቅ፣ ወንዶች ሴቶችንና ህጻናትን ትተው ህይወታቸውን ለማትረፍ እንደሚሸሹ፣ ሙርሌዎችም ህጻናቱንና ሴቶችን ይዘው ከሄዱ በሁዋላ ማህተም አድርገውባቸው መልሰው እንደሚለቁዋቸው ገልጸዋል። የወረዳው ሹማምንትም ሙርሌዎች መምጣታቸውን ሲሰሙ፣ እንደህዝቡ አብረው ይሸሻሉ ብለዋል።

“በአካባቢው የሰፈረው የመከላከያ ሰራዊት የመከላከል እርምጃ አይወስድም?” ወይ ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ደግሞ፣ “ መከላከያው ጥቃት ሲፈጸም በመጀመሪያ ዝም ብሎ እንደሚያይ፣ ህዝቡ ሂዶ አቤቱታ ሲያሰማ ደግሞ “ እኛ ከሌለን እናንተ አትኖሩም፣ እናንተ ደግሞ የመብት ጥያቄ እያነሳችሁ እኛን ትቃወማላችሁ፣ ያለኛ መኖር እንደማትችሉ ተመልከቱ” ብለው እንደሚመልሱላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደነገሩዋቸው መልሰዋል። በሌላ በኩል የመከላከያ ሰራዊቱ በአካባቢው በሚካሄደው ድንበር የለሽ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ መሆኑ እንዲሁም፣ በሳር በተሸፈነው አካባቢ እየገባ ከሙርሌ ታጣቂዎች ጋር የመዋጋት ፍላጎት ስለሌለው የህዝቡን ደህንነት ማስጠበቅ አለመቻሉን ነዋሪዎች እንደነገሩዋቸው ምሁሩ ተናግረዋል። መንግስት ሰዎቹን ለማስለቀቅ ድርድር ቢያደርግ እንደሚሻል፣ የሃይል እርምጃ ከወሰደ ግን የተያዙት ሊገደሉ እንደሚችሉ ፍርሃታቸውን የገለጹት ምሁሩ፣ ጉዳዩ አለማቀፍ ትኩረት ባያገኝ ኖሮ መከላከያ እርምጃ የሚወስድ አይመስለኝም ይላሉ።

በጀኔራል ሳሞራ የኑስ የሚመራው የመከላከያ ሰራዊት ድንበር የማስጠበቅ ሃላፊነቱን ባለመወጣቱ እየደረሰበት ያለውን ወቀሳ ለማስተባበልም ሆነ የኢትዮጵያን ህዝብ በይፋ ይቅርታ ይጠይቅ ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት አልደፈረም። በተለይ ጥቃቱ ላለፉት 20 ቀናት ሲፈጸም መቆየቱን የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት ይፋ ካደረጉ በሁዋላ፣ በመንግስትና በመከላከያው ላይ የሚደርሰው ትችት እየጨመረ ሄዷል።

የአውሮፓ ህብረት ባወጣው መግለጫ ደግሞ የደቡብ ሱዳን መንግስት ህጻናቱ ና ሴቶች እንዲለቀቁ ጥረት እንዲያደርግ እና አጥፊዎቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል።

በሌላ በኩል የመንግስት ካድሬዎች የጋምቤላ ነዋሪዎች መንግስትን ደግፈው ሰልፍ እንዲወጡ አስደርገዋል። ነዋሪዎች “መንግስት ሃላፊነቱን ሳይወጣ ሰልፍ አንወጣም” በማለት ተቃውሞ አሰምተው የነበረ ቢሆንም፣ የመንግስት ካድሬዎች ግን ነዋሪዎችን በማስፈራራት ያለፍላጎታቸው እንዲወጡና መንግስትን እንዲደግፉ ማስደረጋቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

አሶሼትድ ፕሬስ ወደ ዜና ከመግባታችን ትንሽ ቀደም ብሎ ባወጣው ዘገባ ደግሞ፣ የደቡብ ሱዳን መሪዎች ጥቃቱን በማስመልከት እየተወዛገቡ መሆኑን ጠቅሷል።

ሙርሌዎች የሚገኙበት የቦማ ግዛት መሪ ባባ ሜዳን ድርጊቱን የፈጸሙት ተቃዋሚ የሆኑ የኮብራ አንጃዎች ናቸው ብለዋል። ኮብራ የሚባለው አንጃ ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር የሰላም ስምምነት በመፈራረም፣ ከብሄራዊ ጦሩ ጋር ተቀላቅሎ የነበረ ቢሆንም፣ የተወሰነው አንጃ የመንግስት ተቃዋሚ መሆኑ በዜናውን ተመልክቷል። የኮብራ አማጽያንን የሚመሩት ዴቪድ ያው አው፣ ድርጅታቸው ጥቃቱን አለመፈጸሙን ገልጸው፣ በተቀራኒው የደቡብ ሱዳንን መንግስት ተጠያቂ አድርገዋል።

የደቡብ ሱዳን መንግስትና ተቃዋሚዎች እርስ በርስ እየተካሰሱ ቢሆንም፣ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ የደቡብ ሱዳን መንግስትም ሆነ ተቃዋሚዎች እጃቸው የለበትም በማለት ፈጥነው መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።
 

ተዛማጅ:

    UPDATE 1: Death toll from South Sudan Gunmen Rising, As Has Number of Abducted Children

    South Sudan Gunmen Kill 141 Ethiopians in Cross-Border Raid; Ethiopia Harvests Fruits of Ethnic Conflict Poison TPLF Has Sown

    Riek Machar no show at Juba: South Sudan peace at risk, say monitors

    Makuei declines JMEC proposal, Taban accepts

 

%d bloggers like this: