የአማራ ክልል በሕወሃት ጦር ወረራ ዋዜማ!       ሕወሃት ከፍተኛ ጦር በማስገባት የተፈራውን ወረራና ደም ማፍሰስ ሊጀምር ነው! አያሌ ሕይወት ይጠፋል! ከእንግዲህ ሕወሃት ሃገሪቱን መጫወቻ የማድረግ ችሎታው ግን ክፉኛ ተኮላሽቷል!

30 Aug

በከፍያለው ገብረመድኅን The Ethiopia Observatory (TEO)
 

ከየከተማው፣ ወረዳውና ክልሉ ለኢሳት መረጃ አቅራቢዎች በቀጥታ ለኢሣት ባስተላለፉት መረጃ መሠረት፣ የአማራ ሕዝብ በጎንደርና በጎጃም በሕወሃት አልተዳደርም ባይነቱን ጥልቀት በመሥጠት፡ አያሌ ወረዳዎች በብዛት በጎጃም እንዲሁም በጎንደር የጎበዝ አለቃዎችን በመምረጥ ራሳቸውን ማስተዳደር ከጀመሩ ይህ ሣምንት ብዙ አሳይቶናል።

በሚገርም ሁኔታ፣ ኦሮሚያ ውስጥ አሁንም ዜጎች በየቀኑ እየተረገጥ፡ እየተደበደቡና እየትገደሉ፡ የሕወሃት ግንባር የሆነው ኃይለማርያም ደሣለኝ፡ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሠጠው መግለጫ፥ “አሁን በላው ሁኔታ መንግስት በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥረው የነበሩ ግጭቶችን ከህዝቡ ጋር በመሆን በሰራው ስራ ከሞላ ጎደል በክልሉ አብዛኛው ስፍራ መረጋጋት መፍጠር ተችሏል” ብሏል። ይህ አባባል ግን ለምን በዚያ ክልል ውስጥ ዜጎች እንደቅጠል እየተጨፈጨፉ እንደሚረግፉ ነው!

እሁድ በተለቀቀው የኢሕአዴኢግ ምክር ቤት መግለጫ፡ ለዚህ ሁሉ ሕዝባዊ ተቃውሞ መንስዔ የሆነው የኦሮሚያ ተቃውሞ በአንዲት ዐረፍተ ነገር አልተጠቀስም። ይህም የሕወሃት ከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ አካል በመሆኑ፡ የኢትዮጵያ ሕዝብን በአንድነት መነሳት ሊያደናቅፍ አይገባም!

በአሁኑ ወቅትም፣ ሕወሃትን ትንፋሽ እየነሳው ያለው በአማራ የሚካሄደው በይበልጥ የተደራጀውና በመሣሪያ ኃይልም የተጠናከረው የጎንደርና የጎጃም ሕዝባዊ ንቅናቄ መሆኑ ግልጽ ነው።

በዚህም መሠረት – ኢሣት እንደዘገበው – በጎንደር፣ ደባርቅ፣ ዳባት፣ ገብደብየ፣ አምባ ጊዮርጊስ፣ ጎንደር፣ ደምቢያ፣ አዲስ ዘመን፣ በለሳ፣ ወረታ፣ ዓለም በር፣ ደብረ ታቦር፣ ጋሳይ – ክምር ድንጋይ፣ ነፋስ መውጫ፣ ሳሊ፣ ጨጭሆ፣ ጎብጎብ፣ ፍላቂት፣ ደራ ሐሙሲት፣ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ የአገዛዙ መዋቅር እየፈራረስ እንደሚገኝ ከነዚሁ መረጃዎች ለመረዳት ለማወቅ ተችሏል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ባሳለፍነው ሣምንት መጨረሻ ምዕራብ ጎጃም ባሉ ከተሞች ማለትም ባሕር ዳር፣ ፒኮሎ፣ ዱርቤቴ፣ አቸፈር፣ ቋሪት፣ ፍኖተ ሰላም፣ ብርሸለቆ- ጃቢጠናን፣ ቡሬ፣ ሽንዲ፣ ደምበጫ፣ የጨረቃ፣ አንበር፣ ሎማሜ፣ ፈረስ ቤት፣ አዴት ይልማና ዴንሳ፣ ጎንጅ ቆለላ፣ ሞጣ፣ ጉንደ ወይን ከፍተኛ የሆነ ሰላማዊ ሰልፍና የቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ተካሄዷል።

በተለይም ከሕወሃት የመላቀቁ አዝማሚያ ጠንካራ አዝማሚያ በታየባት ባሕር ዳር ማክሰኞ በተካሄደው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ፣ ወታደሮችና የሳባታሚትና ሃንዳሣ አርሶ አደር ሚልሽያዎች ፊት ለፊት ተጋጥመው ከሁለቱም ወገን ብዙ ጉዳት መድረሱ ተዘግቧል።

በተቃውሞ ምክንያት ሕወሃት በየእሥር ቤቱ ሕወሃት ያጎራቸውን በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የገበሬው የሕዝብ ተከላካይ አስለቅቋቸዋል። ብዙ ወታደሮችም መሣሪያዎቻቸውን እየጣሉ መሸሻቸው ይነገራል

 
የአማራ ክልል መስተዳድርም፥ በሁኔታው ላይ የመወሰን መብት ያለው ይመስል፥ ኃላፌው አዲስ አበባ ከተጠራ በኋላ፡ በማራ ክልል “አንዳንድ አካባቢዎች እየተፈጠረ ያለው ሁከትና ግጭት ከዚህ በላይ እንዲቀጥል መንግሥት አይፈቀድም!” ማለቱ ሕወሃት እንደ ዋና ባህሪው ሁሉ አሁን ያለውን የሕዝብ ምሬትና ብሶት በፖለቲካዊ መንገድ የመፍታት ብቃቱም እንደሌው የሚያሳይ ነው።

ላለፉት ጥቂት ቀናት፡ ሕወሃት ከፍተኛ የአጋዚ ኃይል ወደ አማራ ክልል በማጓጓዝ ላይ እንደነበረ ሲነገር የነበረው እውን ሆኖ፥ በጎንደርና በጎጃም አካባቢ ብዙ የሕወሃት ኃይል መከማቸቱ ይነገራል

ወታደራዊ ኃይል አስገብቶ፡ ሕወሃት በቅድሚያ ሕዝባዊ ተቃውሞው በተጠናከረባቸው አካባቢ ጦርነት በአማራ ሕዝብ ላይ ለመጀመር ዝግጅቱ በመጠናቀቁ፣ ይህም ማለት ከራስ ፀጉሩ እስከ እግር ጥፍር የታጠቀው ሕወሃት ለመብታቸው የሚከራከሩትንና የግንባሩ ጥጋብና እርግጫ በቃን ያሉትን ዜጎች ደም ለማፍሰስ – በማኅበራዊ ሚዲያዎች እንደሚነገረው – ወታደሩ የተሠጠውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ እስከሚጀምርባት ያቺ የመጨረሻዋ ደቂቃ እየተጠበቀ ነው።

ሰሞኑን ስለነበረውና እስካሁን ስላለው ሁኔታ፣ የአማራ ክልላዊ መንግሥት ቃል አቀባይ ንጉሡ ጥላሁን የሚከተለውን ማለታቸው ከሸገር ራዲዮ ይጠቀሳል።

Sheger Radio-Amhara

ስለጎንደርና ጎጃም በአጠቃላይ ስለአማራ ስናወራ፣ ኦሮሚያ ሰላም ናት ማለት አይደለም። በየዕለቱ ሰዎች እየተደበደቡና እየተገደሉ ነው።

በዚህም ምክንያት፣ መሣሪያ እንደሰሜኑ የሃገራችን ክፍል የሌላት ኦሮሚያ በኢኮሚክ ምርቶቿ ጠንካራ በመሆኗ (ከ60% ከመቶ የሃገሪቱ ብሔራዊ ምር) ከጳጉሜን 1/2008 እስከ መስከረም 1/2009 በኤኮኖሚ አድማና ጠቅላላ የምርት ግብይይትን እርግፍ አድርጋ በመተው ወንበዴውን መንግሥት ለማሽመድመድ መወስኗ መረጃውና መመሪያው ተሠራጭቷል

ሕዝቡ ለራሱና ለቤተሰቡ በሚገባ ሥንቅ እንዲይዝ ይህ መረጃና አሠራር ጥቂት ቀደም ብሎ ቢለቀቅ ጠቃሚ ይሆን ነበር።

ይህ ጽሁፍ ይህንን መረጃ ይዞ አሁን እንዲወጣ የፈለግሁበት ምክንያት፡ ሕወሃት የአንድ ወር የመፍትሄ መርሃ ግብሩን ተግባራዊ ለማድረግ ተፍ ተፍ በሚልባት በአሁኑ ሰዓት፣ የመላ ኢትዮጵያውያን ግንዛቤ ሊሆን የሚገባው፡ ካለፈው የሠላማዊ ሠልፍ በኋላ ጎልቶ የወጣው የአማራና ኦሮሞ ትብብርና ኅብረት፡ አሁንም የአንዱ ችግርና ሞት የሌላውም ሆኖ ወደ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንንም ትብብር መስፋፋትን አስፈላጊነት ለማስታወስ ነው።

ድንበር ጥሰው ለድኅንነታቸው ሲሉ ወደ አውሮፓ የጎረፉትን ስደተኞች እንኳ ለችግራቸው መፍትሄ ለመሻት ፈቃደኝነት ያላሳየው የአውሮፓ አንድነት ማኅበር – ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ እንደሚለው አባባል – በአሁኗ ሰዓት እንኳ ዕርዳታውን ለሕወሃት ድርጅቶች ብቻ ማድረጉ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ነው። ለምሣሌም ያህል ሰሞኑን የአውሮፓ ኅብረት ለሲቪል ኅብረተሰብ ዕርዳታ በማለት 3.7 ሚሊዮን በላይ ዕርዳታ ሠጥቷል። ይህም ከዘረፋ ከተረፈ፥ የሕወሃትን ሠራዊት የየውጊያው መንፈስ ለመጠበቅ ነው።

ዛሬ ጥዋት ሳነብም፡ በዚህች ሰዓት እንኳ እነ ቢል ጌትስ፡ የራሱና የባለቤቱ (Gates Foundation) ድርጅትና Global Fund ትኩረታቸው በተቻለ መጠን የጤንነትና ደኅንነት ዕርዳታዎችን ትግራይ ውስጥ በተናጠል ማጠናከር ሆኖአል።

በሃገሪቱ የኤኮኖሚ መዳከሙ በመጥናከሩና በተለይም የውጭ ምንዛሪ ዕጥረቱ በመባባሱ፡ በተለያየ መልኩ የውጭ ዕርዳታ እየተንጠባጠበ ነው። ሰኔ መጨረሻ ላይ የዓለም ባንክ የተለያዩ ፕሮጄክቶችን ለማስፈጸም በሚል ሳቢያ፡ $829 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል። ቀኑ እየገፋ በመጣ መጠን የሚሠጠው የዕርዳታ ዐይነትም ሊጨምር ይችላል።

በሕወሃት ጥጋበኞችና የሕዝብ መብት ረጋጮች ሕገ ወጥነት ኢትዮጵያውያን ሲጨፈጨፉ፡ የዓለም ኅብረተሰብ ለረዥም ርቀት በቸልታ እንደሚመለከት አልጠራጠርም። ይህንን የምለው ይኽው ቋሚ ባህሪው ስለሆነ ነው። ይህንንም የምልበት ምክንያት፥ ለምሣሌም ያህል፥ የሲሪያን፡ ሊቢያንና፡ ደቡብ ሱዳንን ከመሞትና መድማታቸው በፊት ተገቢውን ትኩረት ያልሰጧቸው፥ የኢትዮጵያውያን ቁጣ ቅድሚያ ሠጥተው የነበረውን፣ ያለውንና መጭውን የሕወሃት የሕዝብ ጭፍፍጨፋ ያስቆማሉ የሚለው ላይ እምነቴ እምብዛም ነው። ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በራሱ በመተማመን ትግሉን ማፋፋም ያለበት!

የዚህ ሁሉ ጥረትና የሕዝባችን መሥዋዕትነት ዓላማ፡ ኢትዮጵያን ከሕወሃት ወንበዴዎች ነጥቆ ነጻ፡ እኩልነትን የተላበሰችና የሁሉም ኢትዮጵያውያን ማድረግ መሆኑን ማንም ሊስተው፣ ቸል ሊለው የማይገባና የማይደራደርበት መሆን ይኖርበታል!
 

%d bloggers like this: