የቻይና ኩባንያዎችና ኤክሲም ባንካቸው ኢትዮጵያ ፓርኮች ውስጥ ብዙ አረፍ ማለት የፈለጉ ይመስላል፤ ሃገራችንስ ትለማለች? ከተከማቸባት የዕዳ ጫናስ ዕፎይታ ታገኝ ይሆን?

2 Jun

በከፍያለው ገብረመድኅን Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)

ኢትዮጵያ ውስጥ ዝናብ ይጥፋ፣ የሚበላ ምግብና የሚጠጣ ጠፍቶ፥ ድርቅ የሕዝብ ቁጥር እንኳ ቢቀንስ፡፣ ቻይና የምትሰጠውን ብድር አፍንጫ ሰንጋ በወቅቱ ለማስከፈል ስምምነት ታስገባለች፤ ማስከፈል እንደምትችልም አበክራ ታውቃለች።

በተመሳሳይ መንገድ፥ ሩስያም በደርግ ጊዜ ሃገሪቱ ለጦር መሣሪያ የተበደረችውንና በ1998 አምስት ቢሊዮን ዶላር የነበረውን ዕዳዋን ‘በክፍያና በዕዳ ቅነሳ’ አሁን ወደ $126 ሚልዮን ወርዷልና፣ ‘ዘላለም በዚህ ልንቀጥል አንችልም’ በማለት ሞስኮ ሰሞኑን፡ ኢትዮጵያ ቻይናን ከምትቀልባት ፕሮጀክቶች ለእነርሱም ኩባንያዎች ድርሻ እንዲሰጣትና ዕዳውም እንዲከፈል በማለት ግልጽ ጥይቄ ማቅረቧን ስፑትኒክ የተሰኝው የሩስያ ሚድያ አስምቷል።

ነገሩ ድንገተኛ የሆነበት በሞስኮ የሕወሃት አምባሳደርም፡ በምህንድስና፣ ሳይንስና ቴክኖሎጅና ፍብረካ ዘርፎች ብዙ ፕሮጀክቶች እየተዘጋጁ ስለሆነ፥ በመስከረም እነርሱ ሲጠናቅቁ ለእናንተም ከቻይና ጋር ተወዳዳሪ እንድትሆኑ እናሳያችኋለን፣ ‘ነቃ ብላችሁ ተፎካከሩ’ ብሎ መምከሩን ጋዜጣው ጠቀሷል።

ይህም ማለት፡ ፕሮጄክቶች ለልማት መሆናቸው ቀርቶ፥ ሌላው ዱብዳ በዘመነ ሕወሃት አሞሌ ጨው ድሮ የገበያ መሣሪያ እንደነበረ ሁሉ፥ አሁንም መንግሥታዊ ፕሮጀክቶች የዕዳ ክፍያ መሣሪያ ወደሚሆንበት ሁኔታ ሃገራችን ስትሸጋገር፡ ልንመሠክር ዝግጅት ላይ ያለን ይመስላል! በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሃገራችን ዕዳ ከፋይ ብቻ ስትሆን፡ ከዚያ የተረፈውን ደግሞ ሕወሃት እየዘረፈው፡ ሃገራችን በፍጥትነት ዕድገት ላይ ያለች እየተባለ፡ የሕዝባችንንም ጉስቁልና ዓለምም በሚገባ ሳይገነዘበው በብቸኝነት ተጠቂ እንደሆነ ሊቀጥል ነው።

ለጥቂት ሣምንታት እየተንጠባጠበ እንደሚነገረው ክሆነ፥ በአሁኑ ወቅት ዳጎስ ያለ – ከአራት እስከ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ብድር (አንድ ጊዜ ሁለት ቢሊዮን፣ ቀጥሎ ደግሞ አራት ቢሊዮን) – ቻይና ከሰሞኑ ለኢትዮጵያ ትሰጣለች ተብሎ ይጠበቃል።

ከላይ ከላዩ ሲታይ፣ አዲሱ ስምምነቶች በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ልምድ ከመለዋወጥ ባሻገር (ነፃ አይደለም)፣ በሚገኘው ብድር ‘ለምርጥ’ ኢትዮጵያውያን ሥልጠና ይሰጣል። ዓላማውም ኢትዮጵያ በዚህ በመሥፈንጠር – የቻይና የአፍሪካ ፖሊሲ መሥራች ተደርገው የሚጠቀሱትና ኋላም በኮሚኒስት ፓርቲ ውስጥ ኃላፊ የነበሩት አምባሳደር ዦንግ ጂአንኋ (Zhong Jianhua) አይስሙኝ እንጂ – ዓላማው ሌላይቱ ቻይና ለማድረግ እንደሆነ ቻይናዎች (ኤኮኖሚስት ጁስቲን ዪፉ ሊን) ጭምር ቀደም ሲል በተደጋጋሚ አስምተውናል።

ሕወሃቶችና ስምምነቶቹ እንደሚያስተጋቡት ከሆነ፡ የአዳዲሶቹ ስምምነቶች ዓላማም የለማች ሃገር ለመመሥረት መሆኑ ሲታሰብ፥ አንድ ተስፋ ይፈጥራል። ችግሩ ግን እምነት ሊጣልበት የማይችል፡ ከሕግ በላይ የሚኖር፡ ነፍስ ገዳይና ዘራፊ መንግሥት የሚያስተዳደራት ሃገር በመሆኗ፥ ቁጥጥርም ስሌለበት፡ የልማት ጥረቱ – ከከተማ ማስዋብ ባሻገር – ዓየርን በጓንት እንደገጠመ ቦክስኛ ካስመሰለው ሰንብቷል። ትርጉሙም፥ መቺ አለ ተመቺ ግን የለም! ከባድ ኋላቀርነት አለ ሁሉን አቀፍ ልማት ግን የለም!

የሃገራችን ልማት የሰው ልማት ባለመሆኑ፥ ኋላ ቀርነቱ እየተባባሰ፥ ሃገሪቱ የችግሮች መፈንጫ እየሆነች ስትሄድ የሚታየውም ለዚህ ነው። በመሆኑም፡ አመኔታን በሕወሃት መንግስት ላይ መጣልና በእነዚህ መሰል ስምምነቶችና የገንዘብ ብድሮች ልማት ይመጣል ብሎ መዘናጋት፡ ከሰማይ መና እንደ መጠበቅ ነው።

በእነዚህ ስምምነቶች ምክንያት ለውጥ አይመጣም ማለታችን አይደለም። ይመጣል። ሕወሃት ከሃገር በዘረፈው ሃብት የዳለበው የሕወሃት ባለሥልጣኖች፡ ቤተ ሰቦቻቸውና ዝርያዎቻቸው ሕይወት ወደ አንደኛው ዓለም የናጠጠ አኗኗር ይሸጋገራል። ሕክምና ቢያስፈልጋቸው ከውጭ ታዞ ቤት ድረስ ይመጣላቸዋል። ካልሆነም፣ በቅርቡ እንደ ተደረገውም፣ ከየት እንደተነሱ እንኳ የዘነጉ አንዳንድ ቅጥረኞች፡ አውሮፕላን ‘ተከራይተው’ ለሕክምናና አንዳንድ ተፈጥሮ ያደረሰባቸውን እክሎች ለማሳረምና ‘ውበቶቻቸውን’ ለመጨመር በዚህ የርሃብ ዘመን ወደ ጀርመን እንዳቀኑ ይታወሳል – በእነሱ አቆጣጠርም 10.2 ሚሊዮን ሕዝብ ክፉኛ ታርዟል በሚባልባት ሃገርና ወቅት!

ምን ችግር አለ? ወጭውም ገቢውም ላይ ያለቁጥጥር ፈራጅና በታኞች እነርሱ እስከሆኑ ድረስ? ከዚህ ከቻይና ጋር ሐሙስ የተፈራረመቻቸው ሶስት ስምምነቶች ከአራት እስክ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ብድር እንደሚያስገኙ ቀደም ሲል ጭምጭምታው ተሰምቷል። የኢንጂነሪንጉንና የኃይል ፕሮጄክቶችን ሥራዎች የሕወሃት ድርጅቶች (EFFORT companies) እንደ ቀድሞው በቀጥታ ተቋዳሽ የሚያስደርጋቸው ስምምነቶች በቀጥታ ይፈርማሉ፣ ወይንም በብረታብረትና ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን (METEC) አማካይነት በተሳሰሩበት ቱቦ ይቀርብላቸዋል።

ለመሆኑ ስንትና ስንት ጊዜ ነው ለውሃ ልማት፡ ለመብራት መዘርጋት፡ ለዚህና ለዚያ ልማት እየተባለ ሃገራችን እስኪያቅለሸልሻት ድረስ ብደር ከአውሮፓ፣ ከጃፓን፣ ከዓለም ባንክ፡ ከገበያ ብድርና እንዲሁም በችሮታ ገንዘብ ያገኘችው? የታለ ፍሬያቸው?

አሁንም፣ በዚህ የሕወሃት ማደነባበሪያና ማጭበርበሪያ በሆኑት የቻይና ብድሮችና ከሕዝብ በተዘረፉ መሬቶች ላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የአግሮ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያዎች የሚለው ዝብተላም፡ እስከዛሬ ካየናቸውና ከሰማናቸው የተለየ መጠበቅ የዋህነት ነው።

ከሁሉም በላይ፣ ልማት በሕዝባዊ በጎ ፈቃድ ላይ መመሥረት አለበት – ጀብደኛው ሕወሃትና መለስ ዜናዊ የኪም ኢልሱንግን መለኮታዊነት ለመረከብ በወሬና በምኞት ብቻ ሲዘጋጅና ሲቋምጥ እንደነበረው ሳይሆን!

መልካም አስተዳደር ማለት ደግሞ የመሪዎችንና የተመሪዎችን የሃገር ከበሬታ፥ ተቆርቋሪነትና ፍቅር ይጠይቃል። ያ በትምህርትና በኅብረተሰብ ጫና ሥር ሲሰድ፡ ሁሉም ለሕግ ተገዥ እንዲሁን አስገዳጅ ሁኔታ ይፈጠራል – ሁሉም እኩል ድምጽ ያለውና ሁሉም እኩል ተጠቃሚንቱ በተጨባጭ እየታየ!

አለበለዚያ ፖለቲካው የዐባይ ፀሃዪ ዐይነት ቅጥፈት ብቻ ይሆናል። በመለስ ዜናዊ የደማጎጊ ተተኪነቱ – አባይ ፀሃዬ ስለ ግንቦት 20 ሕዝባዊ ትዕዝብትን ሳይፈራና ሳይሳቀቅ – ሕወሃት እኩልነት የሠፈነባት ሃገር፡ ዛሬ ዜጎች በነጻነትና ዲሞክራሲ ሲንቀሳቀሱ ማየት እንዳስደሰተው ሲደሰኩር፡ ያመጡትም ልማት ይህ ነው ማለቱ አይደል የሚል ስሜት ነው ያሳደረብኝ።

በራሱ አንደበት ዐባይ ፀሃዪ እንዲህ ነው ያለው፡

    “የዴሞክራሲ ግንባታው ጅምሩ ጥሩ ነው…ከሁሉ በላይ ህገ መንግስታችን ምርጥ ከሚባሉት አንዱ ነው፤ በወረቀት ላይ ብቻ አይደለም የተሟላ ነው ባይባልም በተግባርም ረጅም ርቀት ሄዷል። ሀገሪቱ ከሁሉ በፊት በእኩልነትና በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ እንድነትን የሚያረጋግጥ የፌዴራል ስርዓት ዝርግታለች…ከኢኮኖሚው ባሻገር በዴሞክራሲ ስርኣት ግንባታ …ሀገሪቱ ከሁሉ በፊት በእኩልነት እና በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ እንድነትን የሚያረጋግጥ የፌዴራል ስርዓት ዝርግታለች።”

አልገባው እንደሆነ አላውቅም፥ ይሀ እነርሱ የሚያደርጉት የውስጥ ለውስጥ ዘረፋና ማጭበርበር የፍርድ ቀን ማቃረቢያ እንጂ ልማት አይደለም!

ከተናገረው ሁሉ የወደድኩለት፣ በውስጣቸው ባለው መከፋፈልና መገልማት፡ ሃገሪቷን ለማሻሻል እርምጃ ለመውሰድ አለመቻላቸው (እርሱ አንዳስቀመጠው – “አድርባይነት፣ የእርስ በእርስ አለመተራረም፣ የተነካካ አመራር መኖርና ለችግሮች ምንም አይነት የሃላፊነት ስሜት የማይሰማው አመራር መኖር ተጠቃሽ ናቸው”) የሚለው የፈራው ቀን መደረሱን መጠንቆል መቻሉ ብቻ ሳይሆን፥ ሃገሪቱ ያላትን የተበላሸ አመራር ቁልጭ አድርጎ ማሳየቱ ነው!

ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያ በመጨረሻው የፓርቲያቸው ስብሰባ ላይ ሰማይ እንደ ራቀና ምድር እንዳልተቀበለቻቸው የተናገሩትን ቃል ያስታውሰኛል!

ባልሳሳት ያን ጊዜ አይደል ዶ/ር ኃይሉ አርአያ “እርሶም ጓድ ፕሬዚደንት ያቺን መራራ ክኒን ይዋጡ ያሉበት!”ወቅት?
 

ተዛማጅ.

    A plundered Ethiopia being forced to cater to TPLF’s whetted appetite: Kombolcha & Mekelle Industrial Parks on rush to roll without let!

 

%d bloggers like this: