ያልነውና የጠበቅነው ሆነ፡ በምርጫ 97 በተፈጠረ ቀውስ የተወረሩና በሕገ ወጥ መንገድ ሕወሃቶችና ሌሎችም የዘረፏቸው መሬቶች ሕጋዊ ተደረጉ – የቀጣዩ የኅብረተሰባችን ቀውስ ማባባሻ!

5 Jun

የአዘጋጁ አስተያየት:

  ከተዘረፉት መሬቶች ተቀራማቾች መካከል በዘር በተመሠረተ ሁኔታ፡ የሪፖርተር ባለቤትና አንዳንድ ጋዜጠኞቹ የቀበሌ ቤቶች ጭምር ባለቤት እንዲሆኑ ከተደረጉት መካከል ስለሚገኙ፡ ዛሬ ይህንን ሲዘግቡ በተቻለ መጠን ሕወሃት በመለስ ትዕዛዝ ያደረገው መሆኑን በሚሸፍጥ መነገድ ነው ያቀረቡት።

  በተደጋጋሚ በፋና ብሮድካስትና በከተማ ቤቶችና ልማት ሚኒስቴር ውስጥ ባሉ የሕወሃት ካድሬዎች፡ ይህ ሕጋዊነት በካዳስተር ስም ፈጥኖ ሕጋዊ እንዲደረግላቸው የተለያዩ መላ ምቶችን በመቀመር፥ የየተለያዩ ግልጽና ሥውር ስብሰባዎችን ሲያደርጉ መክረማቸውንና እኛም እንደ ነቃንባቸው ለማሳየትና ከዘረፋቸው እንዲቆጠቡ ለማስታወስ በተለያዩ ጊዜያት ሕዝባችንም እንዲያውቀው በአምዶቻችን ሞክረናል።

  ለኛ ይህ መንግሥታዊ ዘረፋ አዲስ ነገር ሆኖብን ሳይሆን፥ አሁን እዚህ ያሠፈርነው፡ ከኛ በላይ አዋቂ የለም ብለው የሚያስቡት የሕወሃት ጀሌዎች ድርጊት አንጀታችንን እያበገነውና፡ ሃገራችን የምታዘቅጥበት የጥፋት ጎዳና እየታየን በማዘናችን ነው። ዛሬ በየአካባቢው እንደሚታየው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም እኛም ሕጋዊ መብቶቻችን የሚይከበሩ ከሆነና ድርሻችን በሕጋዊ መንገድ የሚይደርሰን ከሆነ እናንተም አትበሉም እኛም አንበላም ወደ ሚለው አቅጣጫ እየተገፋ ነው! ይህ ማናቸውንም አይበጃቸውም – በፎቅ ላይ ፎቅ በሚስቶቻችወና ሌሎች ቤተሰቦቻቸው ስሞች እየካቡ ያሉትን ጄኔራል ሳሞራ ዩኒስንና እነጂነራል ክንፈ ዳኝውንና ወዘተዎችን ጨምሮ!

  የሕዝብ ቁጣ ወደ ጥፋት ሲለወጥ ግን ጽዋውን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው የሚጠጣው! ይህ ሳይሆን ግን ዘራፊዊዎቹን ከአሁኑ ልክ ማስገባት ያስፈልጋል!

 

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
በሪፖርተር 

ግንቦት 1997 ዓ.ም. የተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በፈጠረው ቀውስ በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መንገድ የተያዙ በርካታ ይዞታዎች ሕጋዊ ሆኑ፡፡

በገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግና በተለይ በቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (ቅንጅት) መካከል፣ ምርጫውን ተንተርሶ በተፈጠረው አለመረጋጋት በአዲስ አበባ በርካታ መሬቶች ያለ መንግሥት ዕውቅና መያዛቸው ይታወሳል፡፡

እነዚህ ይዞታዎች የተያዙት፣ በተለይ ከ1996 እስከ 1998 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት ሲሆን፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ቦሌ ቡልቡላና ወረገኑ፣ በየካ ክፍለ ከተማ የቀድሞ 20/21 ቀበሌ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ ሃና ማርያምና ጀሞ ኮንዶሚኒየም ጀርባ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ አንፎ ሜዳን ጨምሮ በርካታ ባዶ ቦታዎች ተወረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸው እንዳስታወቁት፣ በተጠቀሰው ጊዜ መጠነ ሰፊ የመሬት ወረራ ተደርጓል፡፡

በወቅቱ በሕገወጥነት የሰፈረው የሕዝብ ብዛት ከፍተኛ መሆኑና የተገነባው ቤት ቁጥር በርካታ መሆኑ፣ በኅብረተሰቡና በኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ከግምት በማስገባት፣ አስተዳደሩ ሕጋዊ እንዲሆኑ መወሰኑን አመልክተዋል፡፡

‹‹5,700 አባላት ያላቸው ማኅበራት የያዟቸው ቦታዎች ዕልባት ሳያገኙ ለዓመታት ተንከባለው እዚህ ደርሰዋል፡፡ እነዚህ ይዞታዎች ከከተማው ፕላን ጋር እያጣጣሙ በሊዝ ሥርዓት እንዲገቡ ተደርጓል፤›› በማለት ከንቲባ ድሪባ የካቢኔያቸውን ውሳኔ አሳውቀዋል፡፡

‹‹ይህ ችግሩን ለመፍታት የተወሰደው ውሳኔ ታሪካዊ ሊባል ይችላል፤›› በማለት ከንቲባ ድሪባ ገልጸው፣ ‹‹ነገር ግን በወቅቱ የማኅበራቱ ኃላፊ ሆነው በሕገወጥ ተግባራት የተሠማሩ ግለሰቦች በዚህ ውሳኔ አይስተናገዱም፤›› በማለት ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሳኔ፣ በዚህ ብቻ ሳያበቃ ከኅዳር 2004 ዓ.ም. በፊት የተፈቀደላቸውን የግንባታ ጊዜ ባልጠበቁ 146 ማኅበራት ላይ የተጣለ ዕግድ አንስቷል፡፡ እነዚህ ማኅበራት 3,600 አባላት አሏቸው፡፡ አባላቱ ከአስተዳደሩ ጋር በገቡት ውል ግንባታቸውን ማካሄድ ባለመቻላቸውና የገነቡትም ከ30 በመቶ የማይበልጥ በመሆኑ ታግዶ ነበር፡፡

ነገር ግን አስተዳደሩ ሲንከባለል የቆየውን ይህን ችግር በድጋሚ በመመልከት የሁለት ዓመት የግንባታ ጊዜ ፈቅዶላቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ በአዲስ አበባ ፈር ቀዳጅ የሆነው አያት የመኖሪያ ቤቶች ሥራ ድርጅት ከአስተዳደሩ ጋር በገባው ውል መሠረት ግንባታ ባለማካሄዱ ታግዶ የቆየው ጉዳይ ዕልባት አግኝቷል፡፡

በወቅቱ አያት መኖሪያ ቤት ገንብቶ ለማስረከብ ውል የገባ ቢሆንም፣ ሰርቪስ ቤቶች (ሰርቪስ ኳርተር) እየሠራ ለተጠቃሚዎች ሸጧል በሚል 600 የሚሆኑ ደንበኞች ካርታ እንዳይሰጣቸው ታግዶ ነበር፡፡

ይህ ሲንከባለል የቆየ ጉዳይን አስተዳደሩ በድጋሚ በማጤን ዕግዱ ተነስቶ፣ የይዞታ ስም እንዲዞርላቸውና የተናጠል ካርታም እንዲሰጣቸው ውሳኔ መተላለፉን ከንቲባው ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ጉዳዮች ለዓመታት ሲንከባለሉና በባለጉዳዮች መጉላላት የፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መሆናቸው ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ይህንን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ ለየት ያለ ዕርምጃ መውሰዱን ከንቲባ ድሪባ አመልክተዋል፡፡
 

Related:

  የሽፍታ/ወንበዴ መንግሥት በኢትዮጵያ

  የመሬት ካድስተር ምዝገባ ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው

  በመዲናዋና ዙሪያዋ 93 ሺህ ለሚሆኑ የመሬት ባለይዞታዎች ማረጋገጫ ተሰጥቷል

  አዲስ አበባ ላለባት የመሬት ዝርፍያ ችግር መፍትሄው ጊዜ የሚገዛላቸው ዳግም ቋሚ የንብረት ምዝገባ መሆኑን ዋናዎቹ የሕወሃት መሬት አስዘራፊዎቹ ያሰማሉ – ማንን ለማጃጃል?

  Urban land lease legislation: the prime minister’s new front against urban dwellers

 

One Response to “ያልነውና የጠበቅነው ሆነ፡ በምርጫ 97 በተፈጠረ ቀውስ የተወረሩና በሕገ ወጥ መንገድ ሕወሃቶችና ሌሎችም የዘረፏቸው መሬቶች ሕጋዊ ተደረጉ – የቀጣዩ የኅብረተሰባችን ቀውስ ማባባሻ!

 1. negasi at 17:24 #

  tplf -the world’s israel

  Like

Comments are closed.

%d bloggers like this: