የጥፋት ዘመን! የሞተ በሬ ስጋ እና ባዕድ ነገሮችን ከጤፍ ጋር ቀላቅለው እንጀራ ለመሸጥ የሞከሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ!

22 Jul

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 15 ፣ 2008 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የሞተን በሬ ስጋ ለልኳንዳ ቤት የሚያቀርቡ እንዲሁም የጣውላ ፍቅፋቂንና ጀሶን ከጤፍ ዱቄት ጋር ቀላቅለው እንጀራ የሚሸጡ ግለሰቦች ቁጥር እየተበራከቱ መጥተዋል።

የከተማዋ ፖሊስ ኮሚሽንም በዚህ ህገ ወጥ ተግባር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር እያዋለ ይገኛል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ከሞተ ሁለት ቀን ያለፈውን በሬ በመግፈፍ ስጋውን ለልኳንዳ ቤቶች ለማቅረብ የሞከረው ግለሰብም በቁጥጥር ስር ውሏል።

ግለሰቡ የአካባቢው ነዋሪዎች የሞተው በሬ እንዲነሳላቸው ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት፥ በሬውን ከማስወገድ ይልቅ ምሽትን ተገን አድርጎ ስጋውን በመግፈፍ በማዳበሪያ አዘጋጅቶ ለልኳንዳ ቤቶች ሊያቀርብ ሲል ነበር በቁጥጥር ሰር የዋለው።

የጣውላ ፍቅፋቂ (ሰጋቱራ) እና ለግንባታ የሚውልን ጀሶ ከጥቂት የጤፍ ዱቄት ጋር ቀላቅለዉ እንጀራ አድርገው ለሱቆች እና ሆቴሎች ሲያከፋፍሉ የነበሩ ሰዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ይህ ድርጊት በሰበታ ከተማ ቀበሌ 02 ዋቶ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፣ በኮልፌ ቀራኒዮ ወረዳ 3 እና 5 እንዲሁም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ጭምር የተፈጸመም ነበር።

በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ 4 ማዳበሪያ ጥራቱን ያልጠበቀና ንጹህ ያልሆነ የጤፍ ዱቄትና 8 ማዳበሪያ ጀሶ ተዘጋጅቶ በፖሊስ እጅ ገብቷል።

በቦሌ ክፍለ ከተማ ደግሞ እስካሁን በርካታ ጀሶ እና ከመርዛማ ነገሮች ጋር የተቀላቀለ ጤፍ መገኘቱም ተገልጿል።

በአቋራጭ ለመበልፀግ ሲባል በሚሰራው በዚህ ወንጀል እንጀራዉ እንጀራ ሆኖ ለመውጣት 35 በመቶ እንኳን የጤፍ ዱቄት አይደረግበትም።

ታሞ የሞተን በሬ ገፈው ለልኳንዳ የሚያቀርቡ፣ በርበሬን ከቀይ አፈር ጋር የሚቀላቅሉ፣ ቅቤን ከሙዝ ጋር አወዳጅተው የሚሸጡና ጤፍን ከጀሶና ሰጋቱራ ጋር ፈጭተው ለህዝብ የሚያቀርቡ በርካታ መሆናቸውንም ፖሊስ ይገልፃል።

ዋነኛው የገበያ ማዕከል መርካቶን ጨምሮ በሰባት የመዲናዋ ክፍለ ከተሞች፥ በዚሁ ተግባር ላይ የተሰማሩ በርካታ ሰዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዲቪዚዮን ሀላፊ ምክትል ኮማንደር አበራ ቡሊና ይናገራሉ።

ከአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የተገኘ መረጃ ደግሞ በመዲናይቱ 120 ያክል ህገ ወጥ የከብት እርድ የሚፈፀምባቸው ስፍራዎች ይገኛሉ ይላል፤ ይህም ጤናማ ያልሆኑ በርካታ ከብቶች በየስርቻው ይታረዳሉ ማለት ነው።

ይህ ህገ ወጥ ተግባር ታዲያ ህብረተሰቡን ትልቅ ስጋት ውስጥ እየከተተው መሆኑንም ነው ነዋሪዎች የሚናገሩት።

ከ150 በላይ በሽታዎች ከከብቶች ወደ ሰው የሚተላለፉ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ 11ዱ ለሞት የሚዳርጉ ናቸው።

ባዕድ ነገር ታክሎባቸው ለገበያ የሚቀርቡ የምግብ አይነቶች በአሁኑ ሰዓት የተከሰተውን አተትን ጨምሮ እስከ ካንሰር የሚደርስ በሽታን ያስከትላሉ።

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ የህክምና መምህር ዶክተር ተመስገን በየነ፥ እነዚህ የተበከሉ ምግቦች በፍጥነት የህመም ምልክታቸው ታይቶ መድሃኒታቸው ሊገኝ የሚችል አልያም ያለምንም ህመም ስር ሰደው እስከሞት ሊያደርሱ የሚችሉ ናቸዉ ይላሉ።

በዚህ ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ላይ የተሳተፉ አካላት ላይም ክስ ተመስርቶ አስፈላጊው የፍርድ ሂደት እየተደረገ መሆኑም ተጠቅሷል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም ሆነ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጀት ህብረተሰቡ ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን በመከታተል እና ወንጀለኞችን በማጋለጥ ድርጊቱን ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
 

%d bloggers like this: