አዲስ አበባ ያለው ጀርመን ኤምባሲ ትግርኛን ቅድመ መስፈርት ያደረገ ሥራ ማስታወቂያ አወጣ: “የኢትዮጵያውያንን እኩልነት ያንቋሸሽ …”

18 May

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
by Golgul
 

http://www.goolgule.com/german-embassy-vacancy-requiring-tigrinya-as-pre-condition/
 

ተቀማጭነቱ አዲስ አበባ የሆነው የጀርመን ኤምባሲ የትግርኛ ቋንቋን ቁልፍ ቅድመ መስፍርት የሚያደርግ ክፍት የሥራ ማስታወቂያ አዲስ አበባ ለሚገኘው ጽህፈት ቤቱ አወጣ። ትግርኛ ዋና መስፈርት የሆነበት ምክንያት ይፋ አለመደረጉ ጥያቄ አስነስቷል። ጉዳዩን የሚከታተሉ ወገኖች የኤምባሲው ተግባር የኢትዮጵያውያንን እኩልነትን ከሕወሃት በላይ ያንቋሸሸ ነው ብለውታል፡፡ ኤምባሲው ማብራሪያ እንዲሰጥ ይጠበቃል።

ኢምባሲው በድረገጹ ሜይ 4 ቀን 2016 ያወጣው ማስታወቂያ የሚፈልገው ባለሙያ የቪዛ ማመልከቻ ሥራን የሚያመቻች፣ የሚያረጋግጥ፣ ቪዛ ነክ ጉዳዮችን አስመልክቶ የቃልና የጸሁፍ መረጃዎችን የሚሰጥ፣ የቪዛ ክፍያን የሚፈጽምና የመዝግብ አያያዝ ሥራን የሚያከናውን እንደሆነ ያረጋግጣል። የሥራው ቦታ ከአዲስ አበባ ውጪ ስለመሆኑ የሚለው ነገር የለም። ማስታወቂያውን የተመለከቱ ወገኖችን ያነጋገረውም ይኸው ጉዳይ ነው።

መመዘኛ (requirements) በሚለው የማስታወቂያው አንድ ክፍል ላይ በቀይ ቀለም “Good knowledge of Tigrinya is a precondition/የትግርኛ ቋንቋ በቂ እውቀት የሥራው ቅድመ መስፈርት ነው” ይላል።

ዝቅ በሎ የቋንቋ ችሎታ በሚል የሚፈለገውን ሲዘረዝር እንግሊዝኛና ጀርመንኛ አቀላጥፎ የሚናገር ይላል። አክሎም ትግርኛና አማርኛ መናገር አስፈላጊ እንደሆነ ያመላክታል።

ዲግሪ፣ የኮምፒውተር ችሎታ፣ ተባበሮ የመስራት ተነሳሽነትና በአስተዳደር አገልግሎት በቂ ልምድ ያላቸው ተመራጭ እንደሚሆኑ የሚያስረዳው የኤምባሲው ማስታወቂያ የማመልከቻው ጊዜ የሚጠናቀቀው ሜይ 20 ቀን 2016 መሆኑን ይጠቁማል።

ለጎልጉል ዝግጅት ክፍል አስተያየት የሰጡ ወገኖች እንደሚሉት የኤምባሲው ማስታወቂያ “ሸውራራ ነው፤ ዜጎችን በእኩል አያስተናግድም፤ ፍትሃዊነት የጎደለው ነው፤ ዘረኝነትን የሚያበረታታና የአገሪቱን የስራ ቋንቋ ያናናቀ፣ ወገናዊ፣ የኢትዮጵያውያንን እኩልነት ከገዢው ህወሃት በላይ ያንቋሸሸና ክብር የነካ…” ሲሉ ነቅፈውታል። በማከልም “ኤምባሲው ጽ/ቤቱ አዲስ አበባ ሆኖ ሳለ ትግራይ ክልል ቢሮ ወይም የቆንስላ ጽ/ቤት የከፈተ ይመስል ትግርኛን ለመቀጠሪያ ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ አድርጎ በአንደኛነት ማስፈሩ ምዕራባውያን ኤምባሲዎች እንዴት ለሕወሃት አጎብዳጅ እንደሆኑ የሚጠቁም ነው” ብለዋል፡፡

ማስታወቂያውን ሲያወጣ ኤምባሲው በግልጽ የትግርኛ ቋንቋን ቅድመ መስፈርት ያደረገበትን ምክንያት ሊያስረዳ ይገባው እንደነበር ያመለከቱት ወገኖች የዝግጅት ክፍላችን ኤምባሲውን ጠይቆ ምላሹን እንዲያሳውቃቸው ጠይቀዋል። በዚሁ መሰረትና ዜናውን ማመጣጠን በሚለው ሙያዊ እሳቤ ኤምባሲው ማብራሪያ እንዲሰጥ የዝግጅት ክፍላችን መጠይቅ ልኳል። ይህ ዜና እስከታተመበት ጊዜ ኤምባሲው ምላሽ አልሰጠም፡፡

በሌላ በኩል አስተያየት የሚሰጡ ክፍሎች የቪዛ ጉዳይ ከደህንነት/ስለላ ጋር የተያያዘ በመሆኑ የህወሃት ሰዎች ባላቸው ትሥሥር ይህ እንዲደረግ ጫና ከማሳደር እንደማይታቀቡ ይናገራሉ። አያይዘውም ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ በሆነ “ታላላቅ” ኤምባሲዎች ውስጥ በብዛት የሚቀጠሩት የሕወሃት ሰዎች ስለሆኑ የስለላው ክፍል መረጃ ለማግኘትና ኤምባሲዎች ውስጥ የሚከናውኑ ተግባራትን በቅርብ በመከታተል እንደሚቻለው ጠቁመዋል።
 

%d bloggers like this: