የሕዝባዊ ትግል ውጤት፡                        በሰንዳፋ በአንድ ቢሊዮን ብር በተገነባው ዘመናዊ ደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ መጠቀም ሕዝቡ ከለከለ!

20 Jul

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
በሪፖርተር
 

“ለጊዜው ሌሎች ማጠራቀሚያዎች እየፈለግን ነው”

  የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ

ለደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተገንብቶ በታኅሳስ ወር 2008 ዓ.ም. አገልግሎት መስጠት ጀምሮ የነበረው “ሰንዳፋ ሳኒተሪ ላንድ ፊል” ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ እየተወሰደ የሚደፋው ቆሻሻ እንዳይወገድ ተከለከለ፡፡

አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ሰባት ወራት እንዳስቆጠረ በተገለጸው ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ ቆሻሻ እንዳይጣል የከለከሉት፣ በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳዊት አየለ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በኦሮሚያ ክልል ከካራ በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ሰንዳፋ በተገነባው ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ ገንዳ ውስጥ የአዲስ አበባ ደረቅ ቆሻሻ እንዳይጣል የከለከሉት የአካባቢው አርሶ አደሮች ናቸው፡፡ በመሆኑም ከሐምሌ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የአዲስ አበባ ደረቅ ቆሻሻን ወደዚያ መውሰድ አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡

መጣያ ያጣው የአዲስ አበባ ቆሻሻ በሠንዳፋ። ለመሆኑ ከዓለም ባንክ 100 ሚልዮን ብር ብድር የተወሰደለት፣ ከጃፓንም ከፍተኛ ገንዘብ የተለገሠለት የአቃቂ የቆሻሻ ሳኒቴሽን ፕሮጀክትን ገንዘብ ማነው የበላው? (ፍቶ ሪፖርተር)

መጣያ ያጣው የአዲስ አበባ ቆሻሻ በሠንዳፋ። ለመሆኑ ከዓለም ባንክ 100 ሚልዮን ብር ብድር የተወሰደለት፣ ከጃፓንም ከፍተኛ ገንዘብ የተለገሠለት የአቃቂ የቆሻሻ ሳኒቴሽን ፕሮጀክትን ገንዘብ ማነው የበላው? (ፍቶ ሪፖርተር)

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል የሚመለከተው የአስተዳደር አካል በጉዳዩ ላይ የተወያዩ ቢሆንም፣ ስምምነት ላይ አለመደረሱን ከዋና ዳይሬክተሩ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ላለፉት ሰባት ቀናት የአዲስ አበባ ደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳዎች ሞልተው በመፍሰስ ላይ ሲሆኑ፣ የክረምት ወቅት በመሆኑ ምክንያት ከገንዳ ተርፎ የሚፈሰው ቆሻሻ በዝናብ ውኃ እየታጠበ ስለሚፈስ ነዋሪዎች ሥጋት ውስጥ መሆናቸውን እየገለጹ ነው፡፡

በየካቲት 12 ሆስፒታል አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ግርማቸው አሰፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአካባቢው ያሉት ገንዳዎች በየቀኑ በደረቅ ቆሻሻ ይሞላሉ፡፡ “በአካባቢው ሆስፒታል ያለ በመሆኑም፣ ደረቅ ቆሻሻ የሚያነሱ ተሽከርካሪዎች ቶሎ ቶሎ እየመጡ ያነሱ ነበር፡፡ በገንዳዎቹ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የሞቱ እንስሳት፣ ፈርስና ከፍተኛ መርዝነት ያላቸው ኬሚካሎች ጭምር ስለሚደፉ ገንዳዎቹ ከአንድ ቀን በላይ መቆየት አይችሉም፤” ብለዋል፡፡ ነገር ግን ላለፉት ስድስት ቀናት ገንዳዎቹ ባለመነሳታቸው በአካባቢው መተላለፍ አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡

አቶ ግርማቸው እንደገለጹት ሁሉ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች የተቀመጡ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳዎች በመሙላታቸው፣ ነዋሪዎች በመጥፎ ሽታ እየተቸገሩ መሆኑን በምሬት እየተናገሩ ነው፡፡

የከተማው ነዋሪዎች እንደሚናገሩት ችግሩ የተፈጠረበት ወቅት ክረምት ከመሆኑ አንፃር ሥጋታቸው የተደራረበ ነው፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ በየቀኑና በየሰዓቱ ከአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ነዋሪዎች መጠንቀቅ እንዳለባቸው፣ አካባቢያቸውን ማፅዳትና በንፅህና መጠበቅ ግዴታቸው ጭምር መሆኑን እየገለጹ ባለበት ወቅት፣ አስተዳደሩ ያስቀመጣቸው ገንዳዎች አለመነሳታቸው ሥጋታቸውን ከፍ እንዳደረገው እየተናገሩ ነው፡፡

የከተማ አስተዳደሩም ሆነ መንግሥት ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው ለሕዝቡ ጤንነት በመሆኑ፣ አፋጣኝ መፍትሔ መፈለግና የተጠራቀሙት ቆሻሻዎች መነሳት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የኤጀንሲው ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ስለታሰበው መፍትሔ ተጠይቀው፣ “ሌሎች አማራጮችን እየፈለግን ነው፡፡ አቃቂ ቃሊቲ አካባቢና ሌሎች አካባቢዎችንም እያየን ነው፤” ብለዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ ለምን እንደከለከሉና ከክልሉ ኃላፊዎች ጋር ስምምነት ላይ ያልተደረሰበትን ምክንያት የተጠየቁት ዋና ዳይሬክተሩ ዝምታን መርጠዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ በቀን 2,400 ቶን ወይም 8,050 ሜትር ኪዩብ ቆሻሻ ወደ ማጠራቀሚያ ገንዳ ይወሰድ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
 

%d bloggers like this: