መሬቶቻቸውን ለተዘረፉ የአዲስ አበባ ዙሪያ አርሶ አደሮችና የመፍትሔው ጉዳይ በሕወሃት ዘራፊዎች እየተወሳስበ ነው

29 May

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
በሪፖርተር – የአዲስ አበባ አርሶ አደሮችና መፍትሔ የሚሻው የካሳ ጉዳይ
 

አዲስ አበባ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማስተናገድ ከጀመረችበት ከ1988 ዓ.ም. ወዲህ በማስፋፊያ ቦታዎች የሚገኙ ነባር አርሶ አደሮች መፈናቀል ጀመሩ፡፡ በመቀጠል በ1996 ዓ.ም. በከተማው የተንሰራፋውን የመኖርያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ የተጀመረው የቤቶች ልማት ፕሮጀክት፣ በርካታ አርሶ አደሮችን ማፈናቀል ቀጠለ፡፡

በአዲስ አበባ ዳርቻ በስፋት የተከፈቱ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች፣ እንዲሁም ለመኖርያ ምቹ ያልሆነውን መካከለኛውን የከተማው ክፍል በአዲስ ግንባታ ለመቀየር የተጀመሩ የመልሶ ማልማት ፕሮጀክቶች በአርሶ አደሮች ላይ ክንዳቸውን አሳረፉ፡፡

በአሁኑ ወቅት 20 ሺሕ ሔክታር የሚገመተው የአዲስ አበባ የማስፋፊያ መሬት (በአብዛኛው አርሶ አደሮች የሠፈሩበት) በአዳዲስ ፕሮጀክቶች በመያዙ፣ በርካታ አርሶ አደሮች ከነበሩበት መሬት ለቀዋል፡፡ የተቀሩ አርሶ አደሮችም ከዛሬ ነገ እንደሚነሱ እርግጠኞች ሆነው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

ምናልባት ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ በአዲስ አበባ የሚታረስ መሬትም ሆነ በግብርና ሥራ ሲተዳደሩ የቆዩ አርሶ አደሮች የማይኖሩበት ደረጃ ላይ እንደሚደረስ ምልክቶች በጉልህ እየታዩ ነው፡፡

አርሶ አደሮቹ ግን ከግብርና ሥራቸው መፈናቀላቸው ሳይሆን፣ የሚሰጣቸው ካሳና ምትክ ቦታ አነስተኛ መሆኑ ያሳስባቸዋል፡፡ በእስካሁኑ ሒደት የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች የተሰጣቸው ካሳ አነስተኛ በመሆኑ፣ ለችግር መዳረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተሰጣቸው ካሳ አነስተኛ ቢሆንም እንኳ፣ በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላቸውም ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ እንዳሉ እየታየ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለቤቶችና ለኢንዱስትሪ ልማት የሰጠውን ትኩረት ያህል ለተፈናቃይ አርሶ አደሮች እንዳልሰጠ አርሶ አደሮቹ ያምናሉ፡፡

54 ሺሕ ሔክታር ስፋት ባላት አዲስ አበባ ከተማ 18,174 ሔክታር በሚሆነው መሬት ላይ አርሶ አደሮች ይገኙ ነበር፡፡ በዚህ መሬት ላይ በእርሻና በእንስሳት እርባታ ሥራ ለዘመናት የቆዩ አርሶ አደሮች በልማት ምክንያት እንዲነሱ ሲደረግ፣ የሚከፈላቸው ካሳና ምትክ ቦታ ፍትሐዊ እንዳልሆነ አርሶ አደሮቹ ይናገራሉ፡፡

በ1989 እስከ 1991 ዓ.ም. ተፈጻሚ የሆነው መመርያ እንደሚለው አንድ የለማ የእርሻ ማሳ አንድ ሔክታር (10,000 ካሬ ሜትር ቦታ) በአንድ ካሬ ሜትር ቦታ የሚከፈለው ካሳ 3.74 ብር ነው፡፡ ይህ ካሳ በአሥር ዓመት ተባዝቶ የሚከፈል ሲሆን፣ ይህ ሒሳብ ለአሥር ዓመት ሲካፈል 0.374 ሳንቲም ይሆናል፡፡ ለግጦሽ የሚውል መሬት ደግሞ በአንድ ሔክታር የሚከፈለው 847 ብር ሲሆን፣ አንድ ካሬ ሜትር መሬት በ1.21 ብር ስሌት ነው ክፍያው የሚፈጸመው፡፡ ይህ ዋጋ ለአሥር ዓመት ሲከፈል 1.21 ሳንቲም ነው፡፡

“ይህ የአፈጻጸም መመርያ ከአሥር ሔክታር በላይ ይዞታ ያለውን አርሶ አደር አያስተናግድም፡፡ በጣም አስገራሚና አሳዛኙ ጉዳይ የዚህ መመርያ ክንውን አርሶ አደሩ በዕውቀቱ፣ በጉልበቱና በገንዘቡ ያለማው ግማሽ ይዞታ ከ3.74 ብር ወደ 1.21 ብር ዝቅ አድርጎ አርሶ አደሮችን በመጉዳት በአንፃሩ ደግሞ ባለሀብቶችን ተጠቃሚ አድርጓል፤” በማለት ይህንን ችግር መንግሥት መፍታት እንደሚኖርበት አርሶ አደሮች ያቋቋሙት ኮሚቴ ለመንግሥት ያቀረበው ሰነድ ያመለክታል፡፡

ሰነዱ ጨምሮ እንደሚገልጸው፣ አንድ ባለይዞታ ከሰባት እስከ ስምንት ሔክታር የለማ መሬት ቢኖረውም በለማ መሬት ታስቦ የሚከፈለው 3.5 ሔክታር መሬት ብቻ ነው፡፡ ቀሪው ያለማ የግጦሽ መሬት ተብሎ 1.21 ብር ብቻ በካሬ ሜትር ይከፈለዋል፡፡

አሠራሩ በምትክ ቦታ ላይም ችግር እንዳለበት የአርሶ አደሮች ኮሚቴ ሰነድ ያመለክታል፡፡ 10,500 ካሬ ሜትር መሬት ለነበረው አርሶ አደር የሚሰጠው ምትክ ቦታ 200 ካሬ ሜትር ብቻ ነው፡፡ ከ90,000 ካሬ ሜትር በላይ ላለው አርሶ አደር ደግሞ የሚሰጠው ምትክ ቦታ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ነው ይላል፡፡

ለአርሶ አደር ልጆች የዕድሜና የጋብቻ መሥፈርት ካሟሉ ብቻ 105 ካሬ ሜትር ቦታ ይፈቅዳል፡፡
 

%d bloggers like this: