ግንቦት 20: ወርሃ ግንቦት በሃገራችን፥ በርሃብ የተፈታ ሕዝብ፥ በደም የተጨማለቀው፥ በዘረፋና ቅጥፈት የተበከለው የዘመነ ሕወሃት ፋጻሜ ዋዜማ

23 May

በከፍያለው ገብረመድኅን፣ The Ethiopia Observatory (TEO)
 

    “ሀቁን እንነጋገር ከተባለ፤ ዛሬ ኢትዮጵያ ሕዝቦቿ በነጻነት የሚንቀሳቀሱባት አገር አይደለችም። ይህ ማለት ግን ለጥቂቶች መንግስተ ሰማይ አልሆነችም ማለት አይደለም። ፍሬ ነገሩ ግን ሥልጣን ላይ ካሉት ስዎች ጋር በማበር የምዕራብ መንግሥታትና ኩባንያዎቻቸው፡ ጥቅሞቻቸውን ለማራመድና፡ አሁን ያለውን ስቴተስኮ እንዳለ ለማቆየት የፈልጉትን ያህል ቢደስኩሩም፤ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ባይተዋሮችና በብዙ መልኩ ሕይወታቸው በአረብ አገሮች በግርድና ላይ ካሉ ወገኖቻችን ጋር ያለው ልዩነት መጠነ ጠባብ እየሆነ መምጣቱን መሸፈን አልቻሉም።”

      – ኢትዮጵያ ወደአደገኛ አግጣጫ እያመራች ነው

 

በደጉም ሆነ በክፉ የግንቦት ወር ኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ መልኩ ይታወሳል፤ ይታወቃል።

ከቅርቡ ብንጀምር፣ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ 1935 ዓ.ም. ፋሽስት ኢጣሊያ በዘመናዊ ጦር ሃገራችንን በመውረሯ፡ የኢትዮጵያ ጦር ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በግንቦት ወር 1936 ዓ.ም. መሸነፉ ይታወሳል። ኢጣልያ በኢትዮጵያ ላይ አገዛዟን የመመሥረት ሥራ ጀምራ ነበር – ከአምስት ዓመታት በኋላ ተሸንፋ እስክትባረር ድረስ!

ኢጣልያም ምኞቷ ሁሉ የተሳካላት መስሏት አምስቱን የይዞታ ጊዜዋን – ከጦርነት ጎን ለጎን – ሃገሪቱን ለዘለቄታ ለመግዛት ማናቸውንም ዝግጅት ስታደርግ ብትቆይም፣ ጊዜና ሁኔታዎች ተለዋዋጭ ናቸውና በእነዚያ 60 ያህል ወራት ኢጣልያ ከአሸናፊነት ወደ ተሸናፊነት ተዛውራ በውርደት ለመውጣት መገደዷን ኢትዮጵያውያን በኩራት ያስታውሱታል።

ከጣሊያን ወረራ በኋላ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ወደ ሃገራቸው የተመለሱትና ዙፋናቸው ላይ የተቀመጡትም በግንቦት ወር 1941 ዓ.ም. ነበር።

ከግንቦት ወር ጋር ተያይዘው በገላጭነታቸው ከሚነሱት ሌሎች ነገሮች መካከል በሁሉም የዕምነት ተከታዮች ዘንድ የግንቦት ልደታ ትገኝበታለች። ዕጣኑም እየተጨሰ ክርስቲያን እስላም ሳይባል ጎረቤት በየቄው በየዓመቱ በወርሃ ግንቦት ተሰባስቦ ልቡን ወደ እግዚአብሔር የሚያነሳበት ጊዜ ነው። ይህም የሚሆንበት ምክንያት፣ በተለይም በገጠር አካባቢ በግንቦት ወር ድርቅና ሙቀቱ አስቸጋሪ በመሆኑ፣ ዘወትር በሕዝባችን ልብ ውስጥ ያለው ጭንቀት ሙቀቱ ቀጥሎ ዝናቡ ጠፍቶ ድርቅ ይመጣ ይሆን ከሚለው በመነሳት ነው።

ሊታወሱ ከሚገባቸው ጉዳዮች፥ በአድዋ ጦርነት ዋዜማም ከፍተኛ ርሃበ በመግባቱ፡ ሰው ሰውን አውሬም ሰውን የሚበላበት ጊዜ እንደ ነበርና ድርቅና ርሃብ ሃገራችን ላይ መጥፎ ጠባሳ የተወበት ኢትዮጵያዉያን ሊያስታውሱት የማይፈልጉት የታሪካችን አካል ቢሆንም፡ የኢትዮጵያ የመጀመሪያ የጽሕፈት ሚኒስትር ጸሐፊ ትዕዛዝ ገብረሥላሴ እንደሚከተለው “ታሪክ ዘዳግማዊ ሚኒልክ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ዘግበውታል፦

    “ዘመኑም ጥኑ ርሃብ ሆነ። የፈረስ ሥጋ ያህያ ስጋ ተበላ። ሰውን ሰው በላው። ወሎም አንዲት ሴት ልጇን በላች። እንሣሮም ከሚበለው ሃገር አንዲት ሴት 7 ሕጻናት በላች። አራዊትም ሠለጠኑ። አንበሳው ነምሩን ጅቡ ሰውን በቊሙ ይበላዋል ሆነ።”

ይህ የደረሰበት ሕዝብ፡ መንግሥት እንደማያስጥለው እያወቀ፡ በሥጋት በጾምና ጸሎት ለመኖር መገደዱ ምን ያስገርማል – ከችግሩ አንዳላዳነው ቢገነዘብም?

በግንቦት ወር፥ በአንዳንድ አካባቢዎች በሙቀቱ ምክንያት፣ ዕድሜያቸው ለገፋ ወተት መጠጣት የነፍስ መጠበቂያ ዜዲ ተደርጎ ስለሚወሰድ “በግንቦት አንድ ዋንጫ ወተት” የሚለው አባባል የተለመደ ስለመሆኑ ከአቶ ካሕሣይ ገብረ እግዚአብሔር ጽሁፍ ተገንዝቤያለሁ። ወደ እንስሳቱ ዞር ስንልም “በነሐሴ ባቄላ፣ በግንቦት አተላ” የሚለው አባባልም ሙቀቱና ድርቁ ላስቸገራቸው የቤት እንስሳት አተላው ተሰባስቦ በምግብነት የሚቀርብበት ጊዜ ከልጅነት ጊዜዬ ጭምር ትዝ ይለኛል!

ዘንድሮ ሕወሃት ድርቅ በገባባቸው አካባቢዎች ለእንስሳት መኖ በፋብሪካ እየተዘጋጀ በትራክ፡ ውሃ በቦቴ አቀረብኩ ብሎ በራሱ ሚዲያ ሲያስወራ፡ ወሎ አፋርና ሶማሌ ክልሎች ወዲያውኑ ለጋዜጠኞች እኛም ከብቶቻችንም ያየነው ነገር የለም ሲሉ መስማቱ ሃዘናችንን አክብዶታል – በሃገራችን ለሕዝብ ተቆርቋሪ መንግሥታዊ አስተዳደር በመጥፋቱ!

አፍታም ሳይቆይ በጥር ወር 2016 ፋና ለተራቡ ሰዎች በቂ ምግብ አለ ብሎ ሃሰተኛ ዜና አሰማ!
**********
 

እንዲሁም ሳይታሰብ፣ ፕሬዚደንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ወዳጅ ዘመዶቻቸውን እንኳ ሳይሰናበቱ፣ የሕወሃትና የሻቢያ የተባበረ ወረራና የኤኮኖሚ ድቀት ምክንያትና የምዕራባውያን ግፊት፡ ሃገሪቱን ጥለው ለስደት ወደ ዚምባብዌ ያመሩት በዚሁ በወርሃ ግንቦት 22 ቀን 1991 ነበር።

በደርግ አገዛዝ ሥር ሃገሪቱ ብዙ የተጎዳችና የሕዝቡም ኑሮ በፖሊሲ፡ አስተዳደራዊ ችግሮችና ያልተቋረጡ ጦርነቶች ምክንያት፡ እጅግ ጎስቋላ በመሆኑ፡ እንደ ማንኛውም ሕዝብ ሁሉ ከዚህ ሁኔታ ለመገላገል የደርግን ጀርባ ለማየት ጉጉት ያልነበረው ነበር ለማለት አይቻልም።

ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችብትም ሁኔታ ተመሳሳይና በአንዳንድ መልኩም – ዘረኝነቱ፡ በመንግሥት ስም የሚፈጸም ውንብድና፡ የመንግሥት ለሕዝብ ታማኝ አለመሆን፡ የማንም ዝቃጭ ካድሬ ሕዝብን እንደፈለገው የሚያስርበትና የሚገርፍበት፡ በአጭር መንግሥት መንግሥትነቱን ያጣበት 25 ዓመት በመሆኑ – ዘመነ ሕወሃት ባለጌና እጅግ የከፋ መሆኑ ከማንም አይሰውርም – ለሃገሪቱ ሕልውና ጭምር! እጅግ የከፋውና የከረፋው፣ የሕወሃት ሰዎች በሙሉ ዋሾ፡ ቀጣፊና ሞላጮች መሆናቸው ነው።

ሌላው ቢቀር የሚከተለውን አንባብያን ዘወትር ያስታውሱ!

በጠቅላይ ሚኒስትርነት ስም በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ወንበር ላይ የተቀመጠው ግለሰብ፡ ከብሔራዊ ስታዲዮም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባደረገው ንግግር ግንቦት 28/2014 ሃገሪቱ ከእንግዲህ በምግብ ምርት ራሷን ሰለቻለች የውጭ የምግብ ዕርዳታ እንደማያስፈልጋት ነበር ያወጀው!

እንደሚታወቀው፡ ሕዝባችንን እንኳን አምርቶ ራሱን ሊችል፡ ‘ድርቅም የለም፡ ርሃብም የለም፡ መንግሥት አስፈላጊውን ዕርዳታና የተመጣጠነ ምግብ ለሕዝቡ በየአካባቢው እያዳረሰ ነው በማለት የሕወሃቱ ጌታችው ረዳ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ፕሬስ ኮንፈረንስ በኅዳር ወር 2015 ማድረጉም ይታወሳል!

እንኳን ያ ሊሆን ቀርቶ፣ ዛሬ ሕዝባችን ርሃብ ባልገባበባቸው አካባቢዎች እንኳ የሚላስ የሚቀመስ ጠፍቶ፡ የውጭ እርዳታ እንኳ ጭር ማለቱ ሲታሰብና በዚህ በያዝነው ወር የምዕራብ ሃገሮች በአባልነት የተሳተፉበትን የልዑካን ቡንድ በመምራት የሕወሃቱ ምትኩ ካሣ በአውሮፓና በአሜሪካ ያደረጉት ያልተሳካ የልመና ጉብኝት ይታወሳል!

የሕወሃት ሰዎች ግን በዕርዳታ የተሠጠውን ምግብ በዚታዎ እየጫኑ በየኬላው መያዛቸው (በእውነት ይያዙ ወይንም ሕወሃት ሲያስመስል)
ሲታሰብ፡ ኢትዮጵያ ዘመነ ጥፋት ውስጥ መሆኗ አንዳንዴ በሃሣብችን መመላሱ አልቀረም!

ከዚህ ባሻገር፣ ሕዝቡ ሰብዓዊነቱ ተረግጦ፡ ነጻነቱን ተገፎ ‘ዛሬ ልታሠር፡ ነገ መሬቴን ልነጠቅ፡ ልጆቼን የሕወሃት አጋዚ ይወስድብኝ፡ ይገድልብኝ … ይሆን’ የሚሉት የዛሬው የሃገራችንና የወገኖቻችን የማያቋርጡ ሠቆቃዎች ሆነዋል።
**********
 

በመጋቢት ወር 1993 ዓ.ም. ሕወሃት ከተሰነጣጠቀና መለስ ዜናዊ የራሱን የበላይነት ካረጋገጠ በኋላ፡ ጠላቶቼ የሚላቸውን የሕወሃት ሰዎች (እነ ስዬ አብርሃን) ለመምታት ሕግን ለሥልጣን መሣሪያነት መጠቀም የጀመረበት ጊዜ መሆኑ ከግንቦት ጋር መያያዙ ይታወሳል።

ለምሣሌም ያህል፣ The Federal Ethics and Anti-Corruption Commissionን የሚመሠርተው ሕግ የወጣውና የጸደቀው ግንቦት 16 ቀን 1993 ዓ.ም. ነበር። ዛሬ ኮሚሽኑ፣ የሕወሃቶችን ዘረፋዎች ደብዛ የሚያጠፋና በሙስና ስም ቅርንጫፎችን እየቀነጠበ የግንባሩን ዕድሜ ማራዘሚያ መሣሪያ ነው!

ሕወሃት አስተዳደሩና ሕግጋቱ ለዚህ የተጋለጠ እንዲሆን በመሻቱ፡ በአሥርታት ሺህዎች ቶኖች የሚቆጠር ቡና ከመጋዘን በመለስ ዜናዊ ሰዎችና ደኅንነቱ ተባባሪነት በተደጋጋሚ ሲዘረፍና ሲጠፋ፡ ያየነው ነገር ነጋዴዎችንና አንዳንድ በጸረ-ሕወሃት ፖለቲካ የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን ማሠርና ማጥፋት መሆኑን ከ2008 ጀምሮ ሲካሄድ በየወቅቱ የታዘብነው ነገር ነው!

ዛሬ ዜጎች ከራሳቸው የሕይወት ልምድ እንደሚገነዘቡት፡ የኢትዮጵያ ሕግጋት ሰለዜጎች ግለሰባዊ መብቶች ደንታም የላቸው። ሕጉ ጥቅልል ብሎ – እንደ መንግሥታዊ አካሎች ሁሉ – አገልግሎቱን የሚሠጠው
ለሕወሃት ብቻ ነው። መሬትን ከሕዝብ መዝረፍ ሕወሃት ሕጋዊ ያደረገው በዚህ መንገድ ሕገ ወጥ ሕግጋትን በመቅረጽ ነው! ይህም ማለት፡ መለስ ዜናዊ የተከለው መርዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሃገራችንን ወደ ተባባሰ አዘቅት እያወረዳት እንደሚገኝ በተለይ በጋምቤላ፥ በኦሮሚያና በኦሞ ሸለቆ የተጀመሩትና በመካሄድ ላይ ያሉት አልበገር ባይ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ያመላክታሉ!
*********
 

ከተዓምር ጋር ተያይዞም የግንቦት ማርያም ትታሰባለች፤ በየአምስቱ ዓመታትም ዘወትር ሕወሃት አሸናፊ የሚደረግበት የግንቦት ወር ብሔራዊ ምርጫ የሚካሄድበት ጊዜ ነው፡፡ እንዲሁም በግንቦት ወር ከአሥር ዓምታት በፊት ለሕወሃት ዛሬ የእግር እሳት የሆነበት ግንቦት 7 ተጸንሶ፡ ተረግዞ የተወለደበትና ኢትዮጵያ ያላት አማራጭ በዜጎች ዕኩልነትና በዴሞክራሲ ጎዳና እንድትራመድ የሚመኝና የሚያሰላ የትግል ድርጅት ነው።

በሕወሃቶች በኩል ደግሞ ስለ ወርሃ ግንቦት፣ በተለይም ከራሳቸው ዝክር የሚዘባትሉት ካድሬዎች ከሰሞኑ እንደጻፉልን ከሆነ፡ ግንቦት ከ30 ቀናት ይልቅ አንድ ቀን ብቻ – ግንቦት 20 – የያዘ ወር በመሆኑ፣ አያሌ ቅጥፈቶችን እንሰማለን። ለምሣሌም ያህል ፦

ሰለ 25ኛው ዓመት ግንቦት 20 አከባበር የሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ቢሮ ባወጣው መመሪያ መሠረት፡ የዘንድሮው በዓል “ብዝሃነትን ያከበረ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ያስገኘውን ውጤት በማስቀጠል መሆኑን” አስታውቋል። በዚህም መሠረት፥ “ግንቦት 20 የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከአምባገነናዊ አገዛዝ ተላቀው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማጣጣም ለዓመታት ያደረጉት መራር ትግል ፍሬ አፍርቶ ነፃነታቸውን ያወጁበት ቀን ነው” ብሏል፡፡

‘ተቀዳጅተዋል’ አከማለቱም እግዚአብሔር ይመስገን የሚያሰኝ ነው!

ሌላው እያኘከ ያለ፥ ሙሉ ስሙን እንኳ ለማስፈር የማይደፍር የሕወሃት ካድሬ በበኩሉ – ለደቂቃም የኢትዮጵያን ሕዝብ ትዝብት ሳይፈራ –
ከኢትዮጵያ ሪአሊቲ (ተጨባጭ ሁኔታ) ጋር የሚላተመውን የሕገ መንግሥት ባዶነት በፈጠራ እንደሚከተለው ዘግቧል – !

    “የግንቦት 20 ዓላማና መስመር አገራችን ላለፉት 13 ተከታታይ አመታት ባለሁለት አሃዝ እድገት እንድታስመዘግብ ምክንያት ከመሆኑም በላይ በየጊዜው በአካባቢውና በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነቱ እያደገና እየጠነከረ እንዲሄድ ማስቻሉም ፀሃይ የሞቀው ሃገር ያወቀው እውነት ነው…በሀገራችን ሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ የሚባሉ ፅንሰ ሃሳቦች በሀገሪቱ የመንግስታት አስተዳደር ታሪክ ውስጥ የሚታሰቡ አልነበሩም፡፡ ይህ ሁኔታ የተቀለበሰው የግንቦት 20 1983ን ህዝባዊ ድል ተከትሎ እውን ከሆነው፣ ከ1987ቱ የኢፌዴሪ ህገ መንግሰት መጽደቅ በኋላ ነው፡፡ እንደሚታወቃው፣ የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ህገ መንግስቱ የሌሎች ህጎች መሰረትና ምንጭ ነው፡፡ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ከአምስቱ የህገ መንግስቱ መሰረታዊ መርሆዎች አንዱ ነው፡፡ ሰብአዊ መብቶችና ነፃነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ፣ የማይጣሱና የማይገፋፉ መሆናቸውን ይደነግጋል፡፡ ከህገመንግስቱ 3 እጁ ወይም ከ106 አንቀጾቹ 36ቱ ሰፊ ትኩረት በመስጠት ስለሰብአዊ መብቶችና መሰረታዊ ነፃነቶች ጥበቃና ዕውቅና የሚደነግጉ ናቸው፡፡”

በዛሬይቷ ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ ካየነውና ካነበብነው የባሰ ችግርና ቀባጣሪነት ከየትም አይመጣም!
*********

Blood of Haromaya students, Agazi shed on May 19 (Credit:https://www.facebook.com/Jawarmd/posts/10102292869088763)

በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ ግንቦት 19/2016 የፈሰሰው – ውሃ ፈሶበት እንኳ አልሠወር ያለው – የዜጎቻችን ደም (Credit:https://www.facebook.com/Jawarmd/posts/10102292869088763)

እስከምናውቀው ድረስ ግን፥ ዘመነ ሕወሃት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዘመነ ጥፋት ሆኖበታል!

በተለይም የዘንድሮውና ያለፉት የሕወሃት ሁለቱ ግንቦት 20ዎች ክፉኛ በደም የተጨማለቁ ናቸው! ኢትዮጵያ አያሌ የሁለተኛ ደረጃና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አጥታለች።

እነዚህ ዜጎቻችን በዝርያ ኦሮሞ በመሆናቸው፣ የወላጆቻቸውን መሬት ለሕወት ባላሃብቶች ለማስረከብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸውና መብቶቻቸውን ለማስከበር የሚያቀርቧቸውን ጥያቂዎች ሕውሃት ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኑ በተለያዩ የኦሮሞ አካባቢዎች የታሠሩና የተገደሉ ወጣቶች ናቸው።

አዲስ አበባ፡ ጋምቤላ፡ አፋር፡ ጎንደር፡ የኦሞ ሸለቆ፡ በደም የተለወሱ፥ የዜጎች ልብ የተሠበረባቸው አካባቢዎች በመሆናቸው፡ እስከዛሬ ያለው የዓለም ታሪክ እንደሚያሳየው ከሆነ፡ ሕዝብ ፈንቅሎ የመነሳቱ ጉዞ በውል
ተጀምሯል!

የሕወሃት ሰዎችም ዛሬ በዚህ ወርሃ ግንቦት ስማቸውንና ዝርያቸውን እስከመደበቅ እንደደረሱ በውል የምንመለከተውና የምንገነዘበው ነገር እየሆነ መጥቷል!

አሁን አሁን የሕወሃት ሰዎች ኩባንያ ሲያቋቁሙ እንኳ ጋዜጠኞችን ስማቸውን እንዳይጠቅሱ መማጸን አዲሱ ፈሊጥ ሆኗል፡፡

በእውነት እነርሱም በዚህች እጅግ ያዋረዷትና የረገጧት ኢትዮጵያ ውስጥ ለዘለቄታው እንገዛለን እኖርባታለን ብለው መቶ በመቶ ውስጣዊ ሰላም እንደማይኖራቸው ያውቁታል!

እስካሁን ሕወሃቶች ያልገባቸው ወይንም አልዋጥላቸው ያለው፥ ጊዜ እያላቸው ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር ሰላምን ፈጥረው ሃገራችንን በጋራ እልምተን ከባዕዳን ይልቅ ዜጎቿን ተጠቃሚዎች ቢያደርጉ ከይቅርታ ባሻገር ለመቻቻል በር ይከፍታሉ!
 

ተዛማጅ:

    በዕጦቶችና የሥልጣን ብልግና የተፈጠረው የኢትዮጵያ ምሬቶች የዛሬው ሥዕልና የነገው ሥጋት*

ኢትዮጵያ ወደአደገኛ አግጣጫ እያመራች ነው
 

%d bloggers like this: