በኢትዮጵያ ለሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ቻይና አራት ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ፍላጎት አሳየች፤ የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ አቅም ግን ተመናምኗል!

29 May

የአዘጋጁ አስተያየት:

    የሕወሃት ሰዎች፣ በሕወሃቶችና ግብረአበሮቹቻቸው ለዘረፋ የተጋለጠችን ሃገር እንዴት አድርገው የውጭና የገቢ ንግዷን አስተካክላ ዕዳዋን እንደምትከፍል ሕወሃቶች መነጋገር ከማይሹባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው። ብዙ የተፎከረለት ሁለተኛው የአምስት ዓመት ፕላን ከተጀመረ ዘጠነኛ ወሩን እያስቆጠረ ሲሆን በሃገር ውስጥ ምርትና በውጭ ገበያ በኩል እንደ አንደኛው የአምስት ዓመት ፕላን ሁሉ፥ አሁንም ሃገራችን አልተሳካላትም።

    አበዳሪ አንድ ቀን ይሞታል የሚለውን የሞኞች ፈሊጥ ያምንበት ይመስል፡ ሕወሃት አሁንም ሃገሪቱ ልትሸከም ከምትችለው በላይ ከየቦታው ብድር ሲያጋብስ ይታያል።

    አንድ ቀን የሃገሪቱ ሁኔታ ይሻሻልና ሃገሪቱም በየደረጃ ዕዳዋን መክፈል ትችል ይሆናል ብለን እንዳናስብ አንኳ፥ የታዳጊ ሃገሮች ሸቀጦች ዋጋ እንዳዘቀጠ ከመሆኑም በላይ፡ ታዋቂ የቀድሞ የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስትርና በሃርቫርድ ፕሮፌሰር የሆኑት ላሪ ሰመርስ በቅርቡ እንዳመለከቱት ከሆነ፡ የዓለም የኤኮኖሚ ዕድገት የወደፌት የማንሰራራት ተስፋው ክፉኝ ተችንክሯል (secular stagnation in the Open Economy) ያሉት ብዙ ተቀባይነት ያለው ትንበያ ሆኖአል።

    ትርጉሙ፦ ከኤኮኖሚ ድቀት ከተወጣ ከአምስት ዓመታትና ያ ሁሉ ገንዘብ ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ ከተረጨ በኋላ፡ ዕድገት ጥገት መሆኑን አመላካች ነው!

    ታዲያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሁሉን አዋቂው ሕወሃት እንዴት አድርጎ ያከማቸውን ዕዳ መክፈል እንደሚቻል ያውቃል ብሎ ማመን ያስቸግራል!

 

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
በሪፖርተር
 

የቻይና መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚካሄዱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች አራት ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ማቀዱን፣ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትሩ አቶ አብዱልአዚዝ መሐመድ የተመራው የኢትዮጵያ መንግሥት የልዑካን ቡድን ባለፈው ሳምንት ቤጂንግ በተገኘበት ወቅት፣ ይህ መልካም ዜና እንደተነገረው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በቻይና መንግሥት ፋይናንስ ይደረጋሉ የተባሉት ፕሮጀክቶች ስድስት ናቸው፡፡ እነሱም የአዲስ አበባ ከተማን ንፁህ የመጠጥ ውኃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተያዘው የገርቢ ወንዝ ግድብ፣ የመቀለ ከተማን ንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ለተነደፈው ፕሮጀክት፣ ከአዳማ እስከ አዋሽ የሚገነባው ፈጣን መንገድ፣ ከሞጆ እስከ ሐዋሳ ለሚዘረጋው የባቡር ሐዲድ፣ ለገናሌ ዳዋ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክትና በአዲስ አበባ ከተማ ለሚዘረጋው ከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ መስመር ፕሮጀክት ናቸው፡፡

እነዚህ ፕሮጀክቶች በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ቅድሚያ የተሰጣቸው ሲሆኑ፣ ለግንባታዎች የሚያስፈልገው ገንዘብ ከቻይና መንግሥት እንደሚገኝ መተማመኛ ተገኝቷል ተብሏል፡፡

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢቢሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የልዑካን ቡድኑ ከቻይና መንግሥት ጋር በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ መግባባት ላይ ደርሷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማን የውኃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የገርቢ ወንዝን መገደብ አማራጭ ተደርጓል፡፡ ከእንጦጦ ተራራ ጀርባ የሚገኘው ገርቢ ወንዝ የዓባይ ገባር ሲሆን፣ አጠገቡ ከሚገኘው ሲቢሉ ወንዝ ጋር ተዳምሮ የአዲስ አበባን ንፁህ የመጠጥ ውኃ ችግር በዘላቂነት እንደሚፈታ፣ ከዚህ በተጨማሪ እነዚህ ሁለት ወንዞች ሲገደቡ የሚፈጠረው ሰፊ ሐይቅ ለከተማው ሁነኛ የመዝናኛ ሥፍራ ይሆናል ተብሏል፡፡

ቅድሚያ ተሰጥቶ ለሚገነባው ሲቢሉ ወንዝ የቻይና መንግሥት ገንዘብ እንደሚያቀርብ በመስማማቱ ሥራው በቅርቡ ይጀመራል ተብሏል፡፡ የመGለ ከተማም በከፍተኛ የውኃ ችግር ውስጥ እንደምትገኝ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ የውኃ ችግሩ ሥር የሰደደ በመሆኑ ጥያቄው ከክልል አልፎ እስከ ፌዴራል መንግሥት ድረስ ደርሷል፡፡

ይህንን የመቀሌ ከተማ የውኃ ችግር ለመፍታት ለተነደፉ ፕሮጀክቶች ማካሄጃ የቻይና መንግሥት ፋይናንስ ለማድረግ ፍላጎት ማሳየቱም ተመልክቷል፡፡

መንግሥት በተመረጡ አካባቢዎች የፍጥነት መንገዶችን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ-አዳማ የፍጥነት መንገድ ተገንብቶ ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ ከሞጆ- ሐዋሳም እንዲሁ ግንባታው መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሳምሶን ወንድሙ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ፣ ከአዳማ-አዋሽ ከዚያም ወደ ድሬዳዋና ወደ ጂቡቲ የፍጥነት መንገድ ለመገንባት መታቀዱን አቶ ሳምሶን አስረድተዋል፡፡

በመጀመሪያ ዙር ቅድሚያ የተሰጠውን ከአዳማ-አዋሽ ድረስ የሚገነባውን የፍጥነት መንገድ የቻይና መንግሥት ፋይናንስ ለማቅረብ ፍላጎት ማሳየቱ ታውቋል፡፡

የኢንዱስትሪ ዞን ለማስፋፋት ተመራጭ የሆነችው የደቡብ ክልል መቀመጫ ሐዋሳ ከፍጥነት መንገድ በተጨማሪ የባቡር መስመር እንዲኖራት ተፈልጓል፡፡

ለዚህ ፕሮጀክት የቻይና መንግሥት ፋይናንስ ለማቅረብ መስማማቱ ተገልጿል፡፡ በአጠቃላይ የቻይና መንግሥት ፍላጎት ያሳየባቸውን ፕሮጀክቶች በቀጣይ ጊዜያት በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ድርድር እየተካሄደ ተግባራዊ እንደሚደረግ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
 

%d bloggers like this: