የሕወሃት ትግራይ ጦር የገደላቸውን ሕዝቡ ሲቀብር በኃዘንተኞቹ ላይ አጋዚ አዲስ ተኩስ ከፈተ፤ የኦሮሚያ ሁኔታ አምርሯል፤ ቅዳሜ በመላው ኦሮሚያ የተቃውሞ ሠልፍ ይካሄዳል!

3 Aug

በከፍያለው ገብረመድኅን The Ethiopia Observatory (TEO)
 

ገና ከትግራይ ከመውጣታቸው በፊት፡ የወያኔ ወንበዴዎች ይታወቁ የነበረው በጭካኔያቸው መሆኑን ‘ስድሽተ ዜሮ’ የተሠኘው የኢሣት ዶኪመንተሪ አስተዋውቆን ነበር። ዛሬም ያንኑ ጭካኔ በሕዝባችን ላይ ከጋምቤላ እስከ ኦጋዴን ከኦሮሚያ እስክ ጎንደር፡ ከኦሞ ሸለቆ እስከ መሃል ሃገር በዙ መልኮቹ አይተናቸዋል። እያየናቸውም ነው።

ከዚህ በታች ያለው ፎቶግራፍም የሚያሳየው፣ ሰሞኑን ከሞት ጋር ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ ግብግብ የተያያዘው ወጣት ደም፡ እንዲህ እንደራዊት ደም እንዲፈስ ያደረገው ወንጀለኛው ሕወሃት ተጠያቂ መደረግ አለበት! ይህ ወጣት ከሁለት ቀን በፊት ነው በትግራይ አጋዚ የተመታው፤ ደሙ እየፈሰሰ፤ እርሱም እያስተዋለ ያላንዳች ዕርዳታ ለማሸለብ በመዘጋጀት ላይ ነው!

 Waiting for death while bleeding from Agazi bullet  (FB/JM)

Waiting for death while bleeding from Agazi bullet (FB/JM)


 

በየዕለቱ እንደዚህ በአጋዚ የሚጨፈጨፉትን የኦሮሞ ወጣቶች፡ ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሣኤ ሰሞኑን በለቀቁት ጽሁፍ በጭዳ መልክ የሚመለከቷችው አስመስለውት እንዲህ ይላሉ፦

    “በኦሮምያ ተፈጥሮ የነበረው የሕዝብ አመፅ የመንግስት መዋቅር ላይ በተለይ በክልሉ መንግስታዊ መዋቅር ላይ ፈጥሮት የነበረ ጫና በጣም ከፍተኛ ነው። በፌዴራል መንግስት የፀጥታ ሃይሎች ጣልቃገብነት ነው አመፁ የቆመው። አመፁ በስፋትም በግዜም ቢቀጥል ኖሮ በተጨማሪም ሌሎች ተጓዳኝ የሕዝብ አመፆች ቢነሱ ኖሮ በማዕከላዊ መንግስት ላይ ሊፈጠር ይችል የነበረው ችግር መገመት አይከብድም።”

ይህ የእርሳቸው ግንዛቤና ጥረት የኢትዮጵያን ሕዝብ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ሃሣብ አንግቦ ነው የሚለውን በከፍተኛ ደረጃ ውድቅ አድርጎብኛል።

ይህ ብቻ ሳይሆን ኦሮሚያ ውስጥ ግድያው በየቀኑ ሆኖአል፤ የቆሰለውንና ታስሮ የሚገረፈውን ደግሞ ቤቱ ይቁጠረው! ሃገሩን ለቆ በስደት በየአቅጣጫው የሚፈሰው ኢትዮጵያዊ ቁጥሩ በውል አይታወቅም። በዚህ ሰሞን ብቻ በሱዳን ሊቢያ ድንበር አካባቢ ከ600 በላይ ሃገራቸውን ሸሽተው በነዚያ ሃገሮች ድንበር ላይ መያዛቸው ተዘግቧል።

ሕዝባችን እንዲህ መግቢያ መውጭያ እንዲያጣ ያደረገው ሕወሃት ክወንጀሉ ሊቆጠብ የሚችለው እርሱንም ኢትዮጵያውያን በጋራ መውጭያ መግቢያ ሲያሳጡት ነው! ያላንዳች ማመንታት ትግሉ መፋፋም ያለበትም ለዚህ ነው!

ሕወሃት የሚገባው ቋንቋ መውጫ መግቢያ የሚያሳጣውን አሻፈረኝ ባይነትን የተከናነበ ሕዝባዊ ኃይል ሲያይ ነው!

Among the TPLF victims of daily Oromo deaths
 

ኢሳት (ሐምሌ 26 ፥ 2008) በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሃረርጌ ዞን ስር በምትገኘው የበዴሳ ከተማ ማክሰኞ ተጨማሪ ሁለት ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ተገደሉ። በከተማዋ ሰኞ የተገደሉት ሁለት ሰዎችን ማክሰኞ ለመቅበር በተካሄደ ስነ-ስርዓት ላይ የጸጥታ ሃይሎች ተኩስ በመክፈት ተጨማሪ ሁለት ሰዎች እንዲሞቱ ማድረጋቸውን እማኞች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።

የአራቱ ሟቾችን ስም በመጥቀስ ስለድርጊቱ እማኝነታቸውን የሰጡት የበዴሳ ከተማ ነዋሪዎች በከተማዋ ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት መኖሩን አክለው አስረድተዋል።


 

ሰኞ በከተማዋ የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ሲሆን ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቁ ነዋሪዎችን ለእስር መዳረጋቸው ታውቋል። በከተማዋ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ሃይል ተሰማርቶ የሚገኝ ሲሆን፣ ከ20 የሚበልጡ ሰዎች ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸው ለህክምና ሆስፒታል መግባታቸውን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እማኞች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስታውቀዋል።

በበዴሳ ከተማ አጎራባች የሚገኙ የገጠር ከተማ ነዋሪዎች ወደ በዴሳ ከተማ በመጓዝ ህዝባዊ ተቃውሞውን መቀላቀላቸው ታውቋል። የጸጥታ ሃይሎች ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ከተማዋ የሚገቡ ሰዎችን ለመግታት የሃይል እርምጃ እንደሚወስዱ የተናገሩት ነዋሪዎች ከተማዋ በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት እንቅስቃሴ እየተካሄደባት እንዳልሆነ ለመረዳት ተችሏል።

በአካባቢው ዳግም እየተካሄደ ባለው በዚሁ ህዝባዊ ተቃውሞ ነዋሪዎች ለእስር የተዳረጉ ሰዎች እንዲፈቱና በክልሉ የሰብዓዊ መብት እንዲከበር በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና፣ በኦርሞ ሕዝብ ላይ የትግራይ ድርጅት ጉልበተኞች መሬቶቻችሁን ካልዘረፍን በማለት በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሚፈጽሙትን ጭፍጨፋ አስመልክቶ የሕዝቡ ተቃውሞ በከፍተኛ ደረጃ ተቀጣጥሏል። አሥረኛ ወሩን የጀመረውን ይህንን የሕዝብ ተቃውሞ ለመደፍጠጥ፡ ሕወሃት በየቀኑ ያለ የሌለ ሠራዊቱን ኦሮሚያ ውስጥ በማሠማራት ሕዝቡን በመጨፍጨፍ ላይ ነው።

የኦሮሞ ህዝብ የመብት ጥያቄ የፈታችን ቅዳሜ በመላው ኦሮምያ ተቃውሞ እንደሚካሄድ ታውቋል። የኦሮሞ ህዝብ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ትግሉን ቢያካሂድም እያገኘ ያለው ምላሽ ግን በተቃራኒው ጥይት መሆኑ በርካታ ዜጎችን አስቆጥቷል።

በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ገዢው ፓርቲ የሚያካሂደውን ግድያ እንዲያቆም፣ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ አጋዚ ክልሉን ለቆ እንዲወጣ እና ሌሎችም ጥያቄዎች ይቀርባሉ። በኦሮምያ እየተካሄደ ባለው ተቃውሞ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አልቀዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ታስረዋል። ባለፈው እሁድ በአወዳይ የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ ከ11 በላይ ዜጎች ተገድለዋል። ከ25 በላይ ሰዎች ደግሞ ክፉኛ ቆስለዋል።
 

%d bloggers like this: