ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

12 Sep

Posted by The Ethiopia Observatory (TEO)
 
እሁድ መስከረም 1/2009 አዲስ አበባ/ኢትዮጵያ
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ፣ በጣም አዛኝ በሆነው!
 

ውድ የአገራችን ሕዝቦች ሆይ!

አገራችን ኢትዮጵያ ያሳለፈችው የረጅምና የአጭር ጊዜ ታሪክ አካል የሆነው የሕዝብ ሥልጣን ባለቤትነት አለመከበር፣ የእኩልነትና የእኩል ተጠቃሚነት መርህ አመተግበርና በአጠቃላይ ዜጎችን ሁለ ላያሳተፍ የሚችል ድሞክራሲያዊ ስርዓት እጦት አሁን ላለንበት እጅግ አሳሳቢ ወቅታዊ ሁኔታ እንዳበቃን ለማንም ግልፅ ነው፡፡ በመሆኑም ሕዝብ የመብትና የነፃነት ጥያቄውን አንግቦ አደባባይ የወጣበትና ስርዓቱን የተቃወመበት፣ በብዙ የአገራችን ክፍሎችም እስከ ሕይወት መስዋሥዕትነት እየተከፈለ ያለበት፣ በአገር አቀፍ ድረጃም ከፍተኛ ውጥረት የነገሰበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡

ይህ ሕዝባዊ ተቃውሞ ለዓመታት የተከማቸ የሕዝብ ብሶት ውጤት እንጂ የአንድ ጀምበር ስሜታዊነት የወለደው ክስተት አይደለም፡፡ አገሪቱን በመምራት ላይ ያለው መንግስት ለሕዝብ ጥያቄ ዋጋ ያለመስጠትና የስልጣን ምንጭ የሆነውን ሕዝብ የመናቅ ባህል ስር የሰደደ በመሆኑ ምክንያት ሕገ-መንግስታዊና ሰብዓዊ መብቱን በሰላማዊ መንገድ የጠየቀን የህብረተሰብ ክፍል እንኳ እንደጠላት ሲመለከትና በሽብርተኝነት ሲፈርጅ ቆይቷል፡፡ ለዚህም መንግስት የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን የእምነት ነፃነት ጥያቄ ያስተናገደበት መንገድ አንደ ዋቢ ማሳያ ነው፡፡

የፍትህ ስርዓቱም ከፖለቲካ ውሳኔ ነፃ ያልሆነና አንደ የመንግስት መጨቆኛ መሳሪያ ለመሆኑ በኮሚቴያችን አባላትና በተባባሪዎቻችን ላይ የተላለፈው ኢ-ፍትሃዊ የፍርደ ውሳኔ በዋነኛ አስረጂነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ስለሆነም መሰል የሕዝብ ጥያቄዎች በኃይል በመታፈናቸው፣ ፍትህ በመጓደሉና የዜጎች መብቶችና ነፃነቶች እጦት ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ ሕዝብ ስርዓቱን በመቃወም አደባባይ እንዲወጣ ተገድዷል፡፡

ይህንን ታሪካዊ ክስተት በብስለት ማስተናገድ በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ አገራት የሚገኙ ሁለም የአገራችን ዜጎች ኃላፊነት ነው ብለን እናምናለን፡፡ በጥላቻና በበቀል ፖለቲካ ስትታመስ የኖረችዋ አገራችን ያለባት ዘርፈ-ብዙ ችግሮች ተቀርፈው የዜጎች ነፃነትና መብት የሚከበርባት፣ ዜጎች ተፈቃቅደውና ተከባብረው የሚኖሩባት፣ እኩልነትና እኩል ተጠቃሚነት፣ እንዲሁም የሕግ የበላይነት የሰፈነባት የበለፀገች አገር ትሆን ዘንድ የአገራችን ሕዝቦች ያነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ሊያገኙ ይገባል፡፡

በሌላ በኩል መንግስት የስልጣን ምንጭ የሆነውን ሕዝብ ድምፅ በአፈሙዝ ለማፈን መሞከር ውጤት እንደማያስገኝ ሊረዳና ነፃነትን የተጠማ ሕዝብ ዓላማውን ከማሳካት የሚያግደው አንዲችም ምድራዊ ኃይል እንደሌለ ሊገነዘብ ይገባል፡፡ ሰላምን በማስከበር ሽፋን ሕዝብ ላይ ወታደራዊ ጥቃት መፈፀም መፍትሄ ሊሆን እንደማይችልም ማወቅ ይኖርበታል፡፡ ሕዝብም መሰረታዊ ለውጥ በማያመጣ ማስታገሻ ምላሽ እንደማይታለል ሊረዳ ይገባል፡፡ ይልቁንም መንግስት ከግትርነትና ከፓርቲ ወገንተኝነት ተላቅቆ ከፍ ያለ አገራዊ ምልከታ ሊኖረውና ሕዝቡ ያነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢውን መፍትሄ ያገኙ ዘንድ ሚናውን በመወጣት ከታሪክ ተወቃሽነት ራሱን ሊያድን ይገባል እንላለን፡፡ በተጨማሪም በመንግስታዊ ተቋማት ውስጥ በሁለም የስልጣን እርከን ላይ የሚገኙ ዜጎች ለአገርና ለወገን የሚጠቅሙ ተግባራትን በመፈፀም ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አደራ እንላለን፡፡

የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ከሕዝብ ፍላጎት፣ ጥቅምና ደህንነት፣ እንዲሁም ከእውነት ጎን በመቆም ውጥረቱ በሰላማዊ መንገድ ይፈታ ዘንድ መንግስትን የመምከር፣ የሕዝብን ድምፅ ያከብር ዘንድ የመገሰፅ፣ እንዲሁም ዜጎች ወንድማማችነታቸውንና አንድነታቸውን መጠበቅ እንዲለባቸው የማስተማር ወቅታዊ ኃላፊነት ያሇባቸው በመሆኑ ይህንን ሃይማኖታዊና አገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ሊጥሩ ይገባል እንላለን፡፡ የሃይማኖት መሪዎች ምግባር ይህን መምሰል ቢገባውም የሕገ-ወጡ መጅሊስ አመራሮች ግን በተለያዩ ጊዜያት መንግስት በሕዝብ ላይ እርምጃ እንዲወስድ የሚያበረታቱ ፀብ አጫሪ አስተያየቶችን ሲሰጡ ተስተውለዋል፡፡ ነገር ግን እነኚህ ግለሰቦችም ሆኑ የሚሰጧቸው አስተያየቶች ሕዝበ-ሙስሊሙን ፈጽሞ የማይወክሉ መሆናቸውን ሁላችንም የምናውቀው እውነታ ነው፡፡

ውድ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ሆይ!

ላለፉት አምስት ዓመታት በሕዝበ ሙስሊሙ የእምነት ተቋማት ውስጥ የመንግስትን ህግ-ወጥ ጣልቃ ገብነት በአደባባይ እየተቃወማችሁና የእምነት ነፃነታችሁን ለማስከበር በሰማዊ መንገድ እየታገላችሁ ዛሬ ድረስ በፅናት ዘልቃችኋል፡፡ ለዚህ ልፋታችሁ ልዕለ-ኃያዳ ፈጣሪያችን ምንዳችሁን ያበዛላችሁ ዘንድ እንመኛለን፡፡

ውድ ወገኖቻችን ሆይ!

ነፃነትና መብት በሕዝብ እጅ ያሉ ውድ ሃብቶች ናቸው፡፡ እነዚህን ሃብቶች ተነጥቆ የተገፋ የትኛውም ሕዝብ ስለ እኩልነቱ እና ስለእኩል ተጠቃሚነቱ በተግባር መረጋገጥ የመታገል ኃላፊነትና ሚናው በግንባር ቀደምትነት የራሱ ነው፡፡ ሰው በመሆናችን ብቻ የተጎናጸፍናቸውን ነፃነቶችና መብቶች ማስከበር የህልውና ጉዳይ በመሆኑ የእያንዳንዱ ዜጋ የነፍስ ወከፍ ኃላፊነት መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ስለሆነም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በሙለ አገራችን ኢትዮጵያ የዜጎች ነፃነት የተከበረባት፣ ፍትህ የሰፈነባትና እኩልነት የተረጋገጠባት አገር ትሆን ዘንድ ከመላው የአገሪቱ ዜጎች ጋር እጅ ለእጅ በመሆን ሚናችሁን መወጣት ለነገ የማይባል ኃላፊነታችሁ መሆኑን ለማሳሰብ እንሻለን፡፡ የሃይማኖትና የዘር ልዩነት ሳይገድበን ለፍትህ በአንድነት መቆም እንዳለብን የአላህ መልእክተኛ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰላም በእርሳቸው ይሁንና) አስተምረውናል፡፡ በተግባርም አሳይተውናል፡፡

ውድ የአገራችን ሕዝቦች ሆይ!

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት የሚገኙ ምሁራንና የለውጥ አራማጆች /activists/ አገራችንን አሁን ካለችበት ውጥንቅጥ መታደግ የሚያስችል፣ ሁለንም ባለድርሻ አካላት የሚያሳትፍና የሚያግባባ የመፍትሄ አቅጣጫ ላይ ለመድረስ በአንድነት ሌት ተቀን መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ የፖለቲካ ልሂቃንም በፖለቲካ ዲስኩሮቻቸውም ሆነ በጋዜጣዊ መግለጫዎቻቸው የሕዝብን አንድነትና ወንድማማችነት ከምንጊዜውም በበለጠ በተደጋጋሚ መግለጻቸውና ይቅርባይነትን መሰረት ያደረገ ፖለቲካ ማራመዲቸው እጅግ ጠቃሚ ነው ብለን እናምናለን፡፡ በዚህም የበቀል፣ የጥላቻና የማግለል የፖለቲካ ባህልን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ግብዓት-መሬቱን ለመፈጸም ይቻላል የሚል ጥልቅ እምነት አለን፡፡

ውድ የአገራችን ሕዝቦች ሆይ!

ከየትኛውም ወገን የሚሰነዘሩ፣ ሕዝብን ከሕዝብ ሊያጋጩ የሚችሉ፣ አንድን የተለየ ብሄር ወይም ማህበረሰብ አጠቃላይ በሆነ መልኩ የሚያወግዙ፣ የሚያስገልልና በእኩይነት የሚፈርጁ የጥላቻ ፕሮፓጋንዲዎች አገርን አደጋ ላይ የሚጥሉ በመሆናቸው ይህን መሰል ሁኔታ እንዳይፈጠር ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትም ጸረ-ህዝብና አፍራሽ አካሄዶች እንዳይፈጠሩ የመከላከል ስራቸውን ከመስራት እንዳይዘናጉ አጥብቀን እናሳስባለን፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ያለው ሕዝባችን ለዘመናት የዘለቀ ወንድማዊ ትስስሩን ጠብቆ የበፀገችና ለዜጎች ኑሮ ተመራጭ የሆነች ኢትዮጵያን እውን እንደሚያደርግ አንጠራጠርም፡፡ በዚህ አጋጣሚም ሕዝባችን የዘርና የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድበው አንድነቱን ላሳየበት፣ የአንዱ ጉዳይ የሌላውም መሆኑን ላስመሰከረበት ለዚህ ታላቅ ታሪካዊ ክስተት ያለንን አድናቆት ለመግለፅ እንወዳለን፡፡ በሂደቱም በኦሮሚያ፣ በአማራና በሌሎችም የአገራችን ክፍሎች ሕይወታቸውን ባጡና የአካል ጉዳት በደረሰባቸው ወገኖቻችን ምክንያት የተሰማንን እጅግ መራር ሐዘን እየገለጽን ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን እንመኛለን፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ የዜጎች ነፃነት የተከበረባት፣ ፍትህ የሰፈነባት፣ እኩልነት የተረጋገጠባትና ዜጎች በሰላም የሚኖሩባት የበለፀገች አገር ትሆን ዘንድ ዘወትር በፀልታችን እንድናስባት አጥብቀን አደራ እንላሇን፡፡ አምላካችን ሆይ! እናት አገራችንን ኢትዮጵያን ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነትና ሰላም የሰፈነባት፣ ለሰው ልጆች መኖርያነት ተስማሚ፣ በቁሳዊም ሆነ ሞራላዊ ብልፅግናዋም ከዓለም አገራት ተጠቃሽ ታደርግልን ዘንድ አጥብቀን እንለምንሃለን! አሚን!

——————————————————
ግሌባጭ፡- ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ሚዱያዎች በሙለ

One Response to “ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ”

  1. Dita Tefera September 14, 2016 at 12:51 #

    Dear Deme,FYI,Blessings,Dita T.

    Like

Comments are closed.

%d bloggers like this: