ኢሕአዴግ አገር ለመለወጥ ሳይሆን ለግል ጥቅማቸው የሚሯሯጡ አባሎቼ እየተፈታተኑኝ ነው አለ! ታዲያ ምን ይጠበስ ብሎ ነፍሰ ገዳዮችን ለፍርድ ለማቅረብ ሕዝቡ ትግሉን እንደቀጠለ ነው!

24 Aug

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
ሪፖርተር
 

“በአሁኑ ጊዜ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ከሚፈታተኑት ችግሮች መካከል አንዱ የመንግሥት ሥልጣን የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ፣ የግል ኑሮ መሠረት አድርጎ የመመልከትና በአንዳንዶችም ዘንድ የግል ጥቅም ከማስቀደም ጋር የተያያዙ እንደሆኑ አረጋግጫለሁ፤”

 

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከነሐሴ 10 እስከ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፣ ያለፉትን አሥራ አምስት ዓመታት አፈጻጸም በመገምገም የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ፡፡ አዎንታዊ ለውጦች የተመዘገቡ ቢሆንም ተጨባጭ ድክመቶች እንደታዩበትም ኢሕአዴግ ገምግሟል፡፡ ከእነዚህም መካከል የመንግሥት ሥልጣናቸውን የሕዝብ ኑሮ ለማሻሻልና አገር ለመለወጥ ሳይሆን፣ የግል ጥቅማቸውን ለማስፈጸም ቅድሚያ የሚሰጡ አባላቱ እየተፈታተኑት እንደሆነ ገልጿል፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከቅርብ ወራት ወዲህ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የተቃውሞ ሠልፎች በመካሄዳቸውና በቀላሉ ሊበርዱ ስላልቻሉ ውጥረት ውስጥ ይገኛል፡፡ የተቃውሞ ሠልፎቹ አሁን የያዙትን ደም አፋሳሽ ቅርፅ ከመያዛቸው በፊት፣ የፓርቲው ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ፣ በተቃውሞ ሠልፎቹ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል የቅራኔ ምንጭ የሆኑ ጥያቄዎችን ለመመለስ ፓርቲው ራሱን ለማደስ መዘጋጀቱን አስታውቀው ነበር፡፡ “የሕዝብ ጥያቄ የሆኑትን ከክልል መንግሥታት ጋር በመተባበር ፌዴራል መንግሥት ለመፍታት ይሞክራል፤” ሲሉ አስታውቀው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ገዥው ፓርቲና መንግሥት ለአሥራ አምስት ዓመታት የሄዱበትን የተሃድሶ መንገድ በመገምገም ከጥቅምት ወር 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ መንገድ መሥራት እንደሚጀምር አመልክተው ነበር፡፡ “ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ መንፈስና ጉልበት ተጠናክረን እንመጣለን፤” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ አዲሱ ተሃድሶ በቀድሞው ተሃድሶ ላይ እንደሚመሠረትና የሥርዓቱ አደጋ ተብለው የተለዩ ሦስት ዋነኛ አጀንዳዎች ላይ እንደሚያተኩር አስታውቀዋል፡፡ እነዚህም በዋነኛነት በሙስናና ብልሹ አሠራር የሚገለጸው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት፣ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት አያያዝና የጠባብነትና የትምክህተኝነት አመለካከቶች ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው መጨረሻ የፓርቲው ግምገማ እንደተጠናቀቀ፣ “የመንግሥት መዋቅራችንንም ለሥራው ተገቢና ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ መልሶ የማደራጀትና መልክ የማስያዝ ሒደትም ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል፤” ብለዋል፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫም ከዚሁ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብ ያልራቀ ነው፡፡ ይሁንና የኮሚቴው ዝርዝር ግምገማ ሕዝብን ማገልገል እንጂ የግል መጠቀሚያ ያልሆነ መንግሥት ለመገንባት የተደረገው ጥረት መልካም ዕድገት ያስመዘገበ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እክል እንደገጠመው ማረጋገጡን መግለጫው ያስገነዝባል፡፡ “በአሁኑ ጊዜ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ከሚፈታተኑት ችግሮች መካከል አንዱ የመንግሥት ሥልጣን የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ፣ የግል ኑሮ መሠረት አድርጎ የመመልከትና በአንዳንዶችም ዘንድ የግል ጥቅም ከማስቀደም ጋር የተያያዙ እንደሆኑ አረጋግጫለሁ፤” ብሏል፡፡

“እነሆ ዛሬ ድርጅታችን በዚህ ችግር ምክንያት የተፈጠረውን አደጋ መሠረታዊ መንስዔዎች በሌላ በማንም ሳያሳብብ በመንግሥትና በድርጅቱ ማዕቀፍ እንደሚታይና ቀዳሚ ችግር እንደሆነ ተገንዝቦ፣ ይህንኑ ለማስተካከል የሚያስችል እንቅስቃሴ ጀምሯል፤” ሲል የሥራ አስፈጻሚው መግለጫ ጠቁሟል፡፡ ይሁንና መግለጫው የውጭም ሆነ የውስጥ ጽንፈኛ፣ ፀረ ሰላምና ፀረ ልማት ኃይሎች ሁከትና ትርምስ ለማስፋፋት የሚያደርጉትን ጥረት ሕዝቡ በፅናት እንዲመክት ጥሪ አቅርቧል፡፡
 

ተዛማጅ:

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያለፉትን 15 አመታት የተሃድሶ ጉዞ በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀመጠ
 

%d bloggers like this: