ጋምቤላ ውስጥ በኢትዮጵያዊያን ላይ ግድያ ፈጽመዋል በሚል ተጠርጥረው የተያዙ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ቁጥር 41 ደርሷል

26 Apr

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 18፣ 2008 (ኢዜአ) በጋምቤላ ከተማ አቅራቢያ በጀዊ የስደተኞች ጣቢያ በኢትዮጵያዊያን ላይ ግድያ ፈጽመዋል በሚል ተጠርጥረው የተያዙ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ቁጥር 41 መድረሱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ጋትልዋክ ቱት ዛሬ በተደረገ የህዝብ ውይይት ላይ እንደገለጹት፥ ሰብዓዊ አገልግሎት ላይ በነበረና አንድ ግብረ ሰናይ ደርጅት ተሽከርካሪ በሁለት ስደተኛ ሕጻናት ላይ አደጋ ደርሷል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸው 10 ኢትዮጵያዊያን ላይ ግድያ እንደፈጸሙ የተጠረጠሩ ስደተኞች ተይዘው ጉዳያቸው በህግ እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጠለሉበት ሀገር ዜጎች ላይ ግድያ መፈጸማቸው እኩይ ተግባር መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በድርጊቱ የክልሉ ህዝብና መንግስት ከፍተኛ ሀዘን እንደተሰማው ገልጸዋል።

በከተማው ተፈጥሮ የነበረው አለማረጋጋትም በክልሉ መንግስት፣ በፌደራል ፖሊስና በሀገር መከላከያ ስራዊት የተቀናጀ ጥረት ወደ ቀድሞው የተረጋጋ ሁኔታ መመለሱን አስታውቀዋል።

ከስደተኞቹ ጋር በተያያዘ እየተከሰተ ላለው የጸጥታ ችግር መፍትሔ ለመስጠትም የክልሉ መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ነው ያስረዱት ።

ህዝቡም በጸረ-ሰላም ኃይሎች ግፊት ወዳልተፈለገ ችግር እንዳይገባ በክልል ደረጃ የተጀመረው ህዝባዊ ውይይት እስከ ወረዳና ቀበሌ እንደሚዘልቅ መናገራቸው ተዘግቧል።
 

ተዛማጅ:

Violence rocks Gambella!
 

%d bloggers like this: