ሕወሃት ቤቶቻቸውን አፈራርሶ መሬቱን የነጠቃቸው የወረ ገኑ ተፈናቃዮች የስደተኞችን ያህል ዕርዳታ እንዲፈቀድላቸው ጠየቁ!

24 Aug

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
በሪፖርተር
 

*   ከአምስት ሺሕ በላይ አባወራዎች መጠለያ አልባ ሆነዋል

 
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ ባካሄደው ሕገወጥ ያላቸውን ቤቶች የማፍረስ ዘመቻ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ የወረገኑ አካባቢ ነዋሪዎች፣ ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ስደተኞች እንደሚደረገው ሁሉ ለእነሱም ዕርዳታ የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻች ጠየቁ፡፡

ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉት እነዚህ ወገኖች ባቋቋሙት ኮሚቴ አማካይነት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ፣ ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ጎዳና ላይ መውደቃቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹የምንኖረው ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ነው፡፡ በድንገት ቤታችን በመፍረሱ ጭራሹኑ የኑሮ መሠረታችን ተናግቷል፤›› በማለት ለከተማው ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ የገለጹት እነዚህ ተፈናቃዮች፣ ‹‹ወቅቱ ክረምት በመሆኑ ከልጆቻችን ጋር ለከፍተኛ እንግልት ተዳርገናል፤›› ሲሉም መንግሥት እንዲደርስላቸው ተማፅነዋል፡፡

እነዚህ ተፈናቃይ ወገኖች በጻፉት መማፀኛ ደብዳቤ ሌሎች አማራጮች ባይኖሩ እንኳን፣ ቢያንስ መንግሥት ችግራቸውን ተረድቶ ለደቡብ ሱዳን፣ ለሶማሊያና ለኤርትራ ስደተኞች እንዳደረገው ላስቲክ ወጥረው የሚኖሩበትን መንገድ እንዲያመቻች ጠይቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ያስከተለባቸው የከፋ ችግር ባለበት ወቅት ቀጣዩ የትምህርት ዘመን እየቀረበ በመሆኑ፣ ልጆቻቸውን በቋሚነት ለማስተማር ለመወሰንም እንደተቸገሩ ተፈናቃዮቹ በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ዶ/ር ታቦር ገብረ መድኅን የተፈናቃዮቹን ጥያቄ ከተመለከቱ በኋላ፣ ሊደረግ የሚችል ድጋፍ ካለ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት እንዲመለከተው ጠይቀዋል፡፡

‹‹የከተማው አስተዳደር ምንም መጠለያ ለሌላቸው መፍትሔ ለመሻት ባለው ዕቅድ መሠረት የሚሰጥ ምላሽ ካለ እንዲመለከተው›› በማለት ዶ/ር ታቦር ተፈናቃይ ወገኖች የጻፉትን መማፀኛ ደብዳቤ አባሪ በማድረግ ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት መርተዋል፡፡

ነገር ግን ተፈናቃይ ወገኖች ያቋቋሙት ኮሚቴ አባላት በተደጋጋሚ ወደተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ቢመላለሱም መፍትሔ ማጣታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከዚህ የባሰ ችግር የለም፤›› ያሉት ስማቸውን ቢገልፁ ሌላ ያልጠበቁት ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል የሰጉ የኮሚቴው አባላት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ‹‹መንግሥት ባለበት አገር እንዲህ ዓይነት ስቃይ ሊገጥመን አይገባም፡፡ ቢያንስ ላስቲክ ወጥረን የዕለት ኑሯችንን የምንገፋበት መንገድ ይመቻች፤›› በማለትም ተማፅነዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሚያዝያ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረገኑና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሃና ማርያም አካባቢዎች ሕገወጥ ያላቸውን ግንባታዎች ማፍረሱ ይታወሳል፡፡

በወረገኑ አካባቢ 4,800 ቤቶች ፈርሰዋል፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ ቤቶች በመፍረሳቸው ከአምስት ሺሕ በላይ የሚቆጠሩ ዜጎች እንደተፈናቀሉ የኮሚቴ አባላቱ ይናገራሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ1988 እስከ 1997 ዓ.ም. ድረስ ከተገነቡት በስተቀር፣ የተቀሩት በተለይ ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ የተገነቡት ‹‹ሕገወጥ›› በመሆናቸው መፍረስ እንደሚኖርባቸው ይገልጻል፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታምራት አስናቀ እንደሚሉት፣ እስከ 1997 ዓ.ም. ከተገነባው ‹‹ሕገወጥ›› ግንባታ በስተቀር አግባብ ባልሆነ መንገድ የተያዘን መሬት መንግሥት ሕጋዊ አያደርግም፡፡

ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት ግን የፈረሱባቸውን ቤቶች ሲገዙም ሆነ ሲገነቡ መንግሥት ያውቅ ነበር፡፡ በኮብልስቶን፣ በድልድይ ግንባታ፣ በኮሙዩኒቲ ፖሊሲንግ፣ እንዲሁም በአካባቢው በተካሄዱ የልማት ሥራዎች ከገንዘብ መዋጮ ጀምሮ ተሳታፊ እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡

‹‹ይህ ሁሉ ቀርቶ አሁን የምንፈልገው የላስቲክ መጠለያ ነው፤›› በማለት የኮሚቴ አባላቱ በተለይ የመጠለያ ችግር የተፈናቃዮችን ሕይወት እያናጋ መሆኑን አፅንኦት በመስጠት ተማፅነዋል፡፡
 

ተዛማጅ:

    በአዲስ አበባ በቦሌ ክፍለ ከተማ ከቤት መፍረስ ጋር በተያያዘ ሰዎች ተገደሉ፤ ብዙዎችም ቆሰሉ!

    BREAKING NEWS: Several children & adults protecting their homes from demolition shot by TPLF security forces in Bole area

    The Bole/Were Genu Massacre: Murderous TPLF regime shoots 8 Ethiopians & wounds 100 others to clear land for foreign investors

    Land grab at Lafto, Addis Abeba: Helpless people; home demolitions & impunity of state power; police & city officials killed, injured

 

%d bloggers like this: