ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሣኤ ሕወሃት ሁለትን ለመምራት ዝግጅት በማድረግ ላይ ይሆኑ?

1 Aug

በከፍያለው ገብረመድኅን The Ethiopia Observatory (TEO)
 

ለመጀመሪያ ጊዜ የጀኔራል ጻድቃንን ጽሁፍ እንዳነበብኩ፣ መደስቴን ልደብቅ አልችልም። በአንድ በኩል ዛሬ ሃገሪቱ ካለችበት የችግር አዘቅት ውስጥ ሕወሃት መዝፈቁን በማንሳት ከጥፋቱ ነጻ አለማድረጋቸውን አሳይቶኛል – በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የእርሳቸውን አመለካከት ባልጋራም፣ በአንዳንድ ደግሞ ፈጽሞ ባልስማማም።

በሌላ በኩል ደግሞ፥ ሕወሃትን ለማጋለጥ ከተነሱት መካከል፡ እርሳቸው መለስ ዜናዊን የአንድ ግለሰብ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ መመሥረቱንና ዲሞክራሲን ደብዛውን ማጥፋቱን በሚገባ ማጋለጣቸው ዛሬ ድርጅቱ ዕርቃኑን መቅረቱን የሚያረጋግጥና የእርሳቸው ዐይነት ግንዛቤ ባላቸው ግለሰቦች የሕወሃት መስተዳድር ትንሽ ገፋ ቢደረግ፡ ጀርባውን ለመጨረሻ ጊዜ ልናይ እንደምንችል ተሰምቶኛል።


 

ሆኖም ባለፈው ጽሁፌ እንደገለጽኩት፡ ጀኔራል ጻድቃን የኢትዮጵያ ሕዝብ የማያውቀውን አዲስ ነገር ነግረውታል ለማለት እቸገራለሁ። ነገር ግን እንደርሳቸው ዐይነት ግለሰቦች ሕወሃትን ለማጋለጥ መፈለጋቸው በአንድ በኩል የራሳቸውን የተደላደለ ኑሮ ለማረጋገጥ መሆኑ አያጠራጥርም። በሌላ በኩል ደግሞ
ጽሁፋቸው እርሳቸውን መሰል ከሆኑ የሕወሃት ሰዎች ጋር የመከሩበት ሃሣብ ሊሆን ይችላል የሚለውንም ግንዛቤ ውስጥ ማግባት ያስፈልጋል። ስለሆነም ያቀረቧቸውን ሃሣቦች በሚገባ መርምሮ ኢትዮጵያውያን በጋራ ሊይዟቸው የሚገባቸውን ሃሣቦች ማብሰልሰልና መሳል አስፈላጊ ነው።

እዚህ ገጽ ላይ ከቀረበው ቪዲዮ እንደሚታየው፥ ይህንን በሚመለከት ኢሣት የሚያረካ ጅማሪ ያደረገ ቢሆንም፣ በተለያዩ መንገዶችም የሚቀጥለውን እርምጃ የሚጠቁሙ ሥራዎች ሊከናወኑ ይገባል። ነገር ግን የሚደረገው ውይይት እንደ እርሳቸው መሰል የሕወሃት ባለሥልጣኖች እንዳይወጡ የሚያስበረግግ እንዳይሆን ጥንቃቄ የያስፈልጋል። እርሳቸውም ይህንን እስመልክተው “ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ስለሆነ በሰለጠነ መንገድ የመንደር ስድቡና አሉባልታውን አስቀርተን በጉዳዩ ላይ እንነጋገርበት የሚል ሃሳብ አለኝ” በማለት ጥቆማቸውን ሠጥተዋል።

በነገራችን ላይ ጂነራሉ በጽሁፍ ያቀረቧቸው ሃሣቦች የእርሳቸው ብቻ መሆናቸውን እጠራጠራለሁ። አንደኛ እርሳቸውም በገጽ 25 ላይ “…በቅርብ ቀናት ከብዙዎቹ ጓደኞቼ ጋር ስንወያይ፣ በአንድ የውይይት ወቅት ሃሳቡ ተነሳና ‘የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር ባለው ግንኙነት፤ በተለይ አሁን ጠንክሮ መገኘት አለበት፣ በሚለው ተወያየን” ይላሉ። እነማን ናቸው? ስንት ይሆናሉ? ከምን ሃላፊነትና የሕይወት ጎዳና ነው የሚመጡት? የመሳሰሉት ጥያቄዎች ምናልባት ወደፊት መልስ ያገኙ ይሆናል።

ሁለተኛ፥ ጄኔራል ጻድቃን በትግራይ ያለውን የሕወሃት አመራር መጥፎነት ማጋለጣቸው፥ ትግራውያን እንዳይተባበሩት ጭምር መልዕክት ያዘለ መሆኑን ልብ ልንለው ይገባል። በሌላ በኩል ደግሞ፡ ለትግራውያን ጄነራሉ ያነሷቸው ነጥቦችና ጥይቄዎች አዲስ አይደሉም።

ለምሣሌ ያህል መቶ ያህል ትግራውያን ዋሽግንቶን ዲ.ሲ. የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ ነሐሴ 16፣ 2015 ምሥጢራዊ ስብሰባቸውን ሲያካሄዱ፡ ተሰብሳቢዎቹን ሃሣብ ለማካፈል ከመቀሌ የተላኩት የሕወሃቱ ሊቀመንበር ዓባይ ወልዱ ባለቤት ወይዘሮ ትርፉ ኪዳነማርያምና አቶ ዳንኤል አሰፋ – የደኅንነቱ ሹም ጌታቸው አሰፋ ወንድም ሲሆኑ –ለእነርሱም በወቅቱ ትግራውያን ያነሷቸው ጥያቄዎች ዛሬ ጀኔራል ጻድቃን ካነሷቸው ጋር ዝምድና እንዳላቸው ኢሣት በወቅቱ ዘገባውን ከምሥጢራዊ ምንጮቹ አሰባስቦ እንድናውቅ ረድቶናል።

ተሰብሳቢዎቹ የሕወሃት አመራር ላይ የመረጓቸው ወቀሳዎች እጅግ ያመረሩ ነበሩ! “እናንተ ለትግራይ ህዝብ ምንም አልሰራችሁም… አማራጭ አጥተን እናንተን እየደገፍን ለመቀጠል ተገደናል፣ ከእናነተ ውጭ ያለው አማራጭ ጉድጓድ ስለሆነና፣ የትናንቶቹ ተመልሰው እንዳይመጡ ከነቸግራችሁ ከእናንተ ጋር ቆመናል…” በተጨማሪም በአዲስ አበባ ደረጃ ልማቱ ለምን በትግራይ አይካሄድም? ለኢትዮጵያ ዓመታዊ ስፖርት ውድድር ባሕር ዳር ከመሄድ ይልቅ መቀሌ ውስጥ ለምን ትልቅ ስታዲየም አልተሰራም የሚል ጥያቄ ከተሰብሳቢዎች ተነስቷል። ከትግራይ የመጡት ባለሥልጣኖች ምንም መልስ የሚመስል ነገር ከውስጣቸው ለተሰብሳቢዎች ሊያካፍሉ አልቻሉም።

በተመሣሣይ መንገድ ጄነራል ጻድቃንም፥ የሚከተለውን ያሰምሩበታል።

  “ትንሽ በትምህርት ገፋ ያደረገውና ሃብት ያከማቸው ክልሉን እየተወ አዲስ አበባ ላይ ነው ስራውን የሚሰራው። ይህ የትግራይን ሕዝብ በቀጣይነት ደካማ እያደረገ የሚሄድ ነገር ነው። ለእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ መፈጠር በመሃል ሃገር ያለው ኢኮኖምያዊ ዕድሎች (Opportunities) አስተዋፅኦ እንደሚያድርግ ይገባኛል። ይህ ኢኮኖምያዊ ዕድል ባለሃብቶችን የመሳብ ዓቅም እንዳለው ግልፅ ነው። ከዚሁ ጋር ግን በትግራይ የተመቻቸ ሁኔታ ባለመፈጠሩ የሚሸሸው ባለሃብት ደግሞ ብዙ ነው። ዋናው ጉዳይ ግን ሕወሃትና የክልሉ መስተዳድር እንዴት አድርገን ነው መግፋቱን ትተን መሳብ የምንችለው ብሎ ሌት ተቀን መጨነቅ አለበት። አሁን ላለው ሁኔታ መፈጠር ትልቁን ሃላፊነትና ድርሻ የሚወስደው አሁን ያለው የሕወሃትና የክልሉ መስተዳደር ነው። የትግራይ ሕዝብ በትግሉ ወቅት ይሁን ከዛ በኋላ ባፈራቸው ከሁሉም የላቀ እወቀት ችሎታና ይህንን ለመተግበር ቁርጠኝነት አላቸው ብሎ በሚያምንባቸውና በዴሞክራስያዊ መንገድ በሚመርጣቸው ሲፈልግም በሚያወርዳቸው ልጆቹ መመራት አለበት። ሁለተኛው ዋስትናችን ራሳችን ይህንን ስራ ስንሰራ ነው፡፡”

በእርሳቸውም በኩል፣ ራያ ቢራን ወደ ማይጨው መወሰዳቸው በዚሁ እምነት ላይ የተመሠረተ መሆኑ ግልጽ ይመስላል። ይህንንም አስመልክተው እንዲህ ይሉናል፦ “እኛ ሃገራችንን በጠቅላላ ጠንካራ ለማድረግ ከዚህ ጋር አያይዘን ደግሞ የድርሻችን የሆነውን የትግራይ ሕዝብ ጠንካራ ለማድረግ የምንችለው በዋናነት እዛው ትግራይ ውስጥ በሚሰራ ስራ ነው።”

ዘላቂው ዓላማቸው ግን እርሳቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያን ከጥፋት ለመታደግ ብቻ ሣይሆን፣ አሁንም ሕወሃት ቁልፍ ሚና የሚጫወትበት መሰተዳደር ለመመሥረት ለመሆኑ የተበታተኑ ምልክቶች ጽሁፋቸው ውስጥ ይታያሉ። አሁን ትዝ ከሚሉኝ መካከል፡ የሚከተለው ይገኝበታል፦

  “እዚህ ላይ በርከት ባሉ የትግራያ ተወላጆች የሚነሳ አንድ ጥያቄ አለ፡፡ ይኸውም አሁን ባለው መንግስት ላይ ያለንን “የበላይነት” ካጣን ጠቅላላ መብቶቻችን አንድናጣ መልሰን እንድንጨቆን አድልዎ እንዲፈፀምብን ቢደረግስ ምን ዋስትና አለን? የሚል ነው፡፡ ዋስትናችን በትግላችን ያገኘነው አሁንም ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ሆነን እየታገልን የምንጠብቀው ሕገ-መንግስታችን ያለምንም ማቅማማት ተግባራዊ ማድረግ ነው። ሌላው ዋስትናችን ሕዝቡ ራሱ ነው፡፡ የተወሰኑ የክልሉ ተወላጆች በፖለቲካዊ ሥርዓቱ ወሳኝ በሚባሉ የሥልጣን ቦታዎች ላይ መቀመጥ አይደለም። አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሕገ-መንግስት የትግራይ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ሊጠብቀውና ሊተገብረው የሚፈልገውን ያህል፣ የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የአፋር፣ የሶማሊ፣ የሐረሪ፣ የደቡብ እና ሌሎች ሕዝቦች ሊጠብቁትና ተግባር ላይ እንዲውል የማይፈልጉበት ምክንያት የለም። አሁን ያለው ሕገ-መንግስት የሚቃወሙ ሃይሎች እንዳሉ አውቃለሁ። ከነዚህ በላይ ግን ሕገ-መንግስቱ ሲጸድቅ በነበረው አብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ መንፈስ አለመተግበሩ የሚቃወሙ ይበዛሉ፡፡ ከዚህ የተነሳም ሙሉ በሙሉ ተግባር ላይ ከዋለ ሕገ-መንግስቱን የሚጠብቀው፣ የሚያዳብረው ኋይል ይበዛል ያሸንፋል። ይህንን ሕገ-መንግስት መጠበቅ በሚል ሰበብ አሁን ያለውን ስርዓት የመጠበቅ ሸክም ለምን በትግራይ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ብቻ ይወድቃል?”

በእኔ አተረጓጎም ይህ አባባላቸው፣ ሕዝቡን አስተባብረው ሕገ-መንግስቱን ተገን አድርገው ጉዞአችውን ከመጀመራቸው በፊት የድጋፍና ተቃውሞን ሚዛን ሁሉ ማስላታቸውን ይናገራሉ! ከላይ የተጠቀሰውን፡ እንዴት? በማን አመራር? ከሚሉት ጥያቄዎች ጋር በማገናዘብ መልስ እንዲያፈልቅ መጎትጎት ያስፈልጋል!

አሁን ሃገሪቱን ካጋጠማት ቀውስ አንጻር ምን ሊደረግ ይችላል ለሚለው ዕቅዳቸውን/ሃሣባቸውን እንደ መፍትሄ በመግቢያቸው ውስጥ ያሠፈሩት አንቀጽም በጠቋሚነት እንዲህ ይላል፦

  “…በከፍተኛ የሕዝቦች መስዋዕትነትና ተሳትፎ የፀደቀውን ሕገ መግስታችንን መሠረት አድርገን በሕገ መንግስቱ የተቀመጡትን ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶችን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግና በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ፖለቲካዊ ሃይሎችም ያለምንም ተፅዕኖ ያልተገደበ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አድርገው በመጨረሻም በገለልተኛ በዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ነፃ ዴሞክራዊያዊና ያለምንም ተፅዕኖ የተከናወነ ምርጫ መሆኑ ተረጋግጦ የተካሄደ ምርጫ የሚሰጠንን ውጤት ተቀብለን ለመጓዝ ቆርጠን ስንነሳ ነው በሚል አስተሳሰብ ላይ ያጠነጥናል፡፡ ይህ ፖለቲካዊ ሂደት ብዙ ስራና ጊዜ የሚጠይቅ ስለሆነ ከአሁኑ መጀመር አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡”

ሌላው ከዚሁ ግራ ተያይዞ መታየት ያለበትና ተገቢውን ትርጓሜ ማገኝት የሚገባው ጉዳይ የሚከተለው ይመስለኛል፦

  “[አሁን ያለውን ችግር] ለተወሰነ ግዜ በማዘግየት ችግሩ ይበልጥ ስር እየሰደደ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውም እድል እየጠበበ እንዲሄድ ያደርጋል። በዚህ ግዜም በሃገሪቱ ያለውን ቀውስ እየተባባሰ ከመሄዱም በላይ በመጨረሻም በጣም አውዳሚ በሆነ መንገድ ችግሩን ለመፍታት ለሚፈልጉ ሃይሎች የተመቻቸ ሁኔታ ይፍጥርላቸዋል። ስለሆንም ፈጥኖ የሚታየው የመፍትሔ አቅጣጫ የመሆን እድሉም የሰፋ አማራጭ ሆኖ ሳለ ለሃገሪቱ አሁን የሚያስከፍለው ዋጋ ይህን ኋላ በሚያስከትለው ነውጥ እጅግ የከፋው ነው፡፡ ይህ ሁኔታ እስከ አሁን ድረስ የተመዘገቡትን ድሎች ጠራርጎ ያጠፋል፡፡ አገሪቱን ወደኋላ ይመልሳል ብቻ ሳይሆን ቀጥሎ የሚመጣውም ምን ዓይነት ስርዓት እንደሆነ መተንበይና መገመት አይቻልም፡፡ እነዚህ ሁለት አማራጮች በጊዜ ሊለያዩ ካልሆነ በስተቀር በጣም ተመሳሳይ ናቸው። በራሳቸው መንገድ የሚከሰቱም ስለሆኑ እንዳይከሰቱ ምን እናድርግ በሚለው ሃሳብ ላይ ካልሆነ በእነሱ ላይ ብዙ መናገር አይቻልም።”

ከላይ ጂነራል ጻድቃን ያሠፈሩት እንዳለ ሆኖ፡ ለፕሮፌሰር መሣይ ከበደ የሠጡት መልስ፡ የሃገሪቱ ችግር ከፍቷል፡ ኢትዮጵያውያን ሕወሃትን ለማሽቀንጠር ዕድል ይፈጥርልናል ብለው የሚያሰሉ ካሉ፡ ደጋግመው ያሠመሩበት ነገር በዚህ ሁኔታ ውስጥ አንድ ወገን ብቻውን አሸናፊ አይሆንም የሚል መስሎ ታይቶኛል።

ለምሣሌም ያህል የሚከተሉትን እንመልከት፦

  “I am trying to identify what could work based on the realities on the ground. I don’t see any other frame of reference, for the whole country to initiate peaceful; orderly; managed change, except on the basis of the current constitution. The other alternative I see is to fight and resolve our differences. I don’t take this as an option to discuss. If it comes it will come by itself and I think the final result will be mutual destruction. That is how I see it, hence the call to avert the other scenario that I discussed.”

ደህና የሄዱ ሲመስል፣ እርሳቸውም ያሰቡት ፖሊሲ አሁን ያለው ላይ የተመሠረተ ነገር ደግሞ ጎትተው እንደሚከተለው ያመጣሉ፦

  “በሀገራችን ያለው ፖለቲካዊ ያለመረጋጋት በመጠቀምና ይህንኑ ያለመረጋጋት በማባባስ፣ ከቁጥጥር ውጭ እንዲሄድ የሚፈልጉ የውጭ ሃይሎች ሌት ተቀን እየሰሩ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ለእነዚህ የውጭ ሃይሎች ለማገልገል በመወሰን የሚንቀሳቀሱ የሀገራችን ሃይሎችም አሉ፡፡ እነዚህ ሃይሎ በጋራ የሚፈጥሩትን ፓለቲካዊ ያለመረጋጋትና ከዛም ያለፈ ቀውስ መቋቋምና ማሸነፍ የምንችለው ሃገር ወዳድ የሆኑ ፖለቲካዊ ሃይሎች በሚያማማቸው ፖለቲካዊ መድረሻ ተገናኝተው በመጀመሪያ የሀገራችንን የራሳችንን ችግሮች ስናስወግድ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህንን ደግሞ ህገ-መንግስቱን መነሻ በማድረግ ሊጀመር ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ ቢሆን የሀገር ውስጥና የውጭ ሃይሎች በቅንጅት በሀገራችን ሊፈጥሩት የሚፈልጉትን ቀውስ ማሸነፍ እንችላለን፡፡ አለበለዚያ ለእነዚህ ሃይሎች ምቹ ሁኔታ ካልፈጠርንላቸው ቀውሱን ለመፍታት እየተቸገርን እንሄዳለን የሚል እምነት አለኝ፡፡”

ጄኔራል ጻድቃን ኢትዮጵያን ያገጠሟትን ችግሮች፥ በተለይም ለሕዝቡ ጥያቄዎች በሕገ መንግሥቱ ማዕክልነት መልስ/ መፍትሄ መስጠት ያሰፈልጋል ቢሉም፣ እርሳቸውም እምብዛም መከላከያ ኃይልን በሕዝብ ላይ ከመጠቀም ይቆጠባሉ የሚለው ግምት አሳሳች ነው። ለምሳሌም ያህል ከኅዳር ጀምሮ ኦሮሚያ ውስጥ ተካሂዶ የነበረው ነውጥ “አመፁ በስፋትም በግዜም ቢቀጥል ኖሮ በተጨማሪም ሌሎች ተጓዳኝ የህዝብ አመፆች ቢነሱ ኖሮ በማዕከላዊ መንግስት ላይ ሊፈጠር ይችል የነበረውን ችግር መገመት አይከብድም” የሚለውን መመልከቱ ይጠቅማል!

በየዕለቱ እንደዚህ በአጋዚ የሚጨፈጨፉትን ኦሮሞ ወጣቶች፡ ጄኔራል ጻድቃን በጭዳ መልክ የሚመለከቷችው ከሆነ፡ የእርሳቸው ጥረት የኢትዮጵያን ሕዝብ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ሃሣብ አንግቦ ነው የተነሣው የሚለውን ጥያቄ ላይ ይጥለዋል። ይህ ወጣት ዛሬ ነው በጥይት የተመታው፤ ደሙ እየፈሰሰ፤ እርሱም እያስተዋለ ያልንዳች ዕርዳታ ለማሸለብ በመዘጋጀት ላይ ነው - Waiting for death while bleeding from Agazi bullet (FB/JM)

በየዕለቱ እንደዚህ በአጋዚ የሚጨፈጨፉትን ኦሮሞ ወጣቶች፡ ጄኔራል ጻድቃን በጭዳ መልክ የሚመለከቷችው ከሆነ፡ የእርሳቸው ጥረት የኢትዮጵያን ሕዝብ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ሃሣብ አንግቦ ነው የተነሣው የሚለውን ጥያቄ ላይ ይጥለዋል። ይህ ወጣት ዛሬ ነው በጥይት የተመታው፤ ደሙ እየፈሰሰ፤ እርሱም እያስተዋለ ያላንዳች ዕርዳታ ለማሸለብ በመዘጋጀት ላይ ነው – Waiting for death while bleeding from Agazi bullet (FB/JM)

ስለሆነም፣ ለትግራይ ችግሮችና መብቶች የሚቆረቆሩትን ያህል ኦሮሚያ ውስጥ ያለው የሕዝብ ጥያቄ ግን በኃይል እንዲዳጥ እርሳቸውም ያላቸው ስሜት/ፈቃደኝነት አፈትልኮ መውጣቱን ማሳየቱ፣ ጄኔራል ጻድቃን የተነሳሱበትን ዓላማ ዜጎች አበክረው እንዲመረምሩ ይህ አባባላቸው ያስገድዳል!

የጄኔራል ጻድቃን አቀራረብ ዝግጅት የተደረገበትና የትግራይ ስዎችም ሆኑ ሌሎች የድርሻቸውን ያካፈሉበት ነው የሚል ግምት አለኝ፣ በተለይም ከጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት አቀራረብና ሃሣብ ጋር ሲነጻጸር!
 

%d bloggers like this: