የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ኦኬሎ ኦኳይን ጨምሮ 7 ግለሰቦች እስከ 9 ዓመት እስራት ተፈረደባቸው! የአሸናፊው ዕውነትና ፍርድ!

27 Apr

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 19 ፣ 2008 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞው የጋምቤላ ህዝቦች ብሄራዊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ኦኬሎ ኦኳይን ጨምሮ ሰባት ግለሰቦች ጥፋተኛ በተባሉበት ወንጀል እስከ 9 አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ።

ተከሳሾቹ የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት ኦኬሎ ኦኳይ፣ ዴቪድ ኡጁሉ፣ ኡቻን ኦፔይ፣ ኡማን ኝክየው፣ ኡጁሉ ቻም፣ አታካ ኡዋር እና ኡባንግ ኡመድ ናቸው።

1ኛ ተከሳሽ ኦኬሎ ኦኳይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር በነበሩበት 1996 ዓ.ም፥ በክልሉ የሚገኙ የአኙዋክና የኑዌር ብሄረሰብ አባላት መካከል ግጭት ተቀስቅሶ በግጭቱ ከ400 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

በወቅቱ ርዕሰ መስተዳድሩ ሃላፊነታቸውን ተጠቅመው ግጭቱን በቁጥጥር ስር ሊያውሉት ሲገባ እንዳባባሱት ተጠቅሷል።

በዚህ ብቻ ሳያበቁም ግጭቱን አስመልክቶ ለተለያዩ የውጭ ሃገር መገናኛ ብዙሃን የተዛባ መግለጫ መስጠታቸውና የሚሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እልቂቱን አባብሶት እንደነበርም ነው ክሱ የሚያስረዳው።

ኋላም ድርጊታቸው እንደሚያስጠይቃቸው በመረዳት የግል አጃቢያቸውና ሾፌራቸውን እንደያዙ ጥር 1996 ሃገር ከድተው መውጣታቸውን፣ ሃገር ቤት ሆነው እልቂቱን ያባባሰ መግለጫቸውን መቀመጫቸውን ውጭ ሃገር ላደረጉ መገናኛ ብዙሃን መስጠት መቀጠላቸውን ክሱ አመልክቷል።

ወደ ኖርዌይ በማቅናትም ጥገኝነት ካገኙና ሃገር ከድተው ከወጡ ከሶስት አመታት በኋላ ራሱን የጋምቤላ ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ/ጋህነን/ የተባለውን የሽብር ቡድን ለመቀላቀል በመወሰን በወቅቱ የዚህ ሽብር ቡድን መስራችና ሊቀመንበር ከሆነው ፒተር ካጋ ጋር በመገናኘት የውጭ ግንኙነት ሃላፊ በመሆን ተሹመው የሽብር ቡድኑን ተልዕኮ ማስፈጸም አንድ ብለው መጀመራቸውም ተብራርቷል።

በአውሮፓና በአሜሪካ እየተዘዋወሩ የሽብር ቡድኑን አባላት በመመልመል፣ ከአባላቱ በወር እስከ 50 ዶላር መሰበሰባቸው የተጠቀሰ ሲሆን፥ ታህሳስ 2000 ዓ.ም ላይ ከድርጅቱ የሽብር አመራሮች ጋር ያደረጉት ቴሌ ኮንፈረንስም በክሱ ላይ ተጠቅሷል።

በዚሁ ዓመት ጥር ወር ላይ ጋህነን ለሁለት ሲከፈል አቶ ኦኬሎ ኦኳይ አንዱን ክንፍ ሲይዙ፥ መስራቹ ፒተር ካጋ ደግሞ ሁለተኛውን መያዛቸው በክሱ ተመልክቷል።

የሊቀመንበርነትን በትረ ስልጣን እንደጨበጡም ኤርትራ በመሄድ በሽብር እቅዳቸው ላይ ለ45 ቀናት ያህል ውይይት ማድረጋቸው እንዲሁም ወደ ጀርመን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ስዊድን እና ሌሎች ሀገራት በማቅናት የሽብር ቡድኑን ለማጠናከር መምከራቸውንም ክሱ ይዘረዝራል።

አሜሪካ ተጉዘውም በወቅቱ ከጋምቤላ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ጋዴን/ ሊቀመንበር ጆንሰን ኡጁሉ የሊቀመንበርነቱን ሃላፊነት ተረክበው ጋህነን እና ጋዴንን መርተዋል የሚለውም ተጠቅሷል።

በዚህ ሃላፊነታቸው ኡጋንዳ በመምጣት 860 አዳዲስ አባላትን መልምለው ወታደራዊና ፖለቲካዊ ስልጠና እንዲያገኙ ካደረጉ በኋላ፤ አባላቱ ከደቡብ ሱዳን አማፅያን ጋር እንዲቀላቀሉ ማድረጋቸውም ተዘርዝሯል።

ሁለተኛው ተከሳሽ ዴቪድ ኡጁሉ የደቡብ ሱዳን ዜግነት ያለው የ36 አመት ጐልማሳ ሲሆን ፥ በሽብር ቡድኑ የደቡብ ሱዳን ሃላፊ ነው።

ከመስከረም 2005 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ጊዜያት አሜሪካ ሃገር ሚኒሶታ ከተማ ለሽብር ስራው ማከናወኛ በተለያዩ ባንኮች የሚላክለትን ገንዘብ ሲቀበል ቆይቶ፥ የመለመላቸው አባላቱ የደቡብ ሱዳን አማጽያንን እንዲቀላቀሉ አስተባብሯል የሚለው በክሱ ላይ ተጠቅሷል።

ከእርሱ ሌላ ኦኬሎ አኳይን ጨምሮ ሰባቱም ተከሳሾች ከሌሎች ተመሳሳይ የሽብር ድርጅቶች ያገኟቸውን ልዩ ልዩ የሽብር ስልጠና ተጠቅመው አንድ አስከፊ ድርጊት ሊፈጽሙ ዝግጅት በማድረግ ላይ እያሉ ነው በደቡብ ሱዳን የጸጥታ ሃይሎች የተያዙት።

በጋምቤላ ክልል ወርቅ በሚቆፈርባቸው የዲማ እና ጆር የተሰኙ ወረዳዎች ላይ በማቅናት፤ በወርቅ ቁፋሮ ላይ የተሰማሩ በርካታ ወጣቶችን በማፈን የደቡብ ሱዳን አማጺ መሪ ዴቪድ ያውያው ስልጠና በሚሰጥበት ቦታ በማምጣት፣ ሰልጥነው የሽብር ቡድኑን እንዲቀላቀሉ የማድረግ አላማ እንደነበራቸውም ነው በክሱ የተጠቀሰው።

ይህንን ምክራቸውን ጠንስሰው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ተግባራዊ ለማድረግ ሲዘጋጁ ድንገት የኢትዮጵያ መንግስት ከደቡብ ሱዳን ጋር ባለው የጋራ የጸጥታ ስራ ቅንጅት በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የፌደራል አቃቤ ህግም ሰኔ 5 ቀን 2006 ዓ.ም በሽብር ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል።

ክሱን ተመልክቶ ሲያከራክር የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሾቹ በወቅቱ አቅርበውት የነበረውን የክስ መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ተቀብሏል።

ሁሉም ተከሳሾች ድርጊቱን አልፈጸምንም ብለው በመከራከራቸው በርከት ያሉ የአቃቢ ህግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ተመልክቷል።

ተከሳሾች የቀረበባቸውን ማስረጃ ለመከላከል ያቀረቡት ማስረጃ የሚያስተባብል ሆኖ አልተገኘም።

በዚህ መዝገብ ሰባት ተከሳሾች ላይ አቃቢ ህግ በሽብርተኝነት ወንጀል የከሰሳቸው ቢሆንም፥ ችሎቱ ጋምቤላን ለመበተንና ከፌዴሬሽኑ ለመገንጠል በመሞከር ወንጀል ጥፋተኛ ብሏቸዋል።

በዚህም ተከሳሾቹ ጥፋተኛ በተባሉበት ወንጀል ሁለት የቅጣት ማቅለያ ተይዞላቸው፥ አቶ ኦኬሎ አኳይና 2ኛ ተከሳሽ ዴቪድ ኡጁሉ በ9 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ የወንጀል ችሎት ውሳኔ አስተላልፏል።

ከ3ኛ እስከ 7ኛ ያሉት ሌሎች ተከሳሾች ደግሞ እያንዳንዳቸው በ7 አመት ጽኑ እስራት እዲቀጡ ወስኗል።
 

%d bloggers like this: