ኢሕአፓ (አንድነት) ለትግራይ ምሁራን ጥሪ አቀረበ!

29 Aug

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
ለትግራይ ምሁራን የቀረበ ጥሪ
 

ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርጅት አባላት በበለጠ፣ የኢሕአፓ አባላት ከትግራይ ሕዝብ ጋር ልዩ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መቀራረብ ነበራቸው። የኢሕአፓ ሠራዊት ኢሕአሠ፣ እንቅስቅሳሴውን የጀመረው በምሥራቅ ትግራይ በዓጋመ አውራጃ በዓዲ ኢሮብ ነበር። ሠራዊቱ ትግራይ ውስጥ በተንቀሳቀሰባቸው ዓመታት፣ በዓጋመ፣ በዓድዋና በክልተ አውላዕሎ አውራጃዎች በአመዛኙ የወታደራዊ እንቅስቃሴዎች፣ የፖለቲካ ቅስቀሳና ሕዝብ የማደራጀት ሥራዎችን አከናውኗል። አልፎ አልፎም ኢሕአሠ በአክሱም፣ በሽሬ፣ በተምቤንና በእንደርታ ወታደራዊ ስምሪቶችን አድርጓል።………በpdf ለማንበብ

የትግራይ ተወላጆች በኢሕአሠ ውስጥ በአንፃራዊ ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር ነበራቸው። በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎችም ሠራዊቱንና ፓርቲውን ከመምራት ጀምሮ እስከ ታዋቂ የወታደራዊና የፖለቲካ መሪዎች በመሆን፣ እስከዛሬ ድረስ መልስ ያላገኙትን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ጥያቄዎች በማራመድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። በርካታ አባሎቻችን የነበሩትም ለሀገር አንድነት፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች መከበርና ለሕዝቦች ልዕልና ሲዋደቁ ተሰውተውብናል። ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ሁልጊዜም እንዘክራለን።

በኢሕአሠ ስምሪትና እንቅስቃሴ ወቅት የትግራይ ሕዝብ፣ በተለይም አርሶአደሩ፣ ምንጊዜም ከሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ፣ ቤቱ ካፈራው፣ ሠራዊቱን በሙሉ ልቡ እየመገበና እያጠጣ፣ ልጆቹንም ለሠራዊት አባልነትም ሆነ ለካድሬነት እየለገሰ ከጎናችን በመሆን ታሪክ የሚያስታውሰውና የትግራይን የኢትዮጵያ ሥልጣኔ እምብርትነት በማስረገጥ አኩሪ ታሪክ አስመዝግቧል። የሠራዊቱ አባላት ለተደረገላቸው ውለታ “የቐንየልና” (እናመሰግናለን) ሲሉ፣ አርሶአድሩ “ገንዘብኩም” ገንዘባችሁ ነው የሚል ጨዋ ሕዝብ ነው።

ህዝቢ ወያነ ሓርነት ትግራይ ወይም በቀድሞ አጠራሩ ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ፡ በተሳሳተ ጎዳና ሲሸመጥጥና ትግራይን ከኢትዮጵያ እገነጥላለሁ ብሎ በመርሀ ግብሩ ነድፎ ለመንቀሳቀስ ዳዴ ሲል፣ ገና በእንጭጩ የሃሳቡን ጮርቃነት በመግለጽ “የኢትዮጵያ አካል የሆነችው ትግራይ እንዴት ነው ከራሷ የምትገነጠለው?” በማለት ድርጅቱ እኩይ ዓላማውን እንዲተው በግምባር ቀደም ያስገደደው የትግራይ አርሶአደር ነው።

በሀገራችን ውስጥ ያለው መሠረታዊ ቅራኔ በኢትዮጵያ ሕዝብና በህወሓት መካከል ሆኖ ሳለ፣ ዛሬም ከረፋዱ ላይ ህወሓት በትግራይ ሕዝብ ስም በኢትዮጵያውያን ላይ፣ የትግራይን ሕዝብ ጨምሮ፣ የሚሠራውን ግፍና የሚፈጽመውን ወንጀል፣ የትግራይ ሕዝብ በተቻለ መጠን እየተዋጋና እያወገዘ ለመሆኑ ማስረጃዎች በርካታ ናቸው። ህወሓት የተያያዘው የግትርነት ጎዳና አገራችንን ወደማያበራ የእርስበርስ ጦርነትና ጥፋት የሚወስድ መንገድ ነው። በሀገሪቱ የተንሰራፋውን የሙስና፣ ዘረኝነትና አምባገነንነት ጽዋው ሞልቶ መፍሰስ መጀመሩ ማንም ታዛቢ የሚያየው ነው። ህወሓትና ስመ-ጥፉ ጦሩ አግዓዚ፣ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚያደርሱት እስር፣ ጭፍጨፋና ግድያ የሕዝባችንን ወንድማማችነትና እህትማማችነት በእጅጉ ተፈታትኖታል።

ይህ አስከፊ ሁኔታ እንዳይቀጥል ለማድረግ የትግራይ ምሁራን ከፍተኛ ሚና ይኖራችኋል። ስለዚህም ያለፈውን ዝምታና የዳር ተመልካችነት ለታሪክ በመተው፣ በአዲስ መንፈስ የኢትዮጵያ ሕዝብ የገፋበትን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ በግልጽ መደገፍ ይጠበቅባችኋል። ኢሕአፓ (አንድነት) የትግራይ ምሁራንን ለማሳሰብ የሚወደው፣ አገራችን ወደ እርስበርስ ጦርነት እንዳትገባና ሰላማዊ ሽግግር እንዲደረግ ሕዝባዊ እንቅስቃሴውን በይፋ በመደገፍ ትግሉን የማጠናክር ሚና መጫወት እንደሚገባችሁ ነው። በዚህ አጋጣሚ በራሳቸው አነሳሽነት እንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴና የዜግነት ግዴታን መወጣት የጀመሩትን ወደ 20 ለሚጠጉ የትግራይ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ያለንን አድናቆት ለመግለጽ እንወዳለን። የትግራይ ምሁራን ሁሉ በጥቂቶች የተጀመረውን ይህን እንቅስቃሴ እንዲቀላቀሉም እናሳስባለን። የትግራይ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች እንደሚገኙት ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው በሚካሄደው ፀረ-ህወሓት/ኢህአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ ተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች እንዲሳተፉና ሰላማዊ የሽግግሩን ጥያቄ እንዲደግፉም እናሳስባለን።

የትግራይ ሕዝብ፤ እንደ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹና እህቶቹ ለዘመናት የታገለላቸውንና መስዋዕትነት የከፈለላቸውን አገራዊ ግቦች፣ በህወሓት ዘረኝነትና ሙስና ተቀይረው ማየት፣ የማንኛውንም አገር ወዳድ ዜጋ ልብ ያደማል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ተያይዘን ብሩህ የዴሞክራሲና የሰላም ቀን በሀገራችን እንደምናመጣ እርግጠኞች ነን።

የተባበረ ሕዝብ ያቸንፋል!
ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በተባበረ ትግል ትመሠረታለች!
ነሃሴ ፲፰ ቀን ፪ ሺህ ፰ ዓ. ም
August 24, 2016

%d bloggers like this: