ሕወሃት በጥይቱ ከሚገላቸው በተጨማሪ ለሕዝባችን የደኅንነት ፖሊሲ ስሌለው፣ የሚሠሩ መንገዶች፣ ሕንጻዎችና ግንባታዎች እየተደረመሱ አያሌ ሰዎችን በየሣምንቱ እየፈጁ ናቸው!

5 May

የአዘጋጁ አስተያየት፡
 

  ሁሉም ሃገሮች ግንባታዎች ያካሄዳሉ – የመንገድ ሥራ፡ የሕንጻ ግንባታ፡ የስፖርት ኮምፕሌክሶች ሥራ ወዘተ። ሆኖም በሕወሃት አስተዳደር ተገቢው የደህንነት ፖሊሲና ተጠያቂነት ባለመኖሩ፡ በሃገራቸን ውስጥ በየቀኑ ብዙ ሰዎች ይሞታሉ። በዓለም ላይ የዚህ ዐይነቱ አሰቃቂ ሞት ተራ የየዕለት ሁኔታ የሆነባት ሃገር ምናልባትም ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አትቀርም!

  ይህ ሌላው ዐይነት ችግር ቢሆንም ሁኔታውን አመላካች በመሆኑ፡ በሕንጻ ግንባታ ወቅት ባለፈው ዓመት ብቻ 38 ከመቶ የሚሆኑት ሠራተኞች ኢትዮጵያ ውስጥ በሥራ ላይ አደጋ እንደ ደረስባቸው በጥናት ተደግፎ ተጽፏል።

  ለዚህም አስተዋጽኦ እያደረ ያለው፡ የሕወሃት አስተዳደር ተገቢውን ፖሊሲዎች ባለመቅረጹን ያሉትንም ፖሊሲዎች ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኝነቱ ጉድለት ምክንያት ብዙ ዜጎች እየተጎዱ ነው። የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የሠራተኞ ጉዳዮች ቢሮ ይህንን ችግር አንስቶ በ2013 በጻፈው Assessment of Ethiopia’s Labor Inspection System ሪፖርት የችግሩ ምንጭ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሠራተኞች ተገቢው ትምህርት ባለመሠጠቱን የሠራተኛ ሥራ አፈጻጸም (A well-functioning Labor Inspectorate) ባለመኖሩ እንዲሁም ሲቪል ሰርቪሱ ለእነዚህ ችግሮች ትኩረት እንዲሠጥ አለመደረጉ መሆኑን ይጠቁማል።

  በዛሬው ዕለትም በቦሌ ለስታዲዮም ግንባታ የተቆፈረ ጉድጓድ ሁለት ሰዎችን መብላቱ ተዘግቧል። ሌሎች ሃገሮች ይህንን ዐይነት የሰው ሕይወት መጥፋትን የሚከላከሉት፡ የተቆፈረ ጉድጓድ ዙሪያ አጥር በማቆም ወይንም በጥንካራ እንጨት ወይንም ብረት የጉድጓዱን አፍ በማታ ከድነውት በማደር ነው!

  እኛ ሃገር ግን ቆፋሪውንም አስቆፋሪውንም ተጠያቂ ሊያስደርግ የሚያስችል ሕግ ቢኖርም፡ ተፈጻሚ ለማድረግ ግን ኢትዮጵያ ከሕወሃት የተሻለ ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት ያስፈልጋታል!

 

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 
በአዲስ አበባ ለብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ ተቆፍሮ የተከመረ አፈር ተደርምሶ የ2 ሰዎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ለብሔራዊ ስታዲየም ፕሮጀከት ግንባታ በቁፋሮ ላይ የነበሩ ሁለት ሰዎች የተከመረ አፈር ተደርምሶባቸው ህይወታቸው አለፈ።

የከተማዋ የዕሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን እንዳስታወቀው ሰዎቹ በቦሌ ክፍለ ከተማ ብሔራዊ ስታዲየም ፕሮጀከት ግንባታ የተቆፈረ 10 ሜትር ርቀት ያለው ጉድጓድ ውስጥ እያሉ ነው ክምር አፈር የተደረመሰባቸው።

በቆፋሮ ወቅት የተከመረው አፈር በመደርመሱ ህይወታቸው ካለፈው ሁለት ሰዎች በተጨማሪ ሌላ ተጨማሪ አንድ ሰው ሊኖር ይችላል በሚል የማፈላለጉ ስራ መቀጠሉም ተገልጿል።

ሰራተኞቹን በህይወት ለማተረፍ ተደርጎ የነበረው ስራ ፈታኝ የነበረ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ይህም አፈሩ የተደረመሰበት ጉድጓድ 10 ሜትር ጥልቀት ያለው መሆኑ እና ዝናብ በመዝነቡ ምክንያት አፈሩ እርጥበት ስለነበረው ነው።

በአሁኑ ጊዜም በስራ ላይ የነበሩ ሰራተኞች ቁጥር በሙሉ ተቆጥሮ አንድ ሰራተኛ ጎድሏል ስለበታለ የማፈላለግ ስራ ላይ መሆኑም ነው የተነገረው።

የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ መሰል አደጋ ዳግም እንዳይከሰት በእንዲህ ዓይነቱ የግንባታ ሂደት ውስጥ ሰራተኞችም ሆኑ ግንባታውን የሚያካሂደው አካል ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
 

ተዛማጅ:

  In danger-prone Addis Abeba, early this morning three young plastic factory employees electrocuted

  ተጠያቂነት በሌለበት የሕወሃት አስተዳደር በሕወሃት መሃንዲሶች ከቅጠል የሚሠሯቸው ሕንጻዎችና መንገዶች እየተደረመሱ፣ ሕዝብና ንብረት እየፈጁ ነው — አሳፋሪው የቦሌው ሰሚት ሕንጻ ጉዳይ!

  በአዲስ አበባ ቡልጋሪያ አካባቢ ለህንፃ ግንባታ የተቆፈረ ጉድጓድ ተደርምሶ በ6 ሰዎች ላይ ጉዳት አደረሰ

  በስድስት ወር ውስጥ 41 ሰዎች በመንገድ ጉድጓዶችና ኩሬዎች ውስጥ ገብተው ሞተዋል

  የአንድ ት/ቤት አጥር ተደርምሶ 11 ተማሪዎች ላይ ጉዳት ደረሰ

  በሻሸመኔ ከተማ መጸዳጃ ቤት ላይ የተሠራው ቤተ አምልኮ ተደርምሶ የ10 ሰዎች ሕይውት አለፈ – ሕወሃት መንግሥት መሆን አቅቶት ዘረፋው ላይ ሲያተኩር፥ በሃገሪቱ ስታንዳርድ ጠፍቶ የዜጎች ሕይወት በከንቱ እየተቀጠፈ ነው!

  በዘመናችን ከሚታዩት መንግሥታዊነት ብቃት ማነስ የተከሰቱ የአስተዳደር ጉድለቶችና ለሕይወትና ንብረት ተጠያቂነት አለመኖር ተጠቃሽ መሆን ከሚገባቸው የአዲስ አበባ ምሣሌዎች መካከል

  የፋብሪካዎች ዝቃጭ በአካባቢና በማኀበረሰብ ደህንነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ነው

  Unregulated elevators pose eminent danger on safety

 

%d bloggers like this: