ኢትዮጵያ በእውነት መንግሥት አላትን?        የግራዚያኒና አይሲስ/ሊቢያ ወዳጅ የሆነው ሕወሃት መንግሥታዊ ኃላፊነት እንዴት ሊሸከም ይችላል?

5 Sep

በከፍያለው ገብረመድኅን The Ethiopia Observatory (TEO)
 

ኋላቀር ብትሆንም፣ ሃገራችን የዘመናት መንግሥታዊ ወግና ባሕል ያላት ሃገር በመሆኗ፡ ከመንግሥት ቀደምት ተግባሮችና ሥራዎች መካከል የዜጎችንና የሃገርን ደኅንነት ማረጋገገጥ ዋነኞቹ መሆናቸውን፥ በከተማም ሆነ ገጠር ማንም ኢትዮጵያዊ ይገነዘበዋል። ከጥንታዊው ሮም ሥልጣኔና በዚያን ጊዜ የሮም ሕግጋት (Roman Law) በዓለም ላይ ባሠራጩት የሕግ ባሕል ምክንያት፣ ተማሣሌታዊ ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥም መንግሥታዊ ግዴታን ለአጥቂው ወገን ለማስታወስ፡ ‘በሕግ አምላክ’ ‘በኃይለሥላሴ አምላክ” የሚባሉትን ማስታወስ ይቻላል።

በአንድ ምሽት በጉርምስና ዘመኔ ከአራት ውድ ጓደኞቼ ጋር ስንዝናና ካነጋጋንበት ስንመለስ፡ መኪናዋን ያሽከረክር የነበረው ጓደኛችን ሣት አለው መሠለኝ፥ በዚያን አጉል ሰዓት ትራፊክ ፖሊስ አቆመን። ጊዜው ለብዙ ነገሮች ገና ንጋት ነበር – ጃንሆይ ከሥልጣን የወረዱበት ማግሥት በመሆኑ! መኪናዋን ያሽከረክር የነበረው ጓደኛችን – ሁኔታው በፈጠረው መደፋፈር – ከፖሊሱ ጋር ስህተት/ወንጀል ላለመፈጸሙ ብዙ ሲከራከር፡ ፖሊሱ “ኃይለሥላሴ ይሙት! አጥፍተሃል!” ብሎ ሲምል ሁላችንም ተያየን። ከመሃላችን አንዱ፡ “አንተ አሁንም ኃይለሥላሴ ይሙት እንዴት ትላለህ?” ሲለው፣ ከጥቂት ፀጥታ በኋላ ፖሊሱም ኃፍረት በተቀላቀለበት ስሜት “በሉ እናንተ አሁኑኑ ከዚህ ሂዱልኝ!” ብሎ ያሰናበተንን ሳስታውስ፣ በወቅቱ ካገኘነው ሣቅና ድላችን ባሻገር ማናችንም ነገሩን አንስተንና ጥልቀቱን ተገንዝበን መነጋገራችንን አላስታውስም!

ትናትናም ሆነ ዛሬ ላይ ቆም ብለን ስናየው፣ “ለመሆኑ ሃገራችን መንግሥት አላትን?” ብለን እንደ ዜጎች ስንጠይቅ፣ ባለፉት አርባ ዓመታት በተለይም በመንግሥት ደረጃ የሥልጣን መንከባከብ ፍላጎት ተጠናክሮ ነባሩን ባህላዊውን ሕዝባዊ ስሜት በመስበሩ፣ የሕግ ከለላነትና መንግሥት ለዜጎች ደኅንነት ሰላምና ጤና መቆሙ ከሃገራችን ከጠፋ ስንብቷል። ‘ከኔም በላይ ኃይል ለአሳር ነው’ የሚለው ከንቱነት (vanity of vanities) የተጠናወተው የሕወሃት’ ድርጅታዊ አስተሳሰብና አሠራር መንግሥት ውስጥም በመሥረጹ፣ በሃገራችን ውስጥ ነባሩን የሕዝቡን ኅሊናና ለሕግ ተገዥነት አዳክሞት፥ በሕዝቡ ስሜት መንግሥት (the state) አጋሩ ከመሆን ይልቅ፣ በሩቅ እያየ (“ከሠይፍና መንግሥት ፊት ዞር ነው!”) ብሎ ቂሙን በውስጡ ይዞ አመቺውን ጊዜ የሚጠብቅ ሕዝብ አድርጎታል።

በንጉሡ ጊዜ በግልጽ የሕጉ ምንጭ መሆናቸውን በሕገ መንግሥቱ ያላንዳች ማወላዳት አሥፍረውታል። አፈጻጸሙን በሚመለከት በጊዜው መለካት አለበት። ነገር ግን በዓላማ ደረጃ ከሄድን በ1931 በአንቀጽ 6ና በ1955 (በአንቀጽ 26 Revised Constitution) ሕገ መንግሥታት ደረጃ በ24 ዓመታት ውስጥ የታዩት ልዮነቶች፣ በዛሬው የተራቀቀው ዘመን እንኳ ሕወሃት የአሠራር ማሻሻሎችን እንኳ ለማድረግ ብቃት የሌለው አደገኛ የቀን ጅብነቱን በግልጽ ተራነቱንና ያሳየ የአጓጉሎች ጥርቅም ነው!

ይባስ ብሎ፣ ሕወሃት ሥልጣኑን የሚያጠናክር መስሎት፣ በተለያየ መንገድ ዕለት ተዕለት በፈጸማቸውና በሚፈማቸው ነገሮች ችግሩን አባብሶታል። ለምሣሌም ያህል ኢትዮጵያውያን ሊቢያ ውስጥ የታረዱት በንጉሡ ወይንም በደርግ ጊዜ ቢሆን ኖሮ፡ የሕዝቡን ኃዘኑን ለመገልጽ የሚያደርገውን ከመጋራት ባሻገር፡ የመንግሥትና የሕዝብን ቁጣ አቀላቅሎ፡ የሃገራችን እርምጃ የተለየ በሆነ ነበር።

ኢትዮጵያውያን በሊቢያ የታረዱትን ወንድሞቻቸውን በማሰብ ባደረጉት ሠልፍ ላይ የአጋዚ ራምቦ የሕወሃትን ዘላለማዊነት ለማረጋገጥ በዜጎች ላይ ጥቃት ሲፈጽም(Foto Negere Ethiopia).

ኢትዮጵያውያን በሊቢያ የታረዱትን ወንድሞቻቸውን በማሰብ ባደረጉት ሠልፍ ላይ የአጋዚ ራምቦ የሕወሃትን ዘላለማዊነት ለማረጋገጥ በዜጎች ላይ ጥቃት ሲፈጽም (Foto Negere Ethiopia).


 
ነገር ግን ኢትዮጵያ ብሔራዊ ስሜትና ኢትዮጵያዊነት በሌለው ሕወሃት በጉልበት የምትገዛ ሃገር በመሆኗ፣ የሕዝብ አመኔታ የጎደለው ሕወሃት ወጣት ዜጎቻችንን ደበደበ፡ አጥንታቸውን ሰባበረ፣ በቁጣ የተሰለፈች ነፍሰጡር ተደብድባ አስወረዳት። በዚያን ወቅት ተከሰው የታሠሩ ዜጎች እስከዛሬ እሥር ቤት ናቸው አንዳንዶችም ከእሥር በኋላ ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት በመከታተል ላይ ናቸው! ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ኪትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥራቸው የተባረሩም አሉ።

ይህንን ስንል፣ ለማርሻል ሮዶልፎ ግራዚያኒ የሮማ ከተማ ሃውልት ማሠርቷን በመቃወም፣ ኢትዮጵያውያን ሠልፍ በማድረጋቸው በሕውሃት ሠራዊት መረገጣቸውን ስናስታውስ፡ ሕወሃት ከማን ጋር እንደቆመ ቀደም ብለን ለመገንዘበ በበቃን ነበር።

ሃገሪቱ በሕወሃት ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 52 እንደ ተመለከተው፡ ቀደምት ዓላማዋ የምትንከባከበውና የምትዋደቅለት ለሕገ መንግሥቱ እንጂ ለዜጎች መብቶችና ለሃገሪቱ ዳር ድንበር መከበር እንዳልሆነ ግልጽ ያደርጋል። እንደ ሌሎቹ ሕገ መንግሥቶች ሁሉ፣ መንደርደሪያው (Preamble) በመርሆዎች ሥር በመርሆ ደረጃ ምንም የሚናገረው ስሌለው፣ ያላማኝ ቡራኬ ብቻ ሆኖ ቀርቷል።

ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜም ረጋጭና ነፍሰ ገዳይ ቢሆኑም፡ በምሣሌነት የሩዋንዳን ሕገ መንግሥት ብንመለከት በመርሆ ደረጃ በአንቀጽ አንድ የሠፈረው እንዲህ ይላል፦

    “All power derives from Rwandans and is exercised in accordance with this Constitution. No individual or section of people can arrogate to themselves the exercise of power. National sovereignty belongs to Rwandans who exercise it directly by means of referendum, elections, or through their representatives.”

 

ዛሬ፡ ከምንጊዜውም በከፋ ሕወሃት ሃገራችንን የእያንዳንዱ ዜጋ ሰብዓዊ መብቶችም ሆኑ የሃገሪቱ ዳር ድንበር ጠባቂ፡ ተንከባካቢ የሌለበት፡ ማንም ተጠያቂ የማይሆንበት የሽፍቶች መንደር አድርጓታል። እስከምናውቀው ድረስ፣ ሃገሪቱ ለዚሀ የወንበዴ ቡድን አልገዛም ብላ ሕዝቡ ታይቶ በማይታወቅ ኅብረት መነሳቱ ሕወሃትን ስላስደነገጠው ወደ ተለመደው ተግባሩ ወርዷል፡፡

ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ ባለፉት አሥር ወራት እሥር ቤቶችን እያቃጠለ የብዙኃንን ነፍስ አጥፍቷል። ባለፈው ቅዳሜም መስከረም 3/2016 ቂሊንጦ የሚገኘውን ታዋቂ የፖለቲካ እሥረኞች ያሉበትን እሥር ቤት አጋይቶታል። አሠራሩ ሕወሃት “ከሽድሽተ ዜሮ” የተወረስ የማሠቃያና ተቃዋሚዎቹን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በክፋቱ መጠን አደንዝዞ ሌሎችን ለማቆም የተደረገ ሙከራ ነው! ከሰሞኑ በጻፍኩት እንዳመለከትኩት፡ በተለይ በቀለ ገርባ – እንዲሁም ጓዶቹ የእግር ውስጥ እሳት ሆነውበታል።

ሕገ መንግሥቶችን ትተን ወደ አዳም ስሚት ስንመለስ፣ በታወቀ ጽሁፉ ስለ መንግሥት ምንነንትና ኃላፊነት የሚከተለውን ይዘረዝርልናል፣

    (ሀ) የመጀመሪያው የሉዓላዊው (Sovereign) ተግባር አጠቃላዩንና ነጻውን ኅብረተሰብን ወታደራዊ ኃይል በመጠቀም ከወረራ መነከባከብ ነው፤

    (ለ) ሁለተኛው የሉዓላዊው ተግባር እያንዳንዱን የኅብረተሰብ አባል ከግፍና ጭቆና መንከባከብ ነው፤

    (ሐ) ሶስተኛው የሉዓላዊው ተግባር አስፈልጊውን መዋቅሮች በማቋቋም፡ ታላቁን ኅብረተሰብ (the Great Society) ለመሥረት የሚያስችሉ ለሕዝብ አስፈላጊ ሥራዎችን ማከናወን ነው።

 

ሕወሃት እስከዛሬ በሕዝባችንና በሃገራችን ላይ የፈጸማቸው ሳያንሱ፡ ለምን ይሆን ኢትዮጵያውያን “የኢትዮጵያ መንግሥት” እያሉ የሚጠሩት? ከዚህ በፊት በትዊተር መልዕክቶች ሶስት ጊዜ ባስተላልፍም፡ ኢሣትም ላይ ኢትዮጵያውያን በደብዳቤያቸው በተደጋጋሚ ተቃውሟቸውን ቢያሰሙም፡ ሰሚ አላገኙም።

ይገባኛል ኢሣት የኢትዮጵያውያን ወገናዊ ድርጅት ነው። ነገር ግን ለምን ይሆን ችግር ያጋጠመው ይህንን ‘የኢትዮያ መንግሥት’ የሚለውን አባባል ከዚና ክፍሉ ቆርጦ የማይጥለው። ዜጎች ያልተገነዘብነው ነገር ካለ ይነገረን!

የኢትዮጵያ ሕዝብ የሕወሃትን አገዛዝ አሽቀንጥሮ ለመጣል በሚያደርገው ትግል አርማው በየቦታውና ባለኮከብ ባንዲራው መጣሉን እያየን፡ አሁንም ደጋግመን ‘የኢትዮጵያ መንግሥት’ የሚለውን ይዞ የሚጸና ወገን፡ ከሕዝቡ ጋር መራመድ ያልቻለ ያስመስለዋል!

በአባባሎቻችንም ሆነ በአስተሳሰባችን ጭምር ሕወሃት አሽቀንጥረን ለመጣል ዛሬውኑ ‘የኢትዮጵያ መንግሥት’ የሚለውን – እንደባንንዲራው ሁሉ – ኢትዮጵያውያን ሊነሱት ይገባል!

ባንስማማበትም፣ ሃገሪቱ አስተዳደር አላት፤ ስለሆነም ለጥሪ እንዳያስቸግር “የሕወሃት አስተዳደር” ሊባል ይችላል። ይህ ስያሜ ጊዜያዊነቱን ከመጠቆሙም ባሻገር፡ አፍሪካ ውስጥ የነበሩት ቅኝ ገዥዎች በአፍሪካውያንን አጠራር “አስተዳደር” ነበር የሚባሉት!
 

%d bloggers like this: